Saturday, 18 June 2016 12:45

ከ“ሊቢያ ኦይል ሊሚትድ ኢትዮጵያ”፤ የተሰጠ ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

    በአቶ ሐይሉ ገ/ሕይወትና በሼል ኢትዮጵያ ወይም ኦይል ሊቢያ መካከል ስለነበረው ሁኔታ አቶ አብዱልመሊክ ሁሴን በተባሉ ሰው ወይም ስም የተፃፈውን አቤቱታ ተመልክተነዋል፡፡ የአቶ አብዱልመሊክ ሁሴን አቤቱታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ “በግልፅ ደብዳቤ” የተፃፈ ሲሆን ዋናው ዓላማው አቶ ሐይሉ ገ/ሕይወት በሼል ኢትዮጵያ ወይም ኦይል ሊቢያ “የተነጠቁትን ቦታ” ማስመለስ ነው፡፡ አቶ አብዱልመሊክ፤የአቶ ሐይሉ የሕግ አማካሪ ወይም ጠበቃ ወይም ጋዜጠኛ ይሁኑ በግልፅ ባናውቅም ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ቢሆኑ እንኳን ማንሳት የሚገባቸውን ቁልፍ ጥያቄ ሳያነሱ አገር ምድሩን ወንጅለዋል፡፡ ለነገሩ ቁልፉ ጥያቄ ከተነሳ አቤቱታው አያስፈልግም ወይም እዚያው መልስ ያገኛል፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሆኖ ያገኙት ዙሪያውን መወንጀል ነውና ይህንኑ አድርገዋል፡፡
ለመሆኑ አቶ ሐይሉ ተወሰደባቸው የተባለው ቦታ የተጠቃሚነት መብት ቀድሞ የነበረው ማነው? ሼል ኢትዮጵያ ለዓመታት ሲገለገልበት በነበረው ቦታ ላይ የሼልን መሠረተ - ልማት ተጠቅመው ነዳጅ ማከፋፈል ጠይቀውና ተፈቅዶላቸው የመጡ ሰው ናቸው፡፡ በአጭር አገላለፅ አቶ ሐይሉ የነዳጅ ወኪል ለመሆን ጠይቀው በተፈቀደላቸው መሠረት ነው ከሼልም ከቦታውም ጋር ግንኙነት የፈጠሩት፡፡ ከዚያ ቀድሞ ለዓመታት ሼል ኢትዮጵያ በቦታው ላይ ማደያ ገንብቶ ሲሰራ ነበር፡፡ አሁንም ሼል ኢትዮጵያን የገዛው ኦይል ሊቢያ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን ጥሬ ሀቅ ደብቀው ነው አቶ አብዱልመሊክ ያለ ይሉኝታና ያለ ሀፍረት የስንቱን ስም ያጠፉትና የወነጀሉት፡፡ የሕግ ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎች ተጨማሪ ሀቆችን ለግልፅነት እናንሳ፡፡
የዚህ የማደያ ቦታ ባለቤት አቶ አሰፋ መንገሻ ይባላሉ፡፡ በንጉሱ ዘመን መሬት የግል ሃብት የነበረበት ጊዜ ስለሆነ ሼል ኢትዮጵያ ከአቶ አሰፋ መንገሻ ባዶ መሬት በመከራየትና ማደያ በመገንባት ስራውን ማካሄድ ጀመረ፡፡ በመካከል ደርግ ወደ ስልጣን መጣ፡፡ እናም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ያደረገውን አዋጅ ቁጥር 47/1967 አወጀ፡፡ መሬቱንም ወረሰ፡፡
የነዳጅ ማደያ ስራን ያለ ቦታ ማከናወን ስለማይቻል፣ ይህንኑ በመረዳት ነዳጅ ማደያዎችን ብቻ የተመለከተው መመሪያ በደርግ መንግስት አማካይነት ወጣ፡፡ በዚሁ መሠረት ሼል ኢትዮጵያ በቦታው ላይ የመስራት ህጋዊ መብት እንደማንኛውም የውጭ ኩባንያ አገኘ፡፡ እናም ስራውን ቀጠለ፡፡ አቶ ሐይሉ ወደ ሼል የመጡት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ደምበኛ በማደያው ነዳጅ የማከፋፈሉን ስራ ከሼል ጠይቀው፣ በ1971 ዓ.ም ከተፈቀደላቸው በኋላ የሽያጭ ወኪልነት ውላቸው እየታደሰ ንግድ ፈቃድ አውጥተው በወኪልነት ሲሰሩ፣ማደያውን በህገ ወጥ መንገድ የተቆጣጠሩ መስሏቸው፣ በገዛ ፍቃዳቸውን ውሉን በ2001 ዓ.ም እስኪያቋርጡ ድረስ ሰርተዋል፡፡ በእነዚህ አመታት እንደ ሌሎቹ ማናቸውም የቆዩ ወኪሎች ኩባንያውን ወክለው ከሦስተኛ ወገን ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ አቶ ሐይሉ የቦታው ሕጋዊ ባለቤት ነኝ በማለት ስውር ደባ የጀመሩት፡፡ ዝርዝሩን እዚህ መግለፅ የማንፈልገውን የተለያየ መንገድ በመሄድ፣የቦታው ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሁሉም ግን ሕገወጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቶ ሐይሉ ከወረዳ አስፈፃሚዎችና ፈፃሚዎች ጋር በመመሳጠር፣ ኩባንያው ሳያውቅ ውዝፍ ግብር በፍርድ ቤት ተገደው እንዲከፍሉ የተደረገበትን ድራማ ሌላ ጊዜ በስፋት ማቅረብ የምንችል መሆኑን ለአንባብያን እንገልፃለን፡፡
ሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ ሊሚትድ፤ ይህ ድርጊት ህገወጥ እንደሆነና ከድርጊታቸውም ተቆጥበው ከኩባንያው ጋር እንደ ከዚህ በፊቱ በሰላም እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም፣ ይባስ በለው ኩባንያው መሳሪያዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካላነሳ፣ተጠያቂ እንደማይሆኑ ማስጠንቀቂያ ላኩ፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ኩባንያው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ የተገደደው፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ከአቶ አሰፋ መንገሻ በደርግ ከተወረሰ በኋላ ቦታው የመንግስት ነው፡፡ ሼል ኢትዮጵያ ድሮም የእሱ አልነበረም፡፡ ቀጥሎም የእሱ አልነበረም፡፡ መሬት፣ የመንግስት ነውና፡፡ የመገልገል መብቱ ግን ያኔም የተረጋገጠ ነው፡፡ አሁንም በእጁ ያለ ነው፡፡ አቶ ሐይሉ በውክልና ከተጠጉ በኋላ ስር ለስር በሰሩት ስራ አጽመ-ርስታቸው ሊያደርጉት አሰቡ፡፡ አልተሳካም፣ ሊሳካም አይችልም፡፡ ሕግና ስርዓት ያለበት ሀገር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች (በሁሉም ደረጃ የሚገኙት) የአቶ ሐይሉን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የኦይል ሊቢያን የተገልጋይነት ባለመብትነት በፍርዳቸው አረጋግጠዋል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎትም ውሳኔዎቹ የሕግ ስህተት እንደሌለባቸው አረጋግጧል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አቶ አብዱልመሊክ፤ጥቂት ማጣራት ሳያደርጉ ሌላ ሕገወጥ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ አቶ አብዱመሊክ፤ ለስግብግብና ሕገወጥ ፍላጐት መሟላት ሲሉና ምንም ሳያፍሩ በኢትዮጵያ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ሁሉ በወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የሚል የክስ ማዳበሪያ ይዘወ ቀርበዋል፡፡ ሀገሪቱ እጆቿን ዘርግታ የጋበዘቻቸውን የውጭ ኢንቨስተሮች፤ ሽፍታና ወራሪ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሁሉ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ፣ስራ አላሰራ ብለዋል ለማለትም በቁ፡፡ በሚያሳፍር ሁኔታ የሊቢያ ሕዝብ ተባብሮ ያስወገዳቸውን አምባገነኑን መሀመድ ጋዳፊን ዋቢ በማድረግ ኦይል ሊቢያን በጋዳፊ ስም እስከ መወንጀልም ደርሰዋል፡፡ የሚገርመው ነገር አቶ አብዱልመሊክ ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነትም አንስተዋል፡፡
መርምሮ ደባቂ ነው ወይስ መርምሮ አጋላጭ ነው? እንዴትስ ነው አንድ መርማሪ ጋዜጠኛ ኦይል ሊቢያ፣ የሊቢያ ኩባንያ ስለሆነና ሊቢያን ያስተዳድሩ የነበሩት ጋዳፊ ስለነበሩ፣ ሼልን መግዛቱ አግባብ አይደለም ብሎ የሚነሳው? እውነቱን ለመናገር ለጋዳፊ የሚቀርበው የትኛው አስተሳሰብና ተግባር ነው?
አቶ አብዱልመሊክ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነትም አንስተዋል፡፡ ትክክለኛው ኪራይ ሰብሳቢነት የተፈፀመበትን ጉዳይ ደብቀው፣ ሌሎችን ለመወንጀል ሲጣጣሩ፣ የኪራይ ሰብሳቢዎች የዘመኑ ፋሽን መሆኑን በሚገባ አረጋግጠውልናል፡፡ የማይመለከታቸውን፣ የእርሳቸው ያልሆነውን ቦታ በአቋራጭ ለመንጠቅና ለመክበር ከተደረገው የአቶ ሐይሉ እንቅስቃሴ በላይ ምን ኪራይ ሰብሳቢነት አለ? ከአባት ያልወረሱትን፣ ከሌላ ሰው ያልገዙትን፣ በስጦታ ያላገኙትን የመንግስት ቦታ፤ሼልን ተጠግተው በውክልነት ሲገለገሉ፣ የከፈሉትን ግብር ብቻ መነሻ አድርገው ቦታውን ጠቅልዬ ልውሰድ የሚሉትን ሰው አቤቱታና ክስ፣ በየደረጃው ውድቅ ያደረጉት የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሁሉ፣ በአቶ አብዱልመሊክ ኪራይ ሰብሳቢ ተብለዋል፡፡
ስለዚህ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ፀሐፊው፤ ሼል ኩባንያ በአስተዳደር በኩል መሄድ ሲያቅተው ፍርድ ቤትን አቋራጭ መንገድ አድርጐ የፈለገውን ማስፈፀም እንደቻለ ማቅረቡ የፍርድ ቤቶችን ክብር፣ ህልውና፣ ሥራ እጅጉን ይነካል፡፡ ፍርድ ቤቶች በማንም የሚመሩ፣ የማንንም ጉዳይ አስፈፃሚ ናቸው ማለቱ ነው? ስለሆነም ፍትህ በኢትዮጵያ የለም እያለ ነው? ደግሞስ የወረዳና የክፍለ ከተማ አስፈፃሚዎች ውሣኔ፣ የመጨረሻ ውሳኔ ይሁን እያለ ነው?
ጋዜጣውስ ምን እያደረገ ነው? ያስተናገደው ፅሁፍ ነፃ አስተያየት ነው? የመርማሪ ጋዜጠኛ ሪፖርት ነው? የጠበቃ አቤቱታ ነው? ምንድነው? ሦስተኛ ወገንን በቀጥታ የሚወነጅል ሀሰተኛ መረጃ ሲቀርብ ማጣራት የለበትም? ፍሬ ጉዳዩ፣ ሂደቱ፣ ውሳኔው በማይታወቅ መደምደሚያ፡-
የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ሀገር እያጠፉ፣ የዜጐችን መሬት እየቀሙ ነው፤
ፍርድ ቤቶች በማያገባቸው ጉዳይ እየገቡ፣ የዜጐችን ባለመብትነትና መንግስትን ስራ እያወኩ ነው
ሼል ኢትዮጵያ አለማቀፍ አጭበርባሪ ነው፣
ኦይል ሊቢያ ከጋዳፊ ሀገር ስለመጣ፣ሼልን እንዲገዛ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር----
የመሳሰሉ አሳፋሪና ሕገወጥ ማጠቃለያዎች፣እንዴት ጉዳይ ሆነው በጋዜጣው ላይ ወጡ? ኦይል ሊቢያ ሕግና ስርዓት ባለበት ሀገር እየሰራ ይገኛል፡፡ ሕግና ስርአትንም አክብሮ ይሰራል፡፡ መብቱንም እንደዚሁ በሕግና ስርአት ያስከብራል፡፡

Read 2157 times