Monday, 25 July 2016 09:40

‹‹ራሳቸውን ለመሳም የሚዳዳቸው ደራሲያን››

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(4 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
‹‹የአለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ መፅሐፍ አለህ?›› ስል የጠየኩት ወዳጄ በጥርጣሬ እያየኝ፡-
‹‹የትኛው?›› ሲል መልሶ ጠየቀኝ
‹‹በዶ/ር ሥርግው ገላው አርትኦት የተደረገው፣›› ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› ስለው ጥርጣሬው ወደ ትዝብት ተሻገረ፡፡
‹‹ምነው?›› ስል መልሼ ጠየኩት
‹‹ይሄን መፅሐፍ ለሦስተኛ ጊዜ ስትጠይቀኝ ነው።››
‹‹ጠይቄህ ነበር?›› እራሴን ታዘብኩት
‹‹እ… ግን መፅሐፉን እንዳነበብከው ነግረኸኛል። እኔም አንብቤዋለሁ፡፡ እንዳንተ ልወደው ቀርቶ እንደውም አናዶኛል››
‹‹እንዴት››
‹‹ፀሐፊው እራሱን ይቆልላል››
‹‹ማን? አለቃ ተክለኢየሱስን?››
‹‹አዎ፣ ብዙ ቦታ እራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ሲያጋጥመኝ ቋቅ ይለኛል፡፡ አንብቤ ስጨርስ መፅሐፉን አንድ ቀን ቤቴ አላሳደርኩትም፡፡ ለሰው ሰጠሁት፡፡ አንዳንድ ሰው ይሄው ነው፤ ማሸነፍ የሚችልበት ተሰጥኦ እያለው፣ ሽልማቱን በጉልበት ለመውሰድ ይተናነቃል፡፡›› (ቃል በቃል እንዲህ ያለኝ ይመስለኛል፡፡)
‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ››ን ከአንድም ሁለት፣ ሦስቴ ባነበውም፣ ጓደኛዬን ያናደደውን፣ እኔ ልብ አላልኩም ነበር፡፡ የንባብ ልዩነት የሚከሰተው ከእንዲህ አይነቱ ልዩ ልዩ ትኩረት አንፃር መሆኑ ግርም አለኝ አንዳንድ አንባቢ የሚባለውን ልብ ብሎ ሲከታተል፣ ሌላኛው ደግሞ መባያውን አትኩሮ ይከታተላል፡፡ አለቃ ተክለኢየሱስ ያሉት እኔ ጋ ሲደርስ፣ ያሉበት መንገድ የት ተቆርጦ ቀረ? የተባለው እንዴት መባያውን ጋርደብኝ?
በነባር መዛግብት ሆነ መፃህፍቶቻችን ዘንድ የሚበዛው የደራሲው ትህትና እራስን አሳንሶ የማቅረብ አባዜ እንጂ መብለጥለጥና መታበይ አልነበረም፡፡ የመታበይ ጉዳይ በሐይማኖት አስተምህሮ ዘንድ ጠበቅ ያለ ተግሳፅ የሚያስከትል እንደሆነ ስለሚያውቁም ይሆናል፤ መንፈሳቸው ወደ መታበይ አጋድሎ አይስተዋልም፡፡ ሉቃስ በወንጌል፤ ኢየሱስ ‹‹ፃድቃን›› እንደሆኑ ለራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ›› የሚሆን ምሳሌ እንደተናገረ ይጠቅሳል፡፡ ምሳሌው የቀራጭና የፈሪሳዊ ፀሎት ላይ መሰረቱን የጣለ ነው። ፈሪሳዊው በመታበይ በልቡ እንዲህ ይላል፡-
‹‹እግዚአብሔር ሆይ፤ አንደሌላ ሰው ሁሉ ቀማኞችና ዓመፀኞች፣ አመንዝሮችም ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሀለሁ፡፡ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ፡፡››
ነባር ሰነዶቻችንና መፃሕፍቶቻችን የሚፃፉት ይሄንን ፈሪሳዊ ላለመሆን በሚጥሩ ሊቆች በመሆኑ የበዛ ትህትና ሲቀርብልን ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል የ‹‹ዝክረ ነገር›› መፅሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹እኔም …፤ እዳዬን ለመክፈል ስል ያዋቂነትና የታሪክ ፀሐፊነት ችሎታ አለኝ በማለት አንዳች ትምክህት ሳላስገባ… ይህነን ‹‹ዝክረ ነገር›› የተባለ ስም የሰጠሁትን መፅሐፍ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ አዘጋጅቻለሁ›› ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ፡፡ ከዚህ አልፈው ማስታወሻ ማሰናዳት ‹‹ክፍሌና ትምህርቴ›› አይደለም በሚል ‹‹ትህትና›› እራሳቸውን ሊታዩ ከሚገባቸው መጠን በታች ያሳንሳሉ፡፡
…. ታዲያ አለቃ ተክለኢየሱስ ይሄን ነባር ‹‹ገራገራ›› እንደምን ተዳፍረው ዘለሉና (በጓደኛዬ ገለፃ እራሳቸውን ቆለሉ?) ነው ወይስ ነባሩን እራስን የማሳነስ ማስመሰል ጠልተው ለለውጥ አመፁ? እንዴት ደፈሩ?...
… እነዚህን ጥያቄዎች እርስ በእርሳቸው እያጋባሁና እያዋለድሁ መፅሐፉ እስኪወጣ ጠበኩ። አገኘሁት፡፡ በአንድ አቅጣጫ የተቀየደው ንባቤ፤ ከብዙ ‹‹እኔዎች›› ጋር እያገጣጠሙ፣ የጓደኛዬን ድምዳሜ እንዲያንዣብብኝ ሆንኩ፡፡ አለቃ ተክለኢየሱስ ገና መፅሐፍ የተፃፈበትን አቅድ በሚያስረዱበት መግቢያ ውስጥ እራሳቸውን በነባሩ ብሒል፤ ‹‹እኔ›› ሳይሆን ‹‹እሱ›› እያሉ ብዙ ማሞካሻ መሰል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ እንዲህ….
‹‹….. የአፄ ዮሐንስን ሊቄ መርአዊ፣ የአጼ ምኒልክን የዘጌው አፈወርቅ፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን መልአከ ፀሐይ ብሩ… ባጭር ባጭሩ ጎደሎ ታሪክ፣ ያውም ሐሰትና ውዳሴ ከንቱ የበዛበት ጽፈው ነበር። ነገር ግን ከዚያ ወዲህ ደግሞ አለቃ ተክለኢየሱ መርምሮ፣ የሁሉንም ታሪክ አይቶ በጎ በጎውን ንግግር ቀድቶ፣ ክፉ ክፉውን ንግግር በፀያፍ አውጥቶ ነቅፎ ለማስነቀፍ፣ ነውራቸውን ፅፎባቸዋል፡፡›› ይላሉ። በእርግጥም ደግሞ ሦስቱንም ታሪክ ፀሐፊዎች ነቅፈው የማስነቀፉ ሐይለ ቃል የተቀላቀለበት ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ በተለይ የዘጌውን አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ‹‹ለእለቱ እንጀራ ማውጫ ሊሰራበት›› እስከማለት ዝቅ ብለው ያዋርዳሉ! ታሪክ ፀሐፊዎቹን ከረመረሙ በኋላ በጉዝጓዙ ላይ እራሳቸውን እንዲህ አቆላምጠው ያስቀምጣሉ፡-
‹‹… ደግሞ በየነገሥታቱ ውስጥ በጎጃም ለተደረገው ታሪክ እንደ አለቃ ተክሌ ምርምረው ሙሉ ታሪክ አገናዝበው አልፃፉም፡፡ … አለቃ ተክሌ ግን ንጉሥ ተክለ ኃይማኖት ወዳጁ ነበርና ወረታውን ለመመለስ፣ ደግንነቱንና ቸርነቱን ለኋላ ልጅ ወሬ ለማቆየት፣ አመስግኖ ለማስመስገን፣ ከአሮጌ ልጅ ወገኛ፣ ከጀግና ልጅ አርበኛ፣ ዘምቶ ከአረጀ፣ በልቶ ካፈጀ፣ እየጠየቀ ከቀዳማዊ ራስ ኃይሉ እስከ ዳግማዊ ራስ ኃይሉ ድረስ በእውነት እንበላ ሐሰት ውዳሴ ከንቱ ሳይጨምር ታሪክ ፃፈ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደአለቃ ተክሌ አድርጎ በጎጃም ታሪክ የፃፈ ሰው አልተነሣም፡፡››
ልብ በሉ፤ እራሳችውን ነው እንዲህ የሚያቆለማምጡት፡፡ በውጭው አለም ‹‹CRITICAL APPRECIATION›› የተሰኘ ጥበብንና ጥበበኞችን ማቆላመጥ ላይ ያተኮረ የሒስ ዘርፍ እንዳለ ሰምቼ ነበር፡፡ አለቃ ተክሌ ከዚያም አለፍ ብለው ሌሎች የማቆላመጥ ሒስ እስኪሰሩባቸው አልጠበቁም፡፡ ‹‹እራሴን በራሴ፣ አፌን በምላሴ›› (Self Appreciational(?) ላይ ይጣዳሉ፡፡ እራሳቸውን ለመሳም እስኪዳዳቸው ድረስ እርቀው ይጓዛሉ፡፡ አለቃ ተክሌ፣ እነ አፈወርቅ ተክለኢየሱስ ነገሥታቱን ለማስደሰት ማሞገሳቸውን ነቅፈው፤ ብዙ ሳይርቁ ለራሳቸው ውዳሴ ከንቱ በማቅረብ ትዝብት ላይ ይወድቃሉ፡፡ ከታሪክ አፃፃፍ አንፃር ብቻ ሳይሆን በዋናው ሙያቸውም፤ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ረገድ ለራሳቸው የሚቆርሱት አንሶ አልተገኘም፡፡ እንዲህ…
‹‹…. ከቤተክህነት ጥበባቱን ሁሉ ፈፅመው ያወቁ አለቃ ተገኝ እና አለቃ ተክሌ ነበሩ፡፡ ንጉሱም ይወዳቸው ነበር ‹… ስለዚህ ሰራተኛው ሁሉ የጌጥ ሥራ ሲያምረው አዲስ አዲስ ጥበብ በየዓይነቱ ከአለቃ ተገኝና ከአለቃ ተክሌ ዘንድ ደጅ ጠንቶ፣ አቆላምጦ ይወስድ ነበር፡፡ ንጉሡም ለቤተ እግዚአብሔር  የሚሰጠው ለመስቀልና ለጽዋ፣ ለፅና፣ ለካህናቱ የሚሰጠው ለጸናጽል፣ ለመቋሚያ፣ ለጀግናው የሚሰጠው ላቢተዋና ለሸሆሮ፣ ለኮመድና ለቤነቻ፣ የንቅሉ ጥበብ ከነሱ ልብ ይፈላ (ይመነጭ) ነበር፡፡….. አለቃ ተክሌና አለቃ ተገኝ ከልባቸው ሥፋት፣ ከጥበባቸው ብዛት የተነሣ ሰው ያልያዘው በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያልተሰራ፣ አዲስ አይነት በድንጋይ ማኅተም የታተመ፣ መቋሚያና ጽናጽል ሰርተው… አበርክተው ነበረ፡፡››
አለቃ ተክሌ፤ እንደ አለቃ ተገኝ አይነቱ ለፍቅር ሲያቀርቡ፣ ከሙገሳም የሚያካፍሉትን ያህል የተቃረናቸውን ደግሞ በአቃቂር ዝብትልትሉን ለማውጣት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ወደ መፅሐፉ መገባደጃ ላይ በራስ ሐይሉ አስተዳደር አለቃ ተክሌ ገሸሽ ተደርገው፣ ሌላ ሰአሊ እንደተተካ ይናገሩና ሊቀጠበብት የተሰኘ ማዕረግ የተቸረው ብርሃኑ የተሰኘው ሰዓሊ፤ ‹‹በፎቶግራፍ ያየውን ማንሳት ነው እንጂ ከልቡ አንቅቶ ቤተክርስቲያን መሳል አይሆንለትም ነበረ›› ይሉታል። ይሄ አዲስ ተሿሚ ሰዓሊ፤ አለቃ ተክሌን ‹‹አንቱ›› ከማለት ወደ ‹‹አንተ›› ስለተሸጋገረ፣ ፀብ በመካከል ይነሣል። ስለዚህ በሽማግሌ ከምከሰው ባዋርደው ይሻለኛል ብለው የሙያ ጅል፣ የጠባይ ታናሽ ያላንተ የለም›› የሚል ስድብ እንደላኩበት ይገልፃሉ፡፡
የአለቃ ተክለየሱስ ‹‹የራስ ግምት›› የበዓሉ ግርማን የኪነት ሰው ድምዳሜ አስታወሰኝ፡፡ ‹‹በደራሲው›› ውስጥ ነው፡፡ ዋናው ገፁ ባህርይ ከሰብለ ጋር ስለ ደራሲው እስክንድር ሲያወሩ እንዲህ ይባባላሉ፡-
‹‹እራሱን ያመልካል መሰለኝ›› አለች በልዩ ልዩ አቀማመጥ የተነሳችውን ፎቶግራፎች እየተመለከተች፡፡
‹‹የኪነት ሰው አይደል ?››
‹‹ቢሆንስ ?››
‹‹የፈጣሪን ሚና ይጫወታል››
‹‹ታዲያ እግዜር እራሱን ያመልካል ልትለኝ ነው?››
‹‹እሱማ የሚያመልኩትን ፈጥሮአል››
ለበአሉ ግርማ የኪነት ሰው የሚያመልኩትን ፍጡሮች መፍጠር የተሳነው፤ እራሱን አምላኪ ነው። አለቃ ተክለኢየሱስም፤ ከታሪክ ፀሐፊነታቸው በላይ ሰዓሊና ቀራፂነታቸው፣ በዓሉ ለጠቀሰው ዕጣ-ፈንታ ሳይዳርጋቸው አልቀረም፡፡ ቢሆንም ይሄ ለእኛ እንጂ ለተቀረው ዓለም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደ ፈረንሳዩ ንጉስ Napoleon Bonaparte የተዘጋጀላቸውን ‹‹ዘውድ›› ከጳጳሱ ነጥቀው፣ እራሳቸውን ለራሳቸው ሥርዓትተ ንግሥ የሚያስፈፅሙ የኪነት ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጀርመናዊው ፈላስፋ Friedrich Nietzsche እራሱን የሚያወድስና የሚያንቆለጳጵስ አንድ መፅሐፍ አለው፡፡ Why I am so wise (ለምን በጣም ብልህ እንደሆንኩ) በሚል ርዕስ በ1908 ዓ.ም የታተመው ይሄ መፅሐፍ፤ ሦስት ምዕራፎች አሉት፡፡ ለምዕራፍ የሰጣቸውን ንዑስ ርዕሶችም ‹‹Why I am So wise››፣ ‹‹Why I am so Cleaver›› እና ‹‹Why I write such good books›› የሚል ነበር፡፡ መፅሐፉ በወጣበት ዘመን መነጋገሪያ የሆነ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ኒቼ ላይ በወቅቱ የደረሰው የመነጠልና የአእምሮ ህመም ተደራርቦ፤ መፅሐፍን እንዲፅፍ እንደገፋፋው ተደምድሟል፡፡ የእኛ አለቃ ተክለኢየሱስ ምክንያታቸው ምን ይሆን?... በእርግጥ ከዚህ ጋር አያይዞት እንጂ ዶ/ር ሥርግው ገላው የሚነግሩን አንድ የጥናት ውጤት አለ። አለቃ ተክለኢየሱስ በአብነት ትምህርታቸው እጅግ ደካማ ከሚባሉት የሚመደቡ እንደነበሩ፣ ለቅኔ ሆነ ለዜማ ትምህርት ሳይመጥኑ ቀርተው ወደ ስዕልና ቅርፃቅርፅ መዛወራቸው የበታችነት ስሜት አሳድሮባቸው ወደ ተቃራኒው ጥግ ገፍቷቸው ይሆን? አይታወቅም!...
… የሚታወቀው አለቃ ተክለኢየሱስ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት፣ እኛም እንድንደግምላቸው ግድ የሚለን ግሩም መፅሐፍ እንዳቀረቡልን ብቻ ነው፡፡ እንደ ናፓሊዮን በናፖርቴ፤ ከጳጳሱ እጅ ባይነጥቁም፤ ‹‹ዘውዱ›› ጭንቅላታቸው ላይ፤ መጥለቁ አይቀርም ነበር፡፡ ትንሽ ቸኮሉ ብለን እንለፈው?



Read 1206 times