Saturday, 09 July 2016 10:00

አሰፋ ጫቦ፤ የ60ዎቹ ፖለተከኞች ንስሃ መግባት አለባቸው ይላሉ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

(በተለይ ለአዲስ አድማስ )

* የደርግ አባሎችና ርእሰ ብሔር የነበሩ    ፍርዳቸውን ፈጽመዋል  
* መኢሶንና ወዝሊግን ከተከሳሾች መዝገብ    ውስጥ እናስወጣ
* መንግስቱ ኃይለማርያምን ለፍርድ ማቅረብ  ይኖርብናል  
* ኢሕአፓ ደርግን መክሰስ ሙሉ ስራው   አድርጎታል
ለሁለት አስርት ዓመታት ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የህግ ባለሙያውና ፖለቲከኛው አቶ አሰፋ ጫቦ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት ፖለቲካ - ቀመስ መፅሃፋቸው “የትዝታ ፈለግ” ተወዳጅነትን አግኝቶላቸዋል፡፡ አቶ አሰፋ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በኢ-ሜይል ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መፅሐፍ ለማሳተም እስከ ዛሬ ለምን ዘገየህ?
ዘገየህ የሚባል ነገር ያለ አይመስለኝም። በየጋዜጦችና መጽሔቶች በየዘመናቱ የወጣው ተሰባስቦ መጽሐፍ ይሆናል ብዬ አስቤም አላውቅም። ስብስቡም አልነበረኝም። የነበረኝም አንዴ ሎስ አንጀለስ የምኖርባት አፓርትመንት ጣራው ላይ ቧንቧው ፈንድቶ፣ እንደ ጽሕፈት ቤት የምጠቀምበት ክፍል ኮምፒዩተሬንም ጭምር ጨርሶ በላው። የዚህ መጽሐፍ የማድረጉን ሐሳብ ያመነጩት “ያንተን ጽሁፍ እያነበብን ነው ያደግነው!” የሚሉ ወጣቶች ናቸው። አሁን በFacebook ጭምር እንደዚያ የሚሉ ቁጥራቸው ብዙ መሆኑን ተረዳሁ። እንዳለጌታ ከበደና ወሰንሰገድ ገብረኪዳን እዚያው ውስጥ ቅድሚያ ያላቸው ናቸው።
 መቼ፤ ምን ብዬ ጽፌም እንደነበር ያው ከናንተው ጋር ወይም ትንሽ ቀደም ብዬ ነው ያነበብኩት። ሳነበው “እፎይ!” አልኩኝ። “ምነው ባላልኩት!” የምለው ነገር አላገኘሁበትም። ሊጠራ፤ሊሰፋ፤የበለጠ ሊብራራ የሚገባው ሞልቷል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ ትጽፍ ነበር፡፡ አሁን ግን ከሚዲያ ተሳትፎ እየራቅህ መጥተሃል?
Self-Evident Truth የሚባል አለ። ”የታወቀ ፤የተረጋጋጠ፤ተጨማሪ ማስረጃ አቅርብበት የማይባል!” ለማለት ነው። ለምሳሌ፤አሰፋ ጫቦ ለመሆኔ ማስረጃ ያስፈልጋል። ማስረጃው መታወቂያዬ ነው። ሰፈራችን ውስጥ ሁሉም ሰው ሊያውቀኝ ይችላል። ያ ሌላ የሰፈር፣የመንደር ነገር መሆኑ ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ለመሆኑ ግን ማስረጃ አቅርብ አልባልም። “ምነው?; ቢሉ “አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ዕውነት!” ነዋ። “ከሚድያ ተሳትፎ እየራቅህ የመጣኸው ለሚለው ጥያቄ፣ ርቄ ከሆነ ተጠያቂው እኔ ሳልሆን ሜዲያው ነው። ሚዲያው ነው የራቀኝ። ግልጽ ለማድረግ ማራራቅ የሚችሉ ኃይሎች ሚዲያውን ከኔም፤ከሁላችንም አራራቁትና ቦታው ኦና ወይም ወደ ኦናነት ተጠጋ። ጦቢያ፣ኢትኦጵ፣ምንሊክ …ወዘተርፈ የሚባሉት መጽሔቶች፣ መተንፈሻ የነበሩ መድረኮች ተዘጉ። አዘጋጆቹም፤ከርቸሌ ተቀረቀረባቸው። የተረፉትና እድለኞቹ ተሰደዱ። ድረ-ገጹ ሚዲያ ነው ከተባለ ደግሞ ለራሴ ገና ጠርቶ ያልወጡ የውስጥ ማእቀቦች ያሉብኝ ይመስለኛል። የመጀመሪያው፣“ለመሆኑ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው ከድረገጽ ላይ የሚያነበው?” የሚለው ነው። አብዛኛው፣ ማንበብ የሚችለው ማንበብ ካልቻለ የተመጋቢው ቁጥር በጣም የተመጠነና አብዛኛው የኔቢጤዎች አካባቢ የሚንገዋለል ነው የሚመስለኝ። የሚመስለኝ ማለቴ የተጠና ነገር ስለሌለኝ ነው። ሌላው በአብዛኛው ድረገጽ ላይ፤በተለይም በእንግሊዝኛው የማነበው ብዙም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አይሸትም የሚለው ፍርሐቴም ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ ስም የሌሎች አገሮች፤ ህግ፣ ባሕል፤ ስነ-መንግስት፤ታሪክ ሲያመጡ ስለማይ፣ እዚያ ውስጥ የገባሁ እንደሆነ፣ “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው!” እንደሚባለው እኔንም እዚያ ከቶ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርሰኝ  የሚልም ፍርሐት አላጣም። ሌላው፣በሌላ ጊዜ፣በሌላ ቦታ (መድረክ) አንስቼው የነበረ ነው። ሱባዔ ገብቼ ስለነበር ነው። ራስን ፍለጋ (Introspection) ሊባል የሚችል ይመስለኛል። ከዚያ ስመለስ (ስወጣ) ብዙም የተናገርኩ፣ብዙም የጻፍኩ ስለሚመስለኝ ተመልሻለሁ ብዬ አስባለሁ።
በጽሑፎችህ ብዙ ጊዜ ስለ ትውልድ አካባቢህና የተወለድክበት ማህበረሰብ  ዙሪያ ታተኩራለህ የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። አንተ ምን ትላለህ?
“የትውልድ አካባቢህ ላይ ታተኩራለህ?” ይህ ብዙ የሚያነጋግር ይመስለኛል። በተለይም በአሁኑ፣“ሁልህም ወደ ክልልህ!” በተባለበት ዘመን። “አንተም ክልልህ ውስጥ ነህ ለካ!” የሚል አንድምታም የሚያጣ አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የትዝታ ፈለግ ላይ ያልኩት አለኝ። “እኔ ጋሞ ነኝ! እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ! እነዚህ ሁለቱ ተጣልተውብኝ ሳስታርቃቸው አልኖርኩም!” የሚል ነው። እኔ እንደማስበው ቁምነገሩ ትውልድ አካባቢ ተተኮረ አልተተኮረ አይመስለኝም። መሆን ያለበት፤ “አተኳኮሩ ጤነኛ ነው ወይ?” የሚለው ይመስለኛል። ጤነኛ ያልሆነ አመለካከት ሕገመንግሥት ደረጃ የደረሰበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነውና ከጥያቄው በስተጀርባ ያለው “ጠርጥር!” ይገባኛል። ይህን በዚህ እንዝጋው።
SBS በሚባል ካሳሁን ሶቦቃ በሚያዘጋጀው አውስትራሊያ ባለ ራዲዮ ጣቢያ፤ስለ የትዝታ ፈለግ ስንወያይ፣ “አንተ እንደኔ እንደኔ ሁሉም ኢትዮጵያ እንደ ጋሞ በሆነ ትላለህ!” ብሎኝ፣ ያንን ምን እንዳሰኘኝ አስረድቼ ነበር። SBS ስብስብ (Archive) ስለአለው ቢቻል ያንን ማዳመጡ ጥሩ ይመስለኛል።
ይህ ጥያቄ ሌላም፤ስብሐት ኃይለማርያምንና ማእከላዊንም፤አስታወሰኝ። ስብሐት የባኮ ልጅ ነው። ባኮ ከጅንካ በፊት የገለብና የሐመር ባኮ አውራጃ ይባል የነበረው ዋና ከተማ ነበር። ስብሐት ከብላታ ኃይለማርያም ልጆች ውስጥ አንዱ ነው። ብላታ ኃይለማርያም ደግሞ የመጀመሪያው ወያኔ መስራችና መሪ የነበሩ ናቸው። በዚያ ተከሰው የኃይለ ሥላሴ መንግስት አግዟቸው የኖሩትም፣ልጆቻቸውንም የወለዱትም ባኮ ነው። ደርግ በምህረት ሲለቃቸው፣ አገር አስተዳደር ነበርኩና ብላታ ኃይለማርያን ለአፍታ አነጋግሬአቸው ነበር። ስብሐት የታሰረው በወያኔነት ተጠርጥሮ ነበር። ስብሐት በወያኔነት ታስሮ ግን “የአገሩ ልጅ፤የጋሞ ጎፋ ልጅ!” ብሎ የሚቀርበኝ እኔን ነበር።
አንድ ቀን በረንዳው ላይ ቆመን፣ ያለ የሌለን ስናወራ፣ የጢስ አባይ ፏፏቴ ተነሳ፣ እኔም ጢስ አባይን አውቀው ነበርና፤ሌሎችም ጨምረውበት በማድንቀ፣ስብሐት ቱግ ብሎ፤ “የኛ ይበልጣል! ስላላያችሁት፤ስለማታውቁት ነው እንጅ ባኮ ያለውን ፏፏቴ የሚያስንቅ የትም የለም!” አለ። ”የኛ ይበልጣል!” ነው ያለው። ስብሐት ኃይለማርያም አገሩ፤ተቆርቋሪነቱ ለባኮ፤ብሎም ለጋሞ ጎፋ መሆኑ ነው። ከባኮ፤ከጋሞ ጎፋ ጋር መንፈሱ፣ነፍሱና ስጋው ተዋህደዋል ልንል እንችላለን።
ከስብሐት ሌላ ብዙ ምሳሌዎች ልጠቅስ እችላለሁ። አንድ የሚደንቅ የአማራን ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ። በግራኝ ወረራ ጊዜ ታቦታቸውን ይዘው የሸሹ አማሮች ከየትም በላይ ወደ ጋሞ ጎፋ በብዛት የመጡ ይመስለኛል። ለዚህ ማስረጃው የአባ ባህርይ የብርበር ማርያም፤የዶርዜ ጊዮርጊስ፤የኤሌ ገብርኤል አሉ። ጋሞ “ቆሞ” የሚለው ራሱን የሚለይበት መጠሪያ አለው። ክላን (clan) የሚሉትን የእንግሊዝኛው ቃል ይገልጸው እንደሁ እንጃ። ወደ 10 ቆሞ አለ። ከነዚህ 10 ቆሞዎች አንዱ አማራ ነው። አሁን ዶርዜ ሄደው አማራ የት ነው ቢሉ ማንም ያሳያል። የዶርዜ ጊዮርጊስ አጥቢያው ዶርዜ አማራ ነው የሚባለው። የኤሌ ገብርኤል አጥቢያውም ኤሌ አማራ ነው የሚባለው። የጋሞ አማራ የሚለው ቃል አጠራሩ በመሠረቱ እንደሚባለው ሳይሆን ቅላጼው ለየት ይላል። ”ማ’ እና “ራ” ላይ ላላ፤ለቀቅ ይላል። ይህ እንግዲህ ወደ 400 አመት የሚደርስ ታሪክ መሆኑ ነው።
በኔ ግምት ምናልባትም ከየትኛውም አለም በላይ፤በኢትዮጵያም አንጻር ሲታይ፣ ብዙ ብሔረሰብ ያለበት አካባቢ ቢኖር ጋሞ ጎፋ ነው። አሜሪካኖቹ አሜሪካንን Melting Pot ይሉታል። ማቅለጫ ድስት (ሰታቴ) እንደማለት ነው እንበለው። እዚህ የመጣው ህዝብ ሁሉ ቀልጦ አንድ አሜሪካዊ ሆኗል ለማለት ነው። ወረቀት ላይ አንድ ሆኖ እንደሁ እንጅ በድርጊት አሁንም ፈንጠር ፈንጠር ብሎ እንደቆመ ነው። ሰው ቀልጦ ወደ አንድ ሸማ መልበስ የደረሰበት አካባቢ ቢኖር ጋሞ ጎፋ ነው ማለት የምችል ይመስለኛል። “አሻም!” የሚል ሕዝብ ነው። አሻም ከአማርኛው “እንኳን ደህና መጡ!”፤ከእንግሊዝኛው “Welcome” ከፈረንሳይኛም “Beinvenue” ለየት የሚል የማቀፍ ቃና ያለው አቀባበል ነው። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ባለ- በሌለ፤ከፋብሪካ በወጣ ክስ-ውቅስ ጭምር ያ ሁሉ ንትርክ ሲታይ፣ በአንጻራዊ አነጋገር እጅግ ሰላማዊ አካባቢ ደቡቡ፤በተለይም ጋሞ ጎፋ ነው። ታዲያ ያንን ታሪክ፤ያንን ባህል፣ ይህንን ተመክሮ ለመላው ኢትዮጵያ ለማሳወቅ፤ቢቻልም ለመላው አለም ለማዳረስ የኔ ሙከራ ቅንጭብ (The Tip of the Iceberg) ነች ማለት ነው።
ሌላ ስለ ጋሞ ደጋ የውጭ አጥኝዎችም ብዙ ያሉት አለ። “A Thousand Suns: The View From Ethiopia’s Gamo ...” የሚለውን ፊልም መመልከቱ/ማየት ጋሞ ለስንት ዘመናት፤የመሬት ጥበቃን ስርዐት የያዘ እርሻ ሲያርስ የኖረ ሕዝብ መሆኑን እናያለን። የቋንቋ አጥኝዎች፤የውጭም የኢትዮጵያም የአፍሪቃና የአዚያ ህዝቦች ቋንቋ (Afroasiatic Languages) የሚሉት አለ። ይህ ቋንቋ ቤተሰብ ከሲዳማ እስከ ወለጋ እስከ ባምባሲ የሚዘረጋ ነው። ዝነኛውን የከፋን ንጉሳዊ ግዛትም የሚጨምር ነው። ምናልባትም የዚህ ህዝብ ዋና ቤቱ ጋሞ ሊሆን ይችላል የሚል አዝማሚያ አለ። በቅርቡ ክ4,500 አመት በላይ የሆነ የሰው አፅም ቅሪት ከጋሞ ደጋዎች ተገኝቷል። ”ባይራ!”ብለዉታል። ባይራ ማለት ታላቅ ማለት ነዉ። ይህ ጥንታዊ፣ የሰለጠነና ዘመናዊ የእርሻ ዘይቤ ነበራቸው/አላቸው ከሚባለው ጋር ተደምሮ፣ ጋሞ ጎፋን እንደ ጋና አትኩረን ለማየት የሚጋብዝ ይመስለኛል።
አብዛኛው የናንተ ዘመን ፀሐፊዎች ያለፈ ስርአትን ወቃሽ ናቸው። በየዘመናቱ በነበሩ መንግስታት የተሠሩ በጐ ነገሮችን ለማንሳት ለምን አይሞከርም?
በክስ-በውቅስመልክ መቅረቡ ንጅ ታሪክ የሚባለው’ኮ ያለፈን፣ማብጠልጠል፤ማበራያት፤ፍሬውን ከገለባው፣እውነቱን ከፖለቲካውና ከተረቱ ለይቶ አብጠልጥሎ ማውጣት ይመስለኛል።
 መውቀስ ካልነውም መላ ያለው፤ማስረጃ ያለው ወቀሳም ጥሩ ይመስለኛል። ጅምላ ወቀሳ ከሆነ ደግሞ ወቀሳውንም ወቃሹንም ከፍቶ ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል።
ማለትም፣ “ለመሆኑ አንተ ማነህ?”፣ “ከነማን ጋር ነበርክ?”፣ ”ያኔስ የት ነበርክ?”፣ “ምን ምን ሰራህ?”፣ “ምን ምንስ መስራት ሲገባህ ሳትሰራ ቀረህ?”፣ ”በምን ምክንያት?”፣ “ሌላው አይን ውስጥ ያለውን ትቢያ ማሳየት ብቻ ሳይሆን አንተስ አይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ ምን እናደርገው?” ማለቱ ጥሩ ይመስለኛል።
“የእናንተ ዘመን ጸሐፊዎች” ሲባል እኔ እንደሚገባኝ ይህንን፤በ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ያለውን፤የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ተብሎ የሚታወቀውን፤በአሜሪካና በአውሮጳም ቅርንጫፎች የነበሩትን፤ዘውዱ ወርዶ ከደርግም ጋር ጎራ ለይተው የተፋለሙትንና የተላለቁትን፣አሁንም በርዝራዥ መልክም ቢሆን መንግስት የሆኑትና ተገፍተው ወጥተው ዳር ቆመው “እኔ/ እኛ አይደለንም፤ እነሱ ናቸው!” የሚለውን የምናስተጋባውን ይመስለኛል።
ተከሳሹ ሁሌም ደርግ ነው። ሻዕቢያ፤በወያኔ አማካኝነት “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረችና አሁን ነጻ ብትወጣ እደግፋለሁ!” የሚል ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽፈው ነጻ ወጥተዋል። ስለዚህ ሻዕቢያ ዛሬ፣በአሁን የክሱ ችሎት ውስጥ የለም። የቀሩት ከሳሾች በጋራም ሆነ በተናጠል የሚከሱት ደርግን ነው።
ይህንን የደርግን ተከሳሽነት በሕግ አንጻር እንየው። አንድ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ ጉዳዩ ተሰምቶ፣ ፍርድ ከተሰጠበትና በፍርዱ መሠረት ቅጣቱን ተቀብሎ ከፈጸመ የድርጊቱን ከፍሏል ማለት ነው። የደርግ አባሎችና ርእሰ ብሔር የነበሩ ብቻ ሳይሆን ከደርግ ጋር ነበሩ የሚባሉ፤በወያኔ ቋንቋ ንክኪ የሆኑ ሁሉ ታስረው፣ ማቀው፣ ፍርዳቸውን ፈጽመው ተለቀዋል። መሪዎቹ የሚባሉት የተለቀቁት ከ20 አመት በኋላ ነበር። ብዙዎቹ ከርቸሌ ነበር የሞቱት። ይህም ማለት በክስ መልክ የደርግ ፋይል እስከ ወዲያኛው ተዘግቷል ማለት ነው። ደርግን አሁን መክሰስ፣ እዚህ እኔ ያለሁበት አገር Double Jeopordy ይሉታል። ለዚያው ወንጀል ሁለቴ መክሰስ እንደ ማለት ነዉ። ሕግ አይፈቅድም! ከአሁን በኋላ የደርግ ነገርና ዘመን የሚያገለግለን ለሰከነ የታሪክ ጥናትና ምርምር ብቻ ነው። የደርግ ከሳሾች፤ ይህንን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ ”እስከ ሰባት ትውልድ እበቀልሀለሁ!” ኦሪት ነው። ሐዲስ ተክቶታል! ይልቁንም ለዚህ ሁሉ ክስና- ውቅስ በአብዛኛው የዳረገንን ፤መንግስቱ ኃይለማርያምን እንዴት አድርገን ፍርድ አደባባይ እናድርስ የሚለውን ብንመክርበት የተሻለ ይመስለኛል።
መኢሶንና ወዝሊግን ከተከሳሾች መዝገብ ውስጥ ማስወጣት ያለብን ይመስለኛል። ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ተብሎ የኢትዮጵያን ቀጣይ ትውልድ በፈጀውና የደርግ አባላትንም እርስ በርስ በማባላት የተጫወቱትን ሚና ሌሎች የጻፉት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስና ፍስሀ ደስታ ደህና አድርገው ገልጠዉታል። ያም ሆኖ፣ መኢሶኖች በተለየ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተዋል። መንግስቱ ኃይለ ማርያም፤የመኢሶንን መሪዎች አርዷቸዋል። ከዚህ በላይ የሚከፈል ዋጋ ሊኖር ስለማይችል፣ ከደርግ ጋር በማበር የፈጸሙትን ወንጀል መዝገብ ዘግተን፣ ወደ መዝገብ ቤት በቋሚነት መመለስ ያለብን ይመስለኛል። አሁን ያለው ትንሹ ችግር በሕይወት የተረፉት ይህንን የክስ መዝገብ ያልዘጉ መሆናቸው ነው። ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ለምን ተናገሩ? ለምንስ ይናገራሉ? አይደለም። ንስሀ መግባት ግን አማራጭ ያለው አይመስለኝም።
አሁን የሚቀሩን ሁለት ፤ሙሉ ሥራቸውና ከፊል ሥራቸው ወቃሽ የሆኑ ናቸው። እነሱም ኢሕአፓና ወያኔ ናቸው። ኢሕአፓ ደርግን መክሰስ ሙሉ ስራው ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አዲስ፣ ደርግንም ኢሕአፓንም የማያውቁትን አሰልጥኖ፣ በከሳሽነትና-ወቃሽነት አሰማርቷል። እዚህ አሜሪካ፤ “እገሌ በደርግ ጊዜ ቀበሌም….እዚህም… እዚያም ነበር” እንዲሉ ስራ የተሰጣቸው እድሜያቸው 30ው ውስጥ የሆኑ አሉ። ለመጭው ትውልድ ውርስ መሆኑ ነው። ስለ ደርግ መጥፎነት፤ስለ ኢሕአፓ መስዋእትነት እንጅ የነገሯቸው ሙሉ እውነት የለም። ቢያንስ ከነዚህ አንዱን “ለመሆኑ ስለ ኢሕአፓ ምን ምን ታውቃለህ?” ብዬው ነበር። “ለኢትዮጵያ የቆመ ብቸኛው ድርጅት; መሆኑን ብቻ እንጅ ሌላ ምንም የሚያውቀው አልነበረም። “ጌታቸው ማሩን ታውቀዋለህ?” አያውቀውም።
ያ እንዳለ ይሁን እንበል። ከሁሉም በላይ ግን የኢሕአፓ ሙሉ ለሙሉ ያልተወራረደ ሂሳብም አለ’ኮ። በዚያ ይባስ ብሎ ደግሞ ሂሳቡን ሊያወራርዱ የሚችሉ ከመሪዎች ውስጥ የተረፉ፣ በሕይወት ያሉት ሁለቱ፤ክፍሉ ታደሰና እያሱ አለማየሁ ብቻ ይመስሉኛል። እንደምገምተው፤ሁለቱም እድሜያቸው እንደኔው 70ው ውስጥ ይመስለኛል። “ለንስሀ ሞት አብቃኝ!” የሚባልበት እድሜ መሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው የኢሕአፓ አስኳሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር (አአዩተማ) ነበር። እኔም እዚያው ነበርኩ። ማሕበሩ የተሰባሰበው በሁለት ሰንደቆች ዙሪያ ነበር። እነዚህም ፡-1. የዘውድ አገዛዝ ይብቃው (ይውደም) 2. መሬት ላራሹ ነበሩ።
መስከረም 2,1967 የዘውድ አገዛዝ በኢትዮጵያ ለአንዴም ለዘለዓለምም አከተመ። የካቲቲ 25,1967 የገጠር መሬት አዋጅ ታውጆ፣ መሬት ላራሹ ሆነ። የአአዩማ ጥያቄ መልስ አገኘ ማለት ነው። የቀረ የሚሟላ የለም ማለት አይደለም። የትግላችን እምብርት ጥያቄ የነበረው መልስ አግኝቷል ማለት ነው።እስቲ አሁን ደግሞ ኢሕአፓ ያደረጋቸውን፤በግልጽ በራሳቸው በተለይም በመሪዎች በክፍሉ ታደሰና በብርሐነ መስቀል ረዳ ከተነገሩን ብቻ ልጥቀስ።በኋላ የኢሕአፓ መሪ የሆኑት ብርሐነ መሰቀል ረዳና እያሱ አለማየሁ፤ ፈር ቀዳጅ ሁነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጠላፊዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ሌላ 4 ጊዜ ተጠለፈ። አምስቱንም ጠላፊዎች ያቀነባበረው ጀበሀና ሻአቢያ ነበረ። ይህንን የሚነግረን ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” በሚለው መጽሐፉነው።
ኢሕአፓ ትግራይ ውስጥ፣ አሲምባ የሚባል ቦታ ምሽግ የከፈቱት የካቲት 25 ቀን 1967 ነበር። ይህንን የሚነግረን ብርሐነ መስቀል ነው። መሬት ላራሹ ያሉት፣ መሬት ላራሹን ያወጀን መንግስት ለመውጋት ጫካ የገቡበትን ቀን ልብ ይሏል። (መሬት ለአራሹ) የታወጀ ለት ነበር!) ለሁለት አመት ያክል አስልጥኖ፤መሳሪያ አስታጥቆ፤ስንቅ ሰንቆ አሲምባ ያስገባቸው ሻቢያ ነበር።
ክፍሉ እንደሚነግረን፤ ሶማሌያ ከሲአድ ባሬም ጋር ነበሩ። ሶማሌ ኢትዮጵያን ስትወር፣ የኢትዮጵያን ወታደር ከውስጥ በ5ኛ ረድፈኝነት ወግተዋል። የገጠር መሬት አዋጅን ስራ ላይ ለመተርጎም የዘመተውን በትነዋል። በመላው ኢትዮጵያ ከተማ ከሕጻን እስከ አካለ ስንኩል (የምኒልክ ትምህርት ቤት ዲሬክተር) በየመንገዱና በየቢሮው ገድለው ጥለዋል። የመድኃኔአለም ትምህርት ቤት ተማሪ ሰቅለዋል። ቀበና ወንዝ ውስጥ ፈጥፍጠው ገድለዋል። ጌታቸው ማሩን መግደል ብቻ ሳይሆን በአሲድም አቃጥለዋል። ጫካ ለውጊያ ያሰማሯቸውን፤ይርጋ ተሰማን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ፣መጀመሪያ እስኪቀምሉ ጉድጓድ ውስጥ አስረው አማቀው፣በመጨረሻም ረሽነዋቸዋል። የገደሉትን ሰው ቁጥር በከፊልም ቢሆን ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ በመጽሐፉ ገልጾታል። ኢሕአፓ ከሻቢያም ብቻ ሳይሆን የወያኔ ተባባሪ፣ዛሬም የኢህዴግ አባል ነው። የመጀመሪያው የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚንስቴር ፤ታምራት ላይኔ፤ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲሱ ለገሰ ኢሕአፓ የነበሩ ናቸው። አሁን ብአዴን ሆነናል የሚሉት አክሮባቲክስ አንደተጠበቀ ሆኖ።ይህ ያልተዘጋ ቁስል ነው። መልስ የሚፈልግ ነው። ኢሕአፓ ደርግም ላይ ሆነ ወያኔ ላይ ጣቱን ከመቀሰሩ በፊት ለዚህ ክፍት ለተቀመጠ ቁስላችን መዝጊያ መስጠት ያለበት ይመስለኛል። (እናም ኢሕአፓ ውስጥ ያለችው “ኢ” ኢትዮጵያ መሆንዋ ነው።) በዚህ ድርጊታቸው ውስጥ ለመሆኑ ኢትዮጵያ አለችበት የሚለውም ጥያቄ መልስ የሚሻ ይመስለኛል።የወያኔ ጉዳይ በመሠረቱ ህግ ውስጥ Mutatis mutandis የሚሉትን አይነት ይመስለኛል። በግዕዙ ዚኒ ከማሁ የሚባለው ነው። አነሰም በዛ ከላይ እንደተገለጸው እንደ ማለት ነው። ይህም ማለት ቀደም ሲል ስለ ኢሕአፓ ያልኩት ለወያኔም ያገልግላል። ለምሳሌ፣ ወያኔ የተነሳው፣የተመሠረተው ከደርግ መጥፎ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት አይደለም። ደርግ አልነበረምና አይተዋወቁምና ነው። ደርግ ንጉሱን በማውረዱ በተፈጠረው ክፍተት ትግራይን ነጻ ለማውጣትና የትግርይን ሬፑብሊክ ለመመስረት ነው። የመጀመሪያው የእነብላታ ኃይለ ማርያም ቀጣይ መሆኑ ነው። ይህ ሰነዳቸው የሚመስከረው ነው።
ንፁህ ህዝብም ሆነ ወይም ተቃዋሚ ነው ተብሎ የተፈረጀ በመፍጀት ከኢሕአፓ ቢበልጡ እንጅ አይተናነሱም። ልዩነቱ (እስከ 1983 ግንቦት መሆኑ ነው) የወያኔ አባሎቻቸው በነበሩትም ሆነ በሕዝብ ላይ የተፈጸመው ግፍ ከኢሕአፓ የሚለየው ትግራይ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ነበር። ----- አንድ ነገር ልብ ብንል የሚሻል ይመስለኛል። ባለፈው ወር የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በኤርትራ ጉዳይ ያቋቋመው ቡድን፣ስለ ኤርትራ መንግስት የሰጠውን ሰፊ ሪፖርት ልብ ይሏል። ያ ሠነድ ሲታይ፣ስለ ኢትዮጵያ ጭምር ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስትን ከዚያ ውስጥ የሚመለከተው ክፍል ስንት እጁ (%) ነው? የሚል ጥያቄ መነሳት ያለበት ይመስለኛል፡፡

Read 4397 times