Monday, 25 July 2016 09:53

“የአተት መንስኤ የሽንት ቤት ፍሳሽ፣ ከወንዝ ጋር መቀላቀል ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

በአዲስ አበባ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) የነዋሪዎች ስጋት መሆን ከጀመረ ከወር በላይ አስቆጥሯል፡፡ በመዲናዋ ብቻ የተከሰተው ወረርሽኝ፣ ዋና መንስኤ የሽንት ቤት ፍሳሽ ከወንዝ
ጋር መቀላቀል ነው ብሏል - የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፡፡ በሽታው መጀመርያ የተከሰተው በኮልፌ ክ/ከተማ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከ10ሩም ክ/ከተሞች ታማሚዎች ወደ ህክምና ተቋማት
እየሄዱ መሆኑ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እስካሁን በበሽታው የሞተ አንድም ሰው የለም ቢልም አንዳንድ ነዋሪዎች ግን በአተት የሞተባቸው የቤተሰብ አባል እንዳለ ይናገራሉ፡፡
ለመሆኑ አሁን በሽታው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ወረርሽኙን የሚያባብሱት ምንድን ናቸው? መዲናዋ በተለያየ አቅጣጫ በቆሻሻ ክምር መሞላቷ ወረርሽኙን አያባብሰውም? የበሽታውን
ስርጭት ለመቀነስና ከእነአካቴው ለማጥፋትስ ምን እየተሰራ ነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ
ሂደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች

• በአዲስ አበባ ሳይነሱ የሰነበቱ የቆሻሻ ክምሮች ስጋት ፈጥረዋል
• ከ10ሩም ክ/ከተማ፤ታማሚዎች ወደ ህክምና ጣቢያዎች እየገቡ ነው
• ጥሬ ሥጋና ያልበሰሉ አትክልቶች መመገብ ተከልክሏል

በከተማዋ ለአተት በሽታ መከሰት ትክክለኛው መስኤ ምንድን ነው ?
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ የተከሰተው ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በሽታው ሰዎችን እያጠቃ ይገኛል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መንስኤው፤ ከመፀዳጃ ቤቶች የሚለቀቅ አይነ-ምድር ከወንዞች ጋር በመቀላቀሉ ምክንያት ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህን በአይነ ምድር የተበከሉ ወንዞችን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ንክኪዎች፡- በውሃ መልክ፣ በምግብ ወደ ሰውነታቸው ሲገባ፣ እየታመሙ ነው ያሉት፡፡ ዋናው መንስኤው የሽንት ቤት ፍሳሾች ከወንዞች ጋር መቀላቀላቸው ነው፡፡
በሽታው ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች ክልሎች አልተከሰተም?
ከአዲስ አበባ በፊት በውጭ አገር ማለትም በኬኒያ የተከሰተ ሲሆን በአገራችን ደግሞ በአርባ ምንጭ ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ ከሁለት ወር በፊት ነው። አርባ ምንጭ በሽታው እንደታየ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ወዲያውኑ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር የቆየው፡፡
ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት?
ለጤና ባለሙያዎች፣ ለጋዜጠኞች፣ ለክ/ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት፤ በበሽታው ምልክቶች ዙሪያ፣ ታማሚዎች፣ አካሚዎችና አስታማሚዎች ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ቅድመና - ድህረ ጥንቃቄዎች፣ የበሽታውን ምልክት ያዩ ታማሚዎች ወደየትኛው የህክምና ቦታ መሄድ እንዳለባቸው ---- ለማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ፣አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስልጠና ሲሰጥና ሲዘጋጅ ነው የቆየው፡፡ እንደተፈራውም ሰኔ 2 ቀን አዲስ አበባ ላይ ተከሰተ ማለት ነው፡፡
በአዲስ አበባ መጀመሪያ ህመሙ የተከሰተው የት ክፍለ ከተማ ነው? ምን ያህል ሰዎች  በበሽታው ተይዘው ነበር?
በሽታው መጀመሪያ የተከሰተው በኮልፌ ክ/ከተማ ሲሆን በበሽታው ተጠቅተው የነበሩት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ከአስሩም ክ/ከተማ ታማሚዎች ወደ ህክምና ጣቢያዎች እየገቡ ነው፡፡ ሁለቱ ሰዎች በሽታው ከተገኘባቸው በኋላ በከፍተኛ ደረጃ የመከላከል ስራ መስራት ነው የጀመርነው፡፡
ምን አይነት የመከላከያ ስራ ተከናወነ? ውጤታማነቱስ? ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሽታው እየተስፋፋ ቀጥሏል ተብሏል፡፡ የቆይታ ጊዜውም አልረዘመም?
የመጀመሪያ ስራችን በከተማ ደረጃ በከንቲባው የሚመራ ግብረ ኃይል ማቋቋም ነበር፡፡ ከዚያም በጤና ቢሮው የሚመራ ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቋመ። በቴክኒክ ኮሚቴው ስር ወደ ዘጠኝ ያህል ንኡሳን ኮሚቴዎችም አቋቋምን፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለ ድርሻ መስሪያ ቤቶች አብረውን እንዲሰሩ ካደረግን በኋላ ቀጥታ ወደ ስራ ነው የገባነው፡፡ የመጀመሪያና ዋና ስራችን ደግሞ ለህብረተሰቡ በስፋት ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ሆነ፡፡ በሽታውን ለመግታት ዋናው ዘዴ ማስተማር ነው፡፡
ሰሞኑን በከተማዋ የሚታየው የቆሻሻ ክምር ወረርሽኙን አያባብሰውም? ቆሻሻው እንዲነሳ ምን ያደረጋችሁት ግፊት አለ?
ትክክል ነው፡፡ ከአተት በሽታ መንስኤዎች አንዱ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት ነው፡፡ የአካባቢ ብክለት ሲባል ደረቅ ቆሻሻንም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻን ያካተተ ነው፡፡ ከደረቅ ቆሻሻ ጋር በተያያዘ በከተማ አስተዳደሩ “የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር” የሚባል ክፍል አለ፡፡ የግብረ ሀይሉ ኮሚቴ አባል ነው፡፡ ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ይህን የሚሰሩ አካላት በሰው ኃይልም በደረቅ ቆሻሻ ማመላለሻ መኪናም አቅማቸውን አጠናክረው፣ቆሻሻ ቶሎ ቶሎ ከከተማዋ እያነሱ እንዲያወጡ እየተደረገ ነው። ለምሳሌ በቀን 1.9 ሚሊዮን ኪ.ግ ቆሻሻ እያነሱ እንዳሉ ከእነርሱ ሪፖርት ማግኘት ትችያለሽ፡፡ ነገር ግን አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይደለም፡፡ ከራሳቸው አልፈው የግል ደረቅ ቆሻሻ ማመላለሻ መኪኖችንም ጭምር እየተጠቀሙ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ አሁንም በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ደረቅ ቆሻሻ ተከምሮ እያየን ስለሆነ የበለጠ ኃይል ማደራጀትና ቆሻሻውን ከከተማ ማስወገድ የግድ ነው፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ዝናብ ከዘነበ በኋላ ዋና መንገዶች በጥቁር ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች አለመጽዳት፣ለጎርፍም ሆነ ለጤና እክሎች መፈጠር አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ፍሳሽ ቆሻሻን በሚመለከት፣ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባለድርሻ አካል በመሆኑ አብሮን እየሰራ ነው፡፡ ቱቦዎች ይፀዳሉ፤ ነገር ግን ከተለያዩ ፋብሪካዎች፣ ከሆስፒታሎች፣ ከመኖሪያ ቤቶች ሽንት ቤቶች፣ ከሆቴሎች --- የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻዎች አሉ፡፡ ይሄ ነው ዋናው ችግር፡፡ ፋብሪካዎች በካይ ተረፈ ምርቶችን ይለቃሉ፡፡ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች ሆን ብለው ሽንት ቤታቸውን ከወንዞች ጋር ያገናኛሉ፡፡ ይሄ ቱቦዎች ቀድመው አልፀዱም አያስብልም፡፡ በእርግጥ ሆስፒታሎች የሚለቁት ፍሳሽ ሆን ተብሎ አካባቢን ለመበከል አይደለም፡፡ ሆስፒታሎች በአብዛኛው ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ በመሆኑ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ሲስተማቸው ያረጀና ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ነው፤በካይ ፍሳሽ ከወንዝ ጋር የሚቀላቀለው፡፡ ሆኖም ችግሩ መኖሩ ትክክል ነው፤ መንግስት በቀላሉ የሚያልፈው አይደለም፡፡
እስካሁን በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር በፌደራል ጤና ጥበቃም ሆነ በእናንተ ቢሮ ይፋ አልተደረገም፡፡ ነገር ግን በበሽታው ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሟቾች ቁጥር አለመገለጹ ህብረተሰቡ በሽታውን ችላ እንዲለው አያደርገውም?
እስካሁን በበሽታው የሞተ ሰው ሪፖርት አልደረሰንም፤ በበሽታው የሞተ የለም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች እንደ ኤችአይቪ፣ቲቢ ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎች ይኖሩባቸውና አተት ይዟቸው ቢሞቱ፣ አተት ገደላቸው ማለት አይደለም፡፡ በአተት ሞተዋል ለማለት ያስቸግራል፤ ምክንያቱም ሌላ ተጓዳኝ በሽታ የሌለበትና በወቅቱ በ24 ሰዓት ውስጥ ህክምና ቦታ የደረሰ የበሽታው ተጠቂ፣ በቀላሉ ታክሞ ወደ ቤቱ እየገባ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኤችአይቪ ገዳይ በሽታ አይደለም። በሽተኛው መድኃኒቱን በአግባቡ ከወሰደ ረጅም እድሜ ይኖራል፡፡ በአተት ተይዞ ቢሞት፣ እንዴት አተት አልገደለውም ይባላል? በተጓዳኝ በሽታ የሞተስ ለምን አይገለፅም? “ተጓዳኝ በሽታ” የሚለውን እንደ ሽፋን የተጠቀማችሁበት አያስመስልም?
ተጓዳኝ በሽታ ያለበት ሰው በአተት ተይዞ ቢሞት፣ በአተት ሞተ የማይባለው፣ሌላ ተጓዳኝ በሽታ የሌለበት ሰው በቀላሉ ስለሚድን ነው፡፡ በተጓዳኝ በሽታ የሞቱትስ ለምን ይፋ አይደረጉም ለተባለው፣ በሀኪሞች ተረጋግጦ የደረሰን የሞት ሪፖርት የለም እንጂ ልንሸፍንና ልንደብቅ የምንፈልግበት ምክንያት የለንም፡፡
ቢሮአችሁ፤ጥ ሬ ስጋ አትብሉ፣ ያልበሰለ አትክልት አትመገቡ… የሚል ማሳሳቢያ እየሰጠ ቢሆንም…ስጋ ቤቶችና አትክልት ቤቶች በጥሬ ስጋና ሰላጣ ተመጋቢዎች እንደተሞሉ ናቸው ... ይሄ ነገር አያሰጋችሁም?
እኛ ማስተማራችንን፣ ማስጠንቀቃችንን እንቀጥላለን፡፡ ህብረተሰቡ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ሲል ራሱን ይጠብቅ፡፡ አንድ ሰው ሲሞት የሚጎዳው ሟቹ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡም አገሩም ጭምር ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ማስተማርና የህክምና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ አንድ ሰው ለመጠንቀቅ፣ ሌላው እስኪሞት ወይም የሞተ ሰው ቁጥር እስኪነገረው ድረስ መጠበቅ የለበትም፡፡ እኛ በቢሮ ደረጃ፣ በፌደራል ጤና ጥበቃም በተለያዩ አጋጣሚዎች መልእክትና ትምህርት እያስተላለፍን ነው፡፡ ልብ ያለው ይጠንቀቅ፡፡ አይ አልሰማም ካለ ምንድን ነው የምናደርገው? በሽታው ገዳይ ነው፤ ጥንቃቄ ከተደረገ አይከሰትም፤ ከተከሰተም ቶሎ ወደ ህክምና በመሄድ በቀላሉ ይድናል፤ እያልን እያስተማርን ነው፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ይደረጋል፡፡ ማስታወቂያ ይለቀቃል፡፡ በመኪና እየዞርን በቅስቀሳ መልክ ህብረተሰቡን እያስጠነቀቅን ነው፡፡ ከእኛ በኩል ጎድሏል የምንለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሰው ቅድም እንዳልሺው፣ጥሬ ስጋ እየበላ ነው፡፡ ጥሬ አትክልት እየተመገበ ነው፡፡ ቢያንስ ይሄ ጊዜ እስኪያልፍ ጥንቃቄ ቢያደርግ ችግሩ ምንድን ነው፡፡
አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች፣የሽንት ቤት ፍሳሽ፣ከውሃ መውረጃ ቱቦዎች ጋር እንደሚያገናኙ ቅድም ነግረውኛል፡፡ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ በነዚህ ወገኖች ላይ፣ በተለይ በዚህ ወቅት ምን አይነት እርምጃ እየወሰደ ነው?
በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት ችግር ያለባቸው ሽንት ቤቶች፣ በግብረ ሀይሉ በአፋጣኝ እየተለዩ ነው። በየክፍለ ከተማው አንድ በአንድ ቤቶች እየተፈተሹ እየተለዩ ሲሆን የመጀመሪያው እርምጃ ፍሳሹ ከውሃ ቱቦው ጋር እንዳይገናኝ ማድረግ ነው፤ ቅድሚያ መስጠት ያለብንም ለዚሁ ጉዳይ ነው። ቀጥሎ ይህን ህገ ወጥ ተግባር ሆን ብለው ያደረጉ ግለሰቦች በህግ ይጠየቃሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወረርሽኝ ሰዓት፣ይህን አይነት ወንጀል መስራት ችግሩን ያከብደዋልና፡፡
አንዳንድ የከተማዋ ምግብ ቤቶች፤ ወጥ ቤታቸውና መጸዳጃ ክፍላቸው የተያያዘ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለአሁኑ ወረርሽኝም ሆነ ለዘለቄታው የጤና እክል ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ምን አስባችኋል ?
የምግብ ቤቶችን ደረጃ የማውጣትና የመቆጣጠር ስራ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሳይሆን የአዲስ አበባ የምግብ የመድሀኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ነው፡፡ እኛ በዋናነት የምንሰራው ትምህርት መስጠቱ ላይ ነው፡፡ እነሱም ቢሆኑ አሰራራቸውን እስከ ወረዳ ዘርግተው እየሰሩ ነው። በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በየመንገዱና በትንንሽ ኮንቴነሮች ምግብ የሚያቀርቡትም ቢሆን ምግብ አይሽጡ ሳይሆን ንፅህናውን የጠበቀ ምግብ ያቅርቡ ነው የሚለው፡፡ ሲደራጁ በመንግስት እቅድና በስራ ፈጠራ ዘርፍ የራሳቸው ሚና ስላላቸው ማለቴ ነው። ይህ ቢሆንም ንፅህናውን ያልጠበቀ ምግብ ለተጠቃሚ የሚያቀርቡ ከሆነ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ፤እንጂ ችላ ተብለው የሚታለፉ አይሆኑም፡፡
ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፤ለማህበረሰቡ የሚያቀርበው ውሃ፣ጤናማና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እናንተ ደግሞ ውሃ አፍልታችሁ ጠጡ እያላችሁ ነው፡፡ ሁለቱን ነገሮች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
እዚህ ላይ ጥሩ ሀሳብ ተነስቷል፡፡ ውሃ አፍልታችሁ ተጠቀሙ የምንለው፣ንጹህ የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚዎችን አይደለም፡፡ የተበከለ የምንጭ፣ የጉድጓድ ወይም የወንዝ ውሃ የሚጠቀሙትን ነው አፍልተው እንዲጠጡ እያስተማርን ያለነው። ቢቻል አኳታብስ፣ ውሃ አጋር የተባሉትን የውሃ ማከሚያዎች መጠቀም፣ ካልሆነ አፍልተው እንዲጠቀሙ እያስተማርን ነው፡፡ ከዚያ  ውጭ ከቧንቧ ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሰው የአዲስ አበባ ውሃ፣ከቦታው በደንብ በክሎሪን ታክሞ የሚሰራ ስለሆነ በዓለምአቀፍ የውሃ ደረጃ መሰረት፣የቧንቧ ውሃ ንጹህና ደረጃውን የጠበቀ ነው፤ምንም ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም፡፡ አንድ ልብ ልንል የሚገባው ነገር፣ የቧንቧ ውሃ  በጀሪካንና በበርሜል ተጠራቅሞ ሲቆይ፣ በጊዜ ርዝመት ምክንያት በውስጡ ያለው ክሎሪን የማከም አቅሙ ይቀንሳል፡፡ በዚህ ጊዜ በአኳታብስና በውሃ አጋር ማከም ተገቢ ነው፡፡ ሌላውና ትልቅ ችግር የሆነብን ነገር፣ ከቄራ ውጭ በየመንደሩና በየወንዙ ዳርቻ የሚካሄድ ህገ-ወጥ  እርዶች ናቸው፡፡ ህገ- ወጥ እርድ የሚያካሂዱ ሰዎች፣ ጨጓራ የሚያጥቡት በወንዝ ውሃ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወንዞች ተብክለዋል፡፡ ብዙዎቹ ታማሚዎች፤ እንዴት ጀመራችሁ ሲባሉ፣ “ዱለት በልቼ፣ ቁርጥ ስጋ በልቼ” እያሉ ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ ስለዚህ ማህበረሰቡ ከትክክለኛና ህጋዊ ቦታ የሚመጡ ስጋዎችን መጠቀም አለበት፡፡ ሲጠቀምም አብስሎ መመገብ አለበት፡፡ ቅጠላቅጠል ተመጋቢዎችም በሎሚና በአቼቶ በማጠብ፣አብስለው መመገብ አለባቸው፡፡
አሁን በብዛት ታማሚዎች ወደ ህክምና የሚመጡት ከየትኛው ክ/ከተማ ነው?
በሽታው መጀመሪያ የታየው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ አሁንም በብዛት ታማሚዎች የሚመጡት ከዚያው ነው፤ ይሁን እንጂ አስሩም ክ/ከተማ ላይ በሽታው ተስፋፍቷልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ከታማሚዎች እንደሰማነው----ለዚሁ በሽታ የተቋቋሙት 24 የህክምና ጣቢያዎች፣ የሚጠበቀውን ያህል አፋጣኝ ምላሽ እየሰጡ አይደለም፡፡ እውነት ነው?
አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ፤ የተቋቋሙትም ለዚሁ ዓላማና ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የህክምና ጣቢያዎች ብዙ ታማሚ ሲመጣባቸው፣ ስራ ይበዛባቸውና ታካሚዎች ወረፋ የሚጠብቁበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህንን መረዳት ያስፈልጋል። አፋጣኝ ምላሽ እየሰጡ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እንቆጣጠራለንም፡፡
በወንዞች ጤንነት ላይ ምን የታሰበ ዘላቂ መፍትሄ አለ?
ወንዞችንና የወንዞችን ጤንነት ጉዳይ በተመለከተ ሌላ አካላት አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ወንዞችም ሆነ አየሩ ሲበከል የሚጎዳው ማህበረሰቡም ነው፤አገርም ጭምር፡፡ ስለዚህ የማህበረሰቡን ጤና መጠበቅ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ወይም የጤናው ዘርፍ ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ባለድርሻ አካላትና አደረጃጀቶች በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ይፈጠራሉ፤ ድርሻቸውንና ሃላፊነታቸውን የማይወጡ ከሆነ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በየዘርፉ ሁሉም ሀላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡ በሽታውን በተመለከተ በግብረሃይሉ ውስጥ የተካተቱ ባለድርሻዎችም ስራቸው እየተገመገመ ነው፡፡ ውሃና ፍሳሽ ምን ሰራ? ቄራዎች ድርጅት ምን አከናወነ? ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር፣ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ምን ያህል እየተንቀሳቀሰ ነው? የሚለው፤በየሶስት ቀኑ በከንቲባው እየተገመገመ ነው፡፡ ውሃና ፍሳሽ ለምሳሌ የዛጉ የውሃ መስመሮችን በፍጥነት በማይካና በፕላስቲክ ቱቦዎች እየቀየሩ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡

Read 7518 times