Saturday, 16 July 2016 13:18

የዛሬዋ ልዩ ቀን!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(17 votes)

     የዛሬው ቀን ልዩ የሚያደርገው ፀጉሬን የምቆረጥበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ፀጉር ቆራጩ ሁሌ ሶስት ወራት ቆይቼ ስለምመጣ ይረሳኛል፡፡ ምን አይነት ቁርጥ እንደሚስማማኝ ትዕግስት ወስጄ ማስረዳት ይኖርብኛል፡፡ ትልቅ ገለፃ የሚያስፈልገው የጭንቅላት ቅርፅም ሆነ የፀጉር አይነት የለኝም፡፡ ያው ያድጋል----መታጨድ አለበት ነው ዋናው ቁም ነገር፡፡ ግን በአጠቃላይ ቀላል ነገርን ማስረዳት ከባድ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ብዙ ብታስረዳ የሚረዱህ ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከጥቂቶቹም የተናገርከውን በአንተ መጠን የሚገባቸው ጭራሽ የሉም፡፡
ፀጉሬን ተቆርጬ ስመለስ ልብሴን በጥንቃቄ እለብሳለሁ፡፡ ጥርሴን መፋቅ ይኖርብኛል፡፡ አድርጌ የማላውቃቸውን የገፅታ ጥንቃቄዎች ማድረግ አለብኝ፡፡ ጫማዬ የሚጠረግ አይነት ባይሆንም በሆነ ምትሀት መጠረግ ይኖርበታል፡፡ የቆዳ ጫማዬ ግንባሩ ተጠርምሷል፡፡ ካስፈለገ ጎሚስታ ወስጄ አስነፋዋለሁ እንጂ-----ሳይስተካከልማ አልወጣም፡፡
ሁሉንም የገፅታዬን አቅም እንዲሸከም የተማመንኩበት ትላንት የገዛሁት ጥቁር ጃኬት ነው። ጃኬቱን ባልገዛ፤ ፀጉሬ ባልተቆረጠ፣ ጥርሴንም ባልቦረሽኩ ነበር፡፡ ጃኬት ባልገዛ እናቴን ሄጄ ለማየት አልወስንም ነበር፡፡ በመስቀያ አድርጌ ግድግዳው ላይ ሰቅዬዋለሁ፡፡ በእንቅልፍ ልቤ እየባነንኩ ከመኝታዬ ቀና እያልኩ ሳየው ነበር ያደርኩት፡፡ አሁንም ወለል ላይ በተነጠፈው የጥጥ ፍራሽ ላይ ተጋድሜ በድጋሚ አየሁት፡፡ ያብለጨልጫል፡፡ መስኮት በሌለው ጨለማ ክፍል ውስጥ የራሱን ብርሐን እየፈጠረ ያንፀባርቃል፡፡
እናቴን ለሁለት አመት በስልክ እንጂ በአካል አግኝቻት አላውቅም፡፡ እንድትደነግጥ አልፈለኩም። እሷ እኔን ስታስበኝ ያለው ምስልና እኔ ስለ ራሴ ማሰብ ካቆምኩ ጀምሮ ያለው ምስል እጅግ የተራራቁ ስለነበሩ ሳልፈልግ ሸሽቻት ነበር፡፡ ይህ ጥቁር ብልጭልጭ ጃኬት እናቴ ወደምታውቀው የድሮ የእኔ ምስል የመቅረቢያው መሰላል ነው፡፡ መሰላል ጃኬትን ተመስሎ ወደ ቤቴ ዝቅ የተደረገልኝ መሰለኝ። ጊዜ ሳላጠፋ መንጠልጠል አለብኝ፡፡
በተጋደምኩበት ሆኜ እያንዳንዱን ቀጣይ የዕለቱን ተግባሮቼን በምስል ደግፌ አሰላኋቸው። ፀጉሬን ስቆረጥ ምን እንደምመስል ይታየኛል። በእናቴ ዘመን ያሉ ሰዎች ቆፍጣና እና ሀላፊነት ተሸካሚ ለመምሰል ሲፈልጉ፣ ፀጉራቸውን ወደ ራስ ቅላቸው አስጠግተው ነበር የሚላጩት፡፡ ከነገር የምጠላው የፀጉር አቆራረጥ ነው፡፡ ግን እናቴ እኔን የምታስበኝ እንደዚህ በመሆኑ ለሷ ስል ዛሬ ፀጉሬን እላጭላታለሁ፡፡ ለፀጉር ቆራጩ የምፈልገውን አቆራረጥ የማስረዳቱ ሂደትም የፀጉሬን መላጨት እንደሚጨምር ጠርጥሬአለሁ፡፡
በመሰረቱ የማንም ገፅታ ከአራት ቁርጥራጭ ነው የተሰራው፡፡ ፀጉር አለ፡፡ ጠቆር ያለ ነው፡፡ ሰውን ከሩቅ ጉንዳን መስሎ ጭንቅላቱ እንዲለይ የሚያደርገው ይህ ክፍል ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ሱሪ የሚባለው ነው፡፡ የሚጠለቅ ነው፤ ወገብ ላይ ጠበቅ ማድረጊያ ቀበቶ ያስፈልገዋል፡፡  ሸሚዝ የሚባለው ከውስጥ፣ ጃኬት የሚባለው በሸሚዙ ላይ ይደረባል፡፡ እኔ ግን ሁሉንም ቁርጥራጮች የሚከልለኝ ይህ ጃኬት የተባለው ላይ ነው ተስፋዬን የጣልኩት፡፡
ወደ ፀጉር ቤት ሄድኩኝ፡፡ እናቴ እንደምትፈልገው የራስ ቅሌ እስኪቀር ተላጨሁ፡፡ ወደ ቤቴ ተመልሼ በከፍተኛ ጥንቃቄ አራቱን ቁርጥራጮች ለበስኩኝ፡፡ ዋናው ትኩረቴ ግን ጥቁሩ ጃኬት ነው፡፡ ትላንት ማታ በአልጋዬ ላይ ተጋድሜ ያጨስኩት ሲጋራ ጃኬቱን ያደረቀው መሰለኝ፡፡ በእጄ ደባበስኩት፡፡ የቆዳ ጃኬት የሚመስል ጃኬት ነው እንጂ ቆዳ አይደለም፡፡ ታዲያ እንደ ቆዳ የሕያውነትን ባህሪ የሚያቅ ይመስል ጭስ ሲሸተው ለምንድነው የሚጨማደደው? መሰለ እንጂ እንዳልሆነ ማን በነገረው፡፡
በጥንቃቄ ለበስኩት፤እንደ ቂጣ ተቆራርሶ እናቴ ሳታየው በፊት እንዳይረግፍ እንደሰጋሁ አይነት። እናቴን ማየት የጓጓሁት እኔ ነኝ፡፡ እናቴ ድሮ የምታውቀውን የእኔን ምስል ደግማ ማየት ነው ፍላጎቷ፡፡ እንድለወጥባት አትፈልግም፡፡ ድሮ አንበሬ ጭቃ ፊቴን ቀብታ ትምህርት ቤት ሙልሙል አብልታ ስትሰደኝ እመስል እንደነበረው እንድመስል ነው የምትፈልገው፡፡ ግን እንደዛ መስዬ እንዳድግና ቦርጭ እንዲኖረኝ ----- ልጇ እንደ ድሮው ፍልቅልቅ ሆኖ መኪና እየነዳ ተመልሶ እንዲመጣለት ነው የምትፈልገው፡፡ የምትፈልገውን ብቻ ነው ደግሞ የምትጠብቀው፡፡ ከጠበቀችው በላይ እንጂ በታች የሆነውን አትቀበልም፡፡
ቦርጭ የለኝም ግን እሱ ሊቀር ይችላል፡፡ የጠቆረውን ጥርሴን እንዴት ነው የማደርገው፡፡ በከንፈር ጃኬት ከመሸፈን ውጭ ምንም አማራጭ የለኝም፡፡ በቃ ጥርሴ ጠቁሯል፡፡ እናቴን ሳቅፋት ደግሞ መሳቅ አለብኝ፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ መለወጥ ወይም መሸፈን የማይቻለውን ዋጥ አድርጎ የግድ መቀበል ብቻ ነው፡፡
ሲጋራው ጥርሴን፣ አረቄው ፊቴን ጎድቶታል፡፡ መልኬን በፀጉር ቆራጩ መስታወት ውስጥ ሳየው በፀጉሬ ውስጥ የተደበቀ ብረት ነው መስሎ የታየኝ። ፀጉሩ እየተቆረጠ፣ እያጠረ ሲመጣ ብረቱ ብቻ ቀረ። በአንበሬ ጭቃ የተብለጨለጨ ፊት ከእንግዲህ እንደሌለ እንዴት አስረዳታለሁ ---- እናቴን?
ሁሉንም ጉድለቴን በተብለጨለጨው ጥቁር ጃኬት ላይ አኖርኩት፡፡ የምኖረው ከድሮው የእናቴ ቤት ብዙም አይርቅም፡፡ ግን ባህር ማዶ እንደተሻገረ ሰው ሁለት አመት ድምጽን ከመስማት በስተቀር ተነፋፍቀን ቆየን፡፡
በእግር መሄድ ቢኖረኝም ታክሲ ያዝኩኝ፡፡ ታክሲው ገና እጄን ከፍ ከማድረጌ ወዲያው ፍሬን ሲጥ አድርጎ ሲያቆም ደንገጥኩኝ፡፡ ሀሴት የተሞላ መደንገጥ ነው፡፡ ትላንት ቢሆን ሌላውን ሰው ከጫነ በኋላ ወለል ላይ እንድቀመጥ ነበር ያመለክተኝ የነበረው፡፡ ትላንት ዛሬ አይደለም፡፡ ትላንትን ወደ ዛሬ የቀየረው አንድ ተራ ጥቁር ጃኬት መሆኑን ማመን አልፈልግም፡፡ እኔ ራሴ እንደተቀየርኩ እንጂ አንድ ተራ ቆዳ መሳይ ጨርቅ እንደቀየረኝ መቀበል አሻፈረኝ አልኩኝ፡፡ እሽም አልኩኝ እንቢ እውነቱ ግን ይኼ ነው፡፡
ታክሲ ይዤ የማላውቀው ሰውዬ ታክሲ የተጠቀምኩበት ምክንያቱም ግልፅ ነው፡፡ ለእኔ ሳይሆን በእኔ ላይ የደረብኩትን በክብር ለማጓጓዝ ስል ነው በታክሲ የተንጠለጠልኩት፡፡ ሁሉም ነገር የተዟዟረ መሆኑን መቀበል አልፈለኩም፡፡ ጃኬት የእኔን ገመና መሸፈን ሲኖርበት እኔ የእሱን ክብር ለመጠበቅ ከሆነ የምኖረው ነገር ተዟዙሯል ማለት ነው፡፡ ግን ይሄ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የዘመኑ ሰው ቢሆን እውነት ነው፡፡ ሰውነታቸው የሰባ ሰዎች ውስጥ ቀጭን ሰው ተደብቆ ይታየኛል፡፡ በእቃና ቁሳቁስ ውስጥ ባለቤት ነኝ ብለው ትልቅ ዙፋን መሳይ ሶፋ ላይ አይጥ የሚያክል ሰብእና የተዝናና መስሎ ግን ተጨንቆ ይታየኛል፡፡
 ይኼንን ሁሉ ለእናቴ ማስረዳት ዋጋ የለውም። ግን እኔ መለወጤ ያስፈራታል ብዬ እንደፈራሁት እናቴስ ተለውጣ ብትጠብቀኝ፡፡ ለምሳሌ ምን አይነት ለውጥ?.. እኔንጃ ፀጉሯ በጣም ሸብቶ… ወይ በጣም ከስታ… አጥንቷ ወጥቶ… ጎብጣ ባገኛትስ .. በስመአብ እግዜር አያድርገው፡፡ እኔ ተለውጬ እሷ ብትደነግጥ ይሻላል? እሷ እንደ ድሮ ሆና ትጠብቀኝ… በቃ ቢያንስ አንድ ጊዜ ዛሬ ሳገኛት ድሮ እንደነበረው ሆኖ ትቆየኝና… ከእዛ ከፈለገች እኔ ከሄድኩ በኋላ ትለወጥ…እያልኩ በታክሲው ውስጥ ገና ለማሰብ ስጀምር የድሮው ሰፈሬ ደረስኩኝ፡፡
 ለነገሩ ድሮውንስ ቢሆን መች ከሰፈሬ ቀልቤ ርቆ ያውቃል፡፡ ሀሳቤ ሁሉ እንደ ውቃቤ በእናቴ ቤት አካባቢ ዘወትር እንደተመላለሰ ነው፡፡ ግን ቢመላለስም እናቴን ከክፉ ነገር መጠበቅ አይችልም ነበር፡፡ … ናፍቆት ማለት፡- የማይጎዳ የማይጠቅም… የማያሳይ… የማይፈውስ ሽባ ውቃቤ ነው… አልኩኝ። ከታክሲ ወረድኩኝ፡፡ ቀጭኗን መንገድ ሳገኛት በጣም ወፍራ ጠበቀችኝ፡፡ ኮብል እስቶን ሆናለች። ጸድቻለሁ ብላለች፡፡ ግን ልክ በወፋፍራም ሰዎች አካል ውስጥ የከሳ ሌላ ሰው… ሌላ ማንነት እንደሚታየኝ ሁሉ… በዚህች መንገድ አወፋፈር ውስጥም የድሮዋ ቀጭን መንገድ ተሸሽጋ ታየኝ፡፡ ወፍራሙ መንገድ ቀጭኑን መንገድ እየናፈቀ መሰለኝ በላዩ ላይ በቀስታ ስራመድበት፡፡
… የሰፈሬ ሰዎች አስታውሰውኝ ይሆን በሚል ድሮ የማውቀው ፊትን በአይኔ እያሰስኩኝ ሞከርኳቸው። ... ግን አልለዩኝም፡፡ እኔና ጥቁር ጃኬቴን ሳይሆን ራሳቸውን መለየት የሚችሉ አይመስሉም፡፡ በህልም ውስጥ የሚራመዱ ነው የሚመስሉት፡፡ በፊት የነበሩ ሱቆች በሌላ ሱቆች ተቀይረዋል፡፡ የተቀየሩ ሱቆች በሙሉ ወፋፍራም ናቸው፡፡ በወፋፍራሞች ውስጥ ሁሉ ቀጭን የበፊት ጊዜ ገዝፎ ይታየኛል፡፡ ምናልባት እየኖርኩ ያለሁት ወደ ኋላ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ጠረጠርኩኝ፡፡ ወደ ኋላ እየኖርኩ ሳይሆን አሁን ያለሁት ጊዜ ራሱ የኋላው ነው አልኩኝ፡፡ ታዲያ ለምን ዘመን ተለወጠ… ቀጭኑ የድሮ ዘመን በወፍራሙ ተሰለቀጠ?
ሀሳቤን ወደ እናቴ አደረኩኝ… የሰፈር ሰዎች ----- አብሮ አደጎች የት ሄዱ? ብሎ መጠየቅ ከእኔ አቅም በላይ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የሚመለከተኝ የእናቴ፣ በዛ አለፍ ሲል ደግሞ የራሴ ነገር ነው። በወፋፍራም ነገሮች ውስጥ ቀጭኑን እየፈለኩ የድሮው ቅያስ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ቅያሱ ተለውጦ ራሱን የረሳ መስሎ ሊያጭበረብረኝ ቢሞክርም ---- አወቅሁት፡፡ ቅያሱ ላይ ያሉ የጎረቤቶቼ ቤቶች ቁመት ጨምረዋል። የከተምበሪው ቁመትም እጥፍ ሆኗል። ሸጠው የወጡም አሉ፡፡
 የእናቴ በር ብቻ በነበረበት ቁመትና ስፋት ላይ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ልቤ መምታት ጀመረ። የበሩ ዳፋ ላይ ሳር በቅሏል፡፡ እግር ለብዙ ጊዜ ሳይረግጠው የቆየ ይመስላል፡፡ ቀጭኑ ቀጭን ሆኖ ነው የቆየኝ፡፡ እናቴም እንደነበረችው ሆና ለዛሬ ብትጠብቀኝ ---- ብዬ በቀስታ በሩን ቆረቆርኩኝ፡፡
አሁን ጃኬቴን ረስቼዋለሁ፡፡ ጃኬት መሰላል ነው፡፡ ወደ እናቴ ደጃፍ ደርሼ በሩን ለማንኳኳት ያህል ድፍረት ሰጥቶ የሚያስጠጋኝ መሰላል ነው። አንዴ በሩ ዘንድ ደርሼ ካንኳኳሁ በኋላ ጃኬቱ አያስፈልገኝም፡፡ የማንኳኳት ቆይታው እየረዘመ በመጣ ቁጥር ፍርሀት ወረሰኝ፡፡… ፍርሃቶቼን ላስባቸው እንኳን የምፈልጋቸው አይነት አይደሉም… እንደ ፈላ ዘይት መላ ስሜቴን አጣብቆ ወደ ልብ ትርታ የሚለውጥ የሚያጥወለውል ስሜቶች ናቸው… የምፈራቸውን ነገሮች ላስባቸው አልፈለኩም.. ግን ይሄ ስሜት እንዲለቀኝ በሩ ተከፍቶ የእናቴን ፊት ማየት አለብኝ፡፡ ያኔ ብቻ ነው መፅናናት የምችለው። ስለዚህ በሀይል አንኳኳሁኝ ----
የለበስኩት ጃኬት እንደ ጥቁር ዘይት ሆኖ አፍኖ ሊገድለኝ ነው፡፡ በሩ ካልተከፈተ መፅናናት አልችልም። ግን በሩ ካልተከፈተ ብቻ ነው የእናቴን ሞት አርድተውኝ ለዘላለም ሳልፅናና እንድቀር ቁርጡን የሚነግሩኝ፡፡ በሩ መከፈት አለበት… አለመከፈትም አለበት፡፡ ቀጭኑ የድሮ ዘመን በወፍራሙ ተበልቶ ማለቁ ድንገት ሲታወቀኝ በሩ ተከፈተ፡፡












Read 3910 times