Saturday, 04 June 2016 12:55

የዓለም የጤና ድርጅት ጊኒ ከኢቦላ ነጻ መሆኗን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሪዮ ኦሎምፒክ በዚካ ቫይረስ ሳቢያ መራዘሙን አልተቀበለውም
     የዓለም የጤና ድርጅት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሆኖ የቆየው የኢቦላ ቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባት ጊኒ፣ ከቫይረሱ ነጻ መሆኗን ባለፈው ሰኞ በይፋ ማስታወቁንና በቅርቡ በብራዚል የሚጀመረው የሪዮ ኦሎምፒክ በዚካ ቫይረስ ሳቢያ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ መባሉን እንዳልተቀበለው ተዘገበ፡፡
በጊኒ የኢቦላ ቫይረስን ስርጭት ለመግታትና በቁጥጥር ስር ለማዋል ባለፉት አመታት ሰፊ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሰው የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ፤በአገሪቱ ባለፉት 3 ወራት በቫይረሱ ስርጭት ላይ የተቀናጀ ክትትል ሲደረግ እንደቆየና አንድም ሰው በቫይረሱ እንዳልተያዘ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ ምንም እንኳን በቫይረሱ የተያዘ አዲስ ታማሚ በአገሪቱ ባይገኝም፣ ቫይረሱ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ፈሳሾች ውስጥ ለወራት ተደብቆ የመቆየት ባህሪ ያለው እንደመሆኑ ስርጭቱ ሙሉ ለሙሉ ተገትቷል ማለት እንደማይቻልና ዳግም ሊከሰት እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በ2013 በጊኒ የተቀሰቀሰውና ሴራሊዮንና ሊይቤሪያን ወደመሳሰሉ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በስፋት የተሰራጨው ኢቦላ ቫይረስ፣ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜናም የዓለም የጤና ድርጅት፣ በብራዚል የተቀሰቀሰውና ነፍሰ-ጡሮችን በማጥቃት የተዛባ ጤንነት ያላቸው ህጻናት እንዲወለዱ የሚያደርገው የዚካ ቫይረስ፣ የከፋ የጤና ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል የሪዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም ከ150 የተለያዩ የአለማችን አገራት የጤና ኤክስፐርቶች ለተመድ ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ እንዳደረገው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሪዮን ኦሎምፒክ ለማራዘም የሚያስገድድና የጤና ቀውስ ሊከተል እንደሚችል የሚያሳይ ተጨባጭ ምክንያት የለም፤ ውድድሩን ማራዘምም ሆነ በሌላ አገር እንዲካሄድ ማድረግ፣ ቫይረሱ በአለማቀፍ ደረጃ ያለውን ስርጭት ለመግታት ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ አያበረክትም ብሏል፤ የዓለም የጤና ድርጅት፡፡

Read 908 times