Saturday, 30 July 2016 11:49

ዛሬ ወደ ጠፈር ጉዞ

Written by  ተፊሪ መኮንን
Rate this item
(12 votes)

ዛሬ ይህን ዘረኛነት የተበከለ ምድር ለቅቀን ወደ ጠፈር ብንሄድ ምን ይመስላችኋል?
ጠፈርተኞች ከጠፈር ጣቢያ ሆነው መሬትን ሲመለከቷት በጣም ይወዷታል፡፡ እንደ እናት በስስት ይመለከቷታል፡፡  እጅግ የምታምር፣ ውብና ህይወት ያላት ፍጡር ትመስላለች ይላሉ፡፡ ‹‹እኛ የጠፈር ጣቢያችንን በያ ለማቋረጥ እየጠገንን እንክብካቤ እናደርግላታለን፡፡ ነገር ግን ሰዎች ለእናት መሬት እንክብካቤ አያድርጉላትም፡፡ በጣም ያጎሳቁሏታል›› ይላሉ፡፡  
አንዳንድ ጠፈርተኞች፤ ‹‹ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን፤ መሬትን ቁልቁል ቢመለከቷት፤ ለእነርሱ አንድ ቤት ነች፡፡ በእሷ የሚኖሩ ሰዎችም የአንድ የቤተሰብ አባላት ሆነው ይታይዋቸዋል፡፡ በዚህች መሬት የሚኖሩ ሰዎች በሰው ሰራሽ የፖለቲካ ድንበር ምክንያት ሲፋጁ ቢመለከቱ ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ የማያባራው የፍልስጤምና የእስራኤል ጦርነት፤ ትርጉም የለሽ ነገር ይሆንባቸዋል›› በማለት አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
የሰው ልጅ ወደ ጠፈር የሚያደርገው ጉዞ የሚያሳስባቸው ሰዎች አሉ፡፡ በአንድ ወቅት፤ ‹‹ይኸ መመላለስ ችግር ሊያመጣ ይችላል›› የሚል እምነት የነበራቸው ከተለያዩ ሐገራት የተውጣጡ የህግ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አዘጋጅተው በዚሁ ጉዳይ ምክክር አድርገው ነበር፡፡ በጉባኤው፤ ‹‹ወደ ጠፈር በምናደርገው ጉዞ፤ ሳናውቀው በሌላ ዓለም የሚኖሩ ፍጡራንን ልናስቆጣ እንችላለን፡፡ በነገሩ ሳናስብበት የምናደርገው ጉዞ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከእኛ የተሻለ ሥልጣኔና ቴክኖሎጂ ያላቸው የሌላ ዓለም ፍጡራን፤ ‹ግዛታችን ተደፈረ› በሚል ስሜት በመሬት ጥቃት ሊሰነዝሩና ሊያጠፉን ይችላሉ፡፡ ለመሆኑ፤ በሌላ ዓለም ከሚኖሩ ፍጡራን ጋር ድንገት ብንገናኝ የሚኖረን ምላሽ ምንድነው? በሁለታችን መካከል የሚኖረንን ግንኙነት የሚገዛ ህግ ልናወጣ ያስፈልጋል›› የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡
የህግ ባለሙያዎቹ የነገሩን አስፈላጊነት ያምናሉ፡፡ ነገር ግን አስቸጋሪ የሆነባቸው ጉዳይ፤ ‹‹በሌላ ዓለም ይኖራሉ ብለን የምናስባቸው የማይታወቁ ፍጡራን፤ ምን እንደሚያስደስታቸው ወይም እንደሚያስከፋቸው ሳናውቅ፤ የሚወዱ ወይም የሚጠሉትን ነገር ሳንለይ፤ የሁለታችንን ግንኙነት የሚገዛ ህግ እንዴት አድርገን ልናወጣ እንችላለን? ህግ የሚወጣው የህብረተሰቡን እሴቶች፣ የምግባር መሰረቶችና እምነቶች ወዘተ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የነዚህን ፍጡራን አኗኗር ወይም ባህል ሳናውቅ ህግ ማውጣት አንችልም›› የሚል ክርክር ተነሳ፡፡
ታዲያ ጉባዔተኛው ብዙ ውይይት አድርጎ የደረሰበት መደምደሚያ፤ ‹‹የነሱን ባህልና እሴት ባናውቀውም፤ የሁለታችንን ግንኙነት የሚገዛ ህግ ማውጣት እንችላለን፡፡ ህጉም ‹በአንተ እንዲደረግብህ የማትወደውን ነገር በሌሎች አታድርግ› በሚል መርህ ተመስርቶ ሊወጣ ይችላል›› የሚል ሆኖ፤ በተቃራኒው ‹‹ለማስደሰት ብዬ ያደርግኩት ነገር የሚያስከፋቸው ቢሆንስ?›› የሚል ጥያቄ ያነሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጉባዔው የእዚህን ሰዎች ጭንቀት ማስወገድ ባይችልም፤ ‹‹በአንተ እንዲደረግብህ የማትወደውን ነገር…. ›› የሚል የምግባር መርሆን መነሻ በማድረግ ህጉ ሊቀረጽ ይችላል ተባለ፡፡
ዛሬ ወደ ጠፈር የሚሄዱ ጠፈርተኞች እንዳይጥሱት የሚጠነቀቁለት ‹‹በይነ - ፕላኔታዊ›› ህግ መኖሩን አላውቅም፡፡ ሆኖም የዛሬ ጨዋታችን የህግ ነገር አይደለም፡፡ስለዚህ መሬትን ለቅቆ ወደ ጠፈር ጣቢያ የሚሄድ ሰው ከሚገጥሙት በርካታ እንግዳ ነገሮች ጥቂቱን ልነግራችሁ ነው፡፡                
ወደ ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ የሚሄድ ሰው ፀሐይ በቀን ብዙ ጊዜ እየጠለቀች መልሳ ስትወጣ ይመለከታል፡፡
እኛ በ24 ሰዓታት ፀሐይ አንድ ጊዜ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ ስትገባ ስንመለከት፤ በዓለም አቀፉ የጠረፍ ጣቢያ የሚኖር ጠፈርተኛ፤ በምድር ከምንኖረው ሰዎች የበለጠ የፀሐይ መውጣትና መግባት ሂደትን ይመለከታል፡፡ ጠፈርተኞቹ ፀሐይ በቀን 16 ጊዜ ስትሠርቅና ስታርብ (በምዕራብ ስትገባ) ይመለከታሉ፡፡ ይህ የሚሆነው የጠፈር ጣቢያው በሰዓት 28 ነጥብ 157 ነጥብ 5 ኪ.ሜ በሚሸፍን ፍጥነት ስለሚጓዝ ነው፡፡ በተጠቀሰው በዚህ ፍጥነት የሚጓዝ አንድ ነገር መሬትን አንድ ጊዜ ለመዞር 90 ደቂቃ ብቻ ይፈጅበታል፡፡ በመሆኑም፤ 90 ደቂቃ X በ16 ዙረት = 24 ሰዓት (አንድ ቀን) ይሆናል፡፡
በጠፈር ጣቢያ ከሆናችሁ፤ በምድር ህይወት መኖሩን የሚጠቁም ጉልህ ምልክት የምታዩት በመዐልት ሳይሆን በምሽት ነው፡፡
የናሳ ጠፈርተኛው ቴሪ ቪርትስ እንደሚሉት፤ ‹‹በመዐልት የሚታዩ የምድር ህይወት እንቅስቃሴን የሚያመለክቱ ዋና ዋና ክስተቶች፤ በሰማይ የሚጓዘው አውሮፕላን ትቶት የሚሄደው የጭስ ዱካ ወይም ፋራ፤ የሚጓዙ መርከቦች በውሃ አካል ላይ ጥሎት የሚሄደው ትልምና በትላልቅ ከተሞች ሰማይ ላይ ረብቦ ግራጫ ሆኖ የሚታየው የጭስ ደመና ናቸው፡፡››
‹‹ሆኖም›› ይላሉ ጠፈርተኛው፤ ‹‹እውነተኛ የሰው እንቅስቃሴ የሚታየው የምሽት ጊዜ ነው፡፡ ከጠፈር ሆኖ መሬትን ከሚመለከት አንድ ሰው እይታ የሚገባው ብዙ ህዝብ የሚገኝበት አካባቢ ሳይሆን ሐብት የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ የአውሮፓ ምድር እንደ አምፑል በርታ እያንፀባረቀች ትታያለች፡፡ ሆኖም በአፍሪካ አህጉር የብርሃን ጅረት ፈስሶ የሚታየው እንደ ካይሮና ጆሃንስበርግ ባሉ ከተሞች ዙሪያ ያለው አካባቢ እንጂ በተቀረው የአህጉሪቱ ክፍል የምናየው ጥቂት የብርሃን ነቁጦችን ነው›› ይላሉ፡፡
ከጠፈር ጣቢያ ያለ የሆነ ሰው፣ ልብን ቀጥ የሚያደርግ ውብ የውራውራ ማዕበል ይመለከታል፡፡ ‹‹በህሊናዬ ሰሌዳ ታተሞ እንዲኖርና መቼም መች ልረሳው የማልሻው አንድ ነገር፣ የውራውራ ትዕይንት ነው›› ይላሉ የናሳ ጠፈርተኛው ኬጄል ኤን. ሊንድግሪን (Kjell N. Lindgren)፡፡ ‹‹ግን ይህ ድንቅ ትዕይንት ለብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ለቅጽበት በትክክል በውራውራ ባህር የምትንሳፈፍ ይመስልሃል፡፡  ከዚያ ያ ማዕበላዊ ትዕይንት እንደ ሸማ ተጠቅልሎ ከዓይንህ ይሰወራል፡፡ ያን ድንቅ ትዕይንት የተመለከተ ሰው፤ እንዲህ ያለ ነገር አየሁ ብሎ ሊናገር አይችልም፡፡››
በጠፈር ጣቢያ ላይና ታች የሚባሉ ነገሮች ቋሚ ፍች ያጣሉ፡፡ ላይ ያልከው ታች፤ ታች ያልከው ላይ መሆን ይችላል፡፡ በጠፈር ጣቢያ የሚኖሩ ጠፈርተኞች፤ ራሳቸውን ወደ ጣራው እግራቸውን ወደ ወለሉ ቢያደርጉም በጠፈር ውስጥ እውነተኛ ላይ እና ታች የለም፡፡ ከመኖሪያ መንኮራኩራቸው ጣራ ላይ የተለጠፉ ወይም የተጻፉ ነገሮች ከጣራው ተጣብቀው የሚገኙ አንዳንድ ነገሮች ወይም መሣሪያዎች፤ አናታችን ከየት በኩል መሆን እንዳለበት ሊያመለክተን ይችላል፡፡ ሆኖም ጠፈርተኞቹ  የቁመታቸውን አቅጣጫ እንደፈለጉ መቀየር ይችላሉ፡፡ የናሳው ጠፈርተኛ ባሪ በች ዊል ሞር (Barry “Butch” Wilmore)፤ ‹‹ አንዳንድ ቀን ለለውጥ ብዬ ራሴን ወደ ወለሉ፤ እግሬን ወደ ጣሪያው አድርጌ እገኛለሁ›› ይላል፡፡
ለጠፈርተኞች በጣም አስቸጋሪ የሆኑ አንዳንድ ምግቦች አሉ፡፡ ስበቱ እጅግ ዝቅተኛ በሆነበት የጠፈር ጣቢያ፤ ማንኪያ ተጠቅመን ምግብ ስንበላ፤ በማንኪያው ምግብ ከሰሃን አንስተን ወደ አፋችን መውሰድ የምንችል ቢሆንም፤ ያነሳነውን ምግብ በማንኪያ ይዘን ማቆየት አንችልም፡፡ ስለዚህ ጠፈርተኞች ይዘዋቸው የሚሄዷቸው ምግቦች ይህን እና ሌሎች ችግሮችን ከግምት በማስገባት የሚመረጡ ናቸው፡፡ እዚህ ምድር ላይ እንደለመዳችሁት ማንኪያውን ወደ አፋችሁ በፍጥነት ከወሰዳችሁ፤ አንዱ የጠፈር ሰው በአጠገባችሁ ለማለፍ ሲሞክር ድንገት ከተጋጫችሁ፤ በማንኪያው ያነሳችሁት ምግብ እንደ ቢራቢሮ እየበረረ፣ ከእናንተ በዙሪያችሁ ይበታተናል፡፡
በጠፈር ስትኖሩ በጣም የምትቸገሩበት አንዱ ነገር የዕቃ መጥፋት ጉዳይ ነው፡፡ በመንኮራኩሩ የሚገኝ ማንኛውም ዕቃ ከጣራ ወይ ከግድግዳው (በምድር አነጋገር) የተጣበቀ ካልሆነ በቀር፤ ድንገት ስልብ ብሎ የሚጠፋበት አጋጣሚ የተለመደ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኩት ቪርትስ (Virts) የሚሉት ጠፈርተኛ ገጠመኙን ሲናገር፤ በመጀመሪያው ተልዕኮ ወደ ጠፈር በመጣ ጊዜ፤ እርሱና ሌሎች የጠፈር ባልደረቦቹ ይጠቀሙበት የነበረ አንድ መፍቻ ነገር በድንገት ጠፍቶ አንድ ወር ሙሉ ሲፈለግ ሳይገኝ፤ አንድ ቀን ሳያስቡት ብቅ እንዳለ ይናገራል፡፡ ‹‹ምን እንዳጠፋው ባናውቅም፤ ዕቃው ከተሰወረበት ሥፍራ ወጥቶ እየተንሳፈፈ ከፊታች ድቅን አለ›› ይላል፡፡ ‹‹አሁን የምንገኝበት የጠፈር ጣቢያ፤ ከሁለት - ሦስት አስርት ዓመታት በኋላ በመጨረሻ ወደ ምድር ስትመለስ ጠፍተው የቆዩ በጣም ብዙ መሣሪያዎች፣ መብራቶች፣ የጋብቻ ቀለበቶች፣ ሌላም አሁን የማይታሰብ ነገር ሁሉ ከተሸጎጡበት ሥፍራ ብቅ ብቅ ይላሉ›› ብሎ ነበር፡፡
ከጠፈር ሆናችሁ፤ የአካባቢን ብክለት ችግር ተጽዕኖን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ሰዎች በምድር ላይ የሚያሳድሩት በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ይኖራል፡፡ ‹‹በጠፈር ጣቢያ ሳለሁ፤ ዘወትር የአየር ብክለት ክስተት የምናይበት አንድ የእስያ አህጉር ክፍል ነበር›› የሚለው ሊንድግሪን (Lindgren)፤ ‹‹ታዲያ ወደ ከተማ የሚገባውን የመኪና ቁጥር በቀነሱ እና መሰል እርምጃ ሲወስዱ ሊሆን ይችላል፤ አየሩ ንጹህ ሆኖ ይውላል፡፡ ከዚያ በጥቂት ቀናት ውስጥ አልታይ ይሉን የነበሩ ከተሞችን ማየት ችለን ነበር›› ይላል፡፡
በጠፈር የሚኖር ሰው ከዓይኑ አንድ ነገር ሳይገባበት አይውልም፡፡ በጠፈር ዓይኔ ተቃጠለ እያለ የማያለቃቅስበት ሰው አይገኝም፡፡ ‹‹በጠፈር ጣቢያ ውስጥ የሚበን ነገር ከተፈጠረ፤ መሬት ላይ እንደምናየው፤ ብናኙ ወደ መሬት አያርፍም››  ይላል ጠፈርተኛው ሊነድግሪን (Lindgren) ‹‹በጠፈር ጣቢያ ያለው የአየር ማጣሪያ ስቦ ካልወሰደው በቀር፤ የሚበንን ነገር በዙሪያችሁ እየተንሳፈፈ ይቆያል፡፡ በጠፈር ጣቢያ ከሚያጋጥሙ የተለመዱ በሽታዎች መካክል አንዱ የአለርጂ ነው፡፡ ሌላው ምቾት የሚነሳ የጭንቅላት መወጠር ስሜት ነው:: ይህም ስሜት የሚፈጠረው፤ የስበት ኃይል አለመኖሩ በደም ዝውውር ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ የተነሳ ነው፡፡  
እናት መሬት ከጠፈር ሆነው ሲያይዋት ውብና ህይወት ያላት ነገር መስላ ትታያለች፡፡ ስለዚህ ትናፍቃለች፡፡ አሁን እንውረድና ሣምንት ተመልሰን እንመጣለን፡፡            

Read 5456 times