Saturday, 30 July 2016 11:30

ኮንዶሚኒየም - “ለሴቶች” እና “ለመንግስት ሰራተኞች አድልዎ?

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(11 votes)

ለዓመታት ተጓተተ፤ ዋጋው ሦስት እጥፍ ሆነ እጣው ደግሞ በአድልዎ
   ባለፉት 11 ዓመታት 450 ሺ ቤቶች ተገንብተው፣ በሽያጭ ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ነበር የታቀደው፡፡ በየዓመቱ ከ40 ሺ በላይ ቤቶች መሆኑ ነው፡፡ በተግባርስ? አሁን የሚወጣው እጣ ተጨምሮበት፣ 180ሺ ቤቶች ናቸው ለነዋሪዎች ደረሱት (በዓመት 15ሺ ገደማ)፡፡
ከከተማዋ የቤት እጥረትና ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር፣ የቤት ግንባታው፣ በጣም ተጓትቷል፡፡ በአራት ዓመታት መከናወን የነበረበት ስራ፣ አስራ ሁለት ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ማለት ይቻላል ግን ደግሞ፣ ያኔ በከተማዋ የነበረው የመኖሪያ ቤቶች ብዛት፣ 240ሺ ብቻ እንደነበረ ሲታሰብ፣ የእስከዛሬው ግንባታ የሚናናቅ አይደለም ቢባል አይገርምም፡፡
በዚያ ላይ፣ የመንግስት እቅድ ከዓመት አመት መጓተቱ፣ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ መንግስት የገባበት ስራ፣ በዚያው መጠን ይንዛዛል፣ ይወሳሰባል፡፡ በኤሉክትሪክ ትራንስፎርመርና በቆጣሪ እጦት ሳቢያ፣ ከአንድ አመት በላይ ግንባታ ይጓተት የለ? እንዲያም ሆኖ፣ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት፣ የ85ሺ ቤቶች እጣ ወጥቶ እንደነበረ ስናስታውስ፤ ከዚያ ወዲህ የግንባታው ፍጥነት ቅንጣት እንዳልተሻሻለ መረዳት ይቻላል፡፡
ዛሬ እጣ የሚወጣላቸው ቤቶችኮ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ይጠናቀቃሉ ተብለው የነበሩ ናቸው፡፡ ምን ይሄ ብቻ? ከእነዚህ ጋር፣ ተጨማሪ ያኔ በ2006 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ የተባሉ 100ሺ ቤቶች፣ እስከዛሬ አልተጠናቀቁም ገና ‹ሂደት› ላይ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው አመትም አይደርሱም፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ የከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በእስከዛሬው ቀርፋፋ ፍጥነት ለመቀጠልም አስቸጋሪ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለኮንዶሚኒየም የተመዘገቡ 900ሺ ቤት ፈላጊዎችን በእቅዱ መሰረት እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ለማስተናገድ፣ በየዓመቱ ከመቶ ሺ በላይ ቤቶችን መገንባት … ፈፅሞ የማይታሰብ መሆኑን ለመግለፅ ፈልገው አይደለም፡፡ ይህንንማ ማንም ሰው ሊገምተው ይችላል፡፡ ሚኒስትሩ የገለፁት ችግር፣ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ ግማሽ ያህሉን የመገንባት አቅም እንኳ እንደሌለ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት፡፡ አቅም ቢኖር እንኳ፣ የመገንቢያ ቦታ አዘጋጅቶ ልናገኝ አልቻልንም ማለት ለፓርላማ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ መንግስት የግንባታ ቦታ የመስጠት ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ፓርላማው መፍትሄ እንዲያበጅ ጠብቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን የመፍትሄ ምልክት አልታየም፡፡ የግንባታ መጓተት ላይ፣ የመሬት ችግር ሲጨመርበት ምን እንደሚፈጠር አስቡት፡፡
ወደ ሦስት እጥፍ የኖረው ዋጋስ?
እንደ መንግስት እቅድ ቢሆን ኖሮ፤ የኮንዶሚኒየም ቤት ዋጋ የግንባታው፤ በአማካይ በአንድ ካሬ ሜትር አንድ ሺ ብር ይሆን ነበር፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የስቱዲዮ ዋጋ ከ25ሺ ብር እስከ 30ሺ ብር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባለ አንድ መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ደግሞ፣ 60 ሺ ብር ገደማ እንዲሆን ታቅዶ ነበር፡፡ ዛሬ የቤቶቹ ዋጋ ሶስት እጥፍ ሆኗል፡፡ የስቱዲዮ ሰማኒያ ሺ ብር፣ ባለ አንድ መኝታ ደግሞ 175 ሺ ብር፡፡ እና ከግንባታው መጓተት በተጨማሪ፣ መንግስትን የምናማርርበት ሌላ ምክንያት ተደረበብን ማለት ነው? ያው፣ የዋጋ ንረት ሲከሰት፣ ምን ማድረግ እንዳለብን መንግስት ራሱ አስተምሮናል፡፡ የሸቀጦች ዋጋ በናረ ቁጥር፤ መንግስት ምን እንደሚል እናውቃለን፡፡ “ስግብግብ ነጋዴዎች” በማለት የውግዘት መዓት ያወርዳል፡፡ የዋጋ ቁጥጥር መግለጫዎችን እያግተለተለ ገበያውን ያሸብራል፡፡ የሸማች ማህበራትን አደራጃለሁ እያለ፣ በከንቱ ጊዜንና ሀብትን ያባክናል፡፡ “አላግባብ ዋጋ ጨምራችኋል” እያለ የቢዝነስ ሰዎችን ያዋክባል፡፡ ወደ መቶ የሚጠጉ የግል ትምህርት ቤቶች፣ በዘመቻ እንዲከሰሱ ተደርጎ የለ? ይህንን ተከትለን፣ “ስግብግብ መንግስት፣ ዋጋ አናረብን” ብለን ብናወግዝ እንኳ፤ በመንግስት ላይ የዋጋ ቁጥጥር እያወጀና የሸማቾች ማህበር እያደራጀ ማን ያዋክበዋል? ማን ይከሰዋል?
ለነገሩ፣ ይሄ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ የዋጋ ንረት፣ በውግዘት፣ በቁጥጥርም ሆነ በክስ አይስተካከልም፡፡ የብር ኖት አለቅጥ በብዛት ሲታተም በዚያው ልክ የዋጋ ንረት ይፈጠራል፡፡ የብር ህትመትን አደብ ማስገዛት እንጂ፤ በብዛት የታተመው ገንዘብ ገበያ ውስጥ ከገባ እና ብር ከረከሰ በኋላ፤ የዋጋ ንረቱን በነጋዴዎች ላይ ማላከክ፤ አንድም አላዋቂነት ነው፤ አልያም ከቅንነት የራቀ ነውረኝነት ነው፡፡ ያው፣ የቤት ግንባታው ወጪና ዋጋም፣ ወደ  ሶስት እጥፍ መናሩ አይገርምም፡፡
የእጣ አድልዎስ?
መንግስት፣ በዜጎች መሃል፣ … በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በተወላጅነትና በዘር፣ በኑሮ ደረጃ ሰበብ፣ ልዩነትና አድልዎ ማድረግ እንደሌለበት በህገ መንግስት ውስጥ ተፅፏል፡፡ ግን፣ ይሄ በቂ መከራከሪያ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት፣ ለእያንዳንዱ አንቀፅ፣ ሌላ ተቃራኒ አንቀፅ እንዲኖረው ታስቦበት የተዘጋጀ ነው የሚመስለው፡፡ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለድሆች፣ ለሴቶች፣ ወደኋላ ለቀሩ የብሄር ብሄረሰብ አካባቢዎች፣ … ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚቀርብ፣ በበርካታ የህገ መንግስት አንቀፆች ላይ ተፅፏል፡፡
ለዚህም ነው፣ የኮንዶሚኒዬ እጣ ላይ፣ ሴቶች ከወንዶች በእጥፍ የሚበልጥ ድርሻ እንዲኖራቸው የተደረገው፡፡ ያው፤ አድልዎ ነው፡፡ ህገ መንግስትንም ይጥሳል ሊባል ይችላል፡፡ ግን ህገ መንግስትን አይጥስም ማለትም ይቻላል፡፡ አስገራሚው ነገር፣ ይህንን የሚተች የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎቹ፣ በአንድ በኩል፣ አድልዎ የሌለበት ፍትህን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አድልዎን እያጣቀሱ መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? ተቃራኒ ነገሮን እያቻቻሉ መቀጠል አይቻልም፡፡ አንዱ ሌላኛውን፣ አድልዎ ፍትህን እየዋጠው ይሄዳል፡፡ የኮንዶሚኒየም እጣ ላይ፤ ሴቶች ልዩ ድርሻ ያገኛሉ እንደተባለው፤ አሁን ደግሞ የመንግስት ሰራተኞችም ልዩ አድልዎ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
በጅምላ፣ ለሴቶች፣ ለወንዶች፣ ለመንግስት ሰራተኞች እየተባለ አድልዎን ማስፋፋት … እንዲያው ሌላው ቢቀር፤ ሴት ልጆችን የሚያሳድግ ወንድ የለም? ሴት ልጆቹ ያለ መኖሪያ እንዲቆዩ የሚፈረድባቸው በምን ምክንያት ይሆን? የመንግስት ሰራተኛ ከሌላው ዜጋ ተለይቶ፣ እንደ ጉዳተኛ ወይም እንደ ልዩ ፍጡር ታይቶ አድልዎ ይሰጠዋል የሚባልበት ምክንያትስ?
 

Read 4184 times Last modified on Monday, 01 August 2016 13:01