Saturday, 18 June 2016 13:16

ማይክሮሶፍት ሊንክዲንን በ26.2 ቢ ዶላር ሊገዛው ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ፣ሊንክዲን የተባለውን ዝነኛ የማህበራዊ ድረገጽ በ26.2 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ላይ መድረሱን እንዳስታወቀ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው በታሪኩ ከፍተኛውን ግዢ የሚፈጽምበት ነው በተባለው በዚህ ስምምነት ወደ ማህበራዊ ድረገጽ አለም በይፋ ይቀላቀላል ያለው ዘገባው፤ ማይክሮሶስፍት ሊንክዲንን መግዛቱ ከፌስቡክና ከጎግል ጋር ለሚያደርገው የቴክኖሎጂ ፉክክር ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል መባሉንም ገልጧል፡፡
በቢዝነስ ላይ በተሰማሩ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚዘወተረው ሊንክዲን የማህበራዊ ድረገጽ፤ከ400 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመው ዘገባው፣ ማይክሮሶፍት ግዢውን እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ አጠናቅቆ ሊንከዲንን በእጁ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቋል፡፡
የሊንክዲን ተጠቃሚዎች ቁጥር ባለፉት አመታት በአማካይ በ19 በመቶ እድገት በማሳየት፣ 433 ሚሊዮን ያህል መድረሱን የጠቆመው ሮይተርስ፤ በትርፋማነቱም እንደማይታማና በማይክሮሶፍት ባለቤትነት ስር መተዳደሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን አስረድቷል፡፡
ማይክሮሶፍት ከአምስት አመታት በፊት ስካይፒን በ8.5 ቢሊዮን ዶላር፣ የኖኪያ የሞባይል ቀፎ አምራችነትንም በ7.2 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ሁለቱ ግዢዎች በታሪኩ ከፍተኛ ወጪ ያወጣባቸው ተብለው ተመዝግበው እንደነበርም ገልጧል፡፡

Read 1022 times