Monday, 25 July 2016 07:07

ዶሮ የወባ በሽታ መከላከያ ሆናለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

     የኢትዮጵያና የስዊድን ሳይንቲስቶች ለወባ በሽታ አማጭ ትንኝ መከላከያ ያገኙት የምርምር ውጤት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በህይወት ያለች ዶሮ መኝታ አጠገብ ማስቀመጥ የወባ ትንኝን ድርሽ እንዳይል ያደርጋል ብለዋል፤ ተመራማሪዎቹ፡፡
ከዶሮና ከወፎች የሚወጣው የተፈጥሮ ሽታ ለወባ ትንኝ ጠላቷ ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ በየዓመቱ በአፍሪካ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ለሚገድለው የወባ በሽታ ፍቱን መፍትሄ ይሆናል ብለዋል፡፡ ቢቢሲ ተመራማሪዎቹን ተጠቅሶ እንደዘገበው፤ በምዕራብ ኦትዮጵያ ወባማ አካባቢ ፍቃደኛ በሆኑ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት መኝታ አጠገብ፣ ዶሮ በማስቀመጥ ያደረጉት ሙከራ የተሳካ ነበር ብሏል፡፡
የወባ ትንኝ የሚያባርረው የዶሮ ወይም የወፍ ጠረን መሆኑን ደርሰንበታል ያሉት ተመራማሪዎቹ የምርምር ውጤቱን በሰፊው ለመሞከር በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የምርም ቡድኑ አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሀብቴ ተክኤ፤ ከዶሮዎች የሚወጣውን ጠረን በመውሰድ የመከላከያ መንገድ ለማበጀት እየተሞከረ ነው ብለዋል፡፡
ዶሮዎች በብዛት ባሉበት አካባቢ የወባ ትንኝ መጠን እንደሚቀንስ ማስተዋላቸውን ተከትሎ የምርምር ስራቸውን በጥልቀት ማከናወን መቀጠላቸውን ተመራማሪዎቹ ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡  

Read 6665 times