Saturday, 25 June 2016 12:00

ያሻሽላል የተባለው ያባብሳል

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(11 votes)

በየመን በኩል የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር፣ ዘንድሮ ‘ሪከርድ’ ሰብሯል።
በአሜሪካ፣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ዘንደሮ ተጧጡፏል በ100 ሺ ቸርቻሪ፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካ ፓርላማ (ኮንግረስ)፣ …የድራማ መድረክ ሆኖ ሰንብቷል። የዲሞክራቲክ ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኞች፣... ረቡዕ እለት ነው፤ አዳራሹን ‘በቁጥጥር ስር አውለነዋል’ በማለት ያወጁት። ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ሴናተሮችም ጭምር፣... እንዳኮረፈ ተማሪ፣ የአዳራሹ ወለል ላይ ተቀምጠው፣...
“የጦር መሳሪያ ሽያጭን ለመቆጣጠር አዲስ ህግ መውጣት አለበት፡፡ አለበለዚያ አንነሳም” አሉ፡፡ ታዲያ ምን ችግር አለው? ህግ ማውጣት የነሱ ስራ ነው - የኮንግረስና የሴነት አባላት ስራ። ከአንድም ሁለት ሦስት የሕግ ረቂቆች ተዘጋጅተዋል። ነገር ግን፣ የተረቀቀውን ህግ ለማፅደቅ፣ በቂ የድጋፍ ድምፅ ያስፈልጋል። የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ደግሞ፣ በኮንግረስ... እንዲሁም በሴነት ውስጥ የያዙት የወንበር ብዛት፣ ከግማሽ በታች ነው። የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ተጨማሪ ገደብና ቁጥጥር ለመጫን ያረቀቁት ህግ፣ ሊፀድቅ አልቻለም።
አብዛኛውን ወንበር የያዙ በርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ቁጥጥሮችን አይደግፉም። መሳሪያ የመታጠቅ ጥያቄ፣ በአሜሪካ እንደ ዋዛ የሚታይ ጉዳይ አይደለማ። ትልቅ ጉዳይ ከመሆኑ የተነሳ፣ የሕገመንግስቱ የመብቶች ዝርዝር ውስጥ በተራ ቁጥር ሁለት ነው የተጠቀሰው። ቁጥር አንድ ላይ፣ መንግስት የፕሬስ ነፃነትን የሚጥስ ህግ ማውጣት እንደማይችልና በመንግስት የሚደገፍ ሃይማኖት እንደማይኖር ተደንግጓል። ቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ፣ ጦር መሳሪያ የመታጠቅ መብት!
ይሄ መብት መነካት የለበትም በማለት የሚከራከሩ በርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ አብዛኛውን ወንበር ስለያዙ፣ የቁጥጥር ህጎችን ለማፅደቅ የድጋፍ ድምፅ አይሰጡም። የእለቱ፣ የስራ ሰዓት አበቃ፤ ስብሰባው ተበተነ…
ሁሉም ባይሆኑም፣ በርካታ ዲሞክራቶች፣ ይህንን አሜን ብለው አልተቀበሉም። ህግ ካልፀደቀ፣ ከአዳራሹ ለቀን አንወጣም ብለው ወለሉን “ተቆጣጠሩት”። “Occupy” እንዲሉ። የአዳራሹ ካሜራዎች፣ በቲቪ የቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፉ ይታወቅ የለ? አዳራሹን የተቆጣጠሩት ዲሞክራቶች፣ የቲቪ ካሜራዎቹንም በቁጥጥር ስር አውለው ዲስኩር ሲያስተላለፉ ለመዋልና ለማደር ተስፋ ነበራቸው።
ግን፣ አፈጉባኤው፣ የእለቱ ስራ ተጠናቅቋል ብለው ከአዳራሹ ሲወጡ፣ አዳራሹን ለመቆለፍ ባይችሉም፣ የካሜራዎቹ ማጥፊያና ማብሪያ በእጃቸው ነው። ስለዚህ፣ በቲቪ ሲደሰኩሩ ማደር የለም - የአዳራሽ ወለል ላይ ተቀምጠው ማደር ቢቻልም።
የሰሞኑ ድራማና ግርግር አዲስ ክስተት አይደለም፡፡
ከሁለት ዓመት በፊትም፣ ተመሳሳይ የዘመቻ ሆይ ሆይታ ተፈጥሮ ነበር - የጦር መሳሪያ ሽያጭ ቁጥጥርን ለማጥበቅ፡፡ አስቂኙ ነገር ምንድነው? ፖለቲከኞቹ በዘመቻ ሲጯጯሁ፣  ሁሌም የጦር መሳሪያ ሽያጭ ይጧጧፋል፡፡ ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ በአሜሪካውያን እጅ ውስጥ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ቁጥር፣ ከህዝቡ ቁጥር ይበልጣል፡፡ የህዝቡ ቁጥር፣ ህፃን አዋቂው ሁሉ ተቆጥሮ፣ 320 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡ የጦር መሳሪያው ቁጥር ግን፣ ወደ 400 ሚሊዮን ተጠግቷል፡፡
የጦር መሳሪያ ግዢ በጣም የተጧጧፈው፣ ባለፉት አስር ዓመታት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልጣን ከያዙ ወዲህ፡፡ ለምን? ያው፣ ኦባማ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ለማጥበቅ ተደጋጋሚ ዘመቻ ሲያካሂዱ፤ በርካታ ዜጎች የጦር መሳሪያ ለመግዛት ይሯሯጣሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ተመሳሳይ ሩጫ ታይቷል፡፡
በጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ከመቶ ሺ በላይ ቸርቻሪዎች፤ በገበያተኛ ተጥለቅለዋል፡፡ ለዚያውም፣ ወታደሮች የሚታጠቁት አይነት፣ “ካርታ” ጎራሽ መሳሪያ ነው ሲቸበቸብ የሰነበተው፡፡ በቀን ሁለት ወይም ሶስት ጠመንጃ እንደሚሸጥ የተናገረ አንድ ቸርቻሪ፣ ከሰሞኑ ግን ገበያው እንደደራለት ገልጿል፡፡ “ይሄ መደርደሪያ የካርታ ጎራሽ ጠመንጃ ማስቀመጫ ነው፡፡ 51 ጠመንጃዎች ነበሩ፤ በሁለት ቀን ተሸጦ አሁን ባዶ ቀርቷል” ብሏል ቸርቻሪው፡፡
ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው፣ የካርታ ጎራሽ ጠመንጃዎች ገበያ፣ ከሰሞኑ በአስር እጥፍ ጨምሯል፡፡ አሁን ግን ወደ ሱቅ መሄድም አያስፈልግም፡፡ በኢንተርኔት መግዛት ይቻላል፡፡ በማግስቱ ጠመንጃው ከእጅዎ ይገባል፡፡ በዚህም ነው፤ አንድ ቸርቻሪ በሳምንት ውስጥ 30ሺ ጠመንጃዎችን እንደሸጠ ለፎክስ የገለፀው፡፡ ምናለፋችሁ… ካርታ ጎራሹ ጠመንጃ በ500 ዶላር እንደ ጉድ እየተቸበቸበ ነው፡፡
የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለመቀነስ ፖለቲከኞች በዘመቻ ሲጮሁ፤ የጦር መሳሪያ ገበያው ይደራል፡፡  ኤፍቢአይ እንደገለፀው፤ በየወሩ የሚመዘገቡት የመሳሪያ ግዢ ጥያቄዎች ሁለት ሚሊዮን ገደማ ናቸው፡፡ በአመት ወደ 25 ሚሊዮን ገደማ ማለት ነው፡፡ ከአስር አመት በፊት ግን አስር ሚሊዮን አካባቢ ነበር፡፡ ዛሬ በእጥፍ ጨምሯል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ ቁጥጥር ለማጥበቅ የሚጮሁት ፖለቲከኞች፣ የጦር መሳሪያ ሸያጭን እያባባሱ እንደሆነ ቢያውቁም እንኳ፣ በየጊዜው በዘመቻ ከመጮህ አይቆጠቡም፡፡ ለምን? በሞኝነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ችግሩን ከማሻሻል ይልቅ የሚያባብስ ቢሆንም፤ “ተቆርቋሪ” መስሎ የመቅረብ ወግ፤… “ተቆርቋሪ ነው” የመባል ሱስ ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ በዚያው ልክ፤ የመሳሪያ ሽያጩም ሪከርድ እያስመዘገበ ቀጥሏል፡፡
በአገራችን ደግሞ፣ የስደት ጐርፍ፣ አዲስ ሪከርድ እያስመዘገበ ነው፡፡ አዎ፤ በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት የተጓዙ ኢትዮጵያውያን፡ በደል ይደርስባቸዋል፤ አልፎ አልፎም ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከል መጣር ተገቢ ነው፡፡ ጉዞውን በተራ መግለጫ ማገድ ግን…. አንደኛ ነገር የዜጐችን መሰረታዊ መብትና ህገመንግስትን ይጥሳል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ፣ ችግርን ከማሻሻል ይልቅ ያባብሳል፡፡ ያለ ህጋዊ ምዝገባ በየአቅጣጫው ሌሎች የስደት አቅጣጫዎች ይበራከታሉ፡፡ የሞት አደጋውም በአስር እጥፍ ይጨምራል፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን እውነታ ለማገናዘብ ብዙም የፈቃደኛነት ዝንባሌ አይታይም፡፡ እናም፤ ከሁለት ዓመት በፊት፣
“ወደ አረብ አገገራት መጓዝ ታግዷል” ተባለ፡፡ ውጤቱስ?
ያኔ በ2005 ዓ.ም፣ ወደ የመን የገቡት ኢትዮጵያዊያን 50ሺ ነበር። በቀጣዩ አመት ግን፣ 70ሺ። አምና እንደገና ቁጥሩ ጨምሯል - 80ሺ ኢትዮጵያውያን ተሰደዋል። ዘንድሮ...
የዩኤን ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ዘንድሮ ከመስከረም እስከ ግንቦት ድረስ ብቻ፣ ከ82ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን የመን ገብተዋል።
ይህም እስከ ዛሬ፣ ከተመዘገቡት ‘ሪከርዶች’ ሁሉ ይበልጣል። በዚህ የስደት ጉዞ፣ 10 ኢትዮጵያዊያን ይሞታሉ - በዓመት አይደለም። በየወሩ። ግን፣ በዚህ ምክንያት፣ አገር ምድሩ በመግለጫና በስብሰባ ሲቀወጥ አንሰማም። ጨርሶ አይወራም። ስደተኞችን ከሞት አደጋ ለመከላከል ያስችላል ተብሎ የተጀመረው የጉዞ እገዳ፣ የስደተኞችን ሞት በብዙ እጥፍ የሚያባብስ ሆኗል።
የሰራተኞችን ችግር ያቃልላል ተብሎ የተጀመረ ሌላ ዘመቻም፣ ስራ አጥነትንና ሴተኛ አዳሪነትን የሚያስፋፋ ሆኖ ያርፈዋል። ትራንስፖርትን ያቀላጥፋል የተባለው ቁጥጥር፣ ከተማዋን በታክሲ እጦት ያቃውሳል። በቅርቡ ደግሞ፣ የአውቶቡስ አገልግሎት ላይ፣ ተመሳሳይ ጥፋት አንዣብቧል - ግን ተሳፋሪዎችን ይጠቅማል ተብሎለታል።
“ችግርን ያቃልላሉ” ተብለው በየጊዜው የሚታወጁ ህጎች፣ በየእለቱ የሚፈለፈሉ ደንቦችና መመሪያዎች፤ “ችግርን የሚያባብሱ” ሲሆኑ፤ ትንሽ ቆም ብሎ ማሰብ አያስፈልግም? በጣም ያስፈልጋል እንጂ፡፡ በቀውስ እየተናጠች ባለች አለም፤ ‹ጡዘት› በበዛበት በዛሬው ዘመን፤ … ችግሮች ተደራርበው፣ መቼና በየት በኩል እንደሚፈነዱ ሳይታወቅ ነው፤ አገር የሚቃወሰው፡፡ የተቃወሰውን መልሶ ማረጋጋት ደግሞ፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከወዲሁ መጠንቀቅና በአስተዋይነት መራመድ ይሻለናል፡፡


Read 4482 times