Monday, 25 July 2016 07:29

‘የአጎቴ ታየር’ መንፈስ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንደምን ሰነበታችሁሳ!
አንድ ወዳጃችን በቀደም ምን አለን… “አሁን ከምናያቸው ፊልሞች መሀል ስሜትህን የሳበውና እሱን ብሆን የምትለው ገጸ ባህሪይ የትኛው ነው…” ምናምን ሲባል ማን አለ መሰላችሁ… “አጎቴ ታየር!”  ቂ…ቂ…ቂ… ምን ያድርግ…ዘመኑ እንደሆነ ‘ማንንም ከመጤፍ የማይቆጥሩ’ የእሱ አይነት ሰዎች ዘመን ነው፡፡
ስሙኝማ…የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አሁን፣ አሁን አንዳንድ ሰዎችን ዝም ብዬ ሳስባቸው ‘አጎቴ ታየር’ን ይመስሉኛል፡፡ ሰውየውን ስታዩት…የእውነት የምታውቁት፣ የምታውቁት አይነት ሰው አይመስላችሁም! አለ አይደል…የሆነ አገረ ገዥ ነገር የሚያደርገው የእድር ዳኛ፣ የቀበሌ ሊቀመንበር፣ የሆነ መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ የሆነ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ’ (ቂ…ቂ…ቂ…)፣ የሆነ ከዛሬ ነገ “አፍንጫችህን ላሱ፣ የማውቀው ነገር የለም…” ይላል ብላችሁ የምትፈሩት የዕቁብ ሰብሳቢ…ምናምን ነገር አይመስላችሁም!
‘የአጎቴ ታየር’ መንፈስ እዚቹ “የጉድ ቀን አይመሽም…” በምንላት በእኛዋ ምድር ‘ወረርሽኝ’ ሊሆን ምንም አልቀረው እኮ፡፡
እናላችሁ…እዚሁ እኛው መሀል መአት ‘አጎቴ ታየሮች’ አለን፡፡ ጉዶቻችን አደባባይ ቢወጡ የፊልሙ ‘አጎቴ ታየር’ን ክንፍ የጎደለው መልአክ ሊያስመስሉ የሚችሉ የክፋት ጉዶች የተሸከምን፣ ተቆጥረን የማናልቅ፣ ታሪካችን ለልብ ወለድነት ‘የሚበዛ’ ሞልተናል፡፡
ልክ ነዋ…‘በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ’ ያህል አንዱ ሲቸገር፣ ወይም የሆነ ነገር ሲገጥመው “መልካሙን ያምጣለት…” ከማለት ይልቅ “እንኳን! የት አባቱ፣” የምንል እየበዛን ነው… ‘አጎቴ ታየር’ የኦማርን በጥይት መቁሰል ሲሰማ ደስ ብሎት ፈገግ እንዳለው ማለት ነው፡፡
እናላችሁ…ሰውየው የሰው አካል ‘እየዘረፈ’ ይሸጥ የለ፡፡ (እኔ የምለው…እግረ መንገዴን፣ እንደ አሱ አይነት ነገር እኛ አገር በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚነግረን አጣን እኮ! ካለም እንዲህ፣ እንዲህ አይነት ነገር ስላለ ጠንቀቅ በሉ ማለት የአባት ነው፡፡ ከሌለም…“የሚወራውን አትስሙ፣ የምቀኛ ወሬ ነው…” ምናምን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ዝምታ… ሁልጊዜም ‘እርፍና’ ወይም ‘ብልጠት’ አይደለም፡፡) እናላችሁ…‘አጎቴ ታየር’ የሰው አካል እንደሚመነትፈው ሁሉ እኛ ዘንድ ደግሞ የሰው ሀሳብ፣ የሰው ሥራ የምንመነትፍ መአት አለን፡፡ ስንት ተለፍቶባቸው የተሠሩ የሙዚቃ ሥራዎች ‘አላፊ አግዳሚው’ ሁሉ እንደፈለገው እየተረተረ፣ እየገማመደ፣ እየከታተፈ ይጫወትባቸው የለ! ሰዎች የተጠበቡባቸው የፊልምና የድራማ ሀሳቦች ያለፈጣሪዎቹ ፍቃድ ‘እየተበለቱ’ በአዲስ ሥራ መልክ በሌሎች ሰዎች ስም ይቀርባሉ የሚል መአት ሀሜታ እንሰማ የለ እንዴ!
እናማ… ‘የአጎቴ ታየር’ መንፈስ እዚቹ “የጉድ ቀን አይመሽም…” በምንላት በእኛዋ ምድር ‘ወረርሽኝ’ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
የፊልሙ ‘አጎቴ ታየር’ በገንዘቡ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደሚችል ሲፎክር አይተነዋል፡፡ እያደረገም አሳይቷል፡፡…እኛም ዘንድ ‘በገንዘባቸው’ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችሉ የሚመስላቸው መአት አሉላችሁ፡፡ በእርግም ‘ሁሉንም ነገር ማድረግ’ ይችሉ ይሆን፣ ይሆናል፡፡
እናማ…‘የአጎቴ ታየር’ መንፈስ እዚቹ “የጉድ ቀን አይመሽም…” በምንላት በእኛዋ ምድር ‘ወረርሽኝ’ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
‘አጎቴ ታየር’ በግድ ልጅ ‘ዱብ’ አስደርጎ “ትንፍሽ ትዪና ምላስሽን ነው የምቆርጥልሽ…” ብሎ እንደፎከረው ቆርጦ የለ… እኛም ዘንድ በየቦታው የሰው ሰው በግዴታ ‘ዱብ’ እያስደረጉ  “ትንፍሽ ትዪና ምላስሽን ነው የምቆርጥልሽ…” አይነት ዛቻ የሚዝቱ ‘አጎቴ ታየሮች’ በየቦታው አሉ፡፡ (እግረ መንገዴን…ልጅን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የወንዶቹ ጭቅጭቅ… “የእኔ ልጅ አይደለም…” “ካመጣሽበት ውሰጂው…” ምናምን አይነት ነገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ግን አንዲት ሴትዮ የተገላገለችውን የሆነን ልጅ ሁለቱም ባል ያልሆኑ ሰዎች “የእኔ ልጅ ነው…” “የአንተ አይደለም፣ የእኔ ልጅ ነው…” እያሉ ሲጨቃጨቁ እንደነበር ሰምተን ተገርመን ነበር፡፡ እንዴት ሆነው ይሆን!)
“የእከሊት ልጅ ምነው እሷንም፣ ባሏንም አይመስል!…ጠርጥር ማለት ይሄኔ ነው፡፡”
“አልሰማሁም እንዳትይ…”
“አልሰማሁም…”
“ያ ማነው የሚሉት ባለስልጣን እንኳን…”
“የትኛው ባለስልጣን…”
“ያ እንኳን…መሬት ለመርገጥ የሚጠየፈው…”
“አሃ…ያ እፍ፣ እፍ ቢሉሽ ሊውጡሽ ነው እያልን የምንቀልድበት…”
“አዎ የእሱ ልጅ ነው ይባላል፡፡”
እናማ… ይሄኔ ምስኪኗ እናት “ይቺ ወሬ አንድ ቦታ ብትሰማ አንቺን አያድርገኝ…” ምናምን ተብላ እየተሳቀቀች ትኖር ይሆናል፡፡ ወይንም እፍ፣ እፍ የተባለው ባለስልጣን ተውጦ ይሆናል፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ… “እሱን እንኳን ተወው!” ብሎ ነገር ምንድነው!)
ስሙኝማ…በዛ ሰሞን ያወራናት ትዝ አለችኝ…እንድገማትማ፡፡ ሰውየው ከሚስቱ ይጣላና እሷ በሌለችበት አራት ልጆቻቸውን ይዞ ይወጣል፡፡ ሚስት ስትመለስ ቤቱ ባዶ ሆኖ ታገኘዋለች፡፡ ምን ብላ መልእክት ብትልክለት ጥሩ ነው…
“ሦስቱን ልጆች መልሰህ ላክልኝ፡፡ አንዱ ብቻ ነው የአንተ…” አለችው ይባላል፡፡
እናላችሁ…በ‘አጎቴ ታየሮች’ የተነሳ ባሎቻቸውን… “አንዱ ብቻ ነው የአንተ…” ሊሉ የሚችሉ ሚስቶችና ‘የሚስት ሚና የሚጫወቱ’ እንትናዬዎች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ አሀ… ‘አስይዘው’… “ትንፍሽ ትዪና ምላስሽን ነው የምቆጥርልሽ…” የሚሉ መአት ናቸዋ!
እናማ…‘የአጎቴ ታየር’ መንፈስ እዚቹ “የጉድ ቀን አይመሽም…” በምንላት በእኛዋ ምድር ‘ወረርሽኝ’ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
ቄሱ ወደ እሳቸው እየመጡ በትዳራቸው ላይ ስለመወስለታቸው የሚናዘዙ ሰዎች በመብዛታቸው ተበሳጭተዋል፡፡ አንድ ዕለተ ሰንበት…
“ከእንግዲህ ማንም ሰው መጥቶ በትዳሬ ላይ ማግጫለሁ ቢለኝ ሥራዬን አቆማለሁ…” ሲሉ ለምእመናኑ ተናገሩ፡፡ ምእመናኑ ደግሞ ቄሱን ስለሚወዷቸው እሳቸውን ላለማስቀየም ‘ፊት ለፊት ከመዘርገፍ’ በምስጢር ቃል እንጠቀም ተባባሉ። ስለዚህም ምዕመናኑ እየሄዱ “ትናንት ወድቄ ነበር…” ማለት ጀመሩ፡፡ ቄሱም በዚህ ደስተኛ ሆኑ፡፡ በመጨረሻም እሳቸው ህይወታቸው ሲያልፍ ሌላ ቄስ በቦታቸው ተተኩ፡፡ በትዳራቸው የማገጡ ሰዎች ለአዲሱ ቄስ ሲናዘዙ ፊት ለፊት ከመናገር እንደበፊቱ “ትናንት ወድቄ ነበር…”  ማለት ቀጠሉ፡፡
አዲሱ ቄስ ሁለት ሳምንት ያህል እንደቆዩ የከተማዋን ከንቲባ ያገኟቸውና…
“ለምንድነው የከተማዋን መንገዶች በደንብ የማትጠግኑት! ምዕመናኑ ለኑዛዜ ሲመጡ ‘ትናንት ወድቄ ነበር…’ ይሉኛል፣” ይሉታል፡፡
ከንቲባውም አዲሱ ቄስ ስለ ምስጢራዊው ቃል ማንም እንዳልነገራቸው ስላወቀ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ይሄን ጊዜ ቄሱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ምን እንደሚያስቅህ አይገባኝም፡፡ የአንተ ሚስት እንኳን በዚህ ሳምንት ብቻ ሦስት ጊዜ ወድቃለች…” ብለውት አረፉ፡፡
ከዚች ሚስት ጀርባ ስንት ‘አጎቴ ታየሮች’ እንዳሉ ይታያችኋል!
እናላችሁ…ልክ እንደ ‘አጎቴ ታየር’ በአደባባይ ሩህሩህ፣ ደግ ምናምን ሆነን በየጓዳችን ሉሲፈር እንኳን ሊያስበው የማይችለው ተንኮል የምንሠራ ስንት አለን አይደል!
ለስንብት ይቺን አንብቡልኝማ…
ሰውዬው ውሽምዬዋ ቤት ነው፡፡ እናማ… ጢሙን እንዲላጭ ትነግረዋለች፡፡
“ውዴ ጢምህ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ብትላጨው…መልክህን ያሳምረዋል፡፡”.
“ሚስቴ እኮ ጢሜን ትወደዋለች፡፡”
“ግዴለህም ተላጨው…ይበልጥ ያምርብሀል፡፡”
“ግን እኮ ሚስቴ በጣም የምትወደው ጢሜን ነው፡፡”
በመጨረሻ ግን ይስማማና ጢሙን ይላጫል። ታዲያ ሌሊት ዱካውን አጥፍቶ ይገባና ለሽ ያለችው ሚስቱ ጎን ሹክክ ብሎ ገብቶ ይተኛል። ሚስትዬውም እየተገላበጠች ጉንጩን በእጇ ትነካዋለች፡፡ ከዛ በእንቅልፍ ልቧ ምን ብትል ጥሩ ነው… “አንተ ሰውዬ በዚህ ሰዓት ምን ታደርጋለህ! ባሌ ድንገት ቢመጣስ!” ብላው አረፈች፡፡ እንትናዬዎቻችሁን የምትጠራጠሩ እንትናዎች… ጢማችሁን ተላጩና ሹክክ ብላችሁ ጎኗ ተኙ፡፡ ያኔ ቁርጣችሁን ታውቃላችሁ፡፡
ጢምህን ተላጭ፣ አትላጭ የምትለው ‘ደፋር’ የሌለችበት፣ ከእነጢሙ የሚምነሸነሸው ‘አጎቴ ታየር’ አለ እንጂ! ቂ…ቂ…ቂ… (‘ክፋት እንዳይመስልብኝ’…ጢማም ወዳጆቼን እያሰብኩ ነው፡፡)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4159 times