Saturday, 16 July 2016 12:33

የ‘ብሮች ጉባኤ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይህ ውይይት በቅርቡ የሆነ ዊኪሊከስ ምናምን ይዞት ሊወጣ ይችላል፡፡ እስከዛው ድረስ ካልተረጋገጡ ምንጮች ያገኘነውን…
የእኛው ብሮች ‘በታሪክ አጋጣሚ’ አንድ ላይ ተገናኝተው እያወሩ ነበር አሉ፡፡
ሀምሳ ብር፡— አጀሬው መቶአችን እንዴት ከረምክ? ደህና አልከረምክም እንዴ…ምነው ጠቋቆርክብኝሳ!
መቶ ብር፡— ጭራሽ ሽቅብ ተንጠራርተህ ‘አጅሬው’ ትለኝ ጀመር! ብጠቋቁር ምን ይገርማል፡፡ በፊት እኮ ገና እኔ ብቅ ስል በእፍረት ቢጫነትህ ቀርቶ ግራጫ ነበር የምትሆነው…አሁን ጭራሽ ትከሻዬን ቸብ እያደረግህ አጅሬው ትለኝ ጀመር! የጊዜ ጀግና ነው የቀለደብኝ…
ሀምሳ ብር፡— መቶአችን ምን ነካህ… በአምና በሬ ያረሰ የለም ሲባል አልሰማህም! እንደተኮፈሱ መቅረት እኮ የለም፡፡ ስንቶቹ እንዳንተ እዛ ላይ ተቆልለው ሲኮፈሱ ይከርሙና ሚዛኑ ትንሽ ጋደል ሲልባቸው ጊዜን ያማርራሉ፡፡ ደግሞስ አሁን በአኔና በአንተ መሀል ምን ያሀል ልዩነት አለና ነው፡፡ እየተጠጋሁህ ነው እኮ! ለነገሩ ሁሉን የሚያስተካክል ኮሚኒዝም የሚሉት ሰው ላይ ባይሠራ እኛ ላይ እየሠራ ነው መሰለኝ፡፡
መቶ ብር፡— ሁሉን የሚያስተካክል ሳይሆን ሁሉን ድሀ የሚያደርግ ይሉታል…
ሀምሳ ብር፡— አይ መቶአችን…እነ ዶላርና ፓውንድን እየሰማህ ነው እኮ! ቻይናን ያየ እኮ በኮሚኒዝም አይቀልድም፡፡
መቶ ብር የምሩን ተከዘ፣ ልቡ ተሰበረ…ዕንባ፣ ዕንባ አለው፡፡
መቶ ብር፡— ግዴለም ጥፋቱ የአንተ አይደለም፣ ጊዜ ነው የጣለኝ አልኩ እኮ! ገና ብቅ ስል አገር ሁሉ ይጓጓ እንዳልነበር አሁን ብቅ ስል ከእነመኖሬም የሚያየኝ እየጠፋ ነው፡፡
ሀምሳ ብር፡— መቶአችን፣ እኔ እኮ ላሳዝንህ ፈልጌ አይደለም …መቼም ለምን ይዋሻል፣ አንተ አቅም ባጣህ ቁጥር እኮ እኔም እየመነመንኩ፣ እየመነመንኩ ልጠፋ ምንም አልቀረኝ!
መቶ ብር፡— ሀምሳው፣ ተው እንጂ በሌለህ አንገት ቀና፣ ቀና አታብዛ፡፡ አንተ እኮ ድሮም የተመናመንክ ነህ…
ሀምሳ ብር፡— ተው እንጂ መቶአችን፣ እኔን የያዘ ማለት እኮ ምግቡን በልቶ፣ የሚጠጣውን ጠጥቶ፣ ከእንትናዬው ጋር ለሽ ብሎ…
መቶ ብር፡— በሦስት ብር መኝታ፣ በአሥራ አምስት ሳንቲም ሻይ፣ በስሙኒ ዘቢብ ኬክ  ዘመን ነዋ!
ሀምሳ ብር፡— ለነገሩ መቶአችን፡ እውነት ልንገርህ አይደል፡፡ መንገድ የሚያሳየኝ ጠፍቶ ነው እንጂ ይህን አገር ለቅቄ ለመሄድ ስንቴ አስቢያለሁ መሰለህ፡፡ በአንዲት ፉርኖና በሁለት እንቁላል ድራሼ ሲጠፋ…አብዮት የማላስነሳሳ!
መቶ ብር፡— ለነገሩ እኔም አንዳንዴ አገር ለቅቄ ልሂድ እልና…በማላውቀው አገር የባሰ ጉልበተኛ ይገጥመኛል እያልኩ ሀሳቤን እተዋለሁ፡ ሁሉም ቦታ ጉልበተኛ ነው ያለው፣ ብታምንም ባታምንም ብዙ ቦታ ዋናው ሂሳብ መሆኔ ቀርቶ ቲፕ ሆኛለሁ፡፡ እኔ ያላሳዘንኩ ማን ያሳዝናል!
ሀምሳ ብር፡— ማንም…
መቶ ብር፡— አንድ ዘመዴ ትናንት ያለኝን ልንገርህ…
ሀምሳ ብር፡— ንገረኝ…
መቶ ብር፡— አንዷ ሴት እሱን በትንሽ ቦርሳዋ ሻጥ አድርጋ ትልቅ ፌስታል ይዛ ገበያ ትሄድልሀለች…
ሀምሳ ብር፡— ፌስታሉን በአንተ ዘመድ ልትሞላው…
መቶ ብር፡— ፌስታሉን በእኔ ዘመድ ልትሞላው…ታዲያ ስትዞር፣ ስትዞር ትውልና በመቶ ብር አስቤዛ አደረግሁ ብላ ፌስታሏን እንዳንጠለጠለች ወደ ቤቷ ስትሄድ መንገድ ላይ ሰው ያገኛትና ምን ቢላት ጥሩ ነው… “ገበያ የምትሄጂው ከመሸ ነው እንዴ!” አላት አሉ፡፡
ሀምሳ ብር፡— ባዶ ፌስታል ስለያዘች…
መቶ ብር፡— ታዲያ ይሄ አገር ጥሎ አያስመንንም! አንድ ፌስታል አይደለም መሙላት ለዓይን እንዲታይ ያህል እንኳን ግማሽ ድረስ መሙላት ሲያቅተን አይደለም አማሪካን ቡርኪና ፋሶ ለመሰደድ አያስመኝም!
ዱካውን ሳይሰሙት አሥር ብር ሃያ ሁለት ቀን ያለምግብና ያለ ውሀ ያከረሙት ይመስል ጠውልጎ አጠገባቸው ደርሷል፡፡
አሥር ብር፡— እንደምን ዋላችሁ…
መቶ ብር፡— እንደምን ዋልክ፣ አላወቅሁህም፡፡ ሀምሳው አውቀኸዋል እንዴ…
ሀምሳ ብር፡— አዎ ትንሽ፣ ትንሽ አውቀዋለሁ…አሥር ብር ይባላል…
መቶ ብር፡— (ክው ይላል) አንተ በህይወት አለህ እንዴ! እኔ እኮ ጭራሽ ከእነመፈጠርህ ረስቼሀለሁ፡፡…እስካሁን በህይወት መቆየትህ ዕድለኛ ነህ፡፡
አሥር ብር፡— ምን ዕድል አለ…ይቺን ክረምት ከከረምኩም ጥሩ ነው…ወይኔ ጀግናው! ወይኔ ጀግናው! ፓስታል ፉርኖ እንዳልተበላብኝ፣ ምን የመሰለ ሙክት እንዳልተገዛብኝ የማንም መጫወቻ ልሁን!
መቶ ብር፡— በጣም ተናደህ ነው የመጣኸው…በዚቹ አቅምህ ተናደህ የት ልትደርስ ነው!
አሥር ብር፡— ቲማቲም! ቲማቲም እንኳን ምግብ ሆና ትዘባበትብኝ!
ሀምሳ ብር፡— የቲማቲም ነገርማ ለእኛም አደገኛ እየሆነ ነው…ፈረንጆቹ ‘ክሊር ኤንድ ፕሬዘንት ዴንጀር’ የሚሉትን ጋርጣብናለች…ምን ብትልህ ነው እንዲህ የተናደድከው?
አሥር ብር፡— እዚህ አትክልት የሚሸጥበት ቦታ ቲማቲም ከእነዘር ማንዝሯ የተከማቸችበት ቦታ ይዛኝ የነበረችው ሴትዮ ከቦርሳዋ ብቅ ታደርገኛለች፡ ይሄኔ አንድ የሆነች ቀልበ ቢስ ቲማቲም “በሞትኩት!” ብላ ስትጮህ ደንግጥ አልኩ፡ “ምን ሆነሽ ነው እኔን ስታዪ በሞትኩት ያልሽው…” አልኳት፡፡ እሷም “ምን ልታደርግ እኛ ሰፈር መጣህ?” አለችኝ፡ እኔም “እመቤቴ በእኔ አንዷን ወይም ሁለቷን የአንቺን ዘመድ ልትለውጥብኝ አስባ ነው…” ስላት የሳቀችው መሳቅ!…
መቶ ብር፡— ታዲያ ብትስቅስ ምን አለበት…እንኳን አንተ እኛም እኮ እየሳቀብን ነው…
አሥር ብር፡— መች በዛ አቆመች…ለዘመዶቿ ምን ትላቸዋለች… “ይህንን ጉድ ስሙ፣ አጅሬው ከእኛ አንዳችንን በራሱ ሊለውጥ ነው የመጣው…” ስትል የተፈጠረው ሳቅ!…የነሀሴ ነጎድጓድም እንዲህ መሬት አያነቃንቅም፡፡ ደግነቱ የያዘችኝ ሴትዮ ወሬያችንን ባትሰማም ነጋዴው የሆነ ነገር ብሏት ኖሮ ድንግጥ ብላ ቶሎ ብላ ወደ ቦርሳዋ መለሰችኝ። እንዴት እንዳፈረችብኝ ያወቅሁት የቀላውን ፊቷን ሳየው ነው፡፡
     ታዲያ ገና ቦርሳዋን እየዘጋች ቲማቲሟ ምን ብትለኝ ጥሩ ነው… “ሚጢጢ አምስት ብር አለአቅምሽ አትንጠራሪ…” አለችኛ!
ሀምሳ ብር፡—  እኛ መካከል መቀላቀልህ ራሱ አላቅምህ መንጠራራት አይመስልህም!
አሥር ብር፡— አቶ ሀምሳ፣ አሁን በአንተ ቤት ገንዘብ ነኝ ብለህ ሰው ትናገራለህ! እኔ እኮ ቢያንስ ሁለትም፣ ሦስትም ቡሌ ጉርሻ ይገዛብኛል፡፡ አንተ እኮ ኪስ ውስጥ መኖርህም አይታወቅም፡፡
አንድ ብር፡— እንደምን ዋላችሁ…
ሁሉም ይደነግጣሉ፡፡ ሲመጣ አላዩትማ!
መቶ ብር፡— ይሄ ደግሞ ማነው…የሆነ ድቅቅ ያለ…ምንም ሳይቀምስ ዓመት የከረመ ነው እኮ የሚመስለው…
ሀምሳ ብር፡— አንድ ብር…
መቶ ብር፡— አ…አንድ ብር… አንድ ብር የሚባል ነገር አለ እንዴ!
አሥር ብር፡— አይ አንድ ብር፣ አሁን አንተም አለሁ ትላለህ! ፉርኖ አይበላብህ፣ ሻይ አይጠጣብህ፣ በታክሲ አይኬድብህ… ለራስህ ጊዜው ያንገላታህ…እንደው ምን ብለው ነው የሚያንገላቱህ…
አንድ ብር፡— እኔም እኮ አታንገላቱኝ…አንድ ጊዜ ወይ ራሳችሁ በሆነ መንገድ ከዚህ ዓለም አሰናብቱኝ፡፡ አለበለዛ ሳይናይድ ኪኒን ስጡኝና ራሴን ላጥፋ ብል የሚሰማኝ አጣሁ…ይባስ ብለው በሶልዲ መልክ ሠርተው አመጡኝ፡፡
አሥር ብር፡— ስታሳዝን…
አንድ ብር፡— አንድ ጓደኛዬ በቀደም የያዘው ሰውዬ እጸድቃለሁ ብሎ ለአንድ የእኔ ቢጤ ይመጠውተዋል…የእኔ ቢጤ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው…“ይሄንን ለአክስትህ ስጣት…” ብሎ ማዶ ለማዶ አሽቀንጥረው፡፡
መቶ ብር፡— የጊዜ ጉዳይ ነው ሁላችንም ተራ በተራ እንሽቀነጠራለን…
ሀምሳ ብር፡— አንድ ሀሳብ አለኝ…
መቶ ብር፡— ምን የሚሉት ሀሳብ!
ሀምሳ ብር፡— መሀላችን የሌለውን አምስት ብር እንጨምርና የጭቁን ብሮች መብት ተከላካይ ድርጅት እናቋቁም፡
አሥር ብር፡— ጥሩ ነው ግን መመስረቻ ጽሁፉን ማን ያዘጋጅ?
ይሄኔ ውይይቱ ተበጠበጠ፡፡ ሊስማሙ አልቻሉማ! ሰዉ ያልተስማማ በሰው የተሠሩት እነሱ እንዴት ይስማሙ! መቶ ብር
“የጣልያን ሊሬ ይሁን…” ብሎ ሀሳብ ሲያቀርብ አሥር ብር…
“ድርሀም እያለ የጣልያን ሊሬ የምትለው አባቶችህ የሙሶሊኒ ሰርጎ ገብ ነበሩ እንዴ!” ብሎ ስለመለሰለት ተኳርፈው ተለያዩ፡፡ የ‘ብሮች ጉባኤ’ም በዚሁ ተጠናቀቀ፡፡
ዘግይቶ በደረሰን ዜና መቶ ብር…
“ስሜና አቅሜ ስላልተመጣጣነ የይገባኛል ጥያቄ የማይቀርብበትን አርባ ብር የሚል ስም ይሰጠኝ…” ብሎ ሀሳብ ሊያቀርብ በዝግጅት ላይ ነው የሚል ጭምጭምታ አለ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2714 times