Saturday, 30 July 2016 11:51

አውሮፓ ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት የ1 ቢ.ፓውንድ የጦር መሳሪያ ሸጣለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ስምንት የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ባለፉት አራት አመታት ብቻ ከ1 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት መሸጣቸው በምርመራ መረጋገጡን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ባልካን ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርቲንግ ኔትዎርክና ኦርጋናይዝድ ክራይም ኤንድ ኮራፕሽን ሪፖርቲንግ ፕሮጀክት የተባሉ ተቋማት ያወጡትን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ከ8 የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ከገቡት በሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ከባድና ቀላል የጦር መሳሪያዎች መካከል አብዛኞቹ በእርስ በርስ ጦርነት ወደምትታመሰው ሶርያ ደርሰው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡  የጦር መሳሪያዎቹን የሸጡት አገራት ቦስኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ስሎቫኪያ፣ ሰርቢያና ሮማኒያ እንደሆኑ ለአንድ አመት በዘለቀ የተደራጀ ምርመራ መረጋገጡን የጠቆመው ዘገባው፤ አገራቱ እ.ኤ.አ ከ2012 አንስቶ ባሉት አመታት በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለሳኡዲ አረቢያ፣ ለዮርዳኖስ፣ ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስና ለቱርክ ሸጠዋል ብሏል፡፡ የጦር መሳሪያዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በሚገኙ አክራሪ ቡድኖች በጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የአውሮፓ ህብረት ከሽያጩ ጋር በተያያዘ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንና የህብረቱ ፓርላማ ከፍተኛ ባለስልጣንም አንዳንዶቹ ሽያጮች የአውሮፓ ህብረትን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ብሄራዊና አለማቀፍ ህጎች የሚጥሱ ናቸው ማለታቸውን አመልክቷል፡፡ 

Read 1440 times