Saturday, 02 July 2016 11:46

ፅጋቡ ግርማይ ኢትዮጵያዊው የብስክሌት ኦሎፒምያንና 103ኛው ቱር ደ ፍራንስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

በ31ኛው ኦሎምፒያድ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያን ለመወከል የበቃው ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ፅጋቡ ግርማይ ነገ በሚጀመረው በታላቁ  የቱር ደፍራንስ ተሳታፊ ነው፡፡  በ በውድድር ታሪኩ  ለ103ኛ ጊዜ በሚካሄደው ቱር ደፍራንስ በመሳተፍ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን የበቃ ፅጋቡ ግርማይ ፤ የጣሊያኑን ላምፕሬ ሜሪዳን ክለብ በመወከል በቱር ደፍራንስ ከሚጋልቡ 9 ብስክሌቶች አንዱ ነው፡፡  የኦሎምፒክ ተሳትፎውን በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ የሚናገረው ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛው ፅጋቡ ግርማይ በቱር ደፍራንስ የሚኖረውን ተሳትፎ አስመልክቶ ስለፕሮፌሽናል ልምዱ እና የውጤት ታሪኩ፤ ስለ103ኛው ቱር ደፍራንስ እና ስለኦሎምፒክ ተሳትፎው  ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ ይዳሳል፡፡
ዘንድሮ በፕሮፌሽናል ደረጃ በላምፓሬ ሜሪዳ ክለብ ስኬታማ ሆኖ  ያሳለፈው ፅጋቡ፤  በተለይ በጂሮ ዲ ኢታሊያ እና በቩሌታ ዲ ኤስፓኛ የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድሮች ተሳትፎ  ስኬታማ ስለነበር በቱር ደ ፍራንስ ለሚሰለፍለት ቡድን ምርጥ  ብቃት እንደሚያሳይ ተጠብቋል፡፡

ፕሮፌሽናል ልምዱና ውጤቱ
የ24 ዓመቱ የብስክሌትኦሎምፒያን ፅጋቡ ግርማይ ትውልዱ በመቀሌ ሲሆን በጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድሮች ተሳታፊ የሚሆን ፕሮፌሽናል ጋላቢ ብስክሌተኛ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ለመሆን ከበቃ ወዲህም ባለፉት አምስት ዓመታት ፤በስፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፉክክር ደረጃ ያሳደገ እና የቀየረ የመጀመሪያው ብስክሌተኛ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ተወዳዳሪ ሆኖ የስፖርቱን ጉዞ የጀመረው  ፅጋቡ ግርማይ በኢትዮጵያ የብስክሌት ሻምፒዮና ለሁለት ጊዜያት ካሸነፈ በኋላ  የፕሮፌሽናልነት ዕድል አግኝቶ የመጀመርያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክለብ ለመቀላቀል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት የበቃ ነበር፡፡ ወደዚያ  ከመሄዱ በፊት  2011 እና 2012 እኤአ በትምህርት እና በውድድር  በደቡብ አፍሪካ ፔተርሽሩም እንዲሁም በስዊዘርላንድ ዎርልድ ሳይክሊንግ ማዕከል  በአማተር ብስክሌተኛነት ተሳታፊ ነበር፡፡
 በፕሮፌሽናል ብስክሌተኛነት ከ2012 እኤአ ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ኩቤካ ስር ሲወዳደር ቆይቶ ላምፕሬ ሜሪዳ ለተባለ ክለብ ኮንትራት የፈረመው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅትም በጣሊያኑ የብስክሌት ክለብ ሳምፕሪ ሜሪዳ ፅጋቡ በዓመት እስከ 40,000 ዩሮ ክፍያ የሚፈፀምለት ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ሆኗል፡፡ በፕሮፌሽናልነት ልምዱ  ባስመዘገበው ውጤትም ስኬታማ ነበር ፡፡ ከ2012 እኤአ ጀምሮ እስከ 2014 እኤአ በደቡብ አፍሪካው የኤምቲኤን ኩቤካ ስፖርት ክለብ ተወዳዳሪ ሆኖ በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት ታሪክ በፕሮፌሽናልነት ለመቀጠር የበቃ የመጀመርያው ስፖርተኛ ሊሆን በቅቷል፡፡  በ2010 እኤአ ላይ በአፍሪካ ሻምፒዮና በሩዋንዳ ኪጋሊ 6ኛ ደረጃ የነበረው ሲሆን ከአምስት ቀናት በኋላ በቱር ኦፍ ሩዋንዳ ተሳትፎ አምስተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በ2011 በቶስካና ቼራ ሲሸልስ ውስጥ 5ኛ፤ በ2012 እኤአ በአፍሪካ ሻምፒዮና ሀ 23 ውድድር 1ኛ ደረጃ ፤ በ2013 እአኤአ ላይ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንዲሁም በጎዳና ላይ ብስክሌት ሻምፒዮና አከታትሎ ማሸነፍ ችሏል፡፡  ከትልልቅ ውጤቶቹ በ2013 እኤአ ላይ በቱር ዳይ ታዋን ለኤምቲኤን ኩቤካ ክለብ እየተወዳደረ አምስተኛ ደረጃ ያገኘበት ውጤት በኢትዮጵያ የብስክሌት ታሪክ በፕሮፌሽናል ስፖርተኛ የተመዘገበ የመጀመርያውና  አስደናቂው ውጤቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል በ2015 እኤአ በአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና የሪዮ ኦሎምፒክ ማጣርያ ላይ በአንደኛነት የወርቅ ሜዳልያ ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ በአጠቃላይ ከቱር ደፍራንስ ተሳትፎው በፊት በሰባት ፕሮፌሽናል የብስክሌት ውድድሮች አሸንፏል፡፡

በ31ኛው ኦሎምፒያድ
ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛው ፅጋቡ ግርማይ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ ለሚደረገው 31ኛው ኦሎምፒያድ ማለፉን ያረጋገጠው ከ19 ወራት በፊት ነው፡፡  ከ1940 ዎቹ መጨረሻ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት አምስት ኦሎምፒኮችን የተሳተፈች ሲሆን ፅጋቡ ለኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት ስድስተኛውን የኦሎምፒክ ተሳትፎ ማሳካት ችሏል፡፡ በኦሊምፒክ ለመካፈል የሚያበቃውን ሚኒማ ያስመዘገበውም ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት ታሪክ የመጀመርያው የሆነውን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፏል፡፡ በአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ ድል ነበር፡፡  በተመሳሳይ በዚያው ደቡብአፍሪካ በ48 ኪሎ ሜትር የነጠላ ውድድር ርቀቱን 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 05 ሰከንድ በማጠናቀቅ አምስተኛ ደረጃ ቢያገኝም ለኦሊምፒክ የሚያበቃውን ሚኒማ አሳክቷል፡፡
ይህ ስኬቱም ኢትዮጵያ በወንድ ብስክሌተኛ በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ ስትበቃ ከ44 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡የኦሎምፒክ ተሳትፎውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት “ የኦሎምፒክ ተሳትፎን ቀደም ብዬ አሳክቻለሁ፡፡
ኦሊምፒክ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ከሯጮች ጋር ተሰልፌ ወደ ኦሎምፒክ ለመሄድ በጉጉት እየተጠባበቅሁ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡

በላምፓሬ ሜሪዳ ክለብ እና በቱር ደፍራንስ
ፅጋቡ ግርማይ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በ2015 እና በ2016 እኤአ በላምፓሬ ሜሪዳ ክለብ ቋሚ ጋላቢነት እየተወዳደረ ይገኛል፡፡
በተለይ በላምፓሬ ሜሪዳ ክለብ በተራራ ግልቢያ ምርጥ ብቃቱን ያስመሰከረ ሲሆን በ2015 እኤአ በጂሮ ዲ ኢታሊያ እና በቩሌታ ዴ እስፓኛ የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድሮች ውጤታማ ሊሆን በመቻሉ ከክለቡ ቋሚ የቡድን ተሳላፊዎችአንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በ103ኛ ቱር ደፍራንስ ላይ ፅጋቡ በሚሰለፍበት  የላምፓሬ ሜሪዳ  ክለብ እሱን ጨምሮ 9 የብስክሌት ስፖርተኞች  ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ ከ3 የተለያዩ አህጉራት 7 አገራትን የሚወክሉት እነዚህ የላምፓሬ ሜሪዳ 9 ብስክሌተኞች 2 ጣሊያናዊያን፤ 2 ስሎቫኒያውያን፤ ጃፓናዊ፤ ፖርቱጋል፤ ክሮሽያ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ በተለይ ሁለቱ ስሎቫኒያያንና ኢትዮጵያዊው ፅጋቡ ግርማይ በቱር ደፍራንስ ለመጀመርያ ጊዜ የሚወዳደሩ ብስክሌተኞች ናቸው፡፡
የብስክሌት ኦሎምፒያኑ ፅጋቡ ግርማይ  ከላምፓሬ ሜሪዳ ክለብ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ጋር ባደረገው ልዩ ቃለምልልስ እንደተናገረው በቱር ደፍራንስ ተሳትፎው መሳካት የረጅም ጊዜ ህልሙ እውን መሆኑን ገልፆ፤ ውድድሩን ለመጀመርያ ጊዜ በ2007 እኤአ ላይ አልበርቶ ኮንታንዶር ሲያሸንፍ በቴሌቭዥን ተመልክቶ ጉጉት እንዳሳደረበት አስታውሷል፡፡ ከቅርብ ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊ በር ደ ፍራንስ ላይ እንደሚሳተፍ ማንም ሊያስብ አይችልም ነበር ያለው ፅጋቡ፤ በፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ነይ ይህን ታሪክ በመቀየሬ ደስተኛ ነኝ ካለ በኋላ የኢትዮጵያ ብስክሌተኞች አሁን በቱር ደፍራንስ መሳተፍ እንደሚችላል በማሰብ ይሰራሉ ስለዚህም ፈርቀዳጅ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል ብሏል፡፡

ስለ 103ኛው ቱር ደፍራንስ
ዘንድሮ ለ103ኛ ጊዜ የሚካሄደው ቱር ደፍራንስ በ29 ምእራፎች ተካፋፍሎ የሚካሄድ ነው፡፡ የዓለማችን ትልቁ የብስክሌት ውድድር ሲሆን  በአጠቃላይ የሚሸፍነው ርቀት ደግሞ 3535 ኪሜ ነው፡፡
ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ 22 ምርጥ እና ፕሮፌሽናል የብስክሌት ቡድኖችን የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡
በነገው እለት ተጀምሮ ለ22 ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ዘንድሮ ውድድሩ 4 አገራትን የሚያካልል ሲሆን ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ አንዶራ እና ስዊዘርላንድ ናቸው፡፡
ለፀጥታ እና ጥበቃ ከ23 ሺ በላይ ፖሊሶች ይሰማራሉ፡፡
በአጠቃላይ ለሽልማት የሚቀርበው ገንዘብ 2.3 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ 500ሺ ዩሮ በሽልማት ገንዘብ ይከፈለዋል፡፡     በእያንዳንዱ ምእራፍ የሚያሸንፍ ደግሞ 11ሺ ዩሮ ተሸላሚ ነው፡፡
አንድ የብስክሌት ጋላቢ በውድድሩ ተሳትፎ እስከ 124ሺ ካሎሪ ማቃጠል ይኖርበታል፡፡
በፈረንሳ ኢኮኖሚ እስከ 88 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ያገኛል፡፡
በመላው ዓለም በ1888 አገራት፤ በ121 የቴሌቭዥ ጣቢያዎች ለ4700 ሰዓታት በሚያገኘው የስርጭት ሽፋን ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ድምር ተመልካች ይኖረዋል፡፡2000 ጋዜጠኞች ውድድሩን ለ3 ሳምንታት ተከታትለው ይዘግባሉ፡፡     347 የተለያዩ የህትመት እና የኢንተርኔት ሚዲያዎች፤ 86 የቲቪ ጣቢያዎች እና 68 የሬድዮ ጣቢያዎች ይገኙበታል፡፡
በመወዳደርያዎቹ ጎዳናዎች ከ12 ሚሊዮን በላይ  ተመልካች እይታ እና ድጋፍ ያገኛል፡፡
በየመወዳዳሪያዎቹ ጎዳናዎች ከ28ሺ በላይ የመንገድ ምልክቶች እና የውድድሩን አመልካች ቢልቦርዶች ይሰቀላሉ፡፡

Read 2808 times