Saturday, 09 July 2016 09:58

የሐምሌ አቤቱታ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

ባል ለአንድዬ “ዛራና ቻንድራ” ትዳሬን በጠበጡት ሲል ስሞታ ያቀርባል

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ዓመቱ ሊገባደድ አይደል! አቤቱታ የማያጣው ምስኪኑ ሀበሻ አሁንም “አቤት…” ሊል ሄዷል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ መቼም አይገደኝ፣ ይኸው ደግሜ መጣሁልህ፡፡
አንድዬ፡— ጭራሽ  መጣሁልህ አልከኝና አረፍከው! ስናፍቅህ የከረምኩ አስመሰልከው እኮ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ባትናፍቀኝም ምን መሰለህ…
አንድዬ፡— ተወው፣ ምንም አይመስለኝም፣ እንደ እውነቱ ‘መጣህብኝ እንጂ አልመጣህልኝም’ ልልህ ፈልጌ … ይሄንን ምስኪን ዘላለም መነጫነጭ የማይሰለቸው ፍጡሬን አላስከፋውም ብዬ ነው ዝም ያልኩህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አመሰግናለሁ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እሺ፣ ደግሞ አሁን ምን ሆንክ? ትንሽ እፎይ ብዬ ከርሜ ነበር፡፡ ደግሞ ምን አደረግኸኝ ልትለኝ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እኔ ምንም አደረግኸኝ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን…ምን መሰለህ አንድዬ እንደው ግራ ቢገባኝ ነው፡
አንድዬ፡— መቼ ግራ ሳይገባህ ቀርቶ ያውቃል…በል ቀጥል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በእኛ በምስኪኖቹ ሰውነት፣ በእኛ የአካል ብቃት፣ በእኛ አመጋገብ እንዲህ አጥንት የሚሰብር ብርድ የላክህብን ምን ብናጠፋ ነው! አንድዬ ቲማቲም እንኳን ከአቅሟ እንደ ሽንጥና ብሩንዶ ሩቅ ሆናብን…በዚህ ላይ ብርድ!
አንድዬ፡— ጭራሽ ብርዱንም የላክሁት እኔ ሆኜ አረፍኩ!…በየጊዜው እየመጣህ ከምትጨቀጭቀኝ ወይ አንደኛውን ተሰባሰቡና ክሰሱኛ… አንደኛውን ቢወጣላችሁ አይሻልም!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እንደ እሱ አትበል…
አንድዬ፡— በየጊዜው እየመጣህ ይህንን አደረግኸን፣ ያንን አደረግኸን ትሉኛላችሁ፡፡ አንድ ቀንም ቢሆን የሆነ ችግርን በገዛ እጃችን ያመጣነው ነው ብላችሁ አታውቁም…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኛ ምን ጉልበት አለንና በገዛ እጃችን የምናመጣው…በየትኛው አቅማችን!
አንድዬ፡— እሺ አሁን አመጣጥህ ስለ ብርዱ አቤቱታ ልታቀርብ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ እሱ አንኳን አልነበረም… ግን እኮ አንድዬ አየሩም ብርድ ሆኖ፣ ኑሮም ብርድ ሆኖ፣ የሰዉም ጠባይ ብርድ ሆኖ ግራ ቢገባን ነው፡ ይኸውልህ እንደተንዘፈዘፍን አለንልህ…
አንድዬ፡— ዋናው ስለ ብርዱ አይደለም የመጣሁት ብለኸኝ የለ እንዴ…በል ዋናው ምክንያትህን ንገረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…ይኸው እንግዲህ ዓመቱም ሊጠናቀቅ ነው…አንድዬ ዓመቱ ጦሳችንን ይዞ ይሂድ ብል ቅር ይልሀል?
አንድዬ፡— ለምን ቅር ይለኛል…የእናንተኑ ጦስ አይደለም እንዴ ይዞ የሚሄደው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ግን ለምንድነው ክፉ ዓመት ያደረግህብን…አንድ ጥሩ ነገር ሳንሰማ፣ አንድ ጥሩ ነገር ሳናይ… ነው እኮ እዚሀ የደረስነው…
አንድዬ፡— ክፉ ዓመት ያደረገው የራሳችሁ ሥራ፣ የራሳችሁ ክፋት ነው…የራሳችሀ ተንኮል ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አስቆጣሁህ እንዴ!
አንድዬ፡— መቼ ነው አንዱን ጣት ወደ እኔ ስትጠቁሙ፣ አራቱ ወደ እናንተ እንደሚያመለክት የሚገባችሁ! መቼ ነው ለጥፋታችሁ አጥፍቻለሁ ይቅር በለኝ የምትሉት!  መቼ ነው እርስ በእርሳችሁ ስትበዳደሉ፣ ስትጠፋፉ…ጥፋታችሁን ተቀብላችሁ ራሳችሁ ይቅርታ የምትጠያየቁት
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኧረ እንደ እሱ አትቆጣ…
አንድዬ፡— እኔን ምን ትጨቀጭቁኛላችሁ! ለመሆኑ ከሚስትህ ጋር ሰላም አወረዳችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አላውቅም እንዳትለኝ…
አንድዬ፡— አላውቅም እያልኩህ ነው…እንዴት አይነት ጉድ ነው እባካችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለህ…በበፊቱ በማንስማማቸው ጉዳዮች ላይ እንኳን ሰላም ፈጥረን ነበር…ማለት በመቻቻል…
አንድዬ፡— ነበር ማለት ምን ማለት ነው…ደግሞ በሌላ ነገር ተጋጫችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— መጋጨትማ ምን አላት…ጦርነት ተፈጥሯል ነው የምልህ!
አንድዬ፡— አሁን ደግሞ ምክንያታችሁ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ባልነግርህ ይሻላል፣ ትታዘበናለህ…
አንድዬ፡— እስካሁን ያልታዘብኳችሁ ይመስል…ይልቅ ንገረኝና ጣልቃ የምገባ ከሆነ አስብበታለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እዚህኛው ላይ እንኳን አንተም ጣልቃ መግባት የምትችል…
አንድዬ፡— ጨርሰዋ…የምትችል አይመስለኝም ልትል ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ እሱ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን…አንድዬ ምን መሰለህ፣ የተጋጨንበት ምክንያት…እ…
አንድዬ፡— መንተባተቡን ትተህ ትነግረኝ እንደሆነ ንገረኝ፡፡ አለበለዛ ወደ ሌሎቹ ልሂድበት፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…የተጣላነው በዛራና ቻንድራ ነው፡፡
አንድዬ፡— ም…ምን አልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ዛራና ቻንድራ…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ…ደግሞ እነሱ ምንድናቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ… የሆነ ህንድ ፊልም ውስጥ…
አንድዬ፡— ፊልም! ፊልም ነው ያልከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኧረ ተው አትቆጣ!
አንድዬ፡— ብላችሁ፣ ብላችሁ በፊልም ትጣሉ ጀመር!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ…ላስረዳህ…
አንድዬ፡— እሺ አስረዳኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ዛራና ቻንድራ የሚባለው ፊልምን ቁጭ ብላ ስታይ ታመሽና…አንድዬ፣ ስናገረው እንኳን እንዴት እንደሚያሳፍረኝ…
አንድዬ፡— እናንተ እኮ ዘላለማችሁን እንዲሁ ናችሁ፣ ስትናገሩ እንጂ ስትሠሩ አታፍሩም፡፡ እፍረታችሁን በብረት ሳጥን ትቆልፉና ስንቱን ኃጢአት ስትፈጽሙ ከርማችሁ፣ ስንቱን ስታሳዝኑ ከርማችሁ፣ የስንቱን የሰላም እንቅልፍ ስትረብሹ ከርማችሁ… የልባችሁ ከሞላ በኋላ ለመናገር ያሳፈራችኋል፡፡ በል ቀጥል…
ምስኪን ሀበሻ፡— እየውልህ … አሁን በቴሌቪዥን በአማርኛ የሚተላለፉ የውጪ ፊልሞች አሉ…
አንድዬ፡— ጥሩ ነዋ…በአማርኛ መምጣቱ ጥሩ ነዋ! ይኸው እንግሊዝኛውን እንኩሮ እያደረጋችሁት እኔ ከዛሬ ነገ እንግሊዞች መጥተው አቤት ቢሉ ምን እላቸዋለሁ እያልኩ ሳስብ ነበር፡፡
     እና…ዛራና ቻንድራ ያልካቸው ሰዎች ናቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ፍቅረኞች ናቸው…ያው የህንድ ፊልም አንድዬ ታውቀው የለ… በቃ ሚስቴ እሱን እያየች… አንዴ “የእኔ ዛራ እንዲህ ልቃጠልልሽ!” “ምነው የአንቺን ቦታ ለእኔ በሰጠኝ…” ትልና፣ ቀጥላ ደግሞ ሌላ ፊልም ላይ “የእኔ ኤሊፍ፣ የእኔ እርግብ ምን ባደርግሽ ይሻላል!” ስትል ታመሻለች፡፡ አንድዬ በዚህ ቢበቃት እኮ ጥሩ ነበር፡፡ ትቀጥልና ሌላ ፊልም እያየች “ሰው ማለት ሞሪንሃ፣ ጀግና! ልክ ልካቸውነ ንገሪያቸው ስትል አምሽታ ይደክማትና ለሽ ትልልሀለች፡፡ እኔ እራት የሚሰጠኝ እያጣሁ ጦሜን እያደርኩልህ ነው፡፡
አንድዬ፣ ካልሆነ ወይ ክእኔ ወይ ከዛራ ምረጭ ልላት አስብና፤ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ለመነሳቱ ሰበብ አልሆንም ብዬ እተወዋለሁ፡፡
አንድዬ፡— እውነትም ይሄ ለእኔም ቢሆን አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም…ታዲያ ትዳርህ ከተበጠበጠ ቴሌቪዥንህን አውጥተህ ሽጠዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! ቴሌቪዥንህን ሽጠው ነው ያልከኝ! በማግስቱ ነው ሰማንያውን የምትቀደው፤ ያውም እኔ በህይወት ተርፌ ከወጣሁ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ ግራ የሚገባኝ እንደው ለጠብ ሰበብ ነው የምትፈልጉት፣ ሌላው ሲገርመኝ በፈልም ተጣላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ጊዜው ከፋ…
አንድዬ፡— በዛ ሰሞን እንደው አትኩረቴን ወርወር ሳደርግ ግርግር አየሁ…በኋላ ሳጣራ የሀበሻ ልጆች በኳስ ተጣልተው ነው የሚቆራቆሱት አሉኝ፡፡ ሰበብ ቢጠፋ በኳስ፣ ያውም በማታውቁበት ኳስ ትራበሻላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኔ ብዬህ የለ…ይሄ ዓመት አልሆነንም፡፡ ዛሬም እኮ አንዱ አመጣጤ ከርሞውን ባርክልን ልልህ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ ምን ጊዜም እየባረክሁት ነው…የእናንተ ነገር ለሰማይም፣ ለምድርም አስቸገረ እንጂ! ስማ ስለ አዲሱ ዓመት ሲደርስ ጠይቀኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ቃል ግባልኛ… ዓመቱን እባርከዋለሁ ብለህ ቃል ግባልኛ! የሰፈረባችሁን ሰይጣን አባርርላችኋለሁ ብለህ ቃል ግባልኛ!  የጠፋውን ፍቅራችሁን እመልስላችኋለሁ ብለህ ቃል ግባልኛ!  ደግሞ…
አንድዬ፡— በቃህ፣ በቃህ…ጊዜው ሲደርስ ብየኸለሁ፣ ደህና ሁን፣ በሰላም ግባ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ምስኪን ሀበሻ ለአንድዬ የሐምሌ አቤቱታውን አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ ቤቱ ሲመለስ ሚስቱ ነጠላዋን አዘቅዝቃ (ቂ…ቂ…ቂ…) ስቅስቅ እያለች ታለቅሳለች፡
 ከዘመድ ምን ብትሰማ ነው ብሎ ደንግጦ በተቀመጠችበት ክንዱን ትከሻዋ ላይ ጣል ያደርግና… “ምን ሆንሽብኝ የእኔ ቆንጆ! ማዘር ደህና አይደሉም እንዴ!” እያለ በጥያቄ ያጣድፋታል፡፡
 እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ይሄ ፕራማድ ዛራን ከግድግዳ ጋር አጋጫት! ግንባሯ ላይ ደሟን እየው…” ብላው ለቅሶዋን ቀጠለች፡፡እሱም መኝታ ቤቱ ገባና ጋደም ብሎ… “የእኔን ሆድ ረሀብ ከግድግዳ ሲያጋጨው ማን ያልቅስልኝ!” አለና  ዛራ፣ ኤሊፍ፣ ሞሪንሀ የሚሏቸው ሴቶች ላይ የእርግማን ናዳውን አዘነበው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 6577 times