Saturday, 25 June 2016 12:03

የአለማችን ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ከፍተኛው ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ65.3 ሚ የአለማችን ስደተኞች፣ ግማሽ ያህሉ ህጻናት ናቸው
   በአለማችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞች ብዛት በታሪክ ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡ ሲሆን እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2015 መጨረሻ  በስደተኝነት የተመዘገቡ፣ ጥገኝነት የጠየቁ ወይም በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 65.3 ሚሊዮን መድረሱን ተመድ አስታወቀ፡፡የአለማችን ስደተኞች ቁጥር በ2014 ከነበረበት የ10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጸው የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን፣ በአለማችን ከሚገኙ ስደተኞች መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት የሶርያ፣ የአፍጋኒስታንና የሶማሊያ ዜጎች መሆናቸውን ጠቁሞ 10 ሚሊዮን ስደተኞች ያሏት ሶርያ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች ብሏል፡፡በአለማችን ከ113 ሰዎች መካከል አንዱ ስደተኛ እንደሆነ የጠቆመው ኮሚሽኑ፤በፈረንጆች 2015 በአንድ ደቂቃ 24 ያህል ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መገደዳቸውንና ግማሽ ያህሉ የአለማችን ስደተኞች ከ18 አመት በታች የሚገኙ ህጻናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ዓምና ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን በላይ እንደነበር ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤በርካታ ስደተኞችን በመቀበል ከአለማችን አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ቱርክ መሆኗንና በአገሪቱ 2.5 ሚሊዮን ያህል የሌሎች አገራት ስደተኞች እንደሚገኙ ገልጧል፡፡

Read 951 times