Saturday, 30 July 2016 12:26

“ከሽንኩርት እርሻዬ 180 ሺህ ብር እጠብቃለሁ”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 ወጣት አበራ መኮንን የጊኒር ወረዳ ውጫሌ አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ 10ኛ ክፍል ቢያጠናቅቅም ሥራ አጥ ነበር፡፡ ወላጆቹን፤ ‹‹ይህን መሬት ሰጡኝና ሽንኩርት ልትከልበት›› አላቸው፡፡ ‹‹ኧረ ወስደህ ሥራበት፤ከተሳካልህ ወደፊት ትልቅ ሰው ትሆናለህ›› አሉት፡፡
አንድ የግብርና ባለሙያን እንዲህ ለማድረግ አቅጃለሁ ምን ትመክረኛለህ? ሲል ጠየቀው። ባለሙያውም፤‹‹እኛ የምንፈልገው እንዳንተ ያለ ወጣት ነው፡፡ በምችለው አቅም ሁሉ ከጎንህ ነኝ›› በማለት አበረታታው፡፡ ወጣት አበራ ወደ ስራ ከገባ በኋላ የግብርና ባለሙያው እየመጣ፤‹‹እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ ብታድርግ ኖሮ፣ እንዲህ ያደረከው ጥሩ ነው፣….›› እያለ ይመክረውና እገዛ ያደርግለት እንደነበር ወጣቱ ተናግሯል፡፡
መሬቱ ጪንጫ ስለነበር፤ መጀመሪያ በትራክተር ካረሰ በኋላ፣ ሁለቴ በበሬ አለስልሶ ማዳበሪያ ጨምሮበት 10 ቀን እንዲቆ አደረገ፡፡ ከዚያም ለ5ኛ ጊዜ አርሶ፣ አንዱን ኪሎ ሽንኩርት  በ45.60 ሂሳብ፣ 3 ኩንታል በ19 ሺህ ብር ገዝቶ ሽንኩርቱን በመስመር ተከለ፡፡ ወጣት አበራ ከሁለት ሄክታር ምርት ከ50-60 ኩንታል ሽንኩርት ይጠብቃል፡፡ ገበያው ጥሩ ከሆነ አንዱን ኩንታል ሽንኩርት እስከ 3500 ብር እንደሚሸጥ ገልጾ፣ከምርቱ  በአማካይ 180 ሺህ ብር ያህል እንደሚጠብቅ ተናግሯል፡፡
ሁለገቡ አራሽ፤ ሁሴን መሐመድ
የ47 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አርሶ አደር ሁሴን መሐመድ የወለተኢ አቶታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አቶ ሁሴን ሁለገብ አራሽ ናቸው፡፡ የማይዘሩት ሰብል፣ የማይተክሉት የጓሮ አትክልት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ባላቸው 2 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ይዘራሉ፤ቡና፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ስኳር ድንች፣ ጫት፣… ሌሎችም አትክልቶች ተክለዋል፡፡ “ቡናው አምና ነው የምሥራች የሰጠው፡፡” አምና ከስንዴው ምርት 30 ኩንታል ማግኘታቸውን፣ በአጠቃላይ ከተለያዩ ሽያጮች 120 ሺህ ብር ማግኘታቸው ተናግረዋል። ከስምንቱ ልጆቻቸው አምስቱ 10ኛ ክፍል አጠናቀዋል፡፡ ልጆቹ ሥራ ስላልያዙ አባታቸውን በእርሻ ሥራ እየረዱ ነው፡፡ ሦስቱ እየተማሩ ናቸው፡፡
የቀበሌው የግብርና ባለሙያዎች የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርጉላቸውና ማሳቸውን ስለጎበኙላቸው በጣም መደሰታቸውን ጠቅሰው፣ የሥራ ሞራላቸው መነሳሳቱን ተናግረዋል። ባለሙያዎቹ በሰጧቸው ትምህርትና ምክር በመታገዝ፣ ከፍተኛ ምርት ለማግኘትና ትልቅ ቦታ ለመድረስ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

Read 1251 times