Monday, 25 July 2016 09:37

ሞትም ማስታወሻ ነው!

Written by  ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(1 Vote)

“የሥነጥበቡ ገደል በምንድን ነው የሚሞላወ?”

“The history  of the world is the biography of great men” ወይም ‘የዓለም ታሪክ የታላላቅ ሰዎች ግለ-ታሪክ ነው’ በሚለው ሀሳብ በከፊል እስማማለሁ። ታሪክ በተለየ መልኩ ከግለሰቦች ጋር ይያያዛልና፡፡ (የጥቅሱን ምንጭ ባለማወቄ ይቅርታ እጠይቃለሁ) ታሪክ ሰዎችን፣ሰዎችም ታሪክን ያንፃሉ፡፡ታሪክ የዓለምን፣የሀገርንና የማህበረሰብን ቅርፅ ይገነባልም- ያንፃልም- ይቀርፃልም፡፡ ጠንካራ መሰረት ያለው ግለሰባዊ ማንነትም እንዲሁ… ከዚህ ባሻገርም ታሪክ የሚሰራ ግለሰብ ራሱ ታሪክ ሆኖ ይኖራል፡፡ ዘመን ይሻገራል፡፡ ሰብዓዊነት ያለው ታሪክ ደግም መሻገርን ያልፍና ዘልዓለማዊነትን ያጎናፅፋል።
ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 4፣የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ አባት የሆኑት ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም (1915-2008 ዓ.ም) አረፉ፡፡ ‘ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ‘፤ወይም ‘አለፉ‘ የሚሉ ቃላትን እኝህ ሰው በዚች ዓለም በህይወት አለመኖራቸውን መግለጫ አይሆኑልኝም፡፡ የሠሩትና የዘሩት ሥራ፣ በተለይም በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ምዕራፎች በጉልህ የሚታይ አሻራ በመተዋቸው ‘ማለፋቸው‘ ወይም ‘መለየታቸው‘ እርግጥ መሆን አይችልም፡፡ ሞት ደግሞ (እንደ እኔ እምነት) ተጨባጭ ያልሆነ እውነት በመሆኑ በተለይ እንደ ሰዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ላሉ፣ሥራና ታሪካቸው ሞት ሊያስረሳው የማይችል ታሪክ ለሰሩ ሰዎች ‘ሞት‘ በእርግጥም ተጨባጭ አይሆንም፡፡
ስለ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም፤የህይወት ታሪክ በአጭሩና በቁንጽሉም ቢሆን ባለፈው ሳምንት ይትባረክ ዋለልኝ ስለሄደበት፣ይሄኛው የእኔ ጽሁፍ (ከውቅያኖስ ጠብታውን እንኳ እንደማይሆን ግልጽ ቢሆንም) የሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ታሪክ ሰሪነትን ይበልጥ ከሚያጎሉ ታሪካዊ ዓውዶች በመነሳት፣በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ያንጸባረቋቸውን እውነታዎች በወፍ-በረር (በብርሃን ፍጥነት ያክል የምትበር ወፍ እንደምትከተሉ እያሰባችሁ)፡ ሥነ-ጥበባችን የሳታቸውን አንኳር ነጥቦችንም በመጥቀስ እቀጥላለሁ፡፡ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አጀማመር አካሄድ፣ ከፍታ እንዲሁም ወሳኝ ምዕራፎች የተለያዩ የታሪክ ምሁራን አመክንዮአቸውን በማቅረብ የተለያዩ ዘመናትን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እስከ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክና እስከ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ድረስ ኢትዮጵያን ዘመናዊ የማድረግ ጥረት ቀጥሎ ነበር፡፡ ‘ሀገር‘ የሚለው ታላቅ ምናብና ሀገርን ከቀሪው  ዓለም ጋር እኩል የማራመድ፣ ቀድመናቸው ከነበሩት ነገር ግን ቀድመውን ከተራመዱት ሀገሮች እኩል ባይሆንም የስልጣኔአቸውን ዱካ የመከተል፣ ጠቃሚውን በብልሀት በመምረጥ ከሀገሬው ኑሮና ባህል ጋር ማስተሳሰር የእነዚህ መሪዎች ራዕይ ነበር። ራዕያቸውን ለማሳካት በሮቻቸውን መክፈት፤ ተስፋ ያላቸውንና ራዕያቸውን ያሳኩ ዘንድ የበኩላቸውን ሊወጡ የሚችሉ ግለሰቦችን ወደ ባህር-ማዶ መላክና እውቀትና ሥልጣኔ ቀስመው እንዲመጡ ማድረግ ለውጥናቸው መሳካት የቀየሱት ነበር፡፡ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ሲበዘበዙና ነፃነታቸውን ለማግኘት ሲታገሉ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከማወጅ አልፋ፣እልፍ ዘመናዊነትና ስልጣኔን ለመቀናጀት እየለፋች ነበር፡፡    
የዘመናዊነት እርምጃዎችን እመርታ በሥነ-ጥበብም ለማስቀጠል ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ፤አፈወርቅ ገ/እየሱስን ወደ ጣሊያን ሀገር በመላክ ሥነ-ጥበብ እንዲያጠና ማድረጋቸው ተጠቃሽ ሲሆን ሌሎችንም አከታትለው ልከው ነበር፡፡ ይህ ዘመናዊነትን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ያደርጉት የነበረው ጥረት በሌሎች ዘርፎች የተዋጣለት ከመሆኑም በላይ ይህ ጥረት በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ የዓጼው ጥረት ወደ አሜሪካን ሃገር ተልከው መማር ከቻሉት ውስጥ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ዋንኛው ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ነፃነታቸውን የተቀዳጁ የአፍሪካ ሀገራትና ለነፃነታቸው የሚታገሉትን ጭምር ሀገራቸውን ከድህረ ቅኝ ግዛት ተፅዕኖች ለማላቀቅ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ራሳቸውን ለመቻልና የራሳቸው የሆነ ዘመናዊነት ለመፍጠር ከሚያደርጉት ሙከራዎች እኩል፣ በባህልና በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ የበኩላቸው ጥረት ያደርጉ ነበር። ሥነ-ጥበብ ተኮር ዘመናዊነት ለመከሰት ሰፋ ያለ ተሞክሮ ከነበራቸው ሀገራት መካከል ናይጄሪያ፣ ጋና እንዲሁም ሴኔጋል ተጠቃሾች ናቸው። የተለያዩ የውጭ ሀገራት ተምረው ወደ ሀገራቸው በመመለስ አብዛኛዎቹ ቅኝ ገዢዎቻቸው በሰሩላቸው ት/ቤቶች ማስተማር ጀመሩ፡፡ እዛው ሀገራቸው ላይ ሥነ-ጥበብ ሲሰሩ የነበሩትም በሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ካሉ ምሁራን ጋር በመተባበር ያደርጉ የነበሩት እንቅስቃሴዎች ዘመናዊነትን ለሀገራቸው ለማጎናፀፍ ያለመ ነበር፡፡
የሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ተነሳሽነት፣ከዚህ ከወቅቱ የአፍሪካ ምሁራንና የሥነ-ጥበብ አንቀሳቃሾች በሚስተካከል ብቻ ሳይሆን በሚልቅ አንጻር የኢትዮጵያን ዘመናዊነት የሚያራምድ ተሞክሮ በማድረግ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የወቅቱ የአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት፣የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በልደታቸው ቀን ሐምሌ 16, 1950 ዓ.ም መርቀው ሲከፍቱ የተናገሩትን ከዶ/ር ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮርጊስ የፍልስፍና ዲግሪ (P.h.D) የመመረቂያ ጽሁፍ ላይ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ያገኘሁትን ንግግር ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፡--
“የትምህርት ቤቱን መመስረት ደግፈነዋል። ምክንያቱም ዘመናዊ ሠዓልያን ባሕላዊ ዘዴዎችን ከዘመናዊ አሰራር ጋር በማቀናጀት፣ በምዕራባውያን ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ መድረኮች ሠዓልያኖቻችን የፈጠራ ስራዎቻቸውን በመላክ፤ መላው ዓለም ኢትዮጵያም የሰለጠነው ዓለም አካል እንደሆነች ዕውቀት እንዲኖረው ያስችላል ብለን ስለምናስብ ነው”   (ፍሬ ከናፍር፡ 1957)
ይህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሃገራችንን የማዘመንና ከሌላው አለም እኩል የማራመድ ህልምን ማሳካት ብቻም ሳይሆን ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ በኢትዮጵያ ሥረ-መሰረቱን እንዲይዝ ያስቻሉና ታላቅ ታሪክ መስራት የቻሉ ግለሰብ ናቸው፤ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም። በወቅቱ እጅግ አብላጫዎቹ የትምህርት ቤቱ መምህራን የውጪ ሃገር ዜጎች ቢሆኑም ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን ከተመረቁም በኋላ ወደ ውጪ ሃገራት በመላክና ተምረው ሲመለሱም፣በትምህርት ቤቱ በመምህርነት እንዲቀጥሉ እድል በመክፈት፣ “የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ” እንዲሉ፣ሌላ ፋይዳ ያለው ተግባር ሲፈጽሙና በተነሳሽነት የጀመሩት ስራ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ ደፋ ቀና ብለዋል፡፡ ተሳክቶላቸውማል፡፡
ገብረክርስቶስ ደስታ፡ እስክንድር ቦጋስያን፡ ታደሰ ግዛው፡ ታደሰ ማሜጫ በውጭ ሃገር ተምረው ሲመለሱ፣ በት/ቤቱ ከማስተማርና ያስተማሯቸው ተማሪዎች በተራቸው ውጭ ሃገራት ሄደው እንዲማሩ ከማድረግ ባሻገርም በሃገራችን የሥነ-ጥበብ ታሪክ የአስተሳሰብ ርዕዮትና ንቅናቄ እንዲፈጠር በማስቻል በሃገር ብቻ ሳይሆን በአህጉርና በዓለም ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል እንቅስቃሴ እንዲከወን እድሉን ያመቻቹት ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ሕሩይ ናቸው፡፡ ይህን ታሪክ በአግባቡ ለመሰነድም ሆነ ለማጥናት የተደረገውና እየተደረገ ያለው ጥረት ምናልባትም በትውፊታዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ አቶ አበባው አያሌው፣ ሠዓሊና ሃያሲ ስዩም ወልዴ ራምሴ፣ የሥነ-ጥበብ ታሪክ አጥኚዎቹ  ሠዓሊ እሰዬ ገብረመድህን፣ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ እንዲሁም ሠዓሊነቱን ይበልጥ አጠንክሮ ከያዘውና ሥነ-ጥበባዊ ምርምር በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ሥነ-ጥበብ ላይ ከሰራው ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ  ካጠኗቸውና እያጠኗቸው ካሉ ታሪኮች ውጪ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ታሪክን ስራዬ ብሎ የያዘ ግለሰብም ሆነ አካል አይታየኝም፡፡
እዚህችው ያለን ሠዓሊያንና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች የርቅቀትና የፍልስፍናውን ጥግም ሆነ ጭራ ብዙዎቻችን በአግባቡ  ሳንይዘው የተራቀቁ ሥነ-ጥበባዊ እሳቤዎችን አንስተን ስንራቀቅና ስንፈላሰፍ፣ በዓለም የሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ቦታ ማግኘትም ሆነ ቦታውን መወሰን ያልቻለው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ አየር ላይ የሚንገዋለል ጉም ሆኗል፡፡ የሶስት ሺህ ዓመታት የሥነ-ጥበብ ታሪካችን በአውሮፓና አሜሪካ ሃገረሰባዊ (ethnographic) ሙዚየሞች እንደ ሃገር ቅርስ ከመቀመጥ ውጭ እንደ ሥነ-ጥበብ የተጠናበትን አግባቦች ማግኘት አዳጋች ነው፤-የለም ሊባልም ይችላል፡፡ ቦታውን መወሰን የሚችለው ሥነ-ጥበቡን የሚደግፍ፡ ቦታውን የሚወስን ጥናትና ትረካ ሲኖረው ነው። ምዕራባውያን ይህንን ሊያደርጉልን አይችሉም -- የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸምም ጊዜአቸውን እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ለበዘበዟቸው ሃገራት ሥነ-ጥበብ ብዙ ነገር አድርገዋል፡ ሌሎች አጀንዳቸውን ይቀጥሉ ዘንድ፡፡ እኛ እንግዲህ ገና እየተበዘበዝን በመሆኑ መጎዳታችን እስኪታወቀንና ካሳ እስክንጠይቅ ተራችንን እየጠበቅን ይመስላል። እስከ መቼ እንዲህ እንቀጥል ይሆን? ልብ ያለው አንባቢ ራሱን ይጠይቅ፡፡
በእንቅርት ላይ እንቅርት ሆኖ ሥነ-ጥበባችን ሶስት ወደ ኋላና ሩብ እርምጃ ወደ ፊት እያራመደው ያለው የሂስ ባሕላችን ነው፡፡ በተለይ ዘመንኛው ወይም ያሁኑ ወቅት የሥነ-ጥበብ ታሪካችንን በተመለከተ ደግሞ “አትድረስብኝ አልደርስብህም!” ወይም “እከክልኝ አንተንም ሲበላህ አክልሃለሁ!” ከሚል ያልዘለለና ሥነ-ጥበባዊ ፋይዳን መሰረት ካላደረገ፤ ይልቅስ “ማን ምን ሰራ?” ሳይሆን “ምን ያህል ሸጠ?”፤ “እሱ ማን ሆነና ነው እንዲህ እሚናገረውና የሚጽፈው?” ከሚሉና አልፎ ተርፎም ተራ የስድብ ቃላትን እስከመሰንዘር የሚደርስ ቁልቁለት እየወረድን ያለንበት ዘመን ላይ እንገኛለን። እንዲህ አይነት ብክለት ባለበት የሥነ-ጥበብ ጎዳና የት መድረስ እንችላለን-ብካዩ አፍኖ ሊገለን ይችል ይሆናል እንጂ! በእንዲህ አይነት የመለጎምና የማጉረምረም አሰራርስ ለማኅበረሰብና ለሃገር ምን ማበርከት ይቻላል?
ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም፤ጥብቅ የሆነ መሰረት ያለው ታሪክ ሰርተው አርፈዋል። ከሳቸው ቀጥሎ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ሃገራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡም ሆነ ሥነ-ጥበባዊ ማንነታቸውን ሲገነቡ ያሉና በመገንባት ላይም ያሉ ታላላቅ ሰብዕና ያላቸው ሠዓልያንን አይተናል። ግለሰቦች ታሪክ ቢሰሩም የሰሩት ታሪክ ካልታየ፣ ካልተመረመረ፣ ካልተጠና ሂስ ካልተሰጠበት ሥነ-ጥበባችን እንኳን ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ብቅ ሊል ይቅርና ጓሮም ሆነ ደጃፍ መውጣት አይችልም፡ አልቻለምም፡፡ ሥነ-ጥበባችንና ማኅበረሰቡ ያለውን ርቀት ማየትም በቂ ነው፡፡ የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ጦር፡ ሠፊው ማህበረሰብ ደግሞ ጋሻ ይዘው ነው የሚታዩኝ-አንዳንዴም የተገላቢጦሹ ይሆናል። ይህ ገደል በምንድነው የሚሞላው? ማን ነው የሚሞላው?  የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ አባት የሆኑት ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ማረፋቸው፤ ብዙ... እጅግ በጣም ብዙ የቤት ስራዎቻችንን እንድናስታውስ ይረዳናል ባይ ነኝ። የቤት ስራውን ለመስራት ደግሞ በዋናነት ሥነ-ጥበብ የምትሻውን ማሟላት ይጠይቃል። የቤት ስራው ምን እንደሆነ ያላወቀም ወደ ሸራውና ወደ ስራው ከመሮጡ በፊት ስለሚሰራው ስራ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት የሚያሳስብ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደምንገኝ ይሰማኛል፡፡
ይህ ትውልድ የራሱን ታሪክ ይጽፍ ዘንድ (ከእነ ማነቆዎቹም ቢሆን) ከመቸውም ዘመን የተሻለ እድል አለው -- አለን ባይ ነኝ፡፡ የሚነቃ ይንቃ፡ ነቅቶ ስራውን የሚሰራ ደግሞ የት እንደሚደርስ ያውቀዋልና ማስታወሻም ላያስፈልገው ይችላል፡
ቸር እንሰንብት!

Read 1281 times