Saturday, 25 June 2016 11:52

“ፊቴ ተመልሶ እንዲመጣ እፈልጋለሁ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(36 votes)

ባለፈው ፋሲካ አካባቢ ደወለልኝ፡፡ ሀዋሳ ነው ያለሁት አለኝ፡፡ እኛ ጋ የሚሰራ አንድ ጓደኛ አለው፡፡ እሱ ጋ መጥቶ እንዳረፈ በኋላ ነው
የሰማሁት፡፡ እኔም የምኖረው እዚያው የምሰራበት ሆቴል ክፍል ተሰጥቶኝ ነው፡፡ የምኖረው ሀዋሳ ነኝ ያለው ለካ እዛ መጥቶ ነው፡፡ ለአንድ
ሳምንት ያህል የምሰራበት ሆቴል መጥቶ ምግብ በልቶ አይቶኝ ይሄድ እንደነበር ቆይቼ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን አይቼው አላውቅም፡፡ አንድ ቀን
“አንቺ አምሮብሻል፤ እኔ ግን እየተሰቃየሁ ነው” አለኝ፡፡ እኔ ታዲያ ምን አጠፋሁ አልኩት፡፡ “በይ ለማንኛውም 500 ብር አበድሪኝ” አለኝ፡፡
• አልጋ የለም ተብዬ እየተመላለስኩ ነው የምታከመው
• ለሰርጀሪ ከ60-80 ሺህ ብር ተጠይቄያለሁ
• በደረሰብኝ ጥቃት ህዝብና መንግሥት ይፋረደኝ

አሲዱን የደፋብሽ ማነው?
ጥቃቱን ያደረሰብኝ ሰለሞን በላይ የተባለ የቀድሞ ጓደኛዬ (ፍቅረኛዬ) ነው፡፡ ትናንትና (ሰኔ 17) አንድ ወር ሞላኝ፡፡ እንዲሁ እንደተቃጠልኩና እንደተንገበገብኩ አለሁ፡፡
በምን ምክንያት ነው ጥቃቱን ያደረሰብሽ?
ለሶስት ዓመታት ያህል በፍቅር አብረን አሳልፈናል፡፡ ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ አብረን መሆናችን ካልቀረ ለምን አንጋባምና ተጠቃልለን አንቀመጥም አልኩት፤ ምላሽ የለም፡፡ በተደጋጋሚ ይህንኑ ጥያቄ አነሳሁ፡፡ እሱ ደግሞ “በጓደኝነታችን እንቀጥል እንጂ ላገባሽ አልፈልግም፡፡ አሁን እናቴን እየረዳሁ መቆየት እፈልጋለሁ” አለኝ፡፡ እኔ እናትና አባት የለኝም፤ ነገር ግን ታናናሽ እህቶች አሉኝ፤ የእኔን እጅ ጠብቀው የሚኖሩ፡፡ ስለዚህ በየፊናችን የምናወጣውን ብር ወደ አንድ አምጥተን፣ እኔና አንተ አንድ ቤት ሆነን፣ እኔም እህቶቼን አንተም እናትህን እናግዛለን ብዬ ነገርኩት፡፡ በጭራሽ አንጋባም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ዓላማው ስላልገባኝ “በቃ እንለያይና የየራሳችንን ህይወት እንኑር” አልኩት ጥያቄዬን ተቀበለ፡፡ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር አልተገናኘንም ነበር፡፡
ታዲያ እንዴት ተገናኝታችሁ ነው አሲዱን የደፋብሽ?
ባለፈው ፋሲካ አካባቢ ደወለልኝ፡፡ ሀዋሳ ነው ያለሁት አለኝ፡፡ እኛ ጋ የሚሰራ አንድ ጓደኛ አለው፡፡ እሱ ጋ መጥቶ እንዳረፈ በኋላ ነው የሰማሁት፡፡ እኔም የምኖረው እዚያው የምሰራበት ሆቴል ክፍል ተሰጥቶኝ ነው፡፡ የምኖረው ሀዋሳ ነኝ ያለው ለካ እዛ መጥቶ ነው፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል የምሰራበት ሆቴል መጥቶ ምግብ በልቶ አይቶኝ ይሄድ እንደነበር ቆይቼ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን አይቼው አላውቅም፡፡ አንድ ቀን “አንቺ አምሮብሻል፤ እኔ ግን እየተሰቃየሁ ነው” አለኝ፡፡ እኔ ታዲያ ምን አጠፋሁ አልኩት፡፡ “በይ ለማንኛውም 500 ብር አበድሪኝ” አለኝ፡፡ እኔ ብሩን ላለመስጠት አልነበረም ግን ድጋሚ ካገኘሁት እንደገና ነገር ይመጣብኛል ወይ አብረን እንቀጥል ይለኛል በሚል ፍራቻ፣ ብሩን ልሰጠው ፈቃደኛ አልሆንኩም፡፡ “እሺ ተይው” ብሎ ዝም አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሊት ስምንት ሰዓት፣ ዘጠኝ ሰዓት ስልክ እየወደለ ይረብሸኛል፤ መተኛት አልቻልኩም፡፡ ይህ ሁኔታ ለሳምንት ያህል ዘለቀ፡፡ አሲዱን ከመድፋቱ በፊት በጩቤ ሊገድለኝ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡
እንዴት አወቅሽ?
ስሙንና መታወቂያውን ቀይሮ ለካ እኔ የምሰራበት ሆቴል ውስጥ አልጋ ይዞ ነበር ከዚያ አልጋ ክፍሎቹ እሱ ክፍል ውስጥ ጩቤ ፍራሽ ስር አግኝተው ሪሴፕሽን አስረክበዋል፡፡ ክፍሉ ገብቶ ሲያጣው ክፍሌ ውስጥ እቃ አግኝታችኋል በሚል ሰራተኞቹን ጠይቆ ነበር፡፡ ሰራተኞቹ እኔን ይወቀኝ አይወቀኝ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እኔም ራሴ እዚያ ስለመኖሩ አይቼው አላውቅም ነበር፡፡ እኔ 307 ቁጥር፣ እሱ ደግሞ 304 ቁጥር ነው ያደርነው፡፡
ከዚያስ?
ልክ በ17 ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ የክፍሌ በር ተንኳኳ፡፡ በመስኮት ገለጥ አድርጌ ሳይ ማንም የለም፡፡ ተመለስኩና ልብሴን ለባበስኩ፡፡ ሁለት ረዳቶቼን ቀስቅሼ ወደ ስራ ልገባ የክፍሌን በር ልቆልፍ ስል፣ ከኋላዬ ሆኖ “መሲ” ብሎ ጠራኝ፡፡ ዞር ስል የያዘውን አሲድ ፊቴ ላይ ለቀቀው፡፡ ስጮህና ስቃጠል “እሰይ” አለ፡፡ እንደምታይው ከቀኝ ትከሻዬ እስከ ጣቴ ድረስ ደፍቶብኝ እጄ አይንቀሳቀስም (በፋሻ የተጠቀለለ እጇን እያሳየችኝ) በዚህም አልረካም፡፡ ከአራተኛ ፎቅ እስከ ሁለተኛ ፎቅ እያዳፋና እያንከባለለ ሰባበረኝ፡፡ ሁለተኛ ፎቅ ያደሩ እንግዶች ሲወጡ አንዱ እኔን አነሳኝ፡፡ አንዱ ሮጦ እሱን ያዘው፡፡ ክፍሌ ሁሉ ገብቶ ልብሴ ላይ … አልጋው ላይ … ሳይቀር አሲዱን አርከፍክፎታል፡፡
አሁን የት ነው ያለው?
እስር ላይ ነው ተይዟል፡፡ አሲዱን ሀምሳ ብር እንደገዛውም አምኗል፡፡
የመጀመሪያ ጊዜ ህክምና ያገኘሺው የት ነው?
ባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ለሶስት ቀን ተኛሁ፤ አልተቻለም፡፡ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል መጣሁ፡፡ እዚህ ግን አልጋ የለም ብለውኝ ተኝቼ መታከም ባለመቻሌ፣ አሲዱ በመላ ሰውነቴ እየተሰራጨ፡፡ ነው አሁን አይኔም ደክሟል፤ ጥርሴም ማኘክ አይችልም፤ ልሞት ነው (ለቅሶ …)
ያገኘሽው የህግ ድጋፍ የለም?
ባህር ዳር ሴቶችና ወጣቶች ሄጄ “እርዱኝ” ስል፣ “እኛ የእርዳታ ድርጅት አይደለንም፤ ልንረዳሽ አንችልም ነገር ግን ምክር ልንመክርሽ እንችላለን” አሉኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ምክር የሚያቃጥለኝን አሲድ ከውስጤ አያወጣልኝም፤ እየተቃጠልኩ ነው፡፡
ዳንግላስ የህግ ድጋፍ አላገኘሽም?
ወይ አንቺ ምንም ድጋፍ አላገኘሁም፤ ሄጄ ግን እንዲረዱኝ ጠይቄ ነበር፡፡ ፈለገ ህይወት በነበርኩበት ጊዜ ሲብስብኝ፤ አንድ ጌታቸው የሚባል ከአሜሪካ ለእረፍት ዳንግላ የመጣ ሰው ለአስር ቀናት የግል ሆስፒታል አስገብቶኝ ነበር፡፡ የምሰራበት ሆቴል ነበር የሚመገበው፡፡ “እንዲህ አይነት ምግብ ትስራልኝ” ሲል አለመኖሬንና የደረሰብኝን ሲነግሩት፣ አሳክሞኝ አልሻለኝ ሲል፣ እዚህ አዲስ አበባ ያደረሰኝ እሱ ነው፡፡ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡
ልጁ ፍርድ ቤት አልቀረበም?
ቀርቦ በዋስ ካልተፈታሁ ብሎ እየተከራከረ ነው አሉ፡፡ እዚያ ያሉ ፖሊሶች “ክሱን አጠናክሪ፤ በዋስ ልፈታ” ብሎ እየተከራረከረ ነው ብለው ደወሉልኝ፡፡ እኔ እምለው ፊቴ ፈርሶ እያየሽው ነው፣ አልጋ አጥቼ ሆስፒታል እየተመላለስኩ ነው፣ ለአንድ ለሁለት ጊዜ ለምጠቀመው መድሀኒት 150 እና 160 ብር እየተጠየኩ እየተቸገርኩ ነው ህግ ባለበት አገር ይህንን ችግር ይዤ እንዴት ፍ/ቤት ልቁም? እኔን የሚታደገውስ ህግ ከወዴት ነው ያለው የመንግስት ያለህ እያልኩ ነው፡፡ ወጪውን አልቻልኩትም፡፡
አሁን ያገኘሁሽ አንድነት ባርና ሬስቶራንት አንድ የመኝታ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ቤቱ የማን ነው? እንዴትስ አስጠጉሽ?
ይሄ ቤት ዳንግላ የምሰራበት ሆቴል ባለቤት ልጅ ነው፡፡ እሷ አስጠግታኝ ነው፡፡ ይህቺ የምታያት ታናሽ እህቴ ናት፤ አለምፀሐይ ትባላለች፡፡ እሷ ናት የምታስታምመኝ ምግብና ሌላ ወጪ በራሴ ነው አልጋውን ብቻ ነው እየረዳችኝ ያለችው፤ እግዚአብሔር ይስጣት፡፡
አሁን ምን እንዲደረግልሽ ነው የምትፈልጊው?
ወደ ውጭ ሄጄ የምታከምበትን መንገድ፣ ህይወቴ የሚተርፍበትን መላ፣ መንግስትም ሆነ ለነፍሴ ያለ ማንኛውም ሰው እንዲረዳኝ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ጥቃት ያደረሰብኝን ደግሞ ህግ አስፈላጊውን ቅጣት እንዲሰጥልኝ ፍትህ እጠይቃለሁ፡፡ እስር መታሰር ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከሚላት ላይ አሲድ የደፋው ሰው ታስሯል፤ መንግስት እየቀለበው እንቅልፉን እየተኛ ነው፡፡
የሆነ የፊቱ ክፍል ላይ አሲድ ደፍቶ ስቃዩን እንዲቀምሰው ቢደረግ ሌላው ይህን ለመስራት አይደፍርም ነበር፡፡ አሁንም እኔ ላይ የደፋብኝ ከመታሰር ውጭ ምንም እንደማይደርስበት ስለሚያውቅ ነው፡፡ ይታሰራል በቃ ምን ይመጣበታል… ፊቱ… ሞራሉ… አይበላሽ፡፡
ሀኪሞቹ የጉዳትሽ መጠን ምን ያህል ነው አሉሽ?
ፊቴ እስከ ውስጠኛው ቆዳዬ ድረስ በጣም ተጎድቷል፡፡ አይኔም እንዳይጠፋ ያሰጋኛል፡፡
ሰርጀሪ (የቀዶ ጥገና ህክምና) መሰራት ያስፈልግሻል ብለውኛል፡፡ ግን እንዴት አድርጌ ገንዘቡን እችለዋለሁ? እዚህስ አገር በጥሩ ሁኔታ ፊቴ ተሰርቶ ወደ ቀድሞው ሁኔታዬ መመለስ እችላለሁ ወይ?
ከአሲዱ ቃጠሎ ጋር ግን ይሄው አንድ ወር ሙሉ እያሰቃየኝ ነው፡፡ ፊቴን እፈልገዋሁ፤ ውበቴ ተመልሶ እንዲመጣ እፈልጋለሁ (ለቅሶ …)   
ለሰርጀሪ ምን ያህል ተጠየቅሽ?
ከ60-80 ሺህ ብር እንደሚያስፈልገኝ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር ጥሩ ህክምና አገኛለሁ ወይ? ታናናሽ እህቶቼን የሚረዳቸው የለም፡፡ ሜዳ ላይ ወደቁ ማለት ነው፡፡ እኔም ገና በ24 ዓመቴ እንዲህ መሆኔ ሁሌም የሚያስለቅሰኝ ነው፡፡ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ይፋረደኝ፡፡ ፍርዱን ለህዝብና ለመንግስት ትቼዋለሁ፡፡ አሁን ግን ነፍሴ የሚተርፍበትን፤ ወደ ውጭ ሄጄ የምታከምበትን ነገር መንግስት ይፈልግልኝ፡፡
አሁን የት ነው ሰለሞን የታሰረው? እድሜውስ ስንት ነው?
ዳንግላ ነው የታሰረው፤ እድሜው 29 ወይም 30 ቢሆነው ነው፡፡
 አሁን የሰጋሁት በዋስ ከተለቀቀ ስላልሞትኩ አልረካምና ታናናሽ እህቶቼ ላይ፣ እናትና አባት የሌላቸው ምስኪኖች ላይ ሌላ ጥቃት እንዳያደርስባቸው እያልኩ ነው፡፡ እሱን ደብቆ አስቀምጦ ምግብ ሲያበላው፣ ስለኔ ጥቆማ ሲሰጠው የነበረው ሚካኤል የተባለ የስራ ባልደረባዬ፤ ታስሮ በዋስ እንደተፈታና ይሄኛውም ክሱን ካላጠናከርኩ፣ በዋስ ሊፈታ እንደሚችል እየተነገረኝ ነው፡፡ ስለዚህ ፍትህ… ፍትህ ፍትህ እሻለሁ፡፡ ረጅም ለቅሶ … ሰለሞን ስራው ምንድን ነው?
የአስተናጋጆች ኃላፊ (ሄድ ወይተር) ነው፡፡ ዳንግላም ለአንድ ሳምንት የሆነ ሆቴል ውስጥ ሄድ ዌይተር ሆኖ ተቀጥሮ እኔን ሲከታተል ነበር የቆየው፡፡
አሁን በግል እየረዱሽ ያሉ ሰዎች አሉ?
አንዳንድ ሰዎች በግል እየመጡ አይተውኝ አፅናንተውኝ ይሄዳሉ ባህርዳር “ሰመር ላንድ” ሆቴል ስሰራ የሚያውቀኝ አንድ ፈረንጅ መጥቶ፣ አንድ ሺህ ብር ሰጥቶኝ ሄዷል፡፡ ጌታቸው ያልኩሽ ዳንግላ የሚያውቀኝ አሁን እስካለሁበት ድረስ ደግፎኛል፡፡ አሁንም ግን ማንም የለኝም፡፡  ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገኛል፡፡




Read 18479 times