Saturday, 18 June 2016 12:55

ለካስ “ሆድ የባሰው” በዝቷል…!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የምስኪኑ ሰውዬ አካላት (የሰውነት ክፍሎች) እያደረሰብን ነው ባሉት ጥቃት እያመጹበት ነው፡፡
ዓይኖች፡— አንተ ግን ለምንድነው ራስህ ሀጢአት ሠርተህ እኛንም የምታሳጣን!
እሱ፡— ደግሞ ምን አደረግኸን ልትሉኝ ነው?
ዓይኖች፡— ለምንድነው የምታየውን ነገር የማትመርጠው! ለምንድነው እኛን በሆነ ባልሆነው ነገር ላይ የምትወረውረን!
እሱ፡— ምን እንደምትሉ እኮ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በቃ የፈለግሁት ነገር ላይ እወረውራችኋለሁ፡፡ ልታገለግሉኝ አይደል እንዴ የተፈጠራችሁት!
ዓይኖች፡— ልናገለግልህ ብንፈጠርስ… መሰቃየት አለብን! ስንት የሚታይ መልካም ነገር ባለበት ዓለም፤ እኛን ባልሆነ አቅጣጫ ለምን ትመራናለህ! ደግሞ አንተ ሚስት አለችህ አይደል እንዴ! የእሷ መንፈስስ ምን ይለናል!
እሱ፡— እሷ ደግሞ እዚህ ውስጥ ምን አገባት?
ዓይኖች፡— አንተ ውሻ ይመስል እኛን በሴቶች እግር ላይ የምትወረውረን ምን በደልንህ!… በሴቶች ዳሌ ላይ የምትወረውረን ምን በደልንህ!… በሴቶች…
እሱ፡— በቃ! እኔ ሴቶቹን መንገድ ላይ አላወጣኋቸው! ተሸፍኜ ልሂድላችሁ!
ዓይኖች፡— ማን ተሸፈን አለህ! መንገዱ ላይ ሴቶች ብቻ ነው እንዴ ያሉት! ደግሞስ… ኢንተርኔት በምትከታተልበት ጊዜ የምትከፍታቸው ድረ ገጾች በአንተ ዕድሜ ያለ ሰው የሚያያቸው ነው?
እሱ፡— እናንተ እንዲህ የምትንጣጡት ምናችሁ ተነካና ነው?
ዓይኖች፡— ክፉ ነገር ላይ እየወረወርከን ነዋ! ሞራላችን እየተነካ ነዋ! እንዴ እነኛ ሁሉ መሀረብ የምታክል ጨርቅ እንኳ ያላደረጉ ሴቶችን ፎቶ ስታይ የምትውለው!…እነሱ የተለዩ ፍጡር ሆነው ነው! ለማየት፣ ለማየት ሚስትህ አለችልህ አይደል!
እሱ፡— ሚስቴን እንኳን ተዉአት፣ የት ትሄዳለች!
ዓይኖች፡— ትሄዳለች እንጂ…እኛን ምን ላይ እየወረወርከን እንደሆነ ያወቀች ዕለት ያልቅልሀል! እኛንም ሀጢአት ውስጥ ለምን ትከተናለህ፡፡ ለምን ስለ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ ስለ ዓለም ሁኔታ፣ አዕምሮን ስለማበልጸግ የመሳለሉ ድረ ገጾችን አታይም!
እሱ፡— እናንተ… ዛሬ ማነው እኔ ላይ የላካችሁ!
ዓይኖች፡— ማንም አልላከንም..ግን አሁንም የማህጸን ዶክተሮች እንኳን ያን ያህል ቀርበው የማያዩትን በየድረ ገጹ ማየት እቀጥላለሁ ካልክ፣ ለሚስትህ የሚደርስበትን መንገድ እንፈልጋለን፡፡ ጨርሰናል፡፡
አጅሬው በዚሁ አለፈልኝ ሲል ለካስ “ሆድ የባሰው” በዝቷል!
ጆሮዎች፡— ኧረ እኛም ቀደም፣ ቀደም አንልም ብለን ነው እንጂ… የምንሆነው ነገር አጥተን ነው እንጂ----ዘንድሮ እየደረሰብን ያለው በደል አማሮናል!
እሱ፡— እናንተ ደግሞ ምን ሆንን ነው የምትሉት?
ጆሮዎች፡— ለምንድነው ነገሮችን እያጣራህ ወደ እኛ የማትልከው፡፡ ለምን አሰሱን ገሰሱን ታዘንብብናለህ! ተሳቀን ማለቃችን ነው እኮ!
እሱ፡— እኮ ምን ሆናችሁ…
ጆሮዎች፡— አንተ መስማት የምትወደው ክፉ ክፉውን ብቻ… እከሌ ታሰረ፣ ሀብታም የነበረው እከሌ ደሀ ሆነ፣ እከሌና እከሊት ተፋቱ…
እሱ፡— ታዲያ ወሬዎቹን እኔ አልፈጠርኳቸው…
ጆሮዎች፡— እንዲህ አይነት ነገር ወደ ጆሮዎቼ መላክ አልፈልግም ማለት ትችል ነበራ፡፡ ለምንድን ነው እከሌና እከሊት ሠላሳኛ የትዳር ዓመታቸውን አከበሩ የሚል ዜና የማይስብህ! ለምንድነው ከአብሮ አደግህ ውድቀት፣ ስኬቱን መስማት የማያስደስትህ!
እሱ፡— ይሄን ሁሉ የምታሰሙኝ እናንተው አይደላችሁ እንዴ!
ጆሮዎች፡— አንተ መስማት የምትፈልገውን ብቻ ስለምትልክልን ነዋ! መቼ ነው መልካም ሙዚቃ አሰምተኸን የምታውቀው! መቼ ነው መንፈስ የሚያስደስት ዝማሬ አሰምተኸን የምታውቀው! …
እሱ፡— ይበቃል…የሚላክላችሁን ከፈለጋችሁ ስሙ፣ ካልፈለጋችሁ ተዉት…
ጆሮዎች፡— አይ እንግዲህ…እንደዛ የምትል ከሆነ ያለ ፍላጎታችን ምን፣ ምን እንድንሰማ እያስገደደከን እንደሆነ አንድ ቀን እንዘረግፈዋለን፡፡ ጨረስን፡፡
አጅሬው በዚሁ አለፈልኝ ሲል ለካስ “ሆድ የባሰው” በዝቷል!
ምላስ፡—  ኧረ የእኔ ጉድ ከሌሎቹም ይለያል፡፡
እሱ፡— ዛሬ ሁላችሁም ተማክራችኋል እንዴ! አንተ ደግሞ ምን ሆንኩ ልትል ነው!
ምላስ፡—  ምን ያልሆንኩት ነገር አለ! ምን አለ ደግ፣ ደግ ቃላትን ብታንከባልልብኝ! በእኔ እየተጠቀምክ መርዝ፣ መርዝ ቃላትን የምትወረውረው ለእኔስ ብታስብልኝ ምን አለበት!
እሱ፡— ምን እያልክ ነው?
ምላስ፡— አንድ ቦታ አንድ ነገር ለማለት ትጠቀምብኛለህ፣ ሌላ ቦታ ሄደህ ደግሞ ያንኑ ነገር ገልብጠህ ሌላ ነገር ትናገራለህ! ሰዉ አቤት ምላስ እያለ፣ እኔኑ አይደል እንዴ የሚኮንነው!
እሱ፡— ቀጥል..
ምላስ፡—  ሥልጣን ወይ ገንዘብ ያለው፣ ባለ ጊዜ የሚባል ሰው ዘንድ ስትደርስ… “ደስ የሚል ልማት ነው፡፡ በአገሬ ኮራሁ፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ወላ ዱባይን፣ ወላ ኳታርን አልፈን ባንሄድ ከምላሴ ጸጉር…” ትላለህ፡፡ ማታውኑ ከአንተ ቢጤዎች ጋር ሰብሰብ ስትል… “በአገሬ እንዴት እንዳፈርኩ አልነግራችሁም፡፡ ምን አለ በሉኝ፣ ይቺ አገር ከአሥር ዓመት በኋላ የሞንጎሊያ የገጠር መንደር ባትመስል ትላለህ፡፡
እሱ፡— እና አንተ ምንህ ተነካ…
ምላስ፡— ጸጉር ይነቀል የምትለው ከእኔ ላይ አይደለም እንዴ! ደግሞ ምንህ ተነካ ትለኛለህ! እንዴት ምኔም አይነካም! ቃላቱን የምትናገረው እኔን ተጠቅመህ አይደለም እንዴ! ደግሞ የእኔ ጌታ፣ የእኔ ጌታ የምትለውን ዘወር ስትል ይሄ መልቲ፣ ይሄ ቅብጥርስዮ የምትለው እኔን በመጠቀም አይደለም እንዴ…እከሌን ከምድር ጋር ባለደባየው፣ እከሌን አፈር ድሜ ባላስግጠው፣ እከሊትን ራቁቷን ባላስኬዳት…የምትለው እኔን በመጠቀም አይደል እንዴ!
እሱ፡— እኮ አሁን ሥራ አቆማለሁ ነው የምትለው…
ምላስ፡— ሥራ አላቆምም፡፡ ምን በወጣኝ! ግን እያስገደድከኝ የማልፈልገውን እንድል እያደረገኸኝ እንደሆነ በሆነ ዘዴ አደባባይ አወጣዋለሁ፡፡ ሀጢአትህን ራስሀ ቻል፡፡ ጨረስኩ፡፡
አጅሬው በዚሁ አለፈልኝ ሲል ለካስ “ሆድ የባሰው” በዝቷል!
አእምሮ፡— እኔም ቅሬታ አለኝ፡፡
እሱ፡— አንተ! አንተም ቅሬታ አለኝ ባይ ሆንክ!
አእምሮ፡— ያውም የከበደ ቅሬታ…ለምንድነው መልካም መልካሙን ነገር የማታስብብኝ! ገና ለገና ሰው ገልጦ አያይም እያልክ፣ እኔንም ለምን ሀጢአተኛ ታደርገኛለህ!
እሱ፡— ምን አሰብኩ…ቤት ቢኖረኝ፣ መኪና ቢኖረኝ፣ ገንዘብ ቢኖረኝ… እያልኩ አይደለም እንዴ የማስበው!
አእምሮ፡— እሱን አላልኩም፡፡ ንገረኝ ካልክ…አሁን በቀደም የጓደኛህን ቆንጆ ሚስት እንዴት አባብለህ የልብህን እንደምታደርስ ስታስብ አልነበረም!
እሱ፡— እንዳመጣልህ አትናገር እንጂ …
አእምሮ፡— ንገረኝ ካልክ ገና እጨምርልሀለሁ… ያ የሂሳብ ክፍል ሀላፊ ይሆናል የተባለውን ሰውዬ እንዴት ስሙን እንደምታጠፋውና አንተ ቦታውን እንዴት እንደምትይዝ ስታስብ አልነበረም…
እሱ፡— እኔ በኋላ…
አእምሮ፡— ከአጎትህ ሃያ አምስት ሺህ ብር ተበድረህ፣ በኋላ ታክሲ ላይ ወሰዱብኝ ምናምን ብለህ እንዴት እንደምታስቀርበት ስታስብ አልነበረም! ንገረኝ ካልክ…  ያ በስንት እጥፍ አልፎህ የሄደውን አብሮ አደግህን በፖለቲካ እንዴት አስጠቁረህ ከእንጀራው እንደምታፈናቅለው ስታስብ አልነበረም እንዴ! ደግሞ…
እሱ፡— የፈለግሁትን ባስብ አንተ ምን ቸገረህ… አስብ የተባልከውን ማሰብ ነው…
አእምሮ፡— ምናልባት ለጊዜው አቅም ስለሌለኝ…የተባልኩትን አስብ ይሆናል፡፡ ግን አንድ ቀን ዘዴ ፈልጌ ጉድህን ለዓለም ባልረጨው ምን አለ በለኝ! ጨረስኩ፡፡
አጅሬው በዚሁ አለፈልኝ ሲል ለካስ “ሆድ የባሰው” በዝቷል!
ስሙን የደበቀ፡— ኧረ እኔም የምነግረው አጥቼ ነው እንጂ መከራዬን እያበላኸኝ ነው…
እሱ፡— አንተ ደግሞ ማን ነኝ ባይ ነህ…
ስሙን የደበቀ፡— ስሜ ይቆይልኝ…
እሱ፡— እኔው ላይ እያለህ እንዴት ነው ስምህ የሚቆይልህ…
ስሙን የደበቀ፡— አንተ ብታውቅ ሌላው እንዲያውቀኝ አልፈልግማ…
እሱ፡— እሺ ምን ሆንኩ ነው የምትለው…
ስሙን የደበቀ፡— ደከመኝ…በጣም ደከመኝ! እንዴ ፋታ ስጠኝ እንጂ!
እሱ፡— ምን ሆንኩ ነው የምትለው! የተፈጠርከው ልታገለግል አይደለም እንዴ…
ስሙን የደበቀ፡— ቢሆንስ፣ በቀን አንዴ ትንሽ ሆኖብህ በቀን ሁለቴና ሦስቴ የምታለፋኝ…እኔ ቻርጅ የምደረግ ላፕቶፕ ነኝ…በናፍጣ የምሠራ ጄኔሬተር ነኝ!…እዘንልኝ እንጂ!
እሱ፡— እዘንልኝ ማለት አትገለገልብኝ ለማለት ነው!
ስሙን የደበቀ፡— ታዲያ አንዳንዴ ለቁም ነገር አድርገዋ! እስከ ዛሬ ታለፋኛለህ፣ ታለፈኛለህ-----ከእኔ ስም ጋር የሚያያዝ ግን ምንም ቋሚ ነገር አላስቀመጥክም፡፡
እሱ፡— ትሰማኛለህ…የተፈጠርከው ልታገለግል ነው፣ ታገለግላለህ፡፡
ስሙን የደበቀ፡— እንደ እሱ ነው!…እሺ እንደዛ ካልክ… እኔ ደግሞ ታየኛለህ፣ ለወር ያህል ለግሜ ሥራ ባላቆም!
እሱዬው ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡ ቂ…ቂ..ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6388 times