Saturday, 25 June 2016 12:01

ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት የዶፒንግ ቀውስ እየተወሳሰበ መጥቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

• ራሽያና ኬንያ ጥብቅ ምርመራ ይጠብቃቸዋል
• ሜክሲኮና ኢትዮጵያ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ናቸው
በትውልድ ሶማሊያዊ የሆነው የመካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ጃማ ኤደን በዶፒንግ ጥፋት ተጠርጥሮ በሳምንቱ መግቢያ ላይ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ከ31ኛው ኦሎምፒክ በፊት የዶፒንግ ቀውስ እየተወሳሰበ መጥታቱን ለመረዳት ትቻላል፡፡ በተለይ ሰሞኑን ስበሰባ ያደረገውን ዓለም ቀፉን የፀረዶፒንግ ኤጀንሲ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ሰር ክሬግ ሬይድ በዶፒንግ ጥፋት የሚጠረጠሩት አትሌቶችና አገራት ብዛት እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው መናገራቸው ይህን ያመለክታል፡፡  በ31ኛው ኦሎምፒያድ ለወርቅ ሜዳልያ ስኬት ከሚጠበቁ እና ድምቀት ይሆናሉ የሚባሉ የዓለም ኮከብ አትሌቶችን የያዙት ራሽያ፤ ኬንያ እንዲሁም ኢትዮጲያ በተደጋጋሚ መጠቀሳቸውም የታላቁን የስፖርት መድረክ ክብር እያደበዘዘው መጥቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ ከሳምንት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ ጥብቅ ርምጃዎችን ወስዶ ነበር፡፡ የፀረ ዶፒንግ ፖሊሲዎችን በልዩ የማጭበርበር እንቅስቃሴዎች ጥሳለች ያላትን ራሽያ ከኦሎምፒክ የትራክ እና የሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርቶች ተሳትፎ ሙሉ ለሙሉ ማገዱም አይዘነጋም፡፡ የራሽያ ስፖርት ሚኒስትርም ውሳኔዎን በመቃወም ለዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት  እና ለዓለም ዓቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ይግባኝ ከመጠየቁም በላይ የአይኤኤኤፍ ውሳኔ ከኦሎምፒክ ተሳትፎ እንድንታቀብ ያስገድደናል ብሎ ተከራክሮ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው ማክሰኞ ልዩ ስብሰባ ያደረገው ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ የአይኤኤኤፍ አቋም ቢደግፍም ራሽያን ከኦሎምፒክ ለማገድ አሁን ግዜው አለመሆኑን በመግለፅ ሌሎች ከባባድ ውሳኔያዎችን ግን አሳልፏል፡፡ የአይኤኤኤፍ ውሳኔ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ራሽያ በዶፒንግ ጥፋት ከኦሎምፒክ የታገደች የመጀመርያዋ አገር ትሆን ነበር፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የራሽያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ዓለም አቀፉን የፀረ ዶፒንግ ፖሊሲ ጥሷል በማለት በትራክ እና የሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ውድድሮች በኦሎምፒኩ እንዳይሳተፍ ይደረጋል በተባለበት ወቅት ሁኔታው በተለይ አሜሪካን በሜዳልያ ስብስብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም ሲገለፅ ነበር፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ይፋ ባደረገው የአቋም መግለጫ በተለይ በዶፒንግ ጥሰቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ በሆኑት ራሽያ እና ኬንያ ከኦሎምፒክ ተሳትፏቸው ጋር በተያያዘ በአትሌቶቻቸው ላይ ጥብቅ እና ተደጋጋሚ የዶፒንግ ምርመራዎች እንዲካሄድባቸው አዝዟል፡፡ ራሽያ የፀረ ዶፒንግ ፖሊሲዎችን በማጭበርበር እና በመጣስ እንዲሁም ኬንያ ደግሞ በበጀት እጥረት እና በመንግስት አካላት ድጋፍ ማነስ  ግንባርቀደም ተጠያቂ አገራት መሆናቸውን ያመለከተው ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ሜክሲኮና ኢትዮጲያ ደግሞ ህጉን ተግባራዊ ማድረግ ያዳገታቸው እና ክትትላቸው ያነሰ አገራት አድርጎ ጠቅሷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከጃማ ኤደን መታሰር በኋላ ባወጣው መግለጫ አትሌቶች፤ አሰልጣኞችና ማናጀሮች የመከላከልና የመቆጣጠር ስራውን አጠናክሮ ሲቀጥል መረጃዎችን በመስጠት እና ከህገወጥ እንቅስቃሴዎች በመታቀብ ትብብር እንዲያደርጉለት ጥሪ አቅርቧል፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ አትሌቶችን በአሰልጣኝነት እና በማናጀርነት ያስተዳድራል የተባለው ጃማ ኤደን በፌደሬሽኑ እውቅና የሚሰጠው ባለሙያ አለመሆኑን የገለፀው ፌደሬሽኑ፤ በዶፒንግ ጥፋቱ በታሰረበት ወቅት የአትሌቶች ስም ተያይዞ መነሳቱን እንደሚያውግዝ አመልክቷል፡፡ የአገራችን አትሌቶች በዶፒንግ ጥፋቶች ተጠርጥረው በምርመራ ሂደት ውስጥ ይገኛሉ የሚለው አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ከህገወጥ ተግባራት አትሌቲክሱን ለመታደግ ስላከናወናቸው ተግባራትም በመግለጫው ጠቃቅሷል፡፡ የፀረ አበረታች መድሃኒቶች ቦርድ ፅህፈት ቤት በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ስራ መጀመሩን፤ ለማስተማር እና ግንዛቤ በመፍጠር ተደጋጋሚ መድረኮች መዘጋጀታቸውን በአትሌቶች ላይ የዶፒንግ ምርመራዎች መካሄዳቸውንና ሁሉም እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፉ ፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ ተወካዮች ጥሩ ግምገማ ማግኘታቸውን በተጨማሪ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ግን ዓለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ኤጄንሲ እና አይኤኤኤፍ ከሚያደርጓቸው ዘመቻዎች ባሻገር ሌሎች ተቋማት በተናጠል የሚያወጧቸው ሪፖርቶችም ከአየቅጣጫው እየተሰሙ ናቸው፡፡ በ2014 ራሽያ ባስተናገደችው የሶቺ ኦሎምፒክ የከፉ የዶፒንግ ጥሰቶች መፈፀማቸውን ሪቻርድ ማክለሪን የተባሉ ካናዳዊ ፕሮፌሰር በሰሩት የጥናት ሪፖርት ማጋጠማቸው ከሰሞኑ ተዘግቦ ነበር፡፡ ይህ መረጃ ከ2 ወራት በኋላ ለመታተም ይበቃል መባሉ  ልትታገድ በነበረችው ራሽያ እና ሌሎች አገራት የኦሎምፒክ ተሳትፎ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ እያደረገ ነው፡፡ በተያያዘ የአውስትራሊያ የዶፒንግ ኤክስፕርቶች ከ800 ሜትር እስክ ማራቶን ባሉ ርቀቶች በሚወዳደሩ 800 አትሌቶች የዶፒንግ ጥፋቶችና አጠያያቂ የምርመራ ውጤቶች መኖራቸውን  አረጋግጠናል እያሉ ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎፒክ ኮሚቴ በሪዮ ኦሎምፒክ ወቅት እና በዋዜማው ወራት ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ በተነሱ አጀንዳዎች ባለአምስት ነጥብ እቅድ ተግባራዊ በማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ የመጀመርያው በአይኤኤፍ በሩስያ አትሌቶች ላይ የሚተላለፈውን የመጨረሻ ርምጃ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በማፅደቅ እንደሚቀበል ማሳወቁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽንና የየአገራቱ ፌደሬሽኖች በዶፒንግ ችግር ያለባቸው እና የሚጠረጥሯቸውን አትሌቶች እጅ ከፍንጅ ከመያዛቸው በፊት እንዲከላከሉ ማስጠንቀቁ ነው፡፡ የየአገራቱ ፌደሬሽኖች እና ብሄራዊ ኮሚቴዎች በዶፒንግ ችግር የተያዙ አትሌቶችን በራሳቸው ውሳኔ መሰረት እንዲያግዱ አትሌቶቹን ብቻ ሳይሆን አሰልጣኞቻቸው፤ ማናጀሮቻቸው፤ የፌደሬሽን ሃላፊዎችና ዶክተሮቻቸውን ማገድ እንዳለባቸውም ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ያሳስባል፡፡ በአሰልጣኟ ጃማ ኤደን ማንነትና የስራ ልምድ ፤ በቁጥጥር ስር ስለዋለበት ‹‹ኦፕሬሽን ሪያል››ና ተያያዥ ሁኔታዎች ከዚህ በታች በቀረበው ዘገባ ተዳስሷል፡፡
ጃማ ኤደን፤ ‹‹ኦፕሬሽን ሪያል ›› ፤ የዲባባ ቤተሰብ
አሰልጣኝ ጃማ ኤደን በዶፒንግ ጥፋት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ሰኞ እለት በባርሴሎና ከተማ ሳባልዴል ውስጥ ነበር፡፡ የካታላን ፖሊስ፤ የስፔን የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ፤ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በቅንጅት ባካሄዱትና ‹‹ኦፕሬሽን ሪያል›› ብለው በሰየሙት ዘመቻ ነው፡፡ ኦፕሬሽኑ በሳውዲ አረቢያ እና በኳታር የመገበያያ ገንዘብ ሪያል መሰየሙ ያስገርማል፡፡ በአሰልጣኙ እንቅስቃሴዎች ላይ ከ2013 እኤአ አንስቶ በአይኤኤኤፍ፤ በዓለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ተቋም ዋዳ፤ በኢንተርፖል እና ሌሎች ተቋማት ረጅም ክትትል እና ምርመራ ሲደረግ መቆየቱን  የሰሞኑ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ አይኤኤኤፍ እና የእንግሉዙ ታብሎይድ ዴይሊሜልየስፖርት ሜል አምድ አዘጋጆች  ለ4 ሳምንታት የ24 ሰዓታት ጥብቅ ክትትል እና ስለላም ያደርጉ ነበር፡፡ በባርሴሎና ከተማ  በተካሄደው  የ‹‹ኦፕሬሽን ሪያል›› ዘመቻ  አሰልጣኝ ጃማ ኤደን በቁጥጥር ስር የዋለው  አብሮት ከሚሰራው ሞሮካዊው ፊዝዮቴራፒስት  ጋር ነበር ፡፡  በወቅቱ በተካሄደው ፍተሻ በ6 የሆቴል ክፍሎች  አናቦሊክ ስቴሮይድና ኢፒኦ የተባሉ  አበረታች መድሃኒቶች እና 60 መርፌዎችን በኤግዚብት ማስረጃነት ተይዘዋል፡፡ ከአሰልጣኙ እና ከፊዚዮቴራፒስቱ ጋር ለሪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት አብረው የነበሩት ከ20 በላይ የአፍሪካ እና ኤሽያ አትሌቶች ላይ የዶፒንግ ምርመራ መካሄዱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡  በሳባዴል ከአሰልጣኙ ጋር ልምምድ ይሰሩ ከነበሩ  30 አትሌቶች መካከከል የኢትዮጲያዋ ገንዘቤ ዲባባ፤ የጅቡቲው አያንለህ ሱሌማን፤ የሱዳኑ አቡበከር ካኪ፤ የአልጄርያው አሚኔ ቤንፋሬር እና ሌሎች የኳታር ሶስት አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡
አሰልጣኝ ጃማ እና ፊዚዮቴራፒስቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 72 ሰዓታት በኋላ ፍርድቤት  ቀርበዋል፡፡ የስፔን ጋዜጣ ኤልፓይስን ጠቅሶ ፍሎትራክ እንደዘገበው ከትናንት በስቲያ  ለ72 ሰዓታት በእስር ላይ የቆዩት  ጃማ ኤደን እና ግብር አበሩ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ የፍርድ ሂደቱን የመሩት ዳኛ እነጃማ ኤደን እንዲፈቱ ቢወስኑም ፓስፖርታቸውን ተቀብለው ከ1 ወር በኋላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ወስነዋል፡፡ ከሳሽ አቃቤ ህጉ በእስር ላይ እንዲቆዩ  ቢጠይቁም ጥፋተኛ ሆኖ የተገኙበትን ክስ ባለማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ ከእስር የመልቀቅ ውሳኔውን አፅንቶታል፡፡
አሰልጣኝ ጃማ ኤደን በዶፒንግ ጥፋቶች ተጠርጥሮ መያዙ በዓለም አትሌቲክስ የገነባውን ክብር የሚሸረሽረው ከመሆኑም በላይ ፤ በስሩ በሚሰለጥኑ አትሌቶች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ በ2015 የውድድር ዘመን በሱ የሚሰለጥኑ አትሌቶች በርካታ ሪከርዶችን መሰባበራቸው፤ በተለይ ፈታኝ በሆነው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስኬታማ መሆናቸው፤ በተደጋጋሚ በብዙ ውድድሮች መሳተፋቸው አሰልጣኙ እና አትሌቶች በዶፒንግ ጥፋት ከተፈጠረው ጥርጣሬ ባሻገር አላግባብ ስማቸው እንዲነሳ እያደረገባቸው ነው፡፡
አሰልጣኙ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ከዶፒንግ ጥፋቶች ጋር በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በተለይ በ2015 እኤአ የውድድር ዘመን ላይ ሲያሰለጥናቸው ከነበሩት አትሌቶች የፈረንሳይ አትሌት የሆነችው ላይላ ትሪባና እና የኳታሩ አትሌት ሃምዛ ድሪውች በዶፒንግ ጥፋት ተጠያቂ ሆነው ከውድድር መታገዳቸው አነጋጋሪ ነበር፡፡  በተለይ የኳታሩ አትሌት ሃምዛ በዶፒንግ ጥፋተኛ ሆኖ በታገደበት ወቅት በይፋ አሰልጣኙ አበረታች መድሃኒት ሳላውቀው ሰጥቶኛል በማለት መግለጫ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ይሐው የኳታር አትሌት አሰልጣኙን በመወንጀል ከሰጠው ቃል በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የማገገሚያ ቫይታሚኖች ከመስጠት በቀር ምንም ያጠፋው ነገር የለም ብሎ ማስተባበያ በመስጠቱ ጃማ ኤደን  አደጋ ውስጥ የገባው ስሙ በተወሰነ መልኩ ታድሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ኒክ ዊለስ የተባለ የኒውዝላንድ የመካከለኛ ርቀት አትሌት በጃማ የዶፒንግ ጥፋቶች ዙርያ ተደጋጋሚ ጥቆማዎች በመስጠትና በመተቸት መንቀሳቀሱ ፈተና እንደሆነበት ቆይቷል፡፡  በሌላ በኩል የሚነሳው ስኬታማው የእንግሊዝ አትሌት ሞ ፋራህ ከጃማ ኤደን ጋር በነበረው ቅርበት በዶፒንግ ዙርያ ስሙ መነሳቱን አስመልክቶ ሽሽት ማብዛቱ የተለያዩ ዘገባዎች ትኩረት እንደሆነ መቆየቱ ነው፡፡ ሰሞኑንም የእንግሊዙ አትሌት ሞፋራህ በ2015 እኤአ በጃማ አሰልጣኝነት በኢትዮጵያ በተካሄደ ልዩ የልምምድ ፕሮግራም ለአጭር ጊዜ መስራቱን በመጥቀስ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ሞፋራህ ከጃማ አደን ጋር በሱልልታ ለሰባት ሳምንታት በሰራበት ወቅት ከፍተኛ ግንኙነት እንደነበረው ይገለፃል፡፡ ሞ ፋራህ ከጉዳዩ ራሱን በማራቅ ላይ እንደሆነ በርካታ ዘገባዎች እየተቹበት ባለው ሁኔታ የእንግሊዝ አትሌቲክስን የሚመራው ብሪትሽ አትሌቲክስ በበኩሉ ጃማ ኤደን በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በዋዜማው በ2016 ከእንግሊዝ አትሌቶች ምንም አይነት ግንኙነት  እንደሌለው   አስተባብሎ መግለጫ ሰጥቷል፡፡የብሪቲሽ አትሌቲክስ ማስተባበያ ግን በስፔን ጋዜጦች በወጡ ዘገባዎች እና በሌትስ ራን ትንትኔ መሰረት ልክ አይደለም፡፡ በቀረቡት መረጃዎች ማረጋገጥ እንደተቻለው ሞ ፋራህ ከአሰልጣኙ ጋር በ2016 መግቢያ ላይ ከዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት በተያያዘ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከ2014 ጀምሮ አብረው ይሰሩ ነበር ተበሏል፡፡ እንደሌትስራን ከሆነ ሞፋራህ በሳባዴልም ያደረገው ስልጠና ነበር በተለይ የጃማ አደን አትሌቶች ባሉበት ሁሉ ልምምድ ለመስራት በመፈለጉ የሆነ ጥርጣሬ መፈጠሩ እንደማይቀርም አብራርቷል፡፡
አሰልጣኝ ጃማ ኤደን እና ሞሮካዊው ፊዚዮቴራፒስቱ በዶፒንግ ጥፋት ተጠርጥረው በተያዙ ማግስት በመላው ዓለም የተሰራጩ ዘገባዎች ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው የተነሳው የዲባባ የአትሌቶች ቤተሰብ ናቸው፡፡  በየትኛውም ዘገባ ከዶፒንግ ምርመራው እና ክትትሉ በተገናኘ  ዲባባዎች ተጠያቂ ሊሆኑበት የሚችል ሁኔታ ባይገለፅም የዜና ማጠናከሪያዎች ሆኖ ስማቸው መጠቀሱ ተገቢ አልነበረም፡፡ በተለይ ገንዘቤ ዲባባ  2016 ከገባ በኋላ በትራክ ውድድሮች አለመሳተፏ ጥቂት የማይባሉ አሉባልታዎችና ውዥንብሮች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው፡፡
ልዩ ስፍራው ሳባዴል በተባለ የስፔን ከተማ በተካሄደው የኦፕሬሽን ሪያል ዘመቻ 3 የዲባባ ቤተሰብ አትሌቶች በስፍራው መገኘታቸው አነጋጋሪ ሌላው አጠያያቂ ሁኔታ ነበር፡፡ ሌተስራን የተባለው ታዋቂ የአትሌቲክስ ድረገፅ ትንታኔ ከዲባባ እህትማማቾች በተለይ ጥሩነሽ ዲባባ ምናልባትም በስፔን ሳባዴል ሆቴል የተገኘችው እህቷን ከሚገጥማት አደጋ ለመታደግ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ፡፡ ገንዘቤ በአሜሪካዋ ፖርትላንድ ተደርጎ በነበረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከወሰደች በኋላ ከውድድር ርቃለች፡፡
 በተለይ በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች አለመሳተፏ ግልፅ ሳይሆን የሰነበተ ጉዳይ ነበር፡፡ ይሁንና ሰሞኑ ከእሷ ጋር ተያይዞ በሚወጡ ዘገባዎች ግን አትሌቷ ከተለያዩ የትራክ ውድድሮች ተሳትፎ የራቀችው በአውራ ጣቷ ላይ በገጠማት ጉዳት መሆኑ እየተገለፀ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አሰልጣኝ ጃማ ኤደን በ2016 እኤአ መግቢያ ላይ ከአትሌቲክስ ዊክሊ ጋር ባደረገው ልዩ ቃለምልልስ የገንዘቤን ልዩ ብቃት አስመልክቶ ሰፊ ምላሾችን ሰጥቶ ነበር፡፡  አሰልጣኟ ለመሆን  የበቃበትን አጋጣሚ ባነሳበት ወቅት ገንዘቤ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ለመጀመርያ ጊዜ ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ በ2012 እኤአ ላይ ታላቅ እህቷ ጥሩነሽ አሰልጣኝ እንደምትፈልግ እንደጠየቀችው ገልፆ፤ የሩጫ ውድድሮቿን ፤ልምምዷንና አሯሯጧን ካጠና በኋላ ሃላፊነቱን እንደረተከበም አብራርቷል፡፡ ከአትሌቲክስ ዊክሊ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ አትሌቷን ከዶፒንግ ጋር በሚያያይዙ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሲሰጥ ደግሞ ፤ ሪከርድ በሚያስመዘግቡ አትሌቶች ላይ የዶፒንግ ክስ እየተለመደ መምጣቱን አውግዞ፤ በገንዘቤ ምርጥ ብቃት ላይ በየጊዜው የሚነሳው የዶፒንግ አሉባልታ ከቅናት የተፈጠረ በሚል ነበር ያጣጣለው፡፡ በገንዘቤ ሪከርዶችን የመሰባበር ምርጥ ብቃቶቿ ዙርያ ሲጠየቅም ፤ አትሌቷ ጥሩ አሯሯጭ ካገኘች የ3000ሜ፤ የ5000ሜትር ትራክ እና የ800 ሜትር ክብረወሰኖች በተደጋጋሚ የማሻሻል ብቃት እንዳላት በመመስከር ተናግሯል፡፡ ገንዘቤ በ2015 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከወሰደች በኋላ ስለ አሰልጣኟ ተጠይቃ ‹‹ በሩጫ ዘመኔ የነበረውን አስተዋዕኦ ለመግለፅ ቃላቶች ያጥሩኛል፡፡ በእሱ አሰልጣኝነት አምስት የዓለም ሪከርዶችን በተሳካ ሁኔታ ለመስበር በቅቻለሁ›› ማለቷም ይታወሳል፡፡
የጃማ አደን የዶፒንግ ጥፋት ተጠርጣረቲነት በስፖርቱ ታሪክ በአሰልጣኝ እና በአትሌቶቹ  ላይ ያጋጠመ ከባድ ቀውስ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች ከአገር ጋር ሳይያያዝ የተከሰተ ሁኔታ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ያመለክታሉ፡፡
 በጃማ ኤደን መታሰር በርካታ ሁኔታዎች ተቃውሰዋል፡፡ በተለይ በሱ ስር ከሚሰለጥኑት አትሌቶች ገንዘቤ ዲባባ እና ሌሎች እንዲሁም በአንድ ወቅት አብሮ የሰራው እና ባልንጀሮች እንደሆኑ የተወራበት የእንግሊዙ ሞፋራህ፤ ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ አጋጣሚ በስፔን የነበረችው ጥሩነሽ ዲባባ፤ የትጥቅ አምራቹ ኩባንያ ናይኪ እና በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር ያሉ ባለስልጣናት መነካካታቸው የማይቀር ይመስላል፡፡
ከኦፕሬሽን ሪያል ጋር  በተያያዘ ስማቸው የተነሳባቸው ሁሉ ጥፋተኛ ሆነው እስኪገኙ ንፁህ ቢሆኑም ዘገባዎች በተለያየ መንገድ አያይዘው ስለእነሱ በማንሳታቸው የሚፈጠሩ የዝና ግድፍቶች አሉ፡፡
ጃማ ኤደን ደሞዝ የሚከፈለው እና አብሮ የሚሰራው ከአሜሪካው የትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ጋር መሆኑም የፈጠራቸው አነጋጋሪ ሁኔታዎችአሉ፡፡ አሰልጣኙ በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ብዙውን ግዜ የሚለጥፋቸው መረጃዎች የናይክን ምርት የሚያስተዋውቁ እና የሚያዳንቁ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡ ናይኪ  በጃማ ኤደን መታሰር ብቻ ሳይሆን ከሩስያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በአብይ ስፖንሰርነት የተሳሰረ በመሆኑ የሪዮ ኦሎምፒክ የዶፒንግ አጀንዳዎች የኩባንያውን ተዓማኒነት አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡ ናይክ ከጃማ አደንና ከአትሌቶቹ ጋር ባለው ትስስር ምን አይነት ቀጣይ ርምጃ ሊያደርግ ይችላል የሚለው ሁኔታም እያነጋገረ ነው፡፡
በብስክሌት ስፖርት በዶፒንግ ጥፋቱ ከተቀጣው ሊውስ አርምስትሮንግ እንዲሁም ለአጭር ጊዜ ታግዶ በነበረው የአሜሪካው የአጭር ርቀት ሯጭ ጀጀስቲን ጋትሊን በተያያዘ ኩባንያው ያፈረሰው የስፖንሰርሺፕ ውል አለመኖሩን የጠቆመው ሌትስ ራን ከዚህ አንፃር ሁኔታውን በመመልከት ናይኪ በዶፒንግ ክሱ ብዙም ቀስው ላይፈጠርበት እንደሚችል መገመት ይቻላል ብሏል፡፡ ጃማ አዴን እና ፊዚዮ ትራፒስቱ የተገኘባቸው የኢፒኦ እና የስቴሮይድ አበረታች መድሃኒቶች ትክክለኛነት ከተረጋገጠ፤ በተለያዩ የአትሌቶች መኝታ ክፍሎች በተመሳሳይ በተገኙ መርፌዎችእና አበረታች መድሃኒቶች እያንዳንዳቸው እስከ4 ዓመት መታገድ ሊያስቀጣቸው ይችላል፡፡ ጃማ አደን ከዋዳ እና ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከሚገጥመው የ4 ዓመት መታገድ ቅጠጣት ባሻገር በአበረታች መድሃኒቶች አጠቃቀም እና ህገወጥ ዝውውር የ2 ዓመት እስራትም ሊፈረድበት ይችላል፡፡

Read 2301 times