Monday, 25 July 2016 09:01

የቱርክ መንግስት ሌላ መፈንቅለ መንግስት እንዳይሞከርበት ሰግቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ሰራተኞችን አባሯል

     ባለፈው ሳምንት የተቃጣበትን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፈው የቱርክ መንግስት፤ በድጋሚ ተመሳሳይ ሙከራ ሊደረግ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንደገባ የተጠቆመ ሲሆን በርካታ ዜጎችን ከተለያዩ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ማባረሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት የተቃጣበትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማክሸፉን ተከትሎ በበርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መምህራን ላይ የወሰደው የእስራትና ከስራ ገበታቸው የማባረር እርምጃ፣  በአገሪቱ ተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የኤርዶጋን መንግስት ባለፈው ማክሰኞ፣85 ያህል የአገሪቱን ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችና መኮንኖች ማሰሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አንዳንድ ምንጮች ግን የታሳሪዎቹ ቁጥር 125 እንደሚደርስ መናገራቸውን ጠቅሶ፣ይህም መንግስት በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የጦር ሰራዊቱ ሃላፊዎ እጃቸው አለበት ብሎ መጠርጠሩን ያመለክታል መባሉን አውስቷል። መንግስት የጦሩን እንቅስቃሴ ለመግታት በርካታ የጦር ሰፈሮችን በከባድ የጦር መሳሪያዎች ማስከበቡ የተነገረ ሲሆን የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የኢስታምቡል ተወካይ አስሊ አይዲንታስባስም፤ መንግስት ይህንን እርምጃ መውሰዱ በድጋሚ የመፈንቅለ መንግስት ጥቃት ይፈጸምብኛል የሚል ስጋት ውስጥ መግባቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ እየወሰደው ያለው እርምጃ ጥብቅ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፣ ከስራ ገበታቸው ያገዳቸው ወይም ያባረራቸው ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ መድረሱን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የጠረጠራቸውን 15 ሺህ 200 የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞችና መምህራን ከስራ ገበታቸው ማባረሩንና የሌሎች ተጨማሪ 21 ሺህ መምህራንን የስራ ፈቃድ መቀማቱን የጠቆመው ዘገባው፤ 1ሺህ 577 የዩኒቨርሲቲ ዲኖችም ስራቸውን እንዲለቁ መጠየቁን ገልጧል፡፡
የፖሊስ ባልደረቦች የነበሩ 8 ሺህ ሰዎች፣ 1 ሺህ 500 የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ 2 ሺህ 745 የፍርድ ቤት ዳኞች፣ 8 ሺህ 777 የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ ከ100 በላይ የብሄራዊ ደህንነት ተቋም ባልደረቦች፣ 257 የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሰራተኞችና ሌሎች በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ከስራቸው መባረራቸውንም ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ፓርቲ የተላላካቸው 300 ሺህ ያህል የኢሜይል መልእክቶች አፈትልከው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ዊኪሊክስ የተባለውንና መረጃዎቹን ዘርፎ ያሰራጨውን ተቋም ድረገጽ መዝጋቱን የዘገበው ደግሞ ዘ ጋርዲያን ነው፡፡
ስካይ ኒውስ በበኩሉ፤የቱርክ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ማንኛውም የአገሪቱ ምሁር ወይም ተመራማሪ ላልተወሰነ ጊዜ ከአገር መውጣት እንደማይችል ማስታወቁንና በውጭ አገራት የሚገኙትም በአፋጣኝ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማስተላለፉን ዘግቧል፡፡


Read 1608 times