Monday, 25 July 2016 09:44

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የልማት አጋርነት በተግባር ሲገለጽ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የበጎ አድራጎት ስራ በግለሰቦች መልካም የማድረግ ጽኑ ፍላጎትና ሃሳብ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ተግባር ሲሆን በሃገራችን ረጅም ታሪክ ያለዉና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የማንነት መለያ ዓርማ ሆኖ የሚያገለግል ሃብት ነዉ:: ይህ የበጎ ተግባር ስራ እንደግለሰቡ ወይም ተቋሙ አቅምና አጠቃላይ ይዘት የሚሰጠዉ የድጋፍ አይነት፤ ብዛትና መጠን ይለያያል፡፡ በመሆኑም ከትንሽ እስከ ትልቅ ከግለሰብ እስከ ተቋም በተለያዬ ሁኔታ ዉስጥ ለሚገኙ ድጋፍ ፈላጊዎች የተለያዬ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ምናልባትም በሃገራችን በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ድጋፎች በአይነትም በብዛትም በርካታ እንደሆኑ ቢገመትም ተቌማዊ ቅርጽ ያልያዙ ከመሆናቸዉ አንጻር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የድጋፉን አይነትና መጠን ለማወቅ ስለማይቻል ይህን ያህል ብሎ በቁጥር ለማስቀመጥ አዳጋች ይሆናል፡፡
ከዚሁ ስራ ጋር በተያያዘ በተለይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አሁን ባለንበት ዘመን ሰፊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚታመን ሆኖ አመሰራረታቸዉን ስንመለከት ቀደም ባለዉ ጊዜ ረሃብና ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ነፍስ የማዳን ተልዕኮ ይዘዉ በመንቀሳቀስ በርካታ ህይወት ማትረፍ የቻሉ ሲሆን ከድርቁ በመለስ መልሶ የማቋቋም ስራዎችንና ብሎም ዘላቂ የልማት ግቦችን በማንገብ የልማት ስራዎችን በስፋት ሲያከናዉኑ ቆይተዋል፤ አሁንም እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በ1965 ዓ.ም በወሎና ትግራይ ደርሶ በነበረዉ ከፍተኛ ድርቅ ቁጥራቸዉ በርከት ያለ መንግሰታዊ ያልሆኑ ዕምነት ተኮር ድርጅቶች የማይናቅ ተሳትፎ ከማድረጋቸዉም በላይ ለአሁኑ በሽህ የሚቆጠር የበጎ አድራጎት ድርጅት መፈጠር ምክንያት ነበሩ ለማለት ያስችላል፡፡ ከአስር አመት በኌላ እንደገና በ 1977 ዓ.ም ድርቁ በተመሳሳይ በወሎና ትግራይ አካባቢ በስፋት በመከሰቱ በወቅቱ እነኚህ ድርጅቶች ሰፊ ድጋፍ በማድረጋቸዉ ምንም እንኳ ብዙ ጉዳት ቢደርስም ችግሩን ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡
ከላይ በተገለጸዉ ሁኔታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሃገራችን ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን በተለይም ከደርግ ዘመን በኌላ በአዲሱ ህገ መንግስት የመደራጀት መብትን በመጠቀም በርካታ የሃገር ዉስጥና የዉጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መፈጠር ችለዋል:: ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ እነኚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተለይም ሃገራዊ የልማት ግቦችንና ዕቅዶችን በማገዝ የመንግስትና የህዝብ የልማት አጋር ሆነዉ የወጡበት ሂደት በግልጽ ይታያል:: በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ከ 3000 የሚልቁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚገኙ ሲሆን በአሰራር ስርዐት በርካታ ችግሮች ቢገጥሟቸዉም ችግሮቻቸውን ተቋቁመዉ በተለያዬ የልማት፤ የእርዳታና መልሶ ማቋቌም ስራ ላይ ተሰማርተዉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በተለይም በአሁኑ ሰአት አጠቃላይ የልማት ዕቅዳቸዉን አገሪቱ ካጸደቀችዉ ሁለተኛዉ የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በማጣጣም፤ የዕቅዱን ተፈጻሚነት በየጊዜዉ ከሚመለከታቸዉ የመንግስት መ/ቤቶች ጋር በቅርበት በመገናኘት በመገምገምና የማስተካከያ እርምጃ በመዉሰድ የልማት አጋርነታቸዉን የበለጠ ያሳዩበት ወቅት ቢሆንም ከሚያከናዉኑት ስራ አንጻር ሲታይ ለህዝብ ግልጽ መሆን ያለባቸዉ በርካታ ጉዳዮች ማለትም ከዉጭ ለጋሽ ድርጅቶች የሚያመጡት ገንዘብ፡ በሴክተሩ ዉስጥ ያለዉ የሰዉ ሃይል፡ እንዲሁም በተጨባጭ ለህዝብ የሚያደርጉትና ያደረጉት የልማት ስራ ጥቅል ይዘት ለማህበረሰቡ በሚፈለገዉ መጠን ታዉቌል ለማለት ያስቸግራል።
አንዳንዴም ከዚህ ባለፈ መልኩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይልቅ የግለሰብ መጠቀሚያና መክበሪያ ተደርገዉ የመታየታቸዉ ጉዳይ ህዝቡ የተዛባ አመለካከት እንዲይዝ ከማድረጉም ባሻገር የሴክተሩን ገጽታ የሚያበላሽና ጥላሸት የሚቀባ ሆኖ ይታያል፡፡
በዚህ  ጽሁፍ አዘጋጅ - የኢትዮጵያ በጎ አደራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ አመለካከትም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እጅግ ብዙ ዉጤታማ የልማት ስራዎችን የማከናወናቸዉን ያህል የተወሰኑት ደግሞ በጎ ባልሆነ ተግባር ዉስጥ ሲሳተፉ ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክም ሴክተሩ፤ በአጠቃላይ ተገዥ የሚሆንበትን የስነ ምግባር ደንብ በማዘጋጀትና በማጽደቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ይህም ጥረት በሴክተሩ ዉስጥ ተጠያቂነትን በማስፈን ግልጽ አሰራር እንዲሰፍን እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በሌላ ወገን ሌሎች ስራቸዉን በትጋትና በቅንነት የሚያከናዉኑትን በማበረታታት፤ ችግሮቻቸዉ ላይ በመወያየትና መፍትሄ በማፈላለግ የተቀላጠፈ የስራ ማዕቀፍ እንዲፈጠርላቸዉ መድረኩ በትጋት ይሰራል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በርካታ ስራ ቢሰሩም ድጋፋቸዉ ለህዝብ በቅጡ ያልታወቀ ከመሆኑ አንጻር የተለያዩ የመገናኛ ብዘሁንን በመጠቀም ስራዎቻቸዉን ለህዝብ ማሳወቅ ተገቢ  በመሆኑ ይህንኑ ስራ መስራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም በሃገራችን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምን ምን ድጋፍ እንዳደረጉ በተወሰነ መልኩ ከዚህ በታች በተቀመጠዉ ሁኔታ ለመግለጽ ጥረት ተደርጔል፡፡ ከዚህ በላይ በጥቂቱ ለማየት እንደተሞከረዉ በኢትዮጵያ የተለያዬ ይዘት ያላቸዉ በፌደራል ደረጃ ቁጥራቸዉ ከ 3000 የሚልቅ በክልል ደግሞ ከ 1000 የሚበልጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ይገኛሉ፡፡
በእነኚሁ መረጃዎች መሰረት በሃገራችን ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያተኩሩባቸዉ የልማት ስራዎች በቅደም ተከተል የሚከተለዉን ይመስላሉ፤ ጤና፤ የህጻናት ልማት፤ ትምህርት፤ ማህበራዊ ድጋፍ፡ አቅም ግንባታ፤ ገቢ ማስገኛ አካባቢ ጥበቃ እና እርሻ ስራ ይገኙበታል፡፡ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር በ 2012 በሃገሪቱ በአጠቃላይ 4904 ፕሮጀክቶች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥም 113 በአዲስ አበባ፤ 856 በኦሮሚያ፤ 621 በደቡብ፤ 610 በአማራ፡ 450 በትግራይ፡ 283 በአፋር፤ 267 በድሬዳዋ፤ 59 በቤንሻንጉል፡ 238 በሃረሪ፤ 237 በሶማሌ፤ እንዲሁም 170 ፕሮጀክቶች በጋምቤላ ክልል ተተግብረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉት የጤና ተቌማት ዉስጥ 7% ያህሉ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሙሉ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በተጨማሪም በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ሪፖርት መሰረት  እ.ኤ.አ በ2011፣ 1626 የጤና ፕሮጀክቶች እንደነበሩ የተጠቆመ ሲሆን ወደ 200 የሚጠጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በኤች አይቪ ኤድስ መቆጣጠርና መከላከል ስራ ላይ ተሰማርተዉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ ሪፖርት እ.ኤ.አ ከ 2004 እስከ 2007 ብር 575 ሚሊዬን ለዉሃ ስራ የዋለ ሲሆን ብር 3 ቢሊዬን ደግሞ በ 336 ፕሮጀክቶች ለእርሻና ተያያዥ ተግባራት ዉሏል፡፡ በተመሳሳይ በሃገሪቱ ካሉ 388 የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ዉስጥ 74 የሚሆኑት በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሙሉ ድጋፍና ቁጥጥር በስራ ላይ የሚገኙ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡                                          
በአመታዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፖርት መሰረት እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2011 ባሉት ጊዚያት ዉስጥ ብር 544,201,454.98 ለዉሃና ተያያዥ ስራዎች ብቻ ተመድቦ ስራ ላይ ዉሏል፡፡
በኢትዮጵያ ዉስጥ ቁጥራቸዉ ከ54 የሚልቅ ህብረቶችና ጥምረቶች ያሉ ሲሆን ለናሙናነት በክርስቲያን ልማትና ተራድዖ ማህበር ህብረት (ሲሲአርዲኤ) ሪፖርት መሰረት እ.ኤ.አ በ2011 10.8 ቢሊዬን ብር በ 320 አባል ድርጅቶች መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ አብዛሃኛዉ ገንዘብም ለምግብ ዋስትና፡ ልህጻናት ድጋፍና ለጤና አገልግሎት ስራ በቅደም ተከተል የዋለ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ከአንድ አመት በኃላ በ2012 በተጠናቀረ ሪፖርት ጥቅል ብር 11,841,356,007.87 ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ዉሏል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በተገኘ መረጃ መሰረት በ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 2007 ሙሉ አመትና 2008 – 10 ወር ጊዜ ዉስጥ (አንድ አመት ከአስር ወር ዉስጥ) ከ 2 ቢሊዬን ዶላር (40 ቢሊዬን ብር) በላይ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የዉጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለማግኘት ተችሏል፡፡ 

Read 3486 times