Monday, 25 July 2016 07:27

አባ ጫላ (ለማ ጉርሙ) አባ ጫላ - ከአሲምባ እስከ አዲሳባ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

 

 

 

የአባ ጫላ ወግና ውጋውግ
(ካለፈው የቀጠለ)
ባለፈው ሳምንት ትረካውን የጀመርኩት የአሲምባው ወታደር አባ ጫላ፤ ገና ከሱዳን ወደ አዲሳባ እንደመጣ፣ ከአንድ ጓደኛው ጋር ሆኖ፤ አውቶብስ ተራ ይደርሳሉ፤ ወዴት እንደሚሄዱ አያውቁም፡፡ የማንም ስልክ የላቸውም፡፡ ገበሬ እንደመሰሉ በቁምጣ ሱሪ ናቸው፡፡ “ሰላሳ አምስት ሳንቲም ናት ያለችን ካፒታል” ይል ነበር አባ ጫላ፡፡
“አንድ ወንድም ነበረኝ፤ ወደ ሶስት ቁጥር ማዞሪያ፡፡ ከአውቶብስ ተራ ሶስት ቁጥር ማዞሪያ ለመሄድ ታክሲ ወይም አውቶብስ አያስፈልገንም ለኛ፡፡ የአሲምባን አቀበት ቁልቁለት ስንወጣ ስንወርድ የነበርን ፋኖዎች፣ የአዲሳባ ሜዳ ይበግረናል እንዴ? መጭ አልነዋ! በእግር፡፡ በከፊል እያስታወስኩ፣ በከፊል እየጠየኩ የወንድሜን ቤት አገኘሁት፡፡ አሲምባ ሳለን እንኳን ዐይናችን እያየ ቀርቶ እያንቀላፋንም ቆመን መሄድ ተለማምደን፣ እያንዳንዷን ቁጥቋጦ በጭለማ ዳስሰን እናገኛት ነበር። የአዲሳባ ጫካ ግን ግራ አጋባን! ወንድሜ እንዲህ እንደ ባላገር ለብሼ ሲያየኝ ምን ይል? የወንድሜን በር ቆረቆርኩ፡፡ አንኳኳሁ፡፡ የሆነ ሰው ብቅ አለ፡፡ ዘበኛ ይመስላል። የወንድሜን ስም ጠርቼ፣ “አለ ወይ?” ብዬ ጠየኩት “እነማናችሁ? እንዲህ ያለ ሰው አላቅም ይለን ይሆን?” ብዬ ሰግቻለሁ፡፡ ሰውዬው ግን ፈጠን ብሎ፤ “እነሱ ከዚህ ለቀው ሄደዋል” አለኝ፡፡ ወሽመጤ ቁርጥ አለ፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ፤“የት አካባቢ ይሆን የገቡት?” ስል ጠየኩት፡፡
“ቦሌ ቤት ሰርተው ነው የገቡት ሲሉ ሰምቻለሁ። ሩዋንዳ አካባቢ አሉ፡፡”
እግዚአብሔር ይስጥህ ብለን፣ ከሶስት ቁጥር ማዞሪያ ደሞ ወደ ቦሌ ተያያዝነው፡፡ ምንም ድካም የለብንም፤ ትክክለኛ ቤቱን ካለማወቃችን በስተቀር። ቦሌ ደርሰን ያገኘነውን መንገደኛ ሁሉ፣ እገሌ እሚባል እዚህ ቦታ የሚሰራ? ቤቱን ታቃለህ ወይ? እንል ጀመር፡፡
 “ወይኔ እዚያ ከአሲምባ ተራራ በታች ነዋሪ የሆኑት እኒያ ደግ የኢሮብ ሰዎች ቢሆኑ’ኮ፣ እጃችንን ይዘው ደጃፉ ጋ ነበር የሚያደርሱን?” አለ ጓዴ፡፡
በመካያው አንድ ወንድሜን የሚያውቅ ደግ ሰው አገኘሁ፡፡ እዛው ቤቱ ድረስ ወሰደን፡፡
ዘበኛውም፤ “የጌታዬ የባላገር ዘመዶች መጡ” ብሎ ለወንድሜ ሚስት ነግሮ፤ አስገባቸው ተባለ። ልባችን ፍንድቅድቅ አለች፡፡ የወንድሜ ሚስት በጣም በመለዋወጤ፣ በመከራ ነው ያስታወሰችኝ። ቱሉ ቦሎ እያለሁ ታውቀኝ ነበር፡፡ ወይ ጉድ! ቱሉ ቦሎም ከተማ ሆነችና እኔ የአሲምባ ባላገር ሆንኩኝ ማለት ነው፡፡ ጓደኛዬ ጥቂት ጊዜ አብሮኝ ሰንብቶ ዘመዶቹን አገኘና ተሰናብቶን ሄደ፡፡ ጓዴ ነውና የፈለገውን ያህል ጊዜ ቢቆይ፣ እኔ እንደ መብቱ አይለታለሁ እንጂ የሰው ቤት ነው የሚል ይሉኝታ አልያዘኝም ነበር። ወንድሜ እጅግ ደስ አለው። የአሲምባ ታሪኬን በዝርዝር ተረኩለት! ለባለቤቱ ገንዘብ ሰጥቶ፣መርካቶ ልብስ ግዙ አለን፡፡ መርካቶ ስንሄድ ጉድ ገጠመኝ!
ባለ ሱቁ ቦላሌ ሱሪ ያመጣል፡፡ የወንድሜ ሚስት፤ “ይሄስ?” ትለኛለች፡፡
አገላብጬ አይና “አይ አላማረኝም” እላታለሁ፡፡ ሌላ ሱቅ እንሄዳለን፡፡ “ይሄስ?” ትላለች፡፡
“መልኩ ደስ አይልም” እላለሁ፡፡
ደሞ ሌላ ሱቅ፤ “አያምረኝም” እላለሁ፡፡ ግራ ገባት፡፡ ብዙ ሱቅ አለፍን፡፡ አሁን ግን አንድ ሱቅ ያየሁት ቦላሌ፤ “ይሄ ጥሩ ነው፤ ድንቅ ነው!” አልኳት።
“ግባና ለካው!” ተባልኩ፡፡ ለብሼው ወጣሁ፡፡ ልክክ አለ፡፡
እስካሁን ያየሁዋቸው ቦላሌ ሱሪዎች የማይሆኑኝ ወይም የማያምሩኝ ሆነው አልነበረም። እኔ የቸገረኝ ሌላ ነገር ነው፤ ግልገል ሱሪ (ፓንት) የሌለው ቁምጣ ሱሪ ነው ያደረኩት፡፡ ሶስት ዓመት ሙሉ አሲምባ መለመላችንን ነው ስንዋጋ የኖርነው። ግርዶሽ ያለው መልበሻ ክፍል እስካገኝ ድረስ ነበር ቦላሌው አልተስማማኝም እያልኩ የወንድሜን ሚስት ያንገላታኋት!! ነቢይ፤ አንተ ቤት መኖር የጀመርኩት ቦላሌ ሱሪና ፓንት ከለመድኩ በኋላ ነው፡፡ ያንተ ሚስት፣ደግ እናት፣ ናት፡፡ እናቴ ናት! እንደ ስሟ ንፁህ ናት፡፡ ካንተ እኩል ፓንትና ካልሲ ሳይቀር ትዘጋልኛለች፡፡ አንዳንዴ የትግል ጓዴም ትመስለኛለች!” ይለኝ ነበር አባ ጫላ፡፡ ቡና ታፈላና፤ “ለማ፣ የጠዋት ቡና ትጠጣለህ?” ስትለው፤ “አጋጥሞኝ አያቅም” ይላል፡፡
አባ ጫላ እኛ ቤት እየኖረ ሳለ፤ አንድ ቀን ባለቤቴ አታምሽ ብላኝ አንድ ኤምባሲ ውስጥ ሪሴፕሽን ላይ ቆይቼ መጣሁ፡፡ ባለቤቴና አባ ጫላ ሳሎን ተቀምጠው ደረስኩ፡፡ ባለቤቴ፤“አታምሽ አላልኩህም?!” ብላ ተቆጣች፡፡
“እኔ ብዙ አልጠጣሁም፤ከወዳጆቼ ጋር ውይይት ይዘውኝ ነው፡፡” አልኳት፡፡
“ምን አልጠጣሁም ትለኛለህ፤ ዐይንህ ፍም መስሎ ቀልቶ እያየሁት?” አለች፡፡ ይሄኔ አባ ጫላ ጣልቃ ገብቶ (እንደ ማስታረቅ አስቦ ይመስለኛል፤) “እየው ንፁህ፣ (ባለቤቴን መሆኑ ነው) ንፁህ፤ ዐይን እሚቀላው ቢራ ሲያንስ ነው!” አለ፡፡ ስቃ፤ “የሞትክ! ዱሮስ ካንተ ምን ይጠበቃል?!”
*         *         *
አባ ጫላና የካዛንቺስ ልጆች
ወደ ካዛንቺስ ልጆች ከመሄዴ በፊት ስለ አባ ጫላ አንድ ወግ ላውጋችሁ፡፡ እኔ ባለቤቴና ጓደኛው፤ ዛሬ ነብሷን ይማራትና አንዲት “የሰፈራችን ሼራታን” የምንላት የአንድ ቡና ቤት ጓዳ፤ (ዛሬ ነብሷን ይማራት፤ ለልማት ሲባል ፈርሳለች) እያመሸን ሳለ፤ አባ ጫላ ይመጣና መዝናናታችን እንቀጥላለን። በመካከል፤ አንድ ወጣት እኛ ወዳለንባት ጓዳ ይመጣና ከእኛ ጋር ይዳበላል፡፡ ቤና ቤት ነው ብለን ዝም አልነው፡፡ ጥቂት ቆይቶ ወጣቱ፤ “ጋሽ ነቢይን አውቀዋለሁ፡፡ እሱን አይቼ ነው የገባሁት” ብሎ ራሱን ያስተዋውቃል፡፡ ሞቅ ብሎታል፤ በአበሻ ስታንዳርድ፡፡ ቀጠለ፡፡ ወደ እኔ ዞሮ፤ “ጋሽ ነቢይ፤ ግጥም ማለት፤ ቁጥብ፣ ዜማ ያለው፣ ጥልቅ ይዘት ያለው …” ብሎ ሲጀምር፤ አባ ጫላ አቋረጠው፡-
“አንዴ ታገሰኝ የእኔ ወንድም፤” አለው፡፡ ልጁ ዝም አለ፡፡ አባ ጫላ ቀጠለ፡-
“ይሄውልህ ነቢይ፤ አንድ ጊዜ አሲምባ እያለሁ፣ አለቃዬ ፀሎተ እስቅያስ (ከኢህአፓ/ኢህአሠ መሪዎች አንዱ) በኢህአፓና በህውሃት (ወያኔ) መካከል ስለተደረገ ጦርነት ጉዳይ ሪፖርት ዘግበህ ና ብሎ ላከኝ፡፡ የ12 ሰዓት መንገድ ነው፡፡ ሲሄዱ ስድስት፣ ሲመጡ ስድስት፡፡ ደርሼ ተመለስኩና ለፀሎተ እንዲህ አልኩት፡-
“የኢህአፓ ሰራዊት ባደረገው ተጋድሎ አገር ተደንቋል! ህዝብ ቀፎው እንደተነካ ንብ ተቀስቅሶ ድጋፉን ለኢህአፓ አሳይቷል፡፡ በየጠላ ቤቱ፣ በየመንደሩ እየሄድኩ ስጠይቅ አዛውንቱ፣ አሮጊቱ፣ ወጣቱ ድጋፉን ለኢህአፓ እየሰጠ በህውሃት ላይ ስላገኘው ድል እንደ ጉድ ያወራል …” እያልኩ  ማስረዳቴን ስቀጥል፤ ፀሎተ አቋርጦኝ ምን አለኝ መሰለህ፤ (በሜዳ ስሜ “ሰቦቃ” ብሎ፤)
“ስማ ሰቦቃ፤ ካድሬ ነኝ አትቀስቅሰኝ”
ያ ስለ ግጥም ለእኔ የሚያስረዳኝ ወጣት፣ የአባ ጫላ አካሄድ ገባው - ነቢይ የግጥም ሰው ነው፤ አትቀስቅሰው - መሆኑ ነው፡፡ ወዲያው ልጁ እግዚአብሔር ይስጠው፤ “ደህና እደሩ ጋሽ ነቢይ” ብሎን ወጣ፡፡ አባ ጫላም እግዜር ይስጠው፤ ለከተማው የግጥም ትግል፣ የገጠር ትግል ምሳሌ ሰጥቶ፤ ገላገለኝ!
አባ ጫላ ቆራጥ የኢህአሠ ታጋይ ነው፡፡ በደም ውስጥ ታግሎ በደም ውስጥ የበሰለ ነው። የኢህአሠን (የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊው ሰራዊት) መርህ ከማስፈፀም ሌላ የሚያስደስተው ምንም ነገር የለም። “እስቲ ስለ ኢህአሠ አንዳንድ ነገር አጫውተኝ?” ስለው፤ “ያ የወታደር ህይወት ነው፤ እኔ የኢህአፓ ወታደር ነኝ፤ እዚህ ከተማ ቁጭ ብላችሁ እንደ ፖለቲካ ካድሬ ነው የምታስቡት፡፡ አንዴ ከገባህበት የአሲምባ ወታደር ከሆንክ ወይ ትገላለህ ወይ ትሞታለህ፡፡ በመጀመሪያ በዚህ እንስማማ!” ይለኛል። ከምሩ ነው!
አባ ጫላ፣ እነ መንጌና ካዛንቺስ
አንድ ቀን አባ ጫላ፤ አዘውትሮ እሁድ እሁድ ማልዶ ከሚመጣበት ዩኒቲ ግሮሰሪ ይዘገያል፡፡ ለወትሮው አንድ ሰዓት የሚመጣው አራት ሰዓት ድረስ ቆየ፡፡ ሁሌ የእሁድ ስፖርታቸውን ሰርተው ዩኒቲ ድራፍት የሚጠጡት የአባ ጫላ ወዳጆች፡- እነ መንጌ፣ “አባ ጫላ፣ ዛሬ በደህናው አላረፈደም፤ ከሰው ጋር ተኝቶ ነው - ከሴት ጋር!” አሉ። ይህንኑ አባ ጫላ ሲመጣ ነግረው ሊያፋጥጡት ዶለቱ፡፡ መጣ አባ ጫላ፡፡
“አንተ፤ ከሰው ጋር አድረህ ነው? ከሴት ጋር---” አሉት፡፡
አባ ጫላም፤ “አይ ወንድሞቼ! እኔ፤ እንኳን ከሰው ጋር ከራሴም ጋር አድሬ አላውቅም!” አለ፡፡
ከባዱ የአባ ጫላ ፍልስፍና ይሄ ይመስለኛል። “ከጠጣሁ ከራሴ ጋር መለያየት አለብኝ!” ይላል፤ ራሱን መርሳት!
ዱሮ የኢህአፓ ታጋይ የነበሩ፣ የትግል መሪዎች ከውጭ ሲመጡ ያገኙታል፡፡ ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም። እዛ እሚያወራውና እዚህ ካዛንቺስ እሚጫወተውን እየመረጠ ነው የሚጫወተው!! የጋራ ወሬያቸው ስለ አሲምባ ነው!
ኢህአፓ አላዘዘኝማ!
የአባ ጫላን የቱሉ ቦሎ ህይወት ሳስታውስ የሚመጣልኝ አንድ ነገር አለ፡፡ አንድ ቀን አባ ጫላ ደሞዝ ይጨመርለታል፡፡ በነገራችን ላይ አባ ጫላ በዓመት ሁለት ጊዜ ሁሉ ደሞዝ ይጨመርለት የነበረ ታታሪ ሰራተኛ ነው፡፡ ጠዋት በአንድ ሰዓት ስራው ላይ ይገኛል፤ በሁለት ሰዓት መግባት ቢኖርበትም። ስገምት አምስት ሳንቲም ከመስሪያ ቤቱ ወስዶ አያውቅም፤ አምታቶ ማለቴ ነው፡፡ አንዴ ጠይቄው ነበር፡-
“እዚህ አገር ብዙ ሰው አመቺ ሁኔታ ከተፈጠረለት ገንዘብ የሚመነትፍበት ዘመን ነው፡፡ አንተስ ወስደህ አታውቅም?”
“አላውቅም! እንዴት ተብሎ!” አለኝ፡፡
“ለምን?” አልኩት፡፡
“ኢህአፓ አላዘዘኝማ!!” አለኝ፡፡ “አደ በይ አላዘዘችማ” አለማቱ እኔ ሆኜበት ነው፡፡ የእምነቱ እናት ቆሌዋ መሆኗ ነው፡፡ “ይልቅ ልንገርህ፤” አለና ቀጠለ “አንድ ጊዜ ደሞዝ ጭማሪ አገኘሁና እነዚያን የቱሉ ቦሎ አርሶ አደሮች መጋበዝ አለብኝ አልኩ። ወደ ቱሉ ቦሎ ሄድኩኝ። በዛ ላይ አባ ገዳቸው ነኝ ብዬ ነው፡፡ መጋበዝ ደስ ይላል፤ ምክንያቱም ትልቅ ያደርጋል፡፡ (አባ ገዳ የሆንኩት ከአባቴ ወርሼ ነው።) ሄድኩ ቱሉ ቦሎ፡፡ 12ቱን ኪሎ ሜትር ወደ ገጠር ቤታችን የሚያደርሰውን መንገድ ጨርሼ፣ አርሶ አደሮቹን ወደ ማገኝበት አረቄ ካቲካላ፣ ቤት ሄድኩኝ። የማውቃቸው አርሶ አደሮች የሉም፡፡ ሰፈር ገብቼ ጠየኩ፡፡
“እነሱ’ኮ ካቲካላ መጠጣት ትተዋል፡፡ ወደ ቱሉ ቦሎ ሄደህ ሆቴሎቹ ጋ ፈልጋቸው” አሉኝ፡፡
ሳላመነታ ወደ ቱሉ ቦሎ ከተማ ተመልሼ፣ ወደ ዝነኛው ሆቴል ሄድኩኝ፡፡ ቱሉ ቦሎ ሆቴል፡፡ አሁን ድራፍት ልጋብዛቸው ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስገባ አርሶ አደሮቹ አሉ፡፡ ግን ሁሉም ቢራ ነው የያዙት! የመድኃኔዓለም ያለህ! አርሶ አደሮች? ቢራ?! ደነቀኝ! ነደደኝ!! ነቢይ የተሰማኝን ስሜት ልንገርህ? እነዚህ ሰዎች እንዲያልፍላቸው ብለን አልነበረም እንዴ ስንታገል የኖርነው? ምን አናደደኝ? ቀንቼም ከሆነ፣ ምን አስቀናኝ?!
ለእኔ እጅግ ከባድ ፍልስፍና ያለበት ከባድ ጥያቄ ነው! የታገልክለት ህዝብ ሲያልፍለት መቅናት!! አባ ጫላ የተሰማውን ስሜት አለመደበቁ አንድ ነገር ሆኖ፤ ጥያቄው ግን ብስልና ጥልቅ እንዲሁም ከሌሎች የኢህአፓ አቋም ጋር ልናጤነው የሚገባ ነው፡፡
እንደ ሰው በዜብራ የምትሻገር ቮልስ
ካዛንቺስ ዩኒቲ፤ አባ ጫላ አዘውትሮ የሚሄድባት አንድ ግሮሰሪ ነበረች፡፡ አሁን ነብሷን ይማረውና ፈረሰች፤ለልማት ቦታ ቀይራለች፡፡ ከዩኒቲ ወረድ ብሎ አሰፋ ሞላ ግሮሰሪ አለ፡፡ ዩኒቲ ድራፍት ነው የሚጠጣው። አሰፋ ቤት (ጋሽ አሴ ቤት ይሉታል) በአብዛኛው ጂን ነው የሚጠጣው፡፡ ደሞ በደንብ ነው የሚቀዳው! ታዲያ አባ ጫላ ትንሽ ድራፍት ዩኒቲ ጠጥቶ ሲያበቃ፣ ወደ “ጋሽ አሴ ቤት እንሂድ” ለማለት፣ ሲፈልግ፤ “ጎበዝ! ወደ መጠጥ ቤት እንሂዳ” ይላል፡፡
አንድ ቀን ከዩኒቲ ወደ ጋሽ አሴ ቤት እንሂድ ተብሎ ሲወጡ፣መንጌ ለአባ ጫላ፤ “እኔ በመኪና እወስድሃለሁ” ይለዋል፡፡ መንጌ አንዲት የዱሮ ቮልስ አለችው፡፡ ጥቁር ሰማያዊ (dark blue) ቀለም አላት። አባ ጫላ፤ ቆማ ባያት ጊዜ ሁሉ፤ “ያቻት የመንጌ ቮልስ፤ እግሯን አንፈራጣ ቆማለች!” ይላታል፡፡ ታዲያ ያን እለት መንጌ፣ አባ ጫላን ጭኖ ቮልሷ ተነሽ ብትባል፤ አሻፈረኝ አለች፡፡ አባ ጫላም፤
“ምነው መንጌ፤ አስቀደምከኝ’ኮ!” ይለዋል፡፡ እንደ ምንም ቮልሷ ተቀስቅሳ፣ ጋሽ አሴ ቤት ሲደርሱ፤ ሰው ሁለት ሁለት ጠጥቷል፡፡
“አባ ጫላ፤ የት ቆያችሁ?” ተብሎ ሲጠየቅ፣
“ምን ይሄ መንጌ፣እንደ ሰው በዜብራ የምትሻገር ቮልስ ይዞ ጉድ አደረገኝ’ኮ!” አለ፡፡
ለዱለት ማማተብ!
አንድ ቀን አባ ጫላ፣ ዩኒቲ ባንኮኒ ጋ ቆሞ ይጠጣል። አንድ የካዛንችስ ወዳጄ ይመጣና ዱለት ያዛል፡፡ ጁለቱ ይመጣል ወይም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ መጥታለታለች እንበል፡፡ ወዳጄ መብላት ከመጀመሩ በፊት ያማትባል። ይሄ አባ ጫላ የዘወትር የሹፈት ፈገግታ ፈገግ ብሎና እነዚያን የባላገር መሳይ ወተት ጥርሶቹን፣ በጥቁር ፊቱ ላይ በሹፈት ገለጥ አድርጎ፤
“ስማ ወዳጄ፣ እፍኝ ለምታክል ዱለት ያማተብክ፤ ግማሽ ኪሎ ብታዝዝ የነብስ አባትህን ልትጠራ ነበር እንዴ?” አለው፡፡
ከእነ መንጌ ቡድን ማህል ታየ እሚባል አለ፡፡ ታየ ብዙ ጊዜ አባ ጫላን ወደ ቤቱ ማታ ማታ በመኪና ይወስደዋል። አባ ጫላ እንዳይቸገር ማገዙ ነው፡፡ ያም ሆኖ አባ ጫላ፣ “ሹፌሬን መጠጥ በቃህ በሉት - ሹፌሬን ጥሩት - ወደ ቤቴ መሄድ ፈልጌያለሁ!” ነው የሚለው፤ እንደ መኪናው ባለቤት መሆኑ ነው!
“ራሱም ቢሞት ቀብር አይሄድም”
ዛሬ በህይወት የሌለ አንድ ወዳጃችን ቀብር መሄድ አይወድም፡፡ ታዲያ፤ “ይሄ ሰውዬ ቀብር አይሄድም እንዴ?” ብለው አባ ጫላን ይጠይቁታል፡፡ አባ ጫላም፤ “ይሄን ሰው በደንብ አታውቁትም ማለት ነው፡፡ እሱ’ኮ ራሱም ቢሞት ቀብር አይሄድም!” አለ።
ሁለቱ የጃኬት አይነቶች
ይሄው ቀብር የማይሄድ ወዳጃችን፣አንዲት አዘውትሮ የሚለብሳት አብሮ አደግ ጃኬት አለችው። ሰውም፤ ይሄ ሰውዬ ይሄን ጃኬት መቼ ነው የሚቀይረው? ብሎ አባ ጫላን ሲጠይቀው፤ “ምን መሰላችሁ፤ በሀገራችን ሁለት ዓይነት ጃኬት አለ፡፡ አንዱ የሚገዛና የሚለበስ ነው። ሌላው የሚለበስና የማይወልቅ ነው! እንደዚህ ዓይነት የሚለብሱ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱም ይሄ ወዳጃችን እንደ ዜጋ ሲሆን፤ ከሀገሪቷ መሪዎች አንዱ ቢጫ ኮት የሚያደርግ አለ፡፡ ያኛው እንደ መሪ ነው የሚለብሰው” ሲል አብራራ፡፡
 አባ ጫላ፤ በካዛንቺስ ብዙ ታሪክ አለው፡፡ አንደበቱ ቢሮ ታስሮ ውሎ ካዛንቺስ የሚፈታ ነው የሚመስለው፡፡
ጂን ጠጪውና ጂን የማይጠግበው
ሁለት ተመሳሳይ ስም ያላቸው ጂን ጠጪ ወዳጆች አሉት፡፡ እኔ ስም ጠርቼ እገሌን እፈልጋለሁ አልኩት - ሞክሼ ስም ካላቸው አንዱን፡፡ አባ ጫላም፤ “ሁለቱ እኮ የተለያየ መገለጫ ነው ያላቸው፤ አንደኛው “ጂን ጠጪው” ነው የሚባለው፡፡ ሌላኛው “ጂን የማይጠግበው” ነው የሚባለው!” አለኝ፡፡
ከበግ ጋር ከዋልክ
አባ ጫላ የካዛንቺስ ሰው ይወደዋል፡፡ ድምፁ ጉልህና ስድቡ የሚጣፍጥ ስለሆነ ማንም አይቀየመውም። ለምሳሌ አንዱ የካዛንቺስ ወዳጅ በግ ነጋዴ ነው፡፡ ስጋ ይጋብዘዋል፡፡ አብረው ይቅማሉ፡፡ (እርግጥ ሰው በህይወት እያለ መቃሙ ጮክ ተብሎ አይወራም)
“መቃም አልወድም፤ አቁሜያለሁ ትለኝ ነበር፤አሁን እንዴት ቃምክ?” አልኩት፡፡
“ከበግ ጋር ከዋልክ ቅጠላ ቅጠል መብላት አይቀርልህም’ኮ!” አለኝ፡፡ የሚገርመው በግ ነጋዴ ወዳጁ አይቀየመውም፡፡ አባ ጫላ’ኮ ጥጋበኛ ነው!
አባ ጫላ ድህነት ላይ መቀለድ ይችልበታል፡፡ ጓደኛውን መንጌን አንድ መራራ ይጋብዘውና፤
‹‹ጠጣ! የአባ ጫላ ገንዘብ ብትቀደው አያልቅም›› ይላል፡፡
ክብ ሰርተው አውርተው ይለያያሉ
እነ መንጌና እነ ታየ እሁድ እሁድ ኳስ የሚጫወቱበት የጤና ቡድን አላቸው፡፡ አንድ ቀን አባ ጫላን ይጋብዙታል - ሲጫወቱ እንዲያይላቸው። ሄዶ አይቶዋቸው ተመለሰና፤ ‹‹እሺ እንዴት አገኘሃቸው?›› ተብሎ ተጠየቀ። ‹‹ክብ ሰርተው ስለ ኳስ አውርተው ይለያያሉ›› ብሎ መለሰ፡፡
አባ ጫላ፤ ከሰፈሩ ከቡልጋሪያ አካባቢ ወደ ካዛንቺስ ሲመጣ፣መንገድ ተዘግቶ ታክሲ አጥቶ ቤት ይቆያል፡፡ ሆኖም ቆይቶ ካዛንቺስ ይገኛል፡-
‹‹እንዴት መጣህ?›› ሲሉት፤ ‹‹ቆላ ቆላውን መጣኋ፤ ያሲምባ ልጅ እኮ ነኝ፤ማን መሰልኳችሁ?›› ይላል፡፡
አንዴ ኢህአፓን መርጫለሁ
አንዴ የምርጫ ጊዜ ነበር፡፡ “ምርጫ ጣቢያ ሄድክ እንዴ?” አልኩት፡፡
‹‹አልሄድኩም››
‹‹ለምን?››
‹‹ምን አረጋለሁ? አንዴ ኢህአፓን መርጩ የለ አንዴ!››
(ይቀጥላል)



 

 

 

Read 2082 times