Saturday, 25 June 2016 11:56

የአውሮፓ ነባር ፓርቲዎች ጉድ ፈልቶባቸዋል!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ምክንያቱና ሰበቡ ምንድነው?

    በእንግሊዝ ፓርላማ ከ99% በላይ መቀመጫ በመያዝ የሚታወቁ አራቱ አውራ ፓርቲዎች፤ ለወትሮው በአይነ ቁራኛ የሚተያዩ ብርቱ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ በትናንቱ ምርጫ ግን እርስ በርስ አልተፎካከሩም፡፡ ያለወትሯቸው ለአንድ ዓላማ በጋራ ለሁለት ወራት ቀስቅሰዋል፣ “እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መፈናቀል የለባትም” በማለት፡፡
የገዢ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ዋና ዋና መሪዎች፣ እንዲህ ተባብረው ቢቀሰቅሱም፣ አልተሳካላቸውም፡፡ አብዛኛው እንግሊዛዊ፣ የመሪዎቹን ቅስቀሳና ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ትቶ፤ በትናንቱ ምርጫ፣ “ከአውሮፓ ህብረት ለመገላገል” ወስኗል - 51 በመቶ ያህሉ መራጭ፡፡
ዋና ዋናዎቹ የፓርቲ መሪዎች ብቻ አይደሉም የተሸነፉት፡፡ የእንግሊዝ ብሄራዊ ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት … የማስጠንቀቂያ መዓት ሲያዥጎደጉዱ ከርመዋል፡፡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ከለቀቀች፣ ኢኮኖሚዋ በ6% ያሽቆለቁላል፤ ፓውንስ ስተርሊንግ ይረክሳል፤ ዋጋ ይንራል፤ የዜጎች ገቢ በ3ሺ ዶላር ይቀንሳል … ማስፈራሪያው ስፍር ቁጥር የለውም፡፡
ከአውሮፓ አንጋፋ መሪዎች በተጨማሪ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም፣ እንግሊዛውያንን አስፈራርተዋል፡፡ “በንግድና በኢንቨስትመንት ዙሪያ፣ ቅድሚያ ሰጥተን የምንደራደረው ከአውሮፓ ህብረት ጋር ነው፤ እንግሊዝ ከህብረቱ ከወጣች ውራ ትሆናለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል ኦባማ፡፡
ይሄ ሁሉ የማስፈራሪያ ውርጅብኝ ውጤት አላስገኘም፡፡ በተለይ ደግሞ፤ የአገሪቱ አንጋፋ ፓርቲዎችና ዋና ዋና መሪዎች፣ እንዲህ ተሰሚነት ማጣታቸው አስገራሚ ነው፡፡ እነማን እንዳሸነፉ ደግሞ ተመልከቱ፡፡ ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ያፈነገጡ የተወሰኑ ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም  ለዓመታት በፓርላማ አንዲት ወንበር ለማግኘት ያቃተው ፓርቲ… እነዚህ ናቸው “ከአውሮፓ ህብረት መገላገል አለብን” በማለት ሲቀሰቅሱ የነበሩት፡፡ እናም፣ ነባሮቹ አውራ ፓርቲዎችና መሪዎች ተሸንፈው፣ ድል የአፈንጋጮች ሆነ፡፡
በምርጫው ሽንፈት ማግስት፣ ዳቪድ ካሜሮን፣ ከጠቅላይ ሚንስትርነት እና ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ መሪነት ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
ተቃዋሚያቸው የሌበር ፓርቲ መሪም፣ ከሃላፊነታቸው እንዲወርዱ፣ ከራሳቸው ፓርቲ ፖለቲከኞች ጥያቄ ተነስቶባቸው፣ አፋፍ ላይ ደርሰዋል፡፡
ይበልጥ አስገራሚ የሚሆነው ግን፤ ሌሎች የአውሮፓ አገራትም በተመሳሳይ አስደንጋጭ ማዕበል እየተናጡ መሆናቸው ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት፣ በጣሊያን ከተሞች በተካሄዱ ምርጫዎች፤ በተለይ በዋና ከተማዋ በሮም እንዲሁም በቱሪን፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች አሸናፊ አልሆኑም፡፡ እስከዛሬ ስልጣን በወጉ ያልቀመሰ ፓርቲ ነው ገንኖ የወጣው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በኦስትሪያ ለ60 ዓመታት ስልጣን ላይ ሲፈራረቁ የነበሩ ሁለት ነባር ፓርቲዎችም፣ ተዘርረዋል፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ፣ የሁለቱ ነባር ፓርቲዎች ድርሻ 80% ያህል ነበር፡፡ ባለፈው ወር በተካሄደው ተመሳሳይ ምርጫ ግን፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ የሁለቱ ነባር ፓርቲዎች ድርሻ ቁልቁል ወርዶ ተፈጥፍጧል፡፡ ከ11% የበለጠ ድምፅ ስላላገኙ፣ በማጣሪያው ከምርጫ ተሰናብተዋል፡፡
በተቃራኒው ስልጣን ቀምሰው የማያውቁ … በጭራሽ ከስልጣን አጠገብ ደርሰው የማያውቁ … በአንድ ወገን ከኢንቨስትመንት ይልቅ ድጎማን የሚያወድሱ የሶሻሊዝም ግርፍ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ዘረኝነትን የሚያናፍሱ የፋሺዝም ግርፍ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ብልጫ አግኝተዋል፡፡
በግሪክም፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች ተሸንፈው፣ የሶሻሊዝም አራጋቢዎች ስልጣን ይዘዋል፡፡ በስፔንም እንዲሁ፣ አምስት ዓመት ያልሞላቸው ፓርቲዎች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመግነናቸው፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች፣ የፓርላማ አብላጫ ወንበር መያዝ አልቻሉም፡፡ ምን ይሄ ብቻ! የአየርላንድ ነባር ፓርቲዎች፣ ተመሳሳይ ፅዋ ተጎንጭተዋል፡፡ ፊንላንድና ዴንማርክም እንዲሁ፣ ነባር ፓርቲዎችን በሚያናጋ ማዕበል ተመትተዋል፡፡ በጀርመን ዘንድሮ በተካሄደ የክልሎች ምርጫ፣ ከአምስት ዓመት በፊት ያልነበረ አዲስ ፓርቲ፣ ከነባሮቹ የበለጠ ድምፅ ሲያገኝ ታይቷል፡፡ በፈረንሳይም እንዲሁ፡፡ ….
እንደ ነባሮቹ ፓርቲዎች ሁሉ፣ ነባሩ የኢኮኖሚ ስርዓትም እየተንገራገጨ ነው፡፡ መንግስታት በየጊዜው የድጎማ መዓት ይፈለፍላሉ፡፡ ከዜጎች ገቢ ግማሽ ያህሉን ታክስ እየቆረጡ ይወስዳሉ፡፡  ይህም  አልበቃቸውም፡፡ መረን የተለቀቀ ወጪያቸውን ለመሸፈን፣ መንግስታት በትሪሊዮን ዶላሮች ብድር ተዘፍቀዋል፡፡ እንዲህ በመንግስታት ጣልቃ ገብነት የተቀየጠው የአውሮፓ የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ከቀውስ መውጣት አቅቶታል፡፡ ከመንፏቀቅ ያለፈ እድገት ማስመዝገብ ተስኖታል፡፡ስራ አጥነት፣ ከ10% በታች አልወርድ ብሏል፡፡
ነባሮቹ ፓርቲዎች፣ ቅይጥ ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻልና የነፃ ገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት አልቻሉም፡፡ ተሰሚነታቸውም ከኢኮኖሚው ጋር ተዳክሟል፡፡
ችግሩ ምንድነው? በነባሮቹ ምትክ፣ በምድረ አውሮፓ እየገነኑ የመጡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ ከቀድሞዎቹ የባሱ እንጂ የተሻሉ አይደሉም፡፡ በተጨማሪ የታክስ ጫናና በተጨማሪ የድጎማ ብክነት፣ ኢኮኖሚን የሚያዳክሙ የሶሻሊዝምና የፋሺዝም ግርፍ ናቸው - እንደ አሜሪካውያኑ በርኒ ሰንደርስ እና እንደ ዶናልድ ትራምፕ፡፡

Read 1557 times