Saturday, 09 July 2016 10:45

2 ባለ አምስት ኮከብ፣ አንድ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች እየተገነቡ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

      ሳንታ ማሪያ ሪል ኢስቴትና ሆቴል ኃ.የተ.የግ.ማ በዓለም ትልቁና ታዋቂ ከሆነው ወንድሃም ሆቴል ግሩፕ ጋር የሦስት አዳዲስ ሆቴሎች ማኔጅመንት ውል ተፈራረመ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት በሳንታ ማርያም ግሩፕ በኩል መስራቹና ሊቀመንበሩ አቶ አቤል ሳህለማርያም፣ በወንድሃም በኩል የምስራቅ፣ መካከለኛውና ኢኳቶሪያል አፍሪካ ፕሬዚዳንትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ዳን ሩፉ ውሉን ፈርመዋል፡፡
በአዲ አበባ የሚገነቡት ሁለት ሆቴሎች ባለ5 ኮከቡ ዊንድሃም  አዲስ አበባና ባለ 4 ኮከቡ ትሪፕ (TRYP) ዊንድሃም አዲስ አበባ ሲሆኑ ባለ 5 ኮከቡ ውንድሃም ዘጠኝ ሱቶችን ጨምሮ 161 የመኝታ ክፍሎች፣ ባለ 4 ኮከቡ ትርፕ 12 ሱቶችን ጨምሮ 130 ክፍሎች እንደሚኖሯቸው ተገልጿል፡፡
ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ1.3 ካ.ሜ ርቀት በቦሌ መንገድ ላይ እንቅስቃሴ በሚበዛበት የቢዝነስ ማዕከል እየተሰራ ያለው ትርፕ ባይ ውንድሃም አዲስ አበባ ሆቴልና ዓለም አቀፉን ብራንድ በአፍሪካ ያስተዋውቃል ተብሏል፡፡ በጣሪያው አናት የሚሰሩት ድንቅ መዝናኛዎች፣ የአካል እንቅስቃሴ መስሪያ ማዕከል ሳውናና ስፓ አለው፡፡ እንዲሁም ቀኑን ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ሬስቶራንት፣ ኮክቴል ባርና ላውንጅ ሲኖሩት፣ ሆቴሉ በ2020 መጨረሻ ግንባታው አልቆ እንግዶችን ማስተናገድ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
በቦሌ መንገድ ከትርፕ አቅራቢያ ከሸገር ሕንፃ ዝቅ ብሎ እየተሰራ ያለው ባለ 5 ኮከቡ ውንድሃም አዲስ አበባ፣ ውንድሃም በአፍሪካ የሚከፍተው የመጀመሪያው ሆቴል ሲሆን የብራንዱን ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ለአዲስ አበባ ጎብኚዎች ያቀርባል ተብሏል፡፡ እንግዶች ሆቴሉ ባለው ሁለት ሬስቶራንቶችና ሁለት ላውንጆች ወይም በሆቴሉ ጁስ ባርና ካፌ ሊዝናኑ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ በ2018 መጨረሻ እንግዶችን እንደሚቀበል ይጠበቃል፡፡
ሦስተኛው ሆቴል ከአዲስ አበባ ደቡብ 180 ኪ.ሜ ላይ በኦሮሚያ ክልል በላንጋኖ ሐይቅ እየተሰራ ያለው ውንድሃም ግራንድ ላንጋኖ ሪዞርት ነው፡፡ ሪዞርቱ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ አገልግሎት ሲሰጥ ከሐዋሳው ሂልተን ቀጥሎ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ብራንድ ይሆናል፡፡ ሆቴሉ 12 ሱቶችና 24 ደሉክሰን ጨምሮ 112 ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ደንበኞች ከሆቴሉ ውጭ ከሚገኙት ከመዋኛ፣ ከስፓና ከቴኖስ መጫወቻ በተጨማሪ በሐይቁ ላይ በውሃ ስፖርቶች የሚዝናኑባቸው ቁሶች ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ፣ በሁለት ሬስቶራንቶች፣ ኮክቴል ባርና ላውንጅ ምግብና መጠጥ እንደሚያስተናግድ ታውቋል፡፡ ውንድሃም ግራንድ ላንጋኖ ሪዞርትም በ2018 መጨረሻ ይከፈታል ተብሏል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በዓለም ትልቅ ከሆነው ውንድሃም ሆቴል ግሩፕ ጋር በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አቤል፤ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በ2020 ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቁጥር ከ2-5 ሚሊዮን ለማድረስ አቅዷል፡፡ በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ብራንድና ጥራት ያላቸው ሆቴሎች ፍላጎት ከፍ ይላል፡፡ ስለዚህ የሆቴሎቹን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ በአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ላይ የበኩላችንን ሚና ለመጫወት ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ የምሥራቅ፣ መካከለኛውና ኢኳቶሪያል አፍሪካ የውንድሃም ሆቴል ግሩፕ ፕሬዚዳንትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳን ሩፍ፣ የሦስቱ አዲስ ሆቴሎች ስምምነት፣ ለተጓዦች፣ ከፍተኛ ጥራትና መገልገያ ቁሶች ያሏቸው ማረፊያዎች ከመሆናቸውም በላይ ለ800 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ሳንታ ማሪያ ሪል ኢስቴትና ሆቴል በ2011 የተቋቋመና መቀመጫው አዲስ አበባ የሆነ የሳንታ ማሪያ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግ. ኩባንያ እህት ድርጅት ነው፡፡ ሳንታ ማርያ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ1994 ዓ.ም የተቋቋመ ደረጃ አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፡፡ ሳንታ ማሪያ ኮንስትራክሽን፣ በታማኝነቱ፣ በጊዜ በማስረከብና በከፍተኛ ጥራት ስራ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘ ድርጅት ሲሆን በአሁኑ ወቅት 500 ሰራተኞች አሉት፡፡
ውንድሃም ሆቴል ግሩፕ በዓለም የትልቁ የሆቴል ኩባንያ ሲሆን በ73 አገራት በተለያዩ ሆቴል ብራንዶች ከ679 ሺህ በላይ ክፍሎች ያላቸው 800 ያህል ሆቴሎችና ሪዞርቶች ያስተዳድራል፡፡


Read 1564 times