Saturday, 30 July 2016 11:38

የመሰለ መንግስቱ ልጆች ሰርግ በቀጥታ ስርጭት መተላለፉ አነጋጋሪ ሆኗል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

በ“ኦያያ መልቲ ሚዲያ” ስር የሚተዳደረው የብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ሬዲዮ መሥራችና ባለቤት ዕውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱ፤ ባለፈው እሁድ ሁለት ልጆቹን ካዛንቺስ በሚገኘው ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በደመቀ ድግስ ድሯል፡፡ የሰርጉ ስነ-ስርዓትም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 በብስራት ኤፍ ኤም በቀጥታ ስርጭት ከሆቴሉ ሲተላለፍና ሰርጉን ስፖንሰር ያደረጉ ድርጅቶችም ሲተዋወቁ አምሽተዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ መሰለ የልጆቹን ሰርግ ለ4 ሰዓት በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፉ ተገቢ ነው? ዝነኝነቱ ይሄን አይፈቅድለትም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን፣ ከምሁራንና ጋዜጠኞች አስተያየቶችን አሰባስበናል፡፡  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጉዳዩ ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር፣ ከማህበራዊ ፋይዳውና ከአድማጮች መብትና ፍላጎት አንፃር እንዴት ይታያል … የሚለውን እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡ የጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱን አስተያየት ሬዲዮ ጣቢያው ድረስ በመሄድ ለማካተት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በማንኛውም ጊዜ ምላሽ ካለው ልናስተናግደው ዝግጁ ነን፡፡

“ህዝቡንም ሙያውንም መናቅ ነው”
አንድ ጉዳይ በሬድዮም ይሁን በቴሌቪዥን ሲሰራጭ ማህበራዊ ፋይዳው ምንድነው የሚለው መለካት አለበት፡፡ ለምሳሌ የአትሌት ገዛኸኝ አበራ ሰርግ፤ ከስቴዲዬም የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በቴሌቪዥን አግኝቶ ነበር፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? ምንስ ጥቅም ነበረው? ስንል፤ አንደኛ ገዛኸኝ አበራም ሆነ ባለቤቱ የኦሎምፒክ እውቅ አትሌቶች ናቸው፡፡ ሁለተኛ በሰርጉ እለት 500 ሜትር በሚረዝመው የሙሽራ ቬሎ ላይ ኤድስን በመከላከል ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥር ግልፅ መልዕክት ያለው ፅሁፍ ተፅፎ ከኋላ የተቀጣጠለ ቬሎ እየተነቀለ የተፈለገው መልዕክት ለህዝብ ደርሷል፡፡ ወደ መሰለ ልጆች ሰርግ ስንመጣ፣ በቀጥታ መተላለፉ ለህብረተሰቡ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ አይመልስም፡፡ ለምሳሌ 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን የሚያከብሩ ቢሆኑ ስለ ፍቅር፣ በመቻቻል አብሮ ስለ መኖር፣ ስለ ፅናት ለተከታዩ ትውልድ የሚያስተምሩት ነገር ትልቅ ይሆናል፡፡ ለዜናም ይመጥናል (Newsworthy) የሚለውን ነገር ያሟላ ነበር፡፡ የዜና መመዘኛ የምንለው ለምሳሌ ለማህበረሰቡ የሚያመጣው በጎ ተፅዕኖ፣ የተለየ ነገር ነው ወይ? ወቅታዊነቱ… የሚሉት በጋዜጠኝነት መስፈርት የተቀመጡትን ነገሮች ያካትታል፡፡ ስለዚህ በመሰለ መንግስቱ ልጆች ሰርግ ውስጥ እነዚህ መስፈርቶች አሉ ወይስ ሬዲዮ ጣቢያው የራሱ ስለሆነ ነው? የሚለው ጥያቄ ይነሳና፤ ከላይ የተቀመጡ ነገሮች ከሌሉ፣ ህዝብ እንዲገለገልበት የተሰጠውን የሬዲዮ ጣቢያ ስለሚያስተዳድር ብቻ ውድ በሆነው የአየር ሰዓት አላጋጠ ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ሞትን ብንወስድ በዙሪያችን በየዕለቱ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ የሁሉም ሰዎች ሞት በዜና አይቀርብም ነገር ግን ለአገር ውለታ የዋሉ ታዋቂ ሰዎች፣ የጥበብ ባለሙያዎች ሲሞቱ በዜና መልክ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ አባተ መኩሪያ ሞተ ተብሎ በሬዲዮም በጋዜጣም ቀርቧል፡፡ ትልቅ ዜና ነው፡፡ ግን አባተ መኩሪያ ማን ነው? ምን ሰራ? የሚለው ነው ዜና ያደረገው፡፡ ወደ መሰለ ልጆች ስንመጣ፤ ከብስራት ሬዲዮ ውጭ ያሉ ሌሎች ጣቢያዎች ሲያስተላልፉት ነበር ወይ? አላስተላለፉትም፡፡ የራሱ ሬዲዮ ጣቢያ ስለሆነ ብቻ የልጆቹን ሰርግ አራት ሰዓት ሙሉ ማስተላለፍ ህዝቡንም ሙያውንም መናቅ ነው፡፡ እንዲያውም ዜና የሚሆነው የሬዲዮ ፕሮግራሙ ስለተሰጠው ብቻ የግል ጉዳዩን በቀጥታ ለህዝብ ማስተላለፉ ነው፡፡
ተሻገር ሽፈራው፤ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

“የአየር ሰዓቱ የህዝብና የአገር ነው”
አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ወይም የግል ጋዜጣ በግለሰብ ስም ፈቃዱ ይውጣ እንጂ የአገርና የህዝብ ንብረት ነው፡፡ ለምሳሌ “አዲስ አድማስ” ንግድ ፈቃዱ በአንድ ግለሰብ ስም ወጥቶ ሊሆን ይችላል፤ የሚገለገልበት ግን ህዝብ ነው፡፡ አንድ የሬዲዮ አዘጋጅ ከዚህ ቀደም በሌላ ጣቢያ ላይ ሚስቱ ስትወልድ ስለ ሚስቱ አወላለድ፣ ስለ ልጁ ሲያወራ ነበር፡፡ የመሰለ ልጆችን ሰርግ የቀጥታ ስርጭት ያህል ባይሰፋም ማለት ነው፡፡ ይሄ ከግንዛቤ እጥረት ወይም ያቺ የአየር ሰዓት የኔ ናት ብሎ ከማሰብ የመጣ ነው፤ ግን አግባብ አይደለም፡፡ የልጆቹን ሰርግ አራት ሰዓት ሙሉ በቀጥታ ስርጭት ያስተላለፈው መሰለ መንግስቱ፤ የሬዲዮ ፈቃዱን በስሙ ቢያወጣም አየሩ ግን የህዝብና የአገር ነው፡፡ እንኳንስ የአየር ሰዓቱ፣ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሚገባው ገንዘብ እንኳን የአገር ገንዘብ ነው፡፡
በየኪሳችን ያለው ገንዘብ የግላችን ብቻ አይደለም፡፡ ሚዲያ ደግሞ ይበልጥኑ የህዝብ ጉዳይ የሚስተናገድበት ነው፡፡ በቀጥታ ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆንም የንጉሱ ልጆች ሰርግ ለህዝብ ይቀርብ ነበር ይባላል፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ ልጃቸውን ድረዋል፡፡ በፌስቡክ ሰምቻለሁ፤ ነገር ግን በቴሌቪዥን አሊያም በሬዲዮ በቀጥታ ይተላለፍ ቢባል የአገር ውድቀት መሆኑን ነው የማየው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲወጡ ሲገቡ ሁሉ ነገር ይዘገባል፤ ምክንያቱም እርሳቸው የአገር መሪ ናቸው፤ ስማቸውም የአገር ነው፡፡ የልጃቸው ጉዳይ የግል ጉዳያቸው ነው፤ ስለሆነም ከፌስቡክ ባለፈ የትኛውም የሬዲዮ ጣቢያም ሆነ ቴሌቪዥን ላይ አልሰማሁም፡፡ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት፤ ሌሎች ፕሮግራሞችን አጥፎ፣ የልጆቹን ሰርግ በቀጥታ ሲያስተላልፍ ከዋለ በኋላ በቀጣይ አፉን ሞልቶ፤ “ጣቢያው የህዝብ ነው” ማለት ይችላል ወይ ነው ጥያቄው? “ተወዳጁ ብስራት ኤፍ ኤም” እየተባለ ነው ጣቢያው የሚጠራው፡፡ ተወዳጅነቱ በምንድን ነው? የሚለካው በማን ነው? የሚወደደውስ? ስለዚህ ትክክል አይደለም፡፡
የውጭም ሆነ የአገራችን ታዋቂ ሰዎችን ሰርግና ሌሎች ጉዳዮችን እንዘግብ የለም ወይ ምን ችግር አለው? የሚል ጥያቄ አንስተሻል አዎ እንዘግባለን፡፡ ለምሳሌ የቴዲ አፍሮ ሰርግ ፊት ለፊት ገፅ ላይ መውጣት አለበት ወይ ብትይኝ፣ አዎ መውጣት አለበት፡፡ ጥላሁን ገሰሰ ላይ የደረሰ ችግር ወይም የጋሽ ማህሙድ አህመድ የልደት በዓል ፊት ለፊት መውጣት አለበት ወይ? ግጥም አድርጎ ይወጣል፡፡ ቴዲ አፍሮ አሊያም ጋሽ ማህሙድ ልጁን ሲድር፣ በቀጥታ ስርጭት መተላለፍ ይችላል ወይ ወይም ፊት ለፊት ገፅ ላይ መውጣት አለበት ወይ ካልሽኝ፣ አግባብ አይደለም፡፡ ልዩነቱን አየሽው?! የጠቅላይ ሚኒስትሩን አይነት ጉዳይ ነው፡፡ እነ ቴዲ፣ እነ ማህሙድ የህዝብ ሀብት ናቸው፡፡ ስለነሱ ሲዘገብ አድናቂያቸው ህዝብ በመሆኑ ደስ ይለዋል፤ ተገቢ ነው፡፡ ወደ መሰለ መንግስቱ ስንመጣ፤ አንደኛ እሱ አይደለም ያገባው፡፡ ሁለተኛ ሌላ ፕሮግራም ታጥፎ ይህን ያህል ሰዓት በቀጥታ የልጆቹን ሰርግ ማስተላለፉ ለማህበረሰቡ የሚጠቅመው ምንድን ነው? ሁለተኛ በራሱም ሬዲዮ ይሁን በሌሎች ጣቢያዎችና ጋዜጦች፤ “ልጆችህን ስለዳርክ እንኳን ደስ ያለህ” ተብሎ የተወሰነ ሽፋን ቢሰጠው፤ ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን የሌሎችን ፕሮግራም አጥፎ፣ ይህን ሁሉ ማድረጉ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ብስራት ላይ በዛን ሰዓት የሚተላለፍ ፕሮግራም ቢኖረኝ፣ በምን ስነ - ምግባር ነው፤ “ነገ የልጄ ሰርግ ስለሆነ እንዳትመጣ” የሚለኝ፤ ይሄ እኮ ድሮ ት/ቤት እያለን፣ ዛሬ የመምህራን ስብሰባ ስላለ ት/ቤት እንዳትመጡ እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ በእውነት በጣም ያሳዝናል፡፡
(ስሙን ያልገለፀ ታዋቂ ጋዜጠኛ)

“የሬዲዮ ጣቢያው የህዝብ ንብረት ነው”
የግል ሬዲዮ ጣቢያ፣ የህዝብ ሬዲዮ ጣቢያና የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ የሚባሉት ሚዲያዎች በዋናነት የሚቋቋሙት ለህብረተሰቡ በቂ መረጃና የውይይት መድረክ እንዲሆኑ፣ አገራዊ ጉዳዮችን፣ ትምህርት ነክ የሆኑ ሀሳቦችን እያነሱ ማህበረሰቡን በማንቃት፣ አገር እንዲያገለግሉ ነው፡፡ ከመረጃ ማቀበልና ከማስተማር ባለፈም የማዝናናት ሚናም እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ግባቸው ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ የጋራ የሆነ ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን፣ በሰላም ጉዳይና በልማት ላይ በማተኮር፣ ለአጠቃላይ አገሪቱና ህዝቧ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት አስተዋፅኦ ማበርከት ነው፡፡ ይህ በዋና አላማነት በብሮድካስት አዋጅ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አላማና ግብ ስንነሳ፣ በብስራት ኤፍ ኤም ሬዲዮ እሁድ ዕለት የተከናወነው ነገር ፈፅሞ ህገ ወጥና ከብሮድካስት አዋጁ የሚቃረን ስራ ነው፡፡ ፕሮግራሙን ተከታትየዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ስራ ሲሰራ፣ ይሄ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በሌላ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የአንድ የሬዲዮ ባለቤት ቤተሰብ ሞቶ፣ የሀዘን የዘገባ ሽፋን ተሰጥቶ ነበር፡፡ ይሄ ነገር ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየሄደና የሬዲዮ ፈቃድ ያገኙ ግለሰቦችም በማናለብኝነት እየፈፀሙ ያሉት ህገ ወጥ ተግባር ነው፡፡ እሁድ ዕለትም ሶስት አራት ቋሚ ፕሮግራሞች ታጥፈው ለአራት ሰዓት ያህል የልጆቻቸው ሰርግ በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ሰምተናል፡፡ በሬዲዮ ጣቢያ ባለቤቶች ላይ እያየን ያለነው መጥፎ ዝንባሌ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን የብሮድካስት አዋጁ አይፈቅድም፤ ምክንያቱም የሬዲዮ ሞገድ የህዝብ ንብረትና ሀብት ስለሆነ ነው፤ በህዝብ ሀብት ላይ ለህዝብ የሚጠቅም አገራዊ፣ ማህበራዊ ጉዳይ መተላለፍ ሲገባው የግል ሀዘን፣ የግል ሰርግና መሰል የግል ጉዳዮች የሚስተናገዱ ከሆነ፣ ከህዝብ የሚቃረንና ህጉንም የጣሰ በመሆኑ በእጅጉ አዝነናል፡፡ የሬዲዮ ጣቢያዎቹ በንግድ በግለሰብ ስም ቢወጡም፤ ንብረትነታቸው የህዝብ ነው፡፡ የሬዲዮ ሞገዱ ለምሳሌ ኤፍኤም 101.1 የምንለው ስም፤ የህዝብ ንብረት ስለሆነ፣ ይሄንን ለግል ጉዳይ ማዋል ህገ-ወጥነት ነው፤ መስተካከልም አለባቸው፡፡ እንዲህ አይነት ስህተቶችና ህገ-ወጥነቶች ሲፈፀሙ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የብሮድካስት አዋጁ በግልፅ ባስቀመጠለት መመሪያ መሰረት፤ እርምጃ ይወስዳል፡፡ በዚሁ መሰረት እኛም ጉዳዩን እያየነው ስለሆነ በቅርቡ እርምጃ እንወስዳለን ማለት ነው፡፡
አቶ ልዑል ገብሩ (በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጁ)
 
“በቀጥታ ስርጭት የተላለፈው የጣቢያው 2ኛ ዓመት በዓል ነው”
በእለቱ በዋናነት በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ የነበረው የሬዲዮ ጣቢያው ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንጂ ሰርጉ አልነበረም፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የታደሙት በሬዲዮ ጣቢያው ላይ በተባባሪ አዘጋጅነት የሚሰሩና የጣቢያው ሰራተኞች ነበሩ፡፡ በቀጥታ ሲተላለፍ የነበረውም ሬዲዮ ጣቢያው በሁለት ዓመት ውስጥ ያከናወናቸው ስራዎች፣ ያመጣቸው ውጤቶችና የገጠሙት ፈተናዎች ምንድን ናቸው? የሚሉት ነበሩ፡፡ ተባባሪ አዘጋጆች ማለትም በጣቢያው የአየር ሰዓት ወስደው የሚሰሩት እንዴት ራሳቸውን አጠናክረው መቀጠል ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ነበር እንጂ በዋናነት የመሴ ልጆች ሰርግ ላይ ትኩረት አልተደረገም ነበር፡፡ ይህንን የቀጥታ ስርጭቱን ቅጂ አግኝተሽ ማዳመጥና መመዘን ትችያለሽ፡፡ እርግጥ ነው ሰርግ ነበር ግን ዋናው ፕሮግራም ሰርጉ አልነበረም፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ክስተቶች ናቸው ሰፊ ሽፋን ያገኙት፡፡
(ስማቸውን ያልገለፁ የጣቢያው ጋዜጠኞች)

“ጥሪው ብስራት የተመሰረተበትን 2ኛ ዓመት እናክብር አይልም”
የጥሪ ካርዱ “የልጆቼ ሰርግ ላይ ታድማችሁ የደስታዬ ተካፋይ ሁኑ” እንጂ ብስራት የተመሰረተበትን ሁለተኛ ዓመት እናክብር የሚል አይደለም፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንደ ሽፋን ነው የተወሰደው፡፡ ፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብ፣ ታደለ ሮባ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ዳን አድማሱ፣ ታደለ ገመቹ፣ ማሚላና ኪቺኒ … ሌሎችም ታዋቂ አርቲስቶች ተገኝተው ዘፍነዋል፡፡ እቦታው ላይ የተመደቡ ጋዜጠኞች፤ አርቲስቶችንና ታዋቂ ሰዎችን፣ “እዚህ ሰርግ ላይ በመገኘትህ ምን ይሰማሀል?” አይነት ጥያቄ በቀጥታ አየር ላይ እያስገቡ ሲጠይቁ እቦታው ላይ ነበርን፡፡ በዚህ መሀል ስለ ሬዲዮ ጣቢያው የተነሳ አንድም ነገር የለም፤ ስርጭቱን ፈልጎ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ በዚህ መሀል “የጥበብ ብልጭታ”፣ “ዘመን ተሻጋሪ”፣ “ቡና ጠጡ” የተባሉ ቋሚ ፕሮግራሞች ታጥፈዋል፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ይከበርስ ቢባል፣ አራት ሰዓት ሙሉ በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ ተገቢ ነበር ወይ? በዚያ ላይ የተደገሰበት ሆቴል ኢንተርኮንቲኔንታል፣ የሰርጉን አጠቃላይ የቪዲዮ ስራ የሚሰራው ጆኒ ቪዲዮ፣ መኪናውን ስፖንሰር ያደረገው የዬቱ ሰቨን የመኪና ኪራይ … እነዚህ ሁሉ ከሰርጉ ጋር በተያያዘ ሲተዋወቁ ዋሉ እንጂ ስለ ሁለተኛ ዓመቱ የተባለ ነገር የለም፡፡ በመጨረሻ ያየነው ነገር ቢኖር፣ ሰርገኞቹ ማለትም ሙሽሮቹና አጃቢዎቻቸው ብስራት ኤፍ ኤም ህንፃ ጋር ሄደው ፎቶ መነሳታቸውን ነው፡፡ በቃ ይሄ ነው፡፡ ይህንን በሰርጉ ላይ ታድመን ተመልክተናል፡፡ እንደ ጣቢያው ሰራተኝነታችንና እንደ ጋዜጠኝነታችን በጣም አዝነናል፤ አንገታችንን ደፍተናል፡፡ በእለቱም ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞችን ስናይ ደስተኞች አይመስሉም ነበር፤ ይሄ የግል አስተያየታችን ነው፡፡
(በሰርጉ ላይ ታድመው የነበሩ
የጣቢያው ጋዜጠኞች)

“የመሰለ ልጆች ሰርግ፤ ለህዝቡ ምን ቁም ነገር ያስተላልፋል?”
የህትመት ሚዲያም ይሁን ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የህዝብ ነው፡፡ የሚገለገልበትም ህዝብ ነው፡፡ ግለሰቦች ፈቃድ ቢያወጡበትም እንኳን ማለቴ ነው፡፡ በዚህ የህዝብ ንብረት ላይ በቋሚነት ህዝብ የሚጠብቃቸው መረጃዎች፣ መዝናኛዎችና ትምህርት ሰጪ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ ሲፈቀድ ለህዝብ ያላቸው ፋይዳ ታስቦ ነው፡፡ የመሰለ ልጆች ሰርግ ብቻም ሳይሆን ሌሎችም ፕሮግራሞች ሲተላለፉ ምን ቁም ነገር ለህዝቡ ያስተላልፋሉ? ምንስ  ጥቅም አላቸው? የሚለው መመዘኑ የግድ ነው፡፡ የታዋቂ ሰዎች፣ የአርቲስቶች ሰርግ ይዘገብ የለም ወይ ምን ክፋት አለው ላልሺው፣ የፈለገው አርቲስትና ታዋቂ ሰው ቢሆን፣ ለአራት ሰዓት ያህል ሌላ ፕሮግራም ታጥፎ፣ እንዲህ ረጂም ሰዓት ወስዶ፣ ሰርግም ይሁን ሌላ ጉዳይ ተዘግቦ አያውቅም፤ እኔ ሰምቼም አላውቅም፡፡  ነገር ግን በአጭር ዜና መልክ፣ በእንኳን ደስ ያላችሁ ምኞታዊ መግለጫ መልክ ይሰራል፤ የተለመደ ነው፤ ይህን ህዝቡም ይፈልገዋል፡፡ የማወቅ መብትም አለው፡፡ ከዚያ ውጭ እንዲህ ረጂም ሰዓት የወሰደ የቀጥታ ስርጭት፣ ለግል ሰርግ ተከፍሎት እንኳን ቢሆን፣ ሰዎች ስለከፈሉ ማስተላለፍ የለበትም፤ መደበኛ ፕሮግራሞችም መታጠፋቸው ትክክል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ መሰለ መንግስቱ፤ የሰራው ስራ በምንም መልኩ ቢታይ አግባብ ነው ብዬ አላምንም፡፡
 ፍሬው አበበ (የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ)
“የአየር ሰዓቱን ገዝቶ ቢያስተላልፍ ችግር አልነበረውም”
አንድን የራሴን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላስተላልፍ ብዬ ባስብና የተጠየቅሁትን ብከፍል፣ እስከ ከፈልኩ ድረስ ያንን ማድረግ የምችል ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን መሰለ መንግስቱ፤ “ሬዲዮው የኔ ነው፤ ያሻኝን ባደርግ ማን ከልካይ አለኝ” በሚል መንፈስ አድርጎት ከሆነ፣ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን በዚያ ሰዓት የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ሲያጥፉ፣ የአየር ሰዓቱን ከአዘጋጆቹ ገዝቶ፣ ህዝቡን አስፈቅዶ፣ ሂደቱን ጠብቆ ቢያደርገው ምንም ማለት አይደለም፡፡ ይህ የግል አስተያየቴ ነው፡፡ የልጆቹን ሰርግ ማስተላለፍ ለማህበረሰቡ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው የሚለው፣ በመሰለ ጭንቅላት የሚለካ ነው፡፡ እሱ በኮሜንታተርነቱ ተወዳጅነትን ስላተረፈ፣ የልጆቹንም ሰርግ ቢያስተላልፍ የሚወደድለት መስሎት፣ በቅን ልቦናው አስቦት ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ የሬዲዮ ጣቢያው እርሱ ቢያስተዳድረውም የህዝብ ስለሆነ፣ በሰርጉ ምክንያት የአየር ሰዓት ለታጠፈባቸው ይቅርታ ጠይቆ፣ ህብረተሰቡን አስፈቅዶ ቢያስተላልፍ ነገሩ ቀለል ይል ነበር፡፡ ነገር ግን “በቃ የልጆቼ ሰርግ ነው፤ የራሴ ስለሆነ ማን ምን ያመጣል እንደፈለግሁ አደርገዋለሁ” በሚል የፈፀመው ከሆነ፣ ህዝብን ያለማክበርና ማናለብኝነት ወደሚለው ጉዳይ ልንሄድ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሰው በስፖንሰር መልክ ፋናን፣ ኢትዮጵያ ሬዲዮን መግዛት ይችላል እኮ፡፡ ፕሮግራማቸውን ያጠፈባቸውን አዘጋጆች፤ የአየር ሰዓት ቢገዛና ቀድሞ ፕሮግራሞን ይፋ ቢያደርግ ብዙ ችግር አልነበረውም ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ እኔ “አዲስ አድማስ” ላይ አንድ ገፅ ወይ ሁለት ገፅ ህጉ በሚፈቅድልኝ መሰረት ገዝቼ የምፈልገውን ፕሮግራም ማስተላለፍና ራሴን ማስተዋወቅ አልችልም እንዴ? መሰለም እንደዛ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ አሁን ነገሩን የሚያከብደውና የሚያቀለው እሱ ፕሮግራሙን ያስተላለፈበት መንፈስ ነው፡፡ የራሴ ስለሆነ እንደፈለግሁ እሆናለሁ ብሎ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡
 (ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ)   

Read 5904 times