Saturday, 18 June 2016 13:09

ባንግላዴሽ ከ11 ሺህ በላይ የሽብር ተጠርጣሪዎችን አሰረች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በባንግላዴሽ ባለፈው ሳምንት የታጠቁ ሃይሎች በፈጸሙት ተከታታይነት ያለው ጥቃት፣ በበርካታ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተከትሎ የጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ የጀመረው የአገሪቱ መንግስት፤ ከ11 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሰሞኑን በርካታ ዜጎችን በመግደል ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 150 ታጣቂዎችና በአገሪቱ በተከሰቱ ብጥብጦች በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል በሚል የጠረጠራቸውን ከ11 ሺህ በላይ ግለሰቦች ማሰሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ጃማቱል ሙጅሃዲን የተባለው አክራሪ ቡድን አባላትና ለጥፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ቢልም፣ ባንግላዴሽ ናሽናሊስት ፓርቲ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ ግን፣ የመንግስት እስር በአባላቶቼ ላይ ያነጣጠረ ነው፤ 2 ሺህ 100 አባላቶቼና ደጋፊዎቼ ታስረውብኛል ማለቱ ተዘግቧል፡፡
በባንግላዴሽ ባለፈው አንድ አመት ብቻ 35 ያህል ተመሳሳይ የሽብር ጥቃቶችና ግድያዎች መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአገሪቱ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ አንድ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድንም ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል ሃያ ሶስቱን ለመፈጸሙ ሃላፊነት መውሰዱን ገልጧል፡፡

Read 1144 times