Saturday, 30 July 2016 11:57

ተመድ በደ/ ሱዳን ሹም ሽር ጉዳይ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬርን አስጠነቀቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      በጁባ ባለፉት 3 ሳምንታት ብቻ ከ120 በላይ ጾታዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል
      የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ምክትላቸው የነበሩትን ተቀናቃኛቸውን ሬክ ማቻርን ከስልጣን አውርደው ጄኔራል ታባል ዴንግ ጋይን በቦታው መተካታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገሪቱ የሚደረጉ የስልጣን ሹም ሽሮች በሙሉ የሰላም ስምምነቱን ያከበሩ መሆን አለባቸው በሚል ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬርን ማስጠንቀቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ሹም ሽሩን ማድረጋቸው በሁለቱ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ከስምንት ወራት በፊት የተደረገውን የሰላም ስምምነት የሚጥስና አገሪቱን ወደከፋ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ነው መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በሳልቫ ኬርና በማቻር መካከል በዚህ ወር ዳግም ግጭት መቀስቀሱን ጠቅሷል፡፡
ግጭቱ መቀስቀሱን ተከትሎ ማቻር ወታደሮቻቸውን ይዘው ከመዲናዋ መውጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሳልቫ ኬርም ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ ማቻር በአፋጣኝ ወደ ጁባ ካልተመለሱ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡ በሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በተቃዋሚው ሃይል ይመረጣል የሚል አንቀጽ ማካተቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር አዲሱን ምክትል ፕሬዚደንት መሾማቸው ከስምምነቱ ጋር የማይጣጣም እንደሆነም አስታውቋል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ፤ በአገሪቱ መዲና ጁባ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ ከ120 በላይ የጾታዊ ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች ተፈጽመዋል ሲል ተመድ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡ የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቃን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ወታደሮችና ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ግጭቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በሴቶችና በህጻናት ላይ አሰቃቂ የጾታ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፡፡

Read 1177 times