Saturday, 03 March 2012 14:45

ሱዳናዊው አሉላ

Written by  - ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(1 Vote)

አባታቸው ከጃንሆይ የወርቅ ኒሻን ሸልመዋል

ከኢትዮጵያውያን ጋር ብዙም ልዩነት በሌላቸው ሱዳኖች መሀል ቢሆኑም ኢትዮጵያዊ ደም  እንዳላቸው ለማወቅ ግን የሳቸው ማረጋገጫ አያስፈልጋችሁም፡፡ አሉላ በርሄ ኪዳኔ ይባላሉ፡፡ ጊዜውን በትክክል መናገር ባይችሉም የሳቸው አያት ከትግራይ በመነሳት ገዳሪፍ የተባለችውን የሱዳን ከተማ ካቋቋሙ ሰዎች አንዱ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው አባባል የቤተሰቡ አባል ገዳሪፍ ከከተመ በኋላ በአካባቢው በተመሳሳይ ከከተሙ ሠዎች ጋር የጋብቻ ዝምድና ተመስርቷል፡፡ አቶ አሉላ በሱዳን በሚታተም አንድ ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ የአምድ አዘጋጅ ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አንዱንም መናገር አይችሉም፡፡ እንግሊዝኛቸው ምንም አይነት የአረብኛ ተፅዕኖ ባይኖረውም አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አረብኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ደም አለኝ ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዘመዶቻቸው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ ተቆራርጠዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲያወሩ ከተወሰኑ ቅንጭብጭብ ታሪኮች ውጪ ምንም አያውቁም፡፡ “እንኳን እኔ አባቴም እናቴም ሱዳን ተወልደው ሱዳናዊ ሆነው የኖሩ ናቸው” ይላሉ፡፡

 

ሱዳን አገሬ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የዘመዶቼ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሚገኙ ዘመዶቼን ለማግኘት በተለያዩ ጊዜዎች ሙከራ የተደረገ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ አንድ ሠው ለማጣራት ይሞክርና ከጀመረው በኋላ በመሀል ይቋረጣል፡፡ በዚህ ምክንያት ዘመዶቼ የት ቦታ እንደሚገኙና እነማን እንደሆኑ አላውቅም ይላሉ - ሱዳናዊው አሉላ፡፡

በመጀመሪያ ገዳሪፍን የቆረቆሩት ሰዎች ከአገራቸው ነቅለው ቢወጡም ለልጆቻቸው የሚሰጡት ስም በትግራይ አካባቢ የተለመደውን ነው፡፡ የኔም ስም አሉላ የሆነው በዛ ምክንያት ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ዳግም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አፄ ኃይለስላሴ ወደ አገር የተመለሱት በሱዳን በኩል ነበር፡፡ አቶ አሉላ እንደነገሩኝ ከአፄኃይለ ስላሴ ጋር ወደ ሱዳን የመጡት ሠዎች የማረፊያና የቀለብ ችግር እንዳይገጥማቸው የሳቸው አባት አቀባበል አድርገው ተንከባክበዋቸዋል፡፡ ወደ ሚቀጥለው መንገዳቸው ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ማረፊያ ሠጥተው በሚገባ አስተናግደዋቸዋል፡፡ ለዚህም የጣሊያን ጦር አገሪቱን ለቆ ከወጣ በኋላ ለንጉሡ እና አብረዋቸው ተጉዘው ለነበሩት ሠዎች ያደረጉት ውለታ ተቆጥሮ የክብር የወርቅ ኒሻን ከጃንሆይ ተሸልመዋል፡፡

አቶ አሉላ ለስራ ኢትዮጵያ  ይመላለሳሉ፡፡ ገፅታቸውንና ስማቸውን በማየት ብቻ በተለያዩ ቦታዎች ባሉ የቁጥጥር ቦታዎች የሚቀመጡ ሠዎች በአማርኛ ያናግሯቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው ሱዳናዊ እንደሆኑና ቋንቋውን መናገር እንደማይችሉ ሲያስረዱ በሠዎቹ ላይ ግራ መጋባትና መጠራጠርን እንደሚያነቡ ይናገራሉ፡፡ የሳቸው አያት ገዳሪፍን በቆረቆሩበት ወቅት ሌሎች ብዙ ቤተሠቦች አካባቢው ላይ ሠፍረው እንደነበር ከወላጆቻቸው ያገኙትን መረጃ መሠረት በማድረግ የሚናገሩት አቶ አሉላ፤ የኔ አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ብዙ ሠዎች አሉ፡፡ በደም (በዘር) ሳይሆን በትውልድ አገር የሚያውቋትን ሱዳንን ብቻ የሙኝጥ ብሎ ከቀዳሚው ዘር ጋር መቆራረጥ፡፡

የትውልድ አገርን መሠረት ባደረገ የዜግነት አወሳሰድ ሱዳናዊ ቢሆኑም በደም ኢትዮጵያዊ በመሆንዎ አድልዎ ተደርጎብዎት ያውቃል? ብዬ ጠየኳቸው፡፡ የአቶ አሉላ ምላሽ እጅግ ፈጣን ነበር፡፡

“በፍፁም ምንም አይነት አድልዎ አላጋጠመኝም፡፡ እኔ ሱዳንን ነው የማውቀው፤ ሱዳናውያኑም እንደሱዳናዊ ነው የሚያውቁኝ፡፡

እንዲያውም ከአክስቶቼ ልጆች አንዱ ዶክተር የሱፍ ሚካኤል በኺት ይባላል፡፡ የፕሬዚዳንት ኑመሬ ጃፋር የህግ አማካሪ ነበር፡፡” አሉኝ፡፡

ኑመሬ የሱዳን ፕሬዚዳንት ቢሆኑም በኤርትራ ከረን የሚገኘው የብሌን ጎሳ ደም እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የአቶ አሉላ የአክስት ልጅ የአያት ስም በኺት ይባላል፡፡ ስሙ የትግርኛ ሳይሆን የብሌን ነው፡፡ እዚህ ላይ መመለስ ያለበት ወይም መነሳት ያለበት ነጥብ አቶ ኪዳኔ (የአቶ አሉላ አያት) ገዳሪፍ በሄዱበት ወቅት ትግራይ የሚለው ስያሜ የትኞቹን ቦታዎች ያካትታል? የአሁኑን የትግራይ ካርታ ከመቶ ዓመት በፊት በነበረው በመተካት ማሰብን ይጠይቃል፡፡

 

 

Read 2802 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:38