Saturday, 11 June 2016 13:40

የ100 ሚ. ዶላር ቀጭን ጌታ!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

(ከበረንዳ አዳሪነት የሚጀምር የስኬት ጉዞ ----)

      አሁን ታዋቂ ኮሜዲያንና የቴሌቭዥን ትርኢት (show) አዘጋጅ ሆኗል፡፡ በአሜሪካ MBC የቴሌቪዥን ቻናል “ሊትል ቢግ ሾትስ” የተሰኘ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሕፃናት የሚያስተዋውቅና የሚያነቃቃ ፕሮግራም እያዘጋጀ ያቀርባል - ስቲቭ ሐርቬይ፡፡ የሐርቬይ የልጆች ፕሮግራም ለወላጆችም ጭምር ማራኪና አዝናኝ በመሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በጉጉት ይጠብቁታል፡፡
ሃርቬይ ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት፣ የኮሜዲ ሥራ ለማግኘት በሚፍጨረጨርበት ወቅት ምስኪን ድሃና የጐዳና ተዳዳሪ እንደነበር የጠቆመው “ፒፕል” መፅሔት፤ “የዕለት ጉርሱን የሚያገኘው በመከራ ነበር፤ሳንድዊች ብቻ እየበላ ብዙ ዓመት ገፍቷል፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ የሚበላ ብቻ ሳይሆን መጠለያም አልነበረውም - በፎርድ መኪናው ውስጥ ነበር የሚያድረው፡፡
በእነዚያ የመከራ ሦስት ዓመታት ሐርቬይ መኪናውን ለማንቀሳቀስ ነዳጅ ሰርቋል፤ መንገድ ዳር በተሰሩ መፀዳጃ ቤቶች መታጠቢያ ገላውን ታጥቧል፡፡ “ያ ወቅት በጣም መጥፎ ነበር፡፡” ይላል ሐርቬይ፤ ለራስህ “ይህ እጅግ የከፋና የከረፋ ጊዜ ነው”፤ የምትለው ወቅት አለ፤ አዎ! ብዙ ጊዜ ነው በሽንት ቤቶቹ የተጠቀምኩት” ብሏል፡፡
መከራውን ያባሰበት ደግሞ ከባለቤቱ ጋር መፋታቱ ነበር፡፡ ለእሷና ለሁለት ልጆቻቸው ተቆራጭ አድርጐ ለሳምንት 50 ዶላር ብቻ ነበር የሚተርፈው፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ችግሩ በእጅጉ አይሎበት ነበር - ገላውን መታጠቢያ ገንዘብ እንኳን አልነበረውም፡፡ እናም እንዲህ ያደርግ ነበር፡፡ ወደ ሆቴል ቤት ይሄዳል፡፡ በሆቴሉ ያደሩ እንግዶች እስኪወጡ ድረስ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተደብቆ ይቆያል፡፡ እንግዶቹ ወጥተው ሲሄዱ ወደ ክፍሉ ይገባና ገላውን ይታጠባል፡፡ “ችግሩ ከቋጥኝ የከበደ ነበር፤ ከራስህ በስተቀር ለአንተ ማንም የለም፡፡ ምንም የለህም ወይም የሚደርስልህ አታገኝም፡፡ በዚህ ጊዜ ቁጭ ብዬ አምርሬ አለቀስኩ” ሲል ያን ክፉ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሶ ያስታውሳል፡፡  
እንዲህ ችግር ሲያንገላታው ከቆየ በኋላ ከፍተኛ ክብርና ተቀባይነት ባለው አፖሎ ቴሌቭዥን “በሾው ታይም” ዝግጅቱን በጊዜያዊነት እንዲያቀርብ ተፈቀደለት፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከቴሌቭዥን መስኮት ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ሐርቬይ፣ አሁን የተቀዳጀውን ከፍተኛ ስኬትና ለውጥ በፍፁም በዕድል እንዳገኘው አያስበውም፣ አይቆጥረውም፤ አይቀበለውም፡፡ “በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ‹እዚህ ደረጃ እንደምደርስ ሁሌም አውቅ ነበር› ሲሉ በጣም ያመኛል” ብሏል፤ ራሱን በአሉታ እየነቀነቀ፡፡ “እኔ ግን እዚህ ደረጃ እንደምደርስ በፍፁም አላውቅም ነበር” ሲልም የራሱን እውነታ ይገልፃል፡፡
ዛሬ ሐርቬይ ራሱ እያዘጋጀ በሚያቀርበው “Little Big shots” የተሰኘ የህፃናትን ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ የሚያስስና የሚያበረታታ ፕሮግራሙ፤በመላው አሜሪካ እጅግ ዝነኛና ተወዳጅ ነው፡፡  በጨዋታ አዋቂነቱና ከህፃናት ጋር ባለው ድንቅ የመግባባት ችሎታው ብዙዎች የሚያደንቁት ሐርቬይ፤ ምርጥና አዝናኝ የህፃናት ፕሮግራም መፍጠር ችሏል፡፡ የ100 ሚሊዮን ዶላር ቀጭን ጌታም አድርጎታል፡፡ በእርግጥም “Little Big Shots” ሁሉም ሊያየው የሚገባ ምርጥ የቲቪ ሾው ነው!!

Read 1540 times