Saturday, 18 June 2016 12:42

‘ሃሪ ፖተር’ን በትያትር ለማየት፣ 3ሺ ፓውንድ?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

• በጥቅምት ወር፣ በአንድ ቀን 175 ሺ ቲኬት ተሽጧል።
• ትያትሩ የሚከፈተው፣ በመጪው ሐምሌ ወር ነው።
• በተነባቢነት ‘ሪከርድ’ የሰበረ መፅሃፍ! በፊልምም እንዲሁ።

“ሃሪ ፖተር...” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው የመጀመሪያው መፅሃፍ፣ ሃያኛ ዓመቱን ሊደፍን ተቃርቧል። ያኔ፣ ደራሲዋ ጄኬ ሮውሊን፣ አሳታሚ ለማግኘት ለወራት ተንገላትታለች። በርካታ አሳታሚዎች፣ ‘ድርሰቱ ረዝሟል’ ብለው መልሰውላታል። ድርሰቱኮ፣ 250 ገፅ ቢሆን ነው።
ደግነቱ፣ በጥቂት ኮፒ ለመሞከር ፈቃደኛ የሆነ አሳታሚ ተገኘ። በአንድ ሺ ኮፒ ነበር የታተመው። ደራሲዋ ያገኘችው ክፍያም 4ሺ ዶላር አይሞላም። ለአምስት ዓመት የለፋችበት ድርሰት ነው፡፡ ክፍያው ግን የሁለት ወር አስቤዛ አይሸፍንም፡፡ ምናልባት፣ መፅሃፉ ከተሸጠ፣ ለአሳታሚውና ለደራሲዋ፣ ደህና ገቢ ያስገኝላቸው ይሆናል። ግን፣ ‘ምናልባት’... ብቻ ነው። እናም፣ ተጨማሪ ገንዘብ አገኛለሁ ብላ በተስፋ ብቻ እንዳትቀመጥ፣ አሳታሚው መክሯታል - “የቀን ስራ ብታፈላልጊ ይሻላል” ብሏታል።   
በእርግጥም፣ መፅሃፏ ቶሎ አልተሸጠላትም። ቀስ በቀስ ግን፣ አንባቢዎች እየወደዱት፣ የመፅሃፉ አሪፍነት በሰው በሰው እየተሰማ፣... ውሎ ወድሮም በየሚዲያው እየተነሳ... ገበያው ደራላት።
ከዚያ በኋላማ፣ “ምኑ ይወራል!” ቢባል ይሻላል። መጀመሪያ በእንግሊዝ፣ ከዚያ በአሜሪካ፣ ብዙም ሳይቆይ በየአገሩ፣ “የሃሪ ፖተር...” ዝና አለምን አዳረሰ።
ተዓምር ሆኖ ቢታየን አይገርምም።
የደራሲዋ ሃሳብና ውጥን፣ ሰመረ። የሃሪ ፖተርን ታሪክ፣ በተከታታይ 7 መፃህፍት ለማዘጋጀት ነበር ሃሳቧ። እንዳሰበችውም፣ ከአመት በኋላ፣ ሁለተኛውን ድርሰት፣ ‘እንካችሁ’ አለች። በዚህ አላቆመችም።
በአራት አመታት ውስጥ፣ አራት የ‘ሃሪ ፖተር’ ተከታታይ ድርሰቶችን፣ ለአንባቢያን አድርሳለች። ከህፃን እስከ አዋቂ፣ በጉጉት ተሻምተው የሚያነብቡት፣ ተመራጭ ታሪክ ሆነላት። ግን፣ ከአመት አመት፣ ከቀድሞ የበለጠ መሳጭና ልብ አንጠልጣይ ድርሰት መፃፍ ይከብዳል፡፡ ለዚህች ተአምረኛ ደራሲም ቢሆን፤ ስራው ከባድ ነው።
አንባቢዎች፣ አምስተኛውን መፅሃፍ ለማንበብ፣ ሦስት ዓመታትን ጠብቀዋል። ግን አይቆጭም። የጓጉለትን ያህል ወደውታል።
የመጀመሪያው መፅሃፍ፣ በአንድ ሺ ኮፒ እንዳልታተመ፣ ስድስተኛው መፅሃፍ፣ በአንድ ቀን ብቻ 9 ሚሊዮን ኮፒ ተቸብችቦ፣ አዲስ የታሪክ ሪከርድ አስመዝግቧል። ሰባተኛው መፅሃፍም እንዲሁ፣ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው እለት፣ 15 ሚሊዮን ኮፒ ተሽጧል።
እስካለፈው ዓመት፣ እነዚህ ተከታታይ ድርሰቶች፣ በድምር በ450 ሚሊዮን ኮፒ ታትመዋል። ይሄ የአለም ሪከርድ ነው። ደራሲዋም በአለም የመጀመሪያዋ ቢሊዬነር ደራሲ ለመሆን እንደበቃች ፎርብስ ገልጿል።
ድርሰቶቿ ወደ ፊልም ተቀይረው ለተመልካች የቀረቡ ጊዜም፣ እንደተለመደው ፊልም ቤቶች ተጥለቅልቀዋል። ፊልሞቹ፣ ከ7.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል። በታሪክ፣ ከፍተኛ ገቢ ካስገኙ 50 ፊልሞች መካከል፣ 7ቱ የ‘ሃሪ ፖተር’ ፊልሞች ናቸው።
አሁን ደግሞ በትያትር መጥቷል... የሃሪ ፖተር ታሪክ። ድርሰቱ ግን አዲስ ነው። በመጪው ሃምሌ ተመርቆ የሚከፈተውን ባለ ሁለት ክፍል ትያትር ለማየት፣ የመግቢያ ትኬቶች በአብዛኛው ገና ድሮ ተሽጠዋል። 175ሺ ቲኬቶች፣ በአንድ ቀን ውስጥ እንዳለቁ ቴሌግራፍ ገልጿል - ባለፈው ጥቅምት ወር። እስከሚቀጥለው አመት ግንቦት ወር ድረስ፣ ቦታ ተይዟል ማለት ይቻላል።
ትንሹ የትኬት ዋጋ 30 ፓውንድ ነው፣ ትልቁ ደግሞ 130 ፓውንድ። (ከ900 ብር እስከ 4000 ብር መሆኑ ነው)። በእርግጥ አንዳንዶች፣ በብዛት ትኬት ስለገዙ፣ አሁን መልሰው እየሸጡ ናቸው - ዋጋውን ግን፣ ከአስር እጥፍ በላይ አድርገውታል። ርካሹን ትኬት ወደ 300 ፓውንድ አድርሰውታል። ከፍተኛውን ደግሞ 3ሺ ፓውንድ። ወደ ብር ባንመነዝረው ይሻላል። የመቶ ሺ ብር ትኬት? ዝም ነው።   
 የደራሲዋ ስኬት ግን፣ እልልታም አይበቃውም።

Read 2689 times