Saturday, 16 July 2016 12:07

የ31ኛው ኦሎምፒያድ አንዳንድ እውነታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

      የብራዚሏ ዋና ከተማ ሪዮ ዲጄነሮ የምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ከሶስት ሳምንት በኋላ እንደሚጀመር ይታወቃል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት አንዳንድ እውነታዎች ናቸው፡፡
ብራዚል በደቡብ አሜሪካ አህጉር የመጀመርያው የኦሎምፒክ አዘጋጅ ሆናለች፡፡ ኦሎምፒክ ያላስተናገደችው ብቸኛዋ አህጉር አፍሪካ ናት፡፡    የሪዮ ኦሎምፒክ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፅ 1.5 ሚሊዮን ላይክ አለው፡፡
ኦሎምፒክን በማስተናገድና በተለያዩ ስራዎች በመሰማራት የሚንቀሳቀሱ ብራዚላውያን  ከ130ሺ  በላይ ናቸው፡፡
ብራዚል ለውድድሩ መስተንግዶ እና አጠቃላይ ዝግጅት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት አውጥታለች፡፡ አስቀድሞ ከተመደበው በ1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
አዘጋጇ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት በ2009 እኤአ ላይ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ስትመረጥ ተፎካካሪዎቿ የነበሩት የስፔኗ ማድሪድ፤ የጃፓኗ ቶኪዮ እና የአሜሪካዋ ቺካጎ ከተሞች ነበሩ፡፡
በ28 የስፖርት አይነቶች ለ17 ቀናት 306 ውድድሮች ይካሄዳሉ፡
አዲስ አለም ‹‹ኒው ዎርልድ›› በሚል መርህ ነው፡፡
ኮሶቮ እና ደቡብ ሱዳን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
በሪዮ ዲጄነሮ 33 የመወዳደርያ ስፍራዎች ሲገኙ፤ በሌሎች 5 ከተሞች ሳኦ ፓውሎ፤ ቤሎ ሆሪዜንቴ፤ ሳልቫዶር፤ ብራዚሊያ እና ማኑስ 5 የመወዳደርያ ማዕከሎችም አሉ፡፡
ከ207 አገራት  የተውጣጡ 17ሺ ኦሎምፒያኖች እና ልዑካኖቻቸው ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ከ186 አገራት ቢያንስ 1 ኦሎምፒያን ሚኒማውን አሟልቶ ይሰለፋል፡፡
የብራዚል ብሄራዊ ስታድዬም ማራካኛ የመክፈቻ እና የመዝጊያ ስነስርዓቶች ያስተናግዳል፡፡  የአትሌቲክስ እና የሜዳ ላይ ውድድሮችን የሚካሄዱበት ማራካኛ 78ሺ ተመልካቾች የሚይዝ ሲሆን፤ በ1950 እኤአ ላይ ብራዚል እና ኡራጋይ ባደረጉት የዋንጫ ጨዋታ 173ሺ ተመልካች በማስተናገድ በእግር ኳስ ታሪክ ክብረወሰን እንዳስመዘገበ ይታወቃል፡፡
የኦሎምፒክ መንደሩ በውድድሩ ታሪክ ግዙፉ ነው፡፡ 3604 አፓርትመንቶች ተገንብተዋል፡፡ ከ80ሺ በላይ ወንበሮች፤ 70ሺ ጠረጴዛዎች፤ 29ሺ ምንጣፎች፤ 60ሺ የልብስ መስቀያዎች፤ 6ሺ ቴሌቭዥኖች እና 10000 ስማርትፎኖች ይገኙበታል ፡፡ በቀን 60ሺ ሳህን ምግብም ይቀርባል፡፡
7.5 ሚሊዮን ትኬቶች ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ ካለፈው የለንደን ኦሎምፒክ በ200ሺ ቀንሷል፡፡
የቴሌቭዥን ስርጭት ከአጠቃላይ የኦሎምፒኩ ገቢ 47 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ውድድሩ በሚከናወንባቸው 17 ቀናት  ውስጥ 3.6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች እንደሚኖረው እና በአጠቃላይ እስከ 40ሺ ሰዓት ሽፋን እንደሚያገኝ ተጠብቋል፡፡
ከ25ሺ በላይ ጋዜጠኞች ከመላው ዓለም ተውጣጥተው በብራዚል በመክተም ለኦሎምፒኩ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የዘገባ ሽፋን ይሰጡታል፡፡
ከ500ሺ በላይ ቱሪስቶች ይታደማሉ፡፡
ሁለት አዳዲስ ስፖርቶች የሚካሄዱበት ሲሆን የጎልፍ እና የራግቢ  ውድድሮች ናቸው፡፡ ከ112 ዓመታት በኋላ በኦሎምፒክ የሚካሄደው የጎልፍ ስፖርት  ለመጨረሻ ጊዜ ተደርጎ የነበረው በ1904 እኤአ ላይ በሴንትሊውስ አሜሪካ  ነበር፡፡  ከ92 ዓመታት በኋላ በኦሎምፒክ ባለሰባት ተጨዋቾች ራግቢም የሚደረግ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በ1924 እኤአ ፓሪስ ላይ የተደረገ ነበር፡፡
450ሺ ኮንደሞች ይቀርባሉ፡፡
በእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ  400 ኦሎምፒያን ኳስ ተጨዋቾች ተመዝግበዋል፡፡
15 ዋና የብራንድ ስፖንሰሮች በአጠቃላይ ከ22 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በስፖንሰርነት እና በአጋርነት ይሰሩበታል፡፡  ብሪጅስቶን፤ ኮካ ኮላ፤ ማክዶናልድ፤ ኦሜጋ፤ ፓናሶኒክ፤ ፒ ኤንድ ጂ፤ ቪዛ እና ሳምሰንግ ይገኙበታል፡፡ ከኦሎምፒክ ገቢው 45 በመቶው ከስፖንሰሮች የሚገኝ ነው፡፡    ለአዲሱ የኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ባች የመጀመርያው ኦሎምፒክ ነው፡፡
ለውድድሩ የቀረቡ የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 306 ነው፡፡
ሜዳልያዎች ዲዛይናቸው ለዓለም የተዋወቀው ውድድሩ ከመጀመሩ ከ5 ወራት በፊት ነው ፡፡ መረጃዎች እንደሚገልፁት አንዱን የኦሎምፒክ ሜዳልያ ለመስራት 18 ሰዓታትን ይወስዳል፡፡ የወርቅ ሜዳልያው የሚሰራው 1 % ወርቅ፤92 %ብር እና 6.8 % መዳብ ተቀይጠው ነው፡፡ የብር ሜዳልያው ደግሞ በብርና መዳብ ቅልቅል ሲቀረፅ፤ የነሐስ ሜዳልያው ደግሞ 97% መዳብ፤ 2.5% ዚንክ እንዲሁም 0.5% ቲን በመቀላቀል ይሰራል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ ለአሸናፊ ኦሎምፒያኖች ከሜዳልያዎች በቀር የገንዘብ ሽልማቶች አይሰጡም፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ግን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አማካኝነት ከሜዳልያዎች ባሻገር የገንዘብ ሽልማትም ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈ አትሌት 60ሺ ዶላር ማግኘቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን ለሚያሸንፉ አትሌቶች የሽልማት ገንዘብ በአዘጋጆቹ የማይሰጥ ቢሆንም በርካታ አገራት ሜዳልያ ያገኙ ኦሎምፒያኖቻቸውን በተለያየ ደረጃ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ያበረክቱላቸዋል፡፡ በእኛ አገር የኦሎምፒክ አሸናፊዎች በተለያዩ ጊዜያት ከመንግስት የመሬት እና የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙት ማለት ነው፡፡ ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ኦሎምፒያን ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት በማበርከት በአንደኛ ደረጃ የምትጠቀሰው 500ሺ ዶላር የምትሰጠው ቻይና ናት፡፡ ደቡብ ኮርያ 320ሺ፤ ጀርመን 190ሺ፤ ፈረንሳይ 290ሺ፤ ጣሊያን 300ሺ፤ ሃንጋሪ 200ሺ፤ አውስትራሊያ 175ሺ ፤ ኢራን 250 ሺ፤ ህንድ 210ሺ፤ ስፔን 90ሺ፤ አሜሪካ 125ሺ እንዲሁም ጃማይካ 200ሺ ዶላር የወርቅ ሜዳልያ ላስገኙላቸው አትሌቶች ይሸልማሉ፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው  ለወርቅ፤ ብር እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ኦሎምፒያኖች እንደቅደምተከተላቸው የሚሸልሙት የገንዘብ መጠን ከ1 እስከ 5 ያለው የአገራት ደረጃ ነው፡፡
ቻይና 500ሺ ዶላር፤ 300ሺ ዶላር፤ 150ሺ ዶላር
አዘርባጃን 500ሺ ዶላር፤ 255ሺ ዶላር፤ 125ሺ ዶላር
ብራዚል 320ሺ ዶላር፤ 90ሺ ዶላር፤ 40ሺ ዶላር
ጃፓን 250ሺ ዶላር፤ 50ሺ ዶላር፤ 20ሺ ዶላር
ሩስያ ለአንጋፋ አትሌቶች ብቻ 350ሺ ዶላር፤ 55ሺ ዶላር፤ 22.5ሺ ዶላር
ብራዚል ለ31ኛው ኦሎምፒያድ አስተማማኝ ደህንነት ከ26 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ ወታደሮች፤ ፖሊሶች ፤የስለላ ባለሙያዎች እና የማህበረሰብ ጥበቃ የሚገኙበትን 80ሺ የፀጥታ ሃይሎችን ታሰማራለች፡፡ ከእነዚህ የፀጥታ ሃይሎች መካከል ከ55 አገራት በድጋፍ የተገኙ 250 ፖሊሶች የሚገኙበት ሲሆን አሜሪካ ፤ ቤልጅዬም እና ፈረንሳይ በደህንነት ተቋማቸው ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በኦሎምፒኩ ወቅት ከ500ሺ በላይ ቱሪስቶች ብራዚልን እንደሚጎበኙ ሲጠበቅ 400ሺ ያህሉ ሙሉ መረጃቸው ተጥንቶ የመግቢያ ፈቃድ ሲያገኙ ከ7ሺ 200 በላይ ቱሪስቶች ብራዚል እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የውድድሩ የገድ ምልክት የሆነው የብራዚልን የዱር አራዊት ይወክላል የተባለው ቪኒከስ የተባለ ፍጡር ሲሆን በተለያዩ ንግዶች እስከ 398 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚሆንበት የተጠበቀ ነው፡፡
የስደተኞች ቡድን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ የሚካፈልም ይሆናል፡፡ ውሳኔውን ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ ከ5 ወራት ቀደም ብሎ ይፋ ያደረጉት አዲሱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ሲሆኑ፤ በዓለም ዙርያ ያለውን የስደተኞች ቀውስ ምክንያት በማድረግ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ተቋም ጋር በመተባበር 43 እጩ አትሌቶችን በማወደዳደር 10 ኦሎምፒያኖች ተመርጠዋል፡፡ እነዚህ የስደተኛ ኦሎምፒያኖች ቡድን በኦሎምፒክ መድረኩ ለማከፈል የሚበቁት የኦሎምፒክ ባንዲራን በማንገብ ሲሆን፤ በ3 የተለያዩ የውድድር መደቦች በአትሌቲክስ ከ800 እስከ ማራቶን፤ በውሃ ዋና እና በጁዶ  የሚሳተፉ ይሆናሉ፡፡ 10ሩ ኦሎምፒያኖች በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለእያንዳንዳቸው የ2 ሚሊዮን ዶላር  በጀት ተመድቦላቸው ለኦሎምፒኩ የተዘጋጁ ሲሆን 5 የደቡብ ሱዳን፤ 2 የዲሪ ኮንጎ፤ 2 የሶርያ እንዲሁም አንድ የኢትዮጲያ ስደተኞች ናቸው፡፡ በስደተኛ ኦሎምፒያንነት በ31ኛው ኦሎምፒያድ የሚካፈለው ትውልደ ኢትዮጲያዊ የ36 ዓመቱ ዮናስ ኪዳኔ ነው፡፡ ዮናስ ኪዳኔ በ2013 እኤአ ላይ ከአገሩ በመውጣት በአስቸጋሪ የስደት ጉዞ ሉክዘምበርግ የገባ ሲሆን የኦሎምፒክ ባንዲራን በማንገብ ሪዮ ላይ የሚሳተፈው በማራቶን ነው፡፡

Read 4468 times