Monday, 25 July 2016 07:07

የታላቁ የቲያትር ባለሙያ አባተ መኩሪያ፣ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈፀመ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(9 votes)

    የኢትዮጵያ የቴያትር አባት እየተባለ የሚጠራውና በተወለደ በ72 አመቱ ከትናንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት የተለየው፣ የአንጋፋው የቲያትር አዘጋጅ የአባተ መኩሪያ የቀብር ስነ ስርዓት ትናንት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ፡፡
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴአትር ፈር ቀዳጅነቱ የሚታወቀው አባተ መኩሪያ፤ ከጥቂት ወራት በፊት በጠና ታምሞ አገር ውስጥ የቀዶ ጥገና ህክምና ቢደረግለትም፣ ጤናው ሊመለስ ባለመቻሉ ለተሻለ ህክምና ወደ ግብጽ ሄዶ ነበር፡፡ ከወር በፊት ህክምናውን ተከታትሎ ወደ አገሩ የተመለሰው አባተ መኩሪያ፣ በቅርቡ በገጠመው የፕሮስቴት እጢ፣ አዲስ ህይወት ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ቢደረግለትም ህይወቱን ማትረፍ ባለመቻሉ ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት ላይ ህይወቱ አልፏል፡፡  
ህዳር 10 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ አቧሬ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር አካባቢ የተወለደው ፀሃፌ-ተውኔት፣ የፊልም ዳይሬክተርና የቴአትር አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ለአምስት ዓመታት በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን፣ በብሄራዊ ቲያትር በአርት ዳይሬክተርነት፣ በአዲስ አበባ ባህል ማዕከል በዋና ሥራ አስኪያጅነትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመዝናኛ ክፍል፣ በከፍተኛ አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡
ሀሁ በስድስት ወር፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ መልዕክተ ወዛደር፣ ኦቴሎ፣ ቴዎድሮስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ኤዲፐስ ንጉስ እና አፋጀሽኝን ጨምሮ በርካታ ቴአትሮችን አዘጋጅቶ ለመድረክ በማብቃት የሚታወቀው አባተ መኩሪያ፣ ከ4ሺ በላይ ሰዎች የተሳተፉበትንና አዲስ አበባ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን ባከበረችበት ወቅት ተሰርቶ በየዓመቱ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን “የአድዋ ጦርነት ዘመቻ” የተሰኘ ታሪካዊ ዶክመንተሪ ፊልም በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡
ዕውቁ የቲያትር አዘጋጅ በሥራ ዘመኑ በበርካታ የመድረክ ስራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል እንዳልገጠመው የሚናገሩ የሙያ ባልደረቦቹ፤ ይሄንንም ቅሬታውን በአደባባይ መናገሩን ያስታውሳሉ፡፡ በያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በብሔራዊ ቴያትር ይሄንኑ ባለሙያው ለማክበርና ለመዘከር ታስቦ በተዘጋጀው፤“ዝክረ አባተ መኩሪያ” ፕሮግራም ላይ፤“እባካችሁ መድረኩን ስጡኝ ልስራበት፤እኔ ሰርቼ አልጠገብኩም፤ገና ብዙ መስራት እፈልጋለሁ“ ብሎ ነበር፡፡
አባተ መኩሪያ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡

Read 5601 times