Saturday, 30 July 2016 11:55

በአፍሪካ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከግማሽ ቢ. አልፏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሞባይል ስልክ ለ3.8 ሚ. አፍሪካውያን የስራ ዕድል ፈጥሯል
     በአፍሪካ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 557 ሚሊዮን መድረሱንና  የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015 ከሞባይል ምርትና አገልግሎት 153 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
የአፍሪካ የሞባይል ኢኮኖሚ የ2016 ሪፖርትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአህጉሪቱ አጠቃላይ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍኑት የግብጽ፣ የናይጀሪያና የደቡብ አፍሪካ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ የሞባይል ስልክ ኢንዱስትሪው በ2015 ብቻ ለ3.8 ሚሊዮን አፍሪካውያን  የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በመጪዎቹ አምስት አመታት በአፍሪካ ተጨማሪ 168 ሚሊዮን ሰዎች የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑና ይህም የተጠቃሚዎችን ቁጥር 725 ሚሊዮን ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ በአህጉሪቱ አገልግሎት የሚሰጡ የስማርት ሞባይል ስልኮች ቁጥር በሶስት እጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመትም ገልጧል፡፡ በእነዚህ አምስት አመታት የሞባይል ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ 168 ሚሊዮን አፍሪካውያን መካከልም ከ30 በመቶ በላይ  ኢትዮጵያውያን፣ ናይጀሪያውያንና ታንዛኒያውያን እንደሚሆኑም ተገልጧል፡፡
በሞባይል ስልክ አማካይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙ አፍሪካውያን ቁጥርም፣ ባለፉት ሶስት አመታት በሶስት እጥፍ በማደግ፣ በ2015 የፈረንጆች አመት 300 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በመጪዎቹ አምስት አመታት 550 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡

Read 960 times