Saturday, 25 June 2016 12:21

በአዲስ አበባ የአተት ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

• በበሽታው ሰዎች እየሞቱ መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ
• በከተማው ከ24 በላይ የህክምና ማዕከላት ተቋቁመዋል
   የክረምቱን ወራት ተከትሎ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት)፤ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የታየው የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ፡፡ በየክፍለ ከተሞቹ ከሃያ አምስት በላይ ህሙማን በበሽታው ታይዘው መገኘታቸውን የጠቆመው ጤና ጥበቃ ሚ/ር፤ በሽታውን ለመቆጣጠርና ለህሙማኑ የህክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉ በሃያ አራት በላይ የህክምና መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ሕክምና በመስጠት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የአንድ ቀን ወርክሾፕ ላይ የሚኒስትር መ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ አማኖ እንደተናገሩት፤ በሽታው ባለፈው የካቲት ወር በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ተከስቶ የነበረ ሲሆን ከሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ተከስቷል፡፡ በወቅቱም ሁለት ህሙማን ብቻ በበሽታው ተይዘው የተገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው፣ በየክፍለ ከተሞቹም ከሃያ አምስት የማያንሱ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ ተናግረዋል፡፡ ለህሙማኑ ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ከ24 በላይ ማዕከላት ተቋቁመዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን በበሽታው ተይዞ የሞተ ሰው ስለመኖሩ ከመናገር የተቆጠቡት ዳይሬክተሩ፤ የበሽታው ስርጭት እጅግ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋለ ብለዋል፡፡ ሰማኒያ በመቶ የሚደርሱ የአተት ተጠቂዎች የበሽታውን ምልክት ሳያሳዩ ሊቆዩ እንደሚችሉ የገለፁት አቶ አህመድ፣ ይህመ በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰራጭ ያደርገዋል በማለት ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ የጤና ተቋማት በበሽታው የተያዙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንና በሆስታሎችም በበሽታው ተይዘው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማለ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ “እስከአሁን የደረሰን የሞት ሪፖርት የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሽታው አጣዳፊ ከመሆኑ አንፃር ከፍተኛ ጥንቃቄና አጣዳፊ ህክምና ያስፈልገዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ በበሽታው የተያዘ ወይም መያዛቸው የሚያጠራጥር ሰዎች ሲያጋጥማቸው በአስቸኳይ ወደ ህክምና ማዕከላት መወሰድ እንደሚገባቸውና አፋጣኝ ህክምና ያላገኘ የበሽታው ተጠቂ በ24 ሰዓት ውስጥ ለሞት ሊዳረግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፤ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባለስልጣን መ/ቤቱ ህብረተሰቡ ንፅህናው የጠበቀና የታከመ ውሃ እንዲያገኝ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም የበሽታው መከሰት ከተገለፀበት የሰኔ ወር የመጀመሪያው ቀናት ጀምሮ ከፍተኛ ክትትል በማድረግና ተጨማሪ የውሃ ማከሚያ መድሃኒቶችን በመጠቀም፤ ንፅህናው አስተማማኝ የሆነ ውሃ በማሰራጨት ላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በቧንቧ የሚሰራጨው ውሃ ንፅናህው የተጠበቀና አስተማማኝ መሆኑንም ጨምረው ጠቁማዋል፡፡
ለበሽታው መስፋፋት አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ የመፀዳጃ ቤቶች በመሆናቸው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሞሉ የመፀዳጃ ቤቶችን በዘመቻ የማፅዳት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የግል የፍሳሽ ቆሻሻ መጣጭ መኪኖች እንዲሰማሩ መደረጉንና ህብረተሰቡ ለመንግሥት በሚከፍለው የፍሳሽ ቆሻሻ መምጠጫ ገንዘብ ላይ መንግሥት ጭማሪውን በመክፈል እያስመጠጠ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ለጤና ጠንቅ ይሆናሉ የተባሉ የብረት ቧንቧዎችን የመቀየር ሥራ እየተሰራ መሆኑንና እስከአሁንም 4.5 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የብረት ቧንቧ መቀየሩን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡   


Read 4720 times