Monday, 25 July 2016 09:24

አሰለፈች አሽኔ፤ የነገሰችበት የጥበብ ምሽት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    ባለፈው ማክሰኞ ምሸት ሀገር ፍቅር ቴአትር  ቤት በታዳሚዎች ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ አንዲት አንጋፋ ሁለገብ የጥበብ ንግስት ትዘከራለች አንዳትቀሩ የሚል ጥሪ በመተላለፉ ነበር አዳራሹ የሞላው፡፡ ‹‹አሰለፍ ለኛ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር ኤፍሬም ለማ ተፅፎ የተዘጋጀ ሲሆን ተዋናዮቹ ደግሞ ከ50 በላይ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የቴአትር ተማሪዎች ነበሩ፡፡
አርቲስት አሰለፈች አሸኔ በምሽቱ፤ ሙሉ የሀበሻ ቀሚስ ለብሳና የሚያምር ካባ ደርባ፣ ከልጆቿ አባት ከአቶ ግርማ ብስራት የጥንት ጓደኞቿ ጋር ተሰይማ ነበር፡፡ አጃኢብ ያሰኘው ‹‹አሰለፈች ለኛ›› ሙዚቃዊ ተውኔት ከመቅረቡ በፊት ወደ መድረክ ወጥታ የተዘጋጀላትን ኬክ ቆረሰች፡፡ ከዚያማ ተውኔቱ መቅረብ ጀመረ፡፡ የጥንት ዘፈኖቿ እየተቀነቀኑ፣ የኪነ-ጥበብ ጅማሬዋ፣ ለጥበብ የከፈለችው መስዋዕትነት፣በደርግ ካድሬዎች የደረሰባት እንግልት፣ውበቷ፣ትዳሯ---ብቻ ስለ አሰለፈች አሽኔ በሙዚቃ ተውኔቱ ያልተዳሰሰ የለም፡፡
ተዋናዮቹ በሙዚቃዊ ተውኔቱ በአርቲስቷ ጉዳይ በሶስት ጎራ ተከፍለው የጦፈ ክርክር አድርገዋል፡- አንደኛው ወገን፤ አሰለፍ ለኛ ድምፃዊ ናት፣ ሌላው፤ተወዛዋዥ ናት፣አንዱ ቡድን ደግሞ፤ቴአትር ሰሪ ናት በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሁሉም ታዲያ የመከራከርያ ሃሳቡን ያቀርባል፤በመረጃ ለማሳመን ይጥራል፡፡ አንደኛው ቡድን መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያቀርባል፡፡ ተወዛዋዥ ናት ያለው ቡድን፤በውዝዋዜ እየተውረገረገ ወደር የለሽ ችሎታዋን በአፍ ሳይሆን በተግባር በማሳየት ለማሳመን ይተጋል፡፡ ድምፃዊት ናት የሚለው ጎራ በበኩሉ፤የአሰለፈችን የጥንት ዘፈኖች በማዜም አንጋፋዋን አርቲስትና ታዳሚውን 40 አመት በትዝታ ወደ ኋላ እንዲጓዙ አስገድዷል፡፡
አርቲስቷ በዝግጅቱ ክፉኛ ልቧ ተነክቶ እንባዋን ስታፈስ አምሽታለች፡፡ ሙዚቃዊ ተውኔቱ ሲጠናቀቅም የእለቱ የክብር እንግዳ ሸምጋይ የሬዲዮ ድራማ ደራሲና ተዋናይ ሰለሞን አለሙና አሰለፈች አሽኔ ወደ መድረክ ተጋበዙ። የንግግር እድሉ የተሰጠው ሰለሞን ግን፤“እኔ እሷ በነገሰችበት በዚህ መድረክ የክብር እንግዳ ለመሆን አልመጥንም፤ባይሆን ትመርቀኝ” አለ። የምርቃት መዓት ተዥጎደጎደለት፡፡ ‹‹አሁን ሙሉ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል›› አለ ሰለሞን፤ከምርቃቱ በኋላ፡፡  
ከእነ ውበቷና ግርማ ሞገሷ ያለችው ዘርፈ ብዙ የጥበብ ባለሙያዋ አሰለፈች ባቀረበችው ንግግር፤የጥበብ ት/ቤቷ የነበረውን ትያትር ቤት አሞግሳለች፡- “ሀገር ፍቅር፤ለእኔ ክብሬ ሞገሴ፣.እናቴ አባቴ ነው፤ስልጣኔ የተማርኩበት፣የተከበርኩበት---›› ንግግሯ በለቅሶ ተቋረጠ፡፡ “-“በካድሬዎች ተገፍትሬ በጓሮ በወጣሁበት ቴአትር ቤት፣ዛሬ በፊት ለፊት ገብቼ ስለነገስኩ ክብር ለመድሀኒያለም!››በማለት አርቲስቷ በምስጋና ደስታዋን ስትገልጽ፣ታዳሚውም በጭብጨባና በፉጨት አጅቧት ነበር፡፡
የምሽቱ ፕሮግራም ከመዘጋቱ በፊት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬን ጨምሮ የተለያዩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፤ ለአንጋፋዋ አርቲስት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻ እንዲናገሩ እድል የተሰጣቸው ባለቤቷ አቶ ግርማ ብስራት፤‹‹እኔስ ተጥለን ተረስተን የቀረን መስሎኝ ነበር፤ለካ አስታዋሽ አለን›› ሲሉ ተናገሩ። ሲቀጥሉም፤ “በህይወት እያለሁ የባለቤቴን ክብር በማየቴ ደስታዬ ወደር የለውም፤ወ/ሮ አሰለፈች አንቺም እንኳን ደስ አለሽ›› በማለት ለባለቤታቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ በርካታ የአርቲስቷ አድናቂዎች፣እግሯ ስር ተደፍተው አክብሮትና አድናቆታቸውን ሲገልፁ ነበር ያመሹት፡፡ በመካያውም አንጋፋዋ አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፤ የሁሉም ተዋንያን ፊርማ ያረፈበትና በፎቶዋ የተዋበ ሰሌዳ የተሸለመች ሲሆን እሷም  ምርቃቷንና ምክሯን ለወጣቶቹ አርቲስቶች ለግሳለች፡፡ ከዚያም፤“የአገር ፍቅር ትዝታው-----ያስደስታል ለሚያውቀው” በሚለው የጥንት ዘፈኗ ታዳሚውን ተሰናብታለች፡፡



Read 2487 times