Saturday, 30 July 2016 11:37

እናት ተፈጥሮ ክፉኛ ተይዛለች

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

     የእናት ተፈጥሮ የአተነፋፈስ ስልተ ምት ልክ አይደለም፡፡ የሰው ዘር ቀኖናዋን አፋልሶ ምድራዊ ገሃነምን ዓይን አዋጅ ማድረግ ከጀመረ  ሰነባበተ፡፡ መልካም መዓዛዋ ተፈጥሯዊ ባልሆነ ጣልቃ ገብነት ምክነያት በጠያፍ ጠረን ተበክሏል፡፡ ለምለም ገጽታዋ ከል ለብሷል፡፡ ወንዞች፣ተራሮቿ በችግር አግጥጠው የጣዕረ-ሞት ድባባቸውን ያስተጋባሉ፡፡ እንዲህ ከተፈጥሮ ጋር የከረረ ጠብ ውስጥ የገባው የሰው ልጅ በማንአለብኝነት የሚወረውረው አንካሴ፣ ፊቱን መልሶ ከላዬ ላይ እየተሰነቀረ፣ ጣሩን በገዛ ፍቃዱ እያከፋው ይገኛል፡፡ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣በድርቅ ፣በውሃ ወለድና በዓየር ብክለት ምክንያት ያለ ዕድሜው የሚቀጨው የዓለማችን ዜጋ  ቁጥሩ ዕለት በዕለት እያሻቀበ ነው ፡፡
በ2010 በወጣ ሪፖርት፤ በቻይና ከዓየር ብክለት ጋር የተያያዘ ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ዜጋ ያለ ዕድሜው መቀጨቱ ተዘግቧል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት በአንድ ወገን ብቻ ተወስኖ የሚቀር ባይሆንም በተለይ እንደ አፍሪቃ ላሉ ታዳጊ ሃገራት የችግሩ ዓይነትና መጠን ከሃገራቱ አቅም በላይ ዘልቆ እንደሚሄድ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡
ምዕራባውያን የዘሩት አጥፊ አመለካከት
ምዕራባውያን ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ግብብነት በወረራ ዘይቤ የተበከለ ነው፡፡ ይህ አጥፊ አመለካከት አማክሎ - ሰብነት/Anthropocentrism/ ይባላል። ለእዚህ የተዛባ አመለካከት መንሰራፋት የጁዶ-ክርስትና ዕምነት አስተምህሮትና ዘመነ ኢንላይትመንት ትቶት የሄደው ፍልስፍናዊ አሻራ ተጠቃሽ ጥንስስ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የምዕራባውያን እምነት ወይም ፍልስፍናዊ አስተምህሮት፤ የሰው ልጅን ከፕራሚዱ ጫፍ ላይ ይሰቅላል፡፡ በአምላክ አምሳል የተፈጠረው የሰው ዘር፤ ምድር ያፈራቸውን ሲሳይ በሙሉ እንዳሻው የመቀራመት ስልጣን ተለግሶታል፡፡ እንስሳትም ሆኑ እጽዋት የሰው ልጅን ደስታና እርካታ ለማብዛት የተፈጠሩ እንጂ በራሳቸው የሚመነዘር እሴት ወይም/Intrisic value/ የላቸውም፡፡ የዘመናዊ ፍልሰፍና መሐንዲስ ዴካርት፤ እንስሳትን በተመለከተ ያስተጋባው አቋም ውሉን የሳተ ነው፡፡ እንስሳት ተንቀሳቃሽ  በድን፣ ኅልውናቸው በሰው ዘር ትከሻ ላይ የተንጠላጠለ ሥጋ ለባሽ ማሽን እንደሆኑ አድርጎ ነው የሚፈርጃቸው፡፡
“Non-human animals can be viewed as no more than machines with parts assembled in intricate ways. Based on Descartes ‘ rationale, humans have little responsibility to other animals or the natural world, unless the treatment of them affects other humans.”
እናት ተፈጥሮ በጉያዋ የታቀፈቻቸው አዕዋፋት፣እጽዋት፣ደኖች፣የዱር አራዊትና ሳር ቅጠሉ  ለንጉሱ የሰው ዘር እንዲያሸበሽቡ ስሪታቸው ግድ ይላቸዋል፡፡ የእነርሱ መኖር ያለ ሰው ዘር ምንም ነውና፡፡
ይህ አመለካከት እስከ 1960ዎቹ ድረስ በምዕራባዊያን ስነልቦና ላይ ናኝቶ ነበር፡፡የሰው ልጅን ከንግስናው መንበር ላይ በማቆናጠጥ፣ ሌላውን ፍጡር ተንበርካኪ የሚያደርግ የምራዕባዊያን እምነት፤ እናት ተፈጥሮን ከፉኛ እንዳራቆታት በአደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞገተው ሊይን ዋይት የሚባል አሜሪካዊ የአካባቢ ጥናት ፈላስፋ ነው፡፡ ከእርሱ ለጥቆ ብቅ ብቅ ያሉት የካከባቢ ጥናት ፈላስፎች፤ ታጅሎ የኖረውን የምዕራባዊያን ያልተገባ አመለካከት እርቃን በማስቀረቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የእነዚህ ሊኅቃን ብርቱ ጥረት ውሎ አድሮ ሥነምግባርን ከአካባቢ እውነታ ጋር ለንቅጦ ስለእናት ተፈጥሮ ጠብ እርግፍ በማለት የሚታወቀውን የፍልስፍና ዘውግ /Environmental Ethics/ በአዲስ ቁመና ሊወልድ ችሏል፡፡ ይህ የፍልስፍና ዘውግ የምዕራቡ ዓለም በተፈጥሮ ላይ ሲያራምደው የኖረውን መረን  የለቀቀ የአማክሎ - ሰብነት አቋም ቆም ብሎ እንዲያጤን የማያንቂያ ደውል ሆኖ አገልግሏል፡፡
የአፍሪቃዊያን እምነት
ሞጎቤ ራሞሴ “ፊሎሶፊ ስሩ ኡቡንቱ” በሚለው ድርሳኑ አማካኝነት አፍሪቃዊያን የእናት ተፈጥሮ የልብ ትርታን በማድመጡ ረገድ የተካኑ መሆናቸውን ያትታል፡፡ Motho Ke Motho Ka batho” የሲዎቶዎች ታዋቂ አባባል ነው፡፡ የአባባሉ ፍሬ ነገር እኔነቴ የሚታውቀው በአንተ ውስጥ ነው። እንደማለት ነው፡፡ ምልከታው አንድነትን፣የአርስ በእርስ ትስስርን ያውጃል፡፡ ይህ አይነት አተያይ የሀሉም አፍሪቃዊ ወግ እና ልማድ ነው፡፡ አፍሪቃዊያን እንደ ምዕራባውያን ተፈጥሮን በርብሮ የማራቆት ሱስ አልተጠናወታቸውም፡፡ከእዚህ ይልቅ ከአእዋፋት ዝማሬ፣ከነፍሳት ሲርሲርሪታ፣ከዛፎች ሿሿታ ጋር አብሮ ሐሴት ማድረግ፣ በሁሉም አፍሪቃዊ ልቦና ላይ የተፃፈ ሕግ ነው፤ ይለናል ራሞሴ፡፡
ይህንን ትንታኔ አንድ አንድ የምዕራቡ ዓለም ሊኅቃን በሙሉ ልብ ለመቀበል ይቸገራሉ። አፍሪቃዊያን ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ትስስር በአምክንዮ ፈንታ የባዕድ እምልኮ ትብታብ እንደ መርግ ተጭኖታል፡፡ ለአብነት ያህል “ቶተሚዝም” የሚባለውን ጥንታዊ እምነት ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡
 “ቶተሚዝም” በአንዳንድ አፍሪቃዊያን ብሔረሰብ ዘንድ ከአያት ቅድመአያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እምነት ነው፡፡ በእዚህ እምነት መሠረት የመጀመሪያው የብሔረሰቡ ተወላጅ  ከአንዱ የዱር አውሬ ወይም አእዋፍ ጋር መለኮታዊ ጥምረት እንዳለው ይታመናል፡፡ የዱር አውሬው ዝርያ ቀበሮ፣አንበሳ፣ነበር ወይም ድብ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህ መንፈሳዊ ዝምድና አለው ተብሎ የሚታሰበው የዱር አውሬ ዘር ማንዘር እንደ ቅዱስ እየተቆጠረ ይመለካል፡፡ መዋያ ማደሪያው ቤተመቅደስ ነው፡፡ በእዚህም ምክንያት መጠሊያው ደን ከመጨፍጨፍ ይተርፋል፡፡ ይህን መሰሉ ኋላቀር እምነትና ባህል  በአፍሪቃዊያን ልቦና ላይ ባረበበት ሁኔታ አፍሪቃዊያንን ለተፈጥሮ ባላቸው ስስነት ማወደስ ተገቢ አይደለም ይላሉ፤ ሊኅቃኑ፡፡
የምሥራቃዊያን ተሞክሮ
የቻይና ቀውላላ ሕንጻዎች ልክ እንደ ባቢሎዊያን ከሰማይ ውስጥ ለመሸሸግ የሚሽቀዳደሙ ይመስላሉ። ጫፋቸው ደመና ነው፡፡ ሰው ሠራሽ ደመና፡፡ ይህ ሰው ሰራሽ ደመና ፋብሪካዎች ወደ ከባቢ ዓየር በሚለቁት በካይ ጭስ ምክንያት የሚፈጠር  ነው፡፡ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ለዓለም ሙቀት መጨመር ያላቸው አስተዋፀኦ ከፍተኛ እንደሆነ ምንጮችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን የምሥራቃዊያን ፍልስፍናም ሆነ ዕምነት ስለ እናት ተፈጥሮ ያኖረው ምልከታ፤ ከምዕራባውያን ጋር ለየቅል ቢመስልም በተግባር እየተስተዋለ ያለው ነባራዊ እውነታ ግን አንዱ ከሌላው እንደማይሻል ይመሰክራል፡፡
እንደ ታኦዚምና ቡዲዝም ያሉ ታላላቅ እምነቶች፤ ከእናት ተፈጥሮ ጋር ተከባብሮ የሚኖርበትን መሐተም እንአሰሩ ከቅዱሳን መጽሓፍቶቻቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ የቡድሃ እምነት ተከታዮች ለትልልቅ ዛፎች ያላቸው ክብር ላቅ ያለ ነው፡፡የተበከለ አካባቢ ከተበከለ አእምሮ ይወለዳል፡፡ ሰላማዊ አእምሮ አካባቢውን በሰላም ይባርካል፡፡ ሰላምን ለማብዛት የመንፈስን ከፍታ እውን የሚያደርጉ ነፋሻማ ሥፍራዎች ላይ ተመስጦ ውስጥ መግባት አንዱ መላ ነው፡፡ መንፈሳዊ ከፍታ ያለ ሰላማዊ ከባቢ ዕውን መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ከእናት ተፈጥሮ ጋር ጠብ መፍጠር ካርማን ያወድላል፡፡ ካርማን ወደ  አማርኛ ስንመልሰው የዘሩትን ማጨድ እንደማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህን የመሰለ ከተፈጥሮ ጋር ቀናኢ ትሥሥር ያለው አስተምህሮት በምሥራቃውያን ዘንድ ቢታወቅም፣ አንደ ጃፓንና ቻይና ያሉ ሀገራት ለዓለም ሙቀት መጨመር ያላቸው ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡
የእኛው ገመና
ኢትዮጵያ ሀገሬ ጋራው ሸንተረሩ፣
መስክሽ መለምለሙ፣
ወንዞችሽ ማማሩ ………….
አሁን አሁን እነዚህ ውስጣዊ ልምላሜን የሚፈጥሩ ስንኞች ዕጣ ፈንታ፣ ከዜማ ማድመቂያ የዘለለ ትርጉም ያላቸው አይመስሉም፡፡ በሀገራችን በየማዕዘናቱ እየተስዋለ ያለው የአካባቢ መራቆት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ትናንት ግርማው የሚያስፈራው ሀረማያ ሐይቅ፤ የተነጠፈበት መሬት ጠብታ ውሃ የሰማይ ያህል ርቆት፣ ጦሙን ውሎ ማደር ከጀመረ ከራረመ ፡፡ የሃገራችንን ቆዳ ከሩብ እጅ የላቀ ክፍል የሚሸፍነው ደን ዛሬ ወደ ኩርማን ቁጥር አሽቆልቁሏል፡፡
ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ፊታችን መለስ ስናደርግ፣ የችግሩ ስፋትና መጠን  ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት እየጎለበት እንደሄደ በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡
ሸገር አዲስ ከጥቂት አስርተ ዓመታት ቀደም ብሎ በሠራ አከላቷ የሚሰራጩት ወንዞች ፀዳል፣ አላፊ አግዳሚውን በጥቅሻ የሚጣሩበት አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል ነበራቸው፡፡ አሁን ያ ሁሉ ተረት ሆኗል፡፡ የጠለሸ ገጽታቸው፣ ከሩቁ ከሚገፋተር ጠረናቸው ጋር ተደምሮ፣ የከተማዋን እድፍማነት አደባባይ አውጥተውታል፡፡ ከሰሞኑ የሸገር አዲስን ነዋሪ  እያመሰ የሚገኘው የአተት ወረረሽኝ፣ ከእዚሁ ከወንዞች ብክለት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ባለሙያዎች አስረግጠው እየተናገሩ ነው፡፡ በከተማዋ የፓርኮችን ብዛት ለመቁጠር ብንሻ አንድ እጃችን ላይ ባሉ ጣቶች ቆጥረን እንጨርሳቸዋለን፡፡ መንፈስ የሚያለመልሙ ዛፎች ወድመው በመቃብራቸው ላይ ከአካባቢ ዓየር ንብረት ጋር ጠብ ያላቸው ጉልቤ ፎቆች ይቀለሳሉ፡፡ በእዚህ መንገድ ተፈጥሮን መበደላችንን እስከቀጠልን ድረስ በሠፈርነው ቁና መሠፈራችን የማይቀር ነው፡፡
ውሉ የጠፋው የመፍትሄ አቅጣጫ
በቅርቡ በፈረንሳይ በተካሄደው ጉባኤ፣ የዓለምን ሙቀት መጠን እስከ 2 ዲግሪ ሴንትግሬድ፣ ከተቻለም 1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ድረስ ለማውረድ የዓለም መንግሥታት ቃልኪዳን መግባታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህን ቃልኪዳን ግን እዚያው ወረቀት ላይ እንዲቀር የሚያደርጉት በርካታ ተግዳሮቶች ከፊት ለፊቱ ተጋርጠዋል፡፡ ውጤታማነቱ በሀገሮች መልካም ፍቃደኝነት ላይ መመስረቱ ነገሩን የበለጠ አዙሪት ውስጥ ይከተዋል፡፡ እንደ ጸጥታው ምክር ቤት ጥርስ ያለው ፈጻሚ አካል ይቋቋም እንኳን ቢባል የችግሩ ሽል የተበጃጀው በበለጸጉት ሃገሮች ነው፡፡ አሜሪካና ቻይና ለዓለም ሙቀት መጨመር ያላቸው አስተዋፅኦ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ታዲያ እነዚህን የዓለማችን ቁንጮ ሀገ ራት  ፊት ነስቶ የሚቋቋም ድርጅት ምን አይነት ፍሬ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የመፍትሄውን አቅጣጫ ውሉን የሚያጠፋው ይሄ ነው፡፡
የሰው ዘር ከተፈጥሮ ጋር እርቅ የሚፈጽምበት አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ደርሷል፡፡ ምርጫው ያለው በእጁ ነው፡፡ ከእናት ተፈጥሮ ጋር እርቅ አውርዶ በማዕዷ በረከት መቀደስ አልያም በለመደው ሞገደኛ ባህሪው እርቁን ገፍቶ  የተፈጥሮን መርገም መቀበል!!

Read 1609 times