Saturday, 02 July 2016 11:50

“…የጉድ አገር ነሽ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(16 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ተማሪዎቹ “እስቲ ኢትዮዽያን በስድስት መስመር መግለጽ የሚችል…” ይባላሉ፡፡
አንዱ ልጅ፡… “ምን ያቅታል፣ እኔ እችላለሁ…” ይልና ለመጻፍ ቁጭ ይላል፡፡ እናላችሁ…ቢያስብ፣ ቢያስብ አንዲት ቃል እንኳ አልመጣለት ይላል፡፡ ይሄን ጊዜ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው…ግጥም ገጠማ!
እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይገልጽሽ
እንደው በደፈናው የጉድ አገር ነሽ!
ብሎ አረፈው፡፡ አሪፍ አይደል! አሀ… ምን ያድርግ…በዚህ ቢዞር፣ በዚያ ቢዞር የሚያየው ሁሉ ግራ ገባዋ!
እናላችሁ… “የጉድ አገር ነሽ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉላችሁ፡፡
እኔ የምለው…አሁን፣ አሁን ከላይ እስከ ታች የጭካኔያችንን ቅጥ ማጣት ስታዩት እውነትም… “የጉድ አገር ነሽ…” አያሰኛችሁም! ጤፍና ሰጋቱራ ቀላቅለው የሚሸጡ ጉዶች ያሉባት እውነትም የጉድ አገር ሆናለች እኮ! አሁን ደግሞ ሰጋቱራው አይበቃ ይመስል…ጭራሽ ጤፉ ከጄሶ  ነው ምናምን ጋር እየተቀላቀለ የሚቀርብባት አገር ምን ልትባል ነው!
የእንስሳት ሥጋ የከብት ስጋ አስመስለው የሚሸጡ ጉዶች የበዙባት አገር ታዲያ የጉድ አገር እንጂ ምን ልትባል ነው!
የተፈጨ ሸክላ ከበርበሬ ጋር የሚሸጡ ጉዶች የበዙባት አገር ታዲያ የጉድ አገር እንጂ ምን ልትባል ነው! ቅቤና ሙዝ ቀላቅለው የሚሸጡ አሉ የተባለ ጊዜ ራሳችንን ይዘን “እሪ!” አልን! አሁን የጉድ አገር ውስጥ ሆንንና …የባሰው መጣ! እናላችሁ…እያንዳንዳችን ጥቅም ለማግኘት የምንሄድበት ርቀት “የጉድ አገር ነሽ…” የሚያሰኝ ነው፡፡
ስሙኝማ… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከሰኞ እስከ ዓርብ ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ለመቃጠር እኮ ቸገረን! ቂ…ቂ…ቂ… ለካስ መዝናናት እንዲህ ናፍቆን ኖሯል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዛራና ቻንድራ ራሳቸው እየተራበሹ እኛንም አባልተውን ሊጨርሱን ነው እኮ! ድሮ… አለ አይደል…
“አምስት ቀን በተከታታይ ምስር የምታበዪኝ እኔ የአርባ ስድሳ ኮንዶሚኒየም ነኝ!”…
“አንተ አምቡላህን ገልብጠህ እስክትመጣ ቁጭ ብዬ የምጠበቀው መሄጃ የላትም አሉህ እንዴ!” ምናምን ነበር ጥሉ፡፡ አሁን ዕድሜ ለዛራና ቻንድራ… የጥሉ መነሻ አይነት ለውጥ አሳይቷል፡፡ የጉድ አገር ነች እኮ! ቂ…ቂ…ቂ…
እሱና እሷ በተጋቡ በአሥራ አምስተኛው ቀን አዲሱ ባል… “አሁን እንግዲህ ከተጋባን አይቀር ለወደፊት እንዲስተካከሉ አንዳንድ ጉድለቶችሽን ልንገርሽ…” ይላታል፡፡ ሚስትዬው ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ተወው የእኔ ውድ፣ ጉድለቶቼን አውቃቸዋለሁ፡፡ ከአንተ የተሻለ ባል እንዳላገኝ ያደረጉኝ እነኛ ጉድለቶች ናቸው…” አለችውና አረፈች፡፡
የምር…እኮ ጨዋታም አይደል…“በምርኩዝ እስኪሄዱ ድረስ ምንም ነገር አይለያያቸውም…” የሚባልላቸው ‘ሀዝባንድና ዋይፍ’ በፊልም የሚበጣበጡባት የጉድ አገር ሆናለች፡፡ ነገርዬው በዚሁ ከቀጠለ ስለ ፍቺ ምክንያቶች ወደፊት የሚጠኑ ጥናቶች ላይ… “ኢትዮዽያ ውስጥ ለፍቺ ቁጥር አንድ ምክንያት ዛራና ቻንድራ…” ምናምን ሊባል ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እንበል እንጂ ምን ይደረጋል፡፡
ሰውየው ጓደኛውን ስለ ትዳሩ ሁኔታ እያወያየው ነው፡፡
“እቤትህ እንዴት ነው፣ ማለት የሥራ ክፍፍላችሁ እንዴት ነው?”
ሚስቴ የገንዘብ ሚንስትር ነች፣ እናቷ የጦር ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሠራተኛዋ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነች…”
“አሀ… አንተ ፕሬዝዳንቱ ነህ ማለት ነዋ!”
“አይደለም፡ እኔ ታክስ ከፋዩ ሰፊው ህዝብ ነኝ፣” ብሎት አረፈ፡፡
እንደ ዘንድሮ ወሬ ግን…ወላ ሚስት፣ ወላ የሚስት እናት… የለየላቸው ዲክታተሮች እየሆኑ ነው ይባላል፡፡ የምር ግን…ወንዱ አያይ ይመስል ሁሉ ነገሮች እንትናዬዎች ላይ የሚከመረው ለምንድነው!
በዚህ አይነት እኮ ነገ ተነገወዲያ “ቴሌቪዥን ያለው እዚህ ብቻ መሰለህ…” ብላ ሰማንያዋን ሰማንያ ትናንሽ የምታደርግ ልትኖር ትችላለች፡፡
የሰማንያ መቅደድ ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ያው እንግዲህ በሆሊዉድ ጋብቻና ፍቺ እንደ ልብ ነው ይባላል፡፡ አንድ ጊዜ ማናት የሚሏት ተዋናይት ማታ አግብታ ሲነጋ ተፋታለች፡፡ እናላችሁ…ታዲያ አንዱ የሆሊዉድ ተዋናይ ከሆነች ጋር ሊጋባ ቀን ተቆርጧል፡፡ የሰርጉ ቀን ወደ ሙሽሪት ቤት ሲሄድ መኪናው የሆነ መንገድ ላይ ተበላሽቶ ይቆማል፡፡ ይሄን ጊዜ ምን የሚል የጽሁፍ መልእክት ላከ መሰላችሁ… “መኪና ተበላሽቶ ትንሽ አረፍዳለሁ፡፡ አደራሽን እኔ እስክደርስ ማንንም እንዳታገቢ!”  አለና አረፈው፡፡
እናላችሁ…ይሄኔ ስንት ባል… “ዛራ ምንም እንኳን ብታሳዝኚም እግዚአብሔር ይይልሽ!” እያለ ይሆናል፡፡ የምር ግን…ከየቦታው እየሰማናቸው ያሉ ነገሮች…አለ አይደል…ሳናውቀው ‘ከማሰቢያችን ላይ የጎደሉ ቡሎኖች አሉ እንዴ!’ ያሰኛል፡፡ ልብ ወለድ እየመሰሉ ነዋ! (ለነገሩ ግን…በወሬዎቹ መሀል ራሳቸው ዛራና ቻንድራን የሚያስንቁ የሦስት ዓመት ተከታታይ ፊልሞች የሚወጣቸው ማጋነኖች አሉ፡፡)
እናላችሁ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ዛራና ቻንድራ ‘የሚያነቃንቁት’ ትዳር መጀመሪያኑ ሰበብ የሚፈልግ መሆን አለበት፡፡ ልክ ነዋ! ስንት የጂብራልታር አለት የሚያካክሉ ችግሮች አፍጠው የሚጠብቁት ግንኙነት ውስጥ ፊልም ማየትና አለማየት…የመታኮሻ ምክንያት ከሆነ እውነትም የጉድ አገር ያሰኛል፡፡
እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይገልጽሽ
እንደው በደፈናው የጉድ አገር ነሽ!
ያለው ተማሪ እውነቱን ነው፡፡
በዛራና ቻንድራ ምክንያት ልጆች ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሊከታታሉ አልቻሉም ምናምን የሚባሉ ወሬዎች እንሰማለን፡፡ ታዲያ ዛራስ ምን ታድርግ፣ ቻንድራስ ምን ያድርግ!  ቂ…ቂ…ቂ… ወላጆች ምን ይሠራሉ! አሀ… የምን የአብዬን ወደ እምዬ መላከክ ነው! አንድ የሬድዮ ውይይት ላይ አንዱ የልጅ አባት ደዋይ… “ሪሞቱ እኮ በእጄ ነው…” ያሉት አሪፍ አባባል ነው፡፡
 ሪሞታቸውን አሳልፈው ሰጥተው “ልጆች አላጠናም አሉ…” ምናምን ማለት አሪፍ የወላጅነት ምልክት አይደለም፡፡ በቀለጠው ከተማ የአስራ አራት ዓመት ልጆች ሞቅ ብሏቸው በሚታዩባት የጉድ አገር “ልጆች ዛራና ቻንድራ እያዩ በትምህርት ደከሙ የሚሉ ወላጆች…” ቴሌቪዥናቸውን በቅናሽ ይሽጡት፡፡
“ልጄ እንዴት አስተማሪ ይቆጣዋል!” ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ወላጆች የበዙበት የጉድ አገር እኮ ነው…ቄሱ የሆነ ቀጠሮ ኖሯቸው መኪናቸውን የሚያቆሙበት ስፍራ ያጣሉ፡፡ ስለዚህ ማቆም ክልክል የሆነበት ስፍራ ላይ ያቆማሉ፡፡ ከዛም ማስታወሻ ይጽፋሉ፡፡ “አካባቢውን አስር ጊዜ ዞሬ ማቆሚያ ስፍራ አላገኘሁም፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ካላቆምኩ ቀጠሮዬ ይበላሽብኛል፡፡ የበደልነውን ይቅር በለን፣” የሚል መልእክት መስታወቱ ላይ ለጥፈው ይሄዳሉ፡፡ ተመልስው ሲመጡም መስታወታቸው ላይ ከትራፊክ ፖሊስ የተጻፈ መልእክት ያገኛሉ፡፡ “በዚህ አካባቢ አስር ዓመት ስዞር ኖሬያለሁ፡፡ የቅጣት ወረቀተ ካልጻፈኩልዎት ከሥራዬ እፈናቀላለሁ፡፡ ወደ ፈተናም አታግባን፣” የሚል መልእክት መስታወታቸው ላይ ተለጥፎ አገኙ፡፡ወደ ፈተና የገባነው… ‘በፊልሞች’ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገሮች ይቺ አገር የጉድ አገር እየሆነች ስለሆነ ነው፡፡እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይገልጽሽእ ንደው በደፈናው የጉድ አገር ነሽ! ያለው ተማሪ እውነቱን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!






Read 8970 times