Saturday, 30 July 2016 12:01

ሰለቻችሁ? እኛም እንዲሁ ነው የሰለቸን!

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(1 Vote)

     ዳኛቸው ወርቁ የተባለ ትንኩሽት ደራሲ፤ በዘመኑ የተመለከተው ተስፋ ቢስነትና በጉረኝት የተቃኘ የህይወት ዘይቤ፣ መሰልቸትና ብስጭት አሳድሮበት የሰለቸ ስሜቱን አሰልች ጽሑፍ በመጻፍ ገለጸው፤ ያንንም ‹‹አደፍርስ›› ብሎ ሰየመው፤ ይህን ምሥጢር ተረድቶ የሚያነበው ካልኖረ በቀር ‹‹አደፍርስን›› የመሰለ አሰልች ልቦለድ ላይኖር ይችላል፡፡ ዛሬ ስለዳኘም ስለ አደፍርስም የማውራት ዝግጅት የለኝም፤ እኔም በዘመኔ የደረሰብኝን መሰለቸት በአሰልች ገለጻ ብገልጽስ ለማለት ያህል ብቻ ነው ያደፍርስን ሐሳብ ያነሳሁት፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ መነሻ ሰሞኑን በሀዋሳ ስለተመረቀው የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት ዘገባ አሰልችነት ነው፡፡ በመሰረቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከተለመዱ ቅርጽ አልባና ስሜት የማይሰጡ ዘገባዎች መካከል መንግስታዊ (ፓርቲአዊ) የጩኸትና የጉራ ቅኝትን የሚይዙቱ የዘመቻ ዘገባዎች ብዙውን እጅ ይወስዳሉ፡፡
‹‹ጠንቋይ አሳደን አሰርን፤ የዘመቻ ዘገባ ነበር፣›› ‹‹የሽሻ እቃ ለቅመን አቃጠልን›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹ምግብ ቤቶች የሻገተ ስጋ ሰርተው ሲያቀርቡ ተደርሶባቸው ታሸጉ፣ የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የመሬት ወረራ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራት ችግር›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹አተት›› የዘመቻ ዘገባ ነው፣ ‹‹የአምስት መቶ ሀይገር አውቶብሶች መግባት›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የቢሾፍቱ አውቶብሶች መግባት›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ የስታዲዮሞች መገንባት የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ምርቃት›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ “የጋሽ አበራ ሞላ ዘመቻ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የካስትል ወይን ፋብሪካ ምርቃት›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የታላቁ ሩጫ የክፍለ ሀገር እንቅስቃሴ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የስፖርተኞች አነቃቂ መድሃኒት ጉዳይ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹አምቡላንስን ለግል አገልግሎት መጠቀም›› የዘመቻ ዘገባ ነው፣ ‹‹የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የማዳበሪያ ፋብሪካ የመገንባት እቅድ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የስኳር ፋብሪካዎች እቅድ›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣ ‹‹የኮንዶሚኒየም ምዝገባና ግንባታ የዘመቻ ዘገባ ነበር››፣ ‹‹የኮንዶሚኒየም ህንጻዎች መጥፋት›› የዘመቻ ዘገባ ነበር፣
‹‹የባሌስትራ ወርቅነት፣ የሳውዲ አረቢያ አባራሪነት፣ የሊቢያ አራጅነት፣ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች ወራሪነት፣ የአልሸባብ መደምሰስ፣ የአሜሪካ ወዳጅነት፣ የግብጽ ውይይት፣ የቻይና አጋርነት ወዘተ.(ዘገባዎቹ ይህን ያህል አሰልች ናቸው)
በተለይ በመንግስት ስር የሚተዳደሩ ብዙሃን መገናኛ ተቋማት፣ የዚህ አይነት የዘመቻ ዘገባዎችን ሲሰሩ ላባቸው ጠብ ጠብ እስኪልና ፊታቸው እስኪወዛ ድረስ አለቆቻቸውን ሊያስደስት የሚችል ነገር ብቻ (አለቆቹ መስማት የሚፈልጉትን ማለት ነው) ሲያነበንቡ ይስተዋላሉ፡፡ እንደ ብዙሃን መገናኛ ባለሙያ፣ ስለ ሚዘግቡት ነገር አሉታና አዎንታ የተንጠረጠረ መረጃ ከማቅረብ ይልቅ፤ በሉ የተባሉትን ወይም ቢሉት የሚያስሾማቸውን ሁሉ ይቀበጣጥራሉ፡፡ እስኪ ጥቂት ጉዳይ እናንሳ፡፡
ከስምንት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባን የመጓጓዣ ችግር ያስወግዳሉ የተባሉ አምስት መቶ አውቶብሶች ከቻይና ሊመጡ መሆኑ፣ ለሃብቶች ተሰብስበው መወያየታቸውን፣ ብድር መዘጋጀቱን፣ አውቶብሶቹ እየመጡ እንደሆነ፣ ለአውቶብሶቹ ታርጋ መዘጋጀቱን፣ አውቶብሶቹ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን፣ አዲስ አበባ መድረሳቸውን፣ መመረቃቸውን፣ የሙከራ ጉዞ ማድረጋቸውን፣ በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች መሰማራተቸውን፣ አገልግሎት መጀመራቸውን፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሀይገሮቹ አገልግሎት መደሰታቸውን፣ የመጓጓዣ ችግሩ እየተቃለለ መሆኑን ለዚህም የሀይገር አውቶብሶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ወዘተ. አዳዲስ ርእስ እየሆኑ ቋቅ እስኪለን ስንሰማው የነበረ ዜና ነበር፡፡
ስለ አውቶብሶቹ የተለያየ ርእስ እየሰጡ ይህን ያህል የዘመቻ ዘገባ ሲያራግፉብን የነበሩ አንዳቸውም ስለ አውቶብሶቹ ምንነትና እንዴትነት፣ መንግስት ቃል ገብቶባቸው ስለነበሩ የአውቶብሱ የጥራት ደረጃዎች አንዳች መረጃ አልሰጡም፤ (ወይም መስጠታቸውን አላውቅም) አውቶብሶቹ አገልግሎት በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወንበራቸው መላላጥ፣ አካላቸው መፈራረስ፣ በአንዴ እንደ ፌስታል ጭርምትምት ማለት ሀቅና መንስኤ ሲዘገብ፣ የሰማሁት አንዳች ነገር የለም፡፡ ለዚህ ነው ዘጋቢዎቹ አለቆቻቸውን የሚያስደስት ነገር ለማውራት እንጅ ለህዝቡ መረጃ ለማድረስ እየሰሩ አይደለም ያልሁት፡፡
አንድ ሰሞን ደግሞ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፖሊስ ነዋሪዎችን በማስተባበር የሽሻ እቃዎችን እየሰበሰበ እያቃጠለ መሆኑን፣ ብዙ ድል ማስመዝገቡን፣ ብዙ ማስቃሚያ ቤቶችን መዝጋቱን፣ ብዙ ማስጨሻ ቤቶችን ማሸጉን ወዘተ፡፡ እጅ እጅ እስኪል ድረስ የዘመቻ ዘገባ ዘነበብን፤ ግን እኒያ ዘገባዎች ብዙ መቶ ሰዎች ዱላ ይዘው፣ አንድና ሁለት የሽሻ እቃ ሲደበድቡ የሚያሣይ፣ ይህንኑም እንደገድል የሚዘግብ እንጅ የሽሻ እቃዎች እንዴት ጉምሩክን አልፈው እንደገቡ፣ የሚጨሰውም ቁስ ከየት እንደሚመጣ፣ በከተማዋ ስንት እንዲህ ያለ ቦታ እንዳለ፣ ቢያንስ ሃይስኩሎችን፣ ኮሌጆችንና የዩንቨርሲቲ በሮችን ታክከው ያሉቱ ምን ያህልነት ሲዘገብ አልሰማንም፣ ብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች፤ እንዲህ ላለው ነገር ወኔ ያላቸው አይመስሉም (አሌክስ አብርሃም በፌስ ቡክ ገጹ፤ በቀነኒሳ ሆቴል ውስጥ ሽሻ እንደሚጨስ የጻፈው በቅርብ ጊዜ ነበር) የዘመቻ ዘገባ ግቡ፣ በአለቆች ዘንድ ተወዳጅነትን ማግኘት እንጅ ህዝብን ማገልገል አይደለም ያልሁትም ለዚሁ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማስወገድ ከዚህ ቀደም የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎችን ቢበዛ በአምስት ዓመት፣ አዳዲሶቹን ተመዝጋቢዎች ደግሞ ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ ባሉ ሰባት ዓመታት ውስጥ የቤት ባለቤት ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን፣ ይህን ተከትሎም ብዙ ነዋሪዎች መመዝገባቸውን፣ በመመዝገባቸውም የመንግስትን ልማታዊነት ማመናቸውን፣ መደሰታቸውን ወዘተ. እንዲሁ እስኪታክተን የሰማነው የዘመቻ ዘገባ ነበር፡፡ ግን አሁን ምን እየተሰራ ነው? የተባለው…  የተገባው ቃል ሁሉ የት ድረስ እየተጓዘ እንደሆነ፤ እኒህ ዘጋቢዎች አንዳችም መረጃ አይሰጡንም፡፡
ፋብሪካ መተከሉ ራሱን ችሎ ግብ አይደለም፤ ወይም ፋብሪካዎችን አቅፎ የሚይዝ ፓርክ መሰራቱ ሀገሪቱን በአንዴ የሚያስመነድግ ምትሃት የለውም፤ መገንባቱ በራሱ በቂ ስላልሆነ፤ ዘገባዎችም ይህን ያህል የዘመቻ ከመሆን ይልቅ በመገንባቱ ምን እንደተገኘ ምን እንደሚገኝ አስቀድሞ አታሞ ከመደብደብ ይልቅ በክትትል የፋብሪካዎቹ እቅድና ስኬት እንዴት እንደሆነ፣ ይህ ወይም እኒህ ፋብሪካዎች በመገንባታቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል የሚታይ ለውጥ እንዳመጡ ወይም እንዳላመጡ ማሳወቅ ነው የህዝብ አገልጋይ ዘጋቢነት መገለጫው የሚመሰለኝ፡፡ (እዚህ ጋ ሁሌም የሚገርመኝን ነገር ላንሳ፣ ብዙ የሀገራችን ዘጋቢ ነን ባዮች፣ የዘጋቢነትና ተንታኝነትን ልዩነት ያውቁታል?)
በቅንፍ ውስጥ ላነሳሁት ጥያቄ መልሴ አይመስለኝም ነው፡፡ የአንድን ፋብሪካ መተከል እንዲዘግብ የተላከ ዘጋቢ የቀጥታ አየሩን ሲያገኝ የሚደሰተው ለህዝቡ  የሚጠቅም መረጃ ለማድረስ ሳይሆን ለአሰሪው ፓርቲ ወይም ለአለቃው ተንታኝ ሆኖ ለመታየት ይሄ ነው እኛን የሚያሰለቸን፤ ፋብሪካው ምን? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች እሱን አያስጨንቁትም፡፡

 (በግንባታው ሂደት የተበላ ጉቦ ካለማ፣ ጭራሽ ጉዳዩ ሊሆን አይችልም) ይልቁንም የመንግስታችን ልማታዊነት፣ የአውራ ፓርቲው ሀገር አልሚነትና ታታሪነት፣ የብሔረሰቦች እኩልነትና የትምክህተኞች አከርካሪ መሰበሩ፣ የትራንስፎርሜሽን ጉዞው መሳለጡ፣ የህዳሴው እውንነት፣ የግንቦት ሃያ ፍሬነትና የጀግኖች ሰማዕታት የደም ውጤት መሆኑን ለረዥም ሰዓት ያብራራል፡፡ እዘግባለሁ ስለሚለው ፋብሪካ ግን ከስሙ ያለፈ ያን ያህል መረጃ ማድረስ አያስጨንቀውም፡፡ (በባለእድል ወይም በእድለኛና  በባለእድለኞች መሃከል ያለውን የልክነትና የጋጠወጥነት ሀሁ ሳይቆጥር፣ ልተንትን ሲል ትን እስኪለን እንደምንስቅበት የት ያውቅና!) አሁን ይህን ሁሉ የምጽፈው ለምንድን ነው? ስለሰለቸኝ እኮ ነው! ያሰንብተን!

Read 1093 times