Saturday, 18 June 2016 13:08

የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት 800 ሺህ ዜጎችን ስራ ሊያሳጣ ይችላል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

13 የአገሪቱ ታዋቂ ሳይንቲስቶች በአባልነቷ መቀጠሏን ደግፈዋል
የእንግሊዝን የአውሮፓ ህብረት አባልነት ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሚወስነው ህዝበ ውሳኔ በመጪው ሳምንት የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአባልነቷ ትውጣ የሚለው አብላጫ ድምጽ የሚያገኝና ውሳኔው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፣ 800 ሺህ ያህል እንግሊዛውያን ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተዘገበ፡፡
ሴንተር ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ቢዝነስ ሪሰርች የተባለው የአገሪቱ የጥናት ተቋም ያወጣውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ በአገሪቱ ህዝቦች ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው የተባለው ይህ ህዝበ ውሳኔ፣ እንግሊዝን ከህብረቱ አባልነት ውጭ ካደረገ፣ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ህይወታቸውን ይመሩ የነበሩ 800 ሺህ ያህል ዜጎች ስራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ 13 እንግሊዛውያን ሳይንቲስቶችም፣ እንግሊዝ በህብረቱ አባልነቷ ትቀጥል የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ እንደሚቀበሉት ለቴሌግራፍ ጋዜጣ በላኩት ይፋ የአቋም መግለጫ ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣዩ ህዝበ ውሳኔ ላይ በህብረቱ አባልነቷ ትቀጥል ብለው ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ያስታወቁት ሳይንቲስቶቹ፣ አገሪቱ ከህብረቱ አባልነቷ መውጣቷ ሳይንሳዊ ምርምሮችንና ጥናቶችን የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸው፣ ህብረቱ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች በትብብር እንዲሰሩ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ላቅ ያለ ሚና ሲጫወት እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡

Read 1510 times