Saturday, 30 July 2016 12:38

የንባብ ለህይወት አጭር ጉዞና ተስፋው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ባለሀብቶቻችን ጭንቅላትንም ስፖንሰር እናድርግ››
   አቶ ቢንያም ከበደ የ“ንባብ ለህይወት” መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በሀምሌ ወር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን
ማዕከል የመጀመሪያው የ“ንባብ ለሕይወት” የመጽሐፍትና የሚዲያ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ዘንድሮም ባለፈው ሳምንት
ሁለተኛው ዙር የ“ንባብ ለሕይወት” የመጽሐፍት አውደ ርዕይ በተመሳሳይ ቦታ ተዘጋጅቶ ስኬታማ እንደነበር አቶ ቢንያም ለአዲስ
አድማስ ተናግረዋል፡፡ አውደ ርዕዩ መጻህፍት አሳታሚና ሻጮችን ጨምሮ በንባብና በትምህርት ዙሪያ የሚሰሩ በርካታ ተቋማት
የተሳተፉበት ነበር፡፡ ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም በርካታ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ በግጥም፣በአጭር ልብወለድና በሌሎች
ሥነጽሁፋዊ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎች ጥናት አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በ“ንባብ ለህይወት” ፕሮጀክት ዙሪያ፣የንባብ ባህልን ለማስፋፋት ምን ለመስራት
እንደታቀደ፣እንዲሁም በወደፊት ራዕዩና ተስፋው ዙሪያ ከአቶ ቢንያም ከበደ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

 “ንባብ ለህይወት” እንዴት ተጠነሰሰ ?
የንባብ ጉዳይ የሚያስተናግዱና በዋነኝነት የሚሰሩ ተቋማት ቀደም ሲልም አሉ፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር አንዱ ነው፡፡ ሌላው አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከ50 ዓመት በላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በተለይ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት የንባብ ጉዳይ ስራዬ ብሎ ሲሰራ ነበር፡፡ በግልም ይህን ስራ የሚሰሩ አሉ፡፡ እነ ዳንኤል ወርቁን ብትወስጂ፡- ‹‹ኢትዮጵያ ታንብብ››፣ “አዲስ አበባ ታንብብ›› በሚል ከጀርመን የባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ይሰሩ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስም እንዲሁ በንባብ ላይ ይሰራል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም በንባብ ዙሪያ የሚያሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡
በሌላ በኩል ግን ለንባብ ለህይወት መፈጠር ትልቅ ፈለግ የነበረው ‹‹አዲስ ጉዳይ መፅሔት›› አዘጋጅተው የነበረው ዓለም አቀፍ የመፅሀፍት አውደ ርዕይ ነበር፡፡ እነዚህ ተጠቃሽ ነገሮች እንዳሉ ሆነው፣ የኢትዮጵያ የንባብ ታሪክ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም ብቅ ጥልቅ እያለ እንጂ በወጥነት ሲሰራ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ እኛ ይህንን ከፍተት ለመሙላት፣‹‹ንባብ ለህይወት›› የተባለውን ፕሮጀክት ይዘን ብቅ አልን ማለት ነው፡፡
በንባብ ደረጃ የሌላውን ዓለም ተመክሮ እንደ መነሻ ተጠቅማችኋል?
የአገራችንን የንባብ ጉዳይ ከጎረቤታችን ከኬንያ ጋር ብታወዳደሪ እንኳን በጣም ልዩነት አለን፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ‹‹ካሪቡ›› የተሰኘ ትልቅ የመፅሐፍት አውደ ርዕይ አላቸው፡፡ በኬንያ ለአዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ለህፃናትም ተብሎ ራሱን የቻለ አውደ ርዕይ ይዘጋጃል፡፡ የግብፅን ብንመለከት፣ከመቶ አመት በላይ ዕድሜ ያለው አውደ-ርዕይ አላቸው፡፡ ሀርጌሳ ብትሄጂ ኢትዮጵያዊም ጭምር የሚያስተባብሩበት የመፅሀፍት አውደ ርዕይ አለ፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስንመጣ፣ በነፃነታቸው ማግስት አንዱን ግዛት ከሌላው የሚያገናኙበትና አንድ የሚሆኑበትን ነገር ሲፈልጉ የመጣላቸው የመፅሀፍት አውደ ርዕይ ነው። በየአመቱ በየግዛቱ የሚካሄድ ትልልቅ የመፅሀፍት አውደ ርዕዮች አላቸው፡፡
እኛ በሥነ ፅሁፍ ሀብታም የምንባል አገር ነን። በሀይማኖቱም ቢሆን በእስልምናውም ይሁን በክርስትናው ብዙ ያልተመረመሩ ግን ሊታዩ የሚገባቸው ድርሳናት ሞልተዋል፡፡ ከሀይማኖትም ውጭ በስነ እፅዋት፣በስነ ምህዳር፣ በስነ-ህንፃው ብዙ ያልተነኩ መፅሐፍት ስላሉን፣እነዚህን ይዘን ወደ አደባባይ መውጣት አለብን ነው አላማችን፡፡ ዋና አላማው፤ ያነበበ አዕምሮው የለማ ትውልድን መፍጠር ነው፡፡ ያነበበ የነቃ ሰው ሲወድሽም ሲጠላሽም በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ትውልዱ አንባቢ አይደለም፤እየተባለ ይነገራል፡፡ ለመሆኑ ለትውልዱ የተመቻቸ ነገር ፈጥረንለታል ወይ? በአመት አንድ ጊዜ በድንኳንና በመሰል ቦታዎች ለተወሰኑ ቀናት አውደ ርዕይ በማዘጋጀትና መፅሀፍ በመሸጥ ብቻስ ትውልዱን አንባቢ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ንባብ ለህይወት ይህንን ጥያቄ በተቻለ መጠን ለመመለስ እየተጋ ነው፡፡
በምን መልኩ?
በጣም ጥሩ፡፡ ንባብ ለሕይወት ሲዘጋጅ መፅሀፍት ብቻ አይደለም የሚሸጡት፡፡ የተለያዩ ለትውልዱ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ትምህርቶች ሴሚናሮች፣ ጥናታዊ ፅሁፎች፣ የልጅ አስተዳደግ ስልጠናዎች ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ? አንብቡ ከማለት በፊት ምን አይነት መፅሀፍ ማንበብና እንዴት መነበብ  እንዳለበት ቅድሚያ ግንዛቤ መፍጠር ስለሚያስፈልግ ነው። በንባብ ለህይወት ብዙ ክንውኖች አሉ፡፡ በተለይ የሰሞኑ ማለትም ሁለተኛው የንባብ ለህይወት አውደ ርዕይ ከተጠበቀው በላይ ውጤታማ ነበር። በዚህ ፕሮግራም ብዙዎች የተደሰቱበት፣ብዙዎች ጥያቄያቸው መልስ ያገኘበት ነው፡፡ ንባብ ለሕይወት የተመሰረተውም አንተነህ ከበደ፣ እኔ፣ እስክንድር ከበደ፣ ጥበቡ በለጠና ሳምሶን አመሀ ተሰበሰብንና እስኪ ይህንን ነገር እንስራ፤አንድ የሚያደርገን ነገር ነው አልን፤ውጤማ ሆነ፡፡
ለአውደ ርዕዩ ሀምሌ ወር የተመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው?
ሀምሌ የተማሪዎች መደበኛ ትምህርት የሚዘጋበትና ብዙ ተማሪዎችና ወጣቶች ፋታ የሚያገኙበት ወቅት ስለሆነ ነው የተመረጠው። ዘንድሮም ሀምሌ የሆነው ለዚህ ነው፤ በዚሁ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሁለገብ እውቀት የሚያገኙበት ዕድል ይፈጥራል ማለት ነው፡፡
በአውደ ርዕዩ ላይ ከመፅሐፍት ነጋዴዎች ሌላ የተሳተፉት እነማን ናቸው?
አውደ ርዕዩ የተለያየ አይነት እውቀትና እሳቤ እንዲንሸራሸርበት የታሰበ በመሆኑ በርካታ ወገኖች እንዲሳተፉ ማድረግ ዋነኛ አላማው ነበር፡፡ ስለዚህ የምርምር ተቋማት፣ ለምሳሌ ስራ አመራር ኢንስቲቲዩት፣ ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ፣ አልታ የስልጠና ማዕከል፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ትምህርት ቢሮዎች በተቋም ደረጃ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ይዘው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ በሌላ በኩል የእምነት ተቋማትም እንዲሁ በክርስትናውና በእስልምናው ያሉ፣የበለጠ አስተምህሯቸውን በንባብ ላይ ያደረጉትን ይዘው እንዲቀርቡ አቅደን ይሄ ተሳክቶልናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ማህበረ ቅዱሳን፣ ቅድስት ማሪያም ገዳም፣ የጆቫ ዊትነስ (የሁዋ ምስክሮች)፣ የፕሮቴስታንት አማኞች፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ በእስልምናም አልነጃሺ፣ አልተውባና አላክሳ የተባሉ የእምነት ተቋማት ድርሳኖቻቸውን፣ ዶክመንቶችንና መፅሐፍት በበቂ ሁኔታ ይዘው ቀርበዋል፡፡ እነዚህን የእምነት ተቋማት በአንድ ቦታ በማድረግ ያሏቸውን የንባብ ባህሎች ልምድ እንዲለዋወጡና እንዲወያዩ አድርገናል፡፡ ‹‹የእምነት ተቋማትና የንባብ ባህላቸው ምን ይመስላል›› የሚል ፕሮግራም በማዘጋጀት ምሁራኖቻቸው ሀሳባቸውን ለታዳሚ አካፍለዋል፡፡ ለምሳ ዶ/ር መሀመድ ዘይን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአረቢክ ዲፓርትመንት መምህር፤በእስልምናው ልክ እንደ ቆሎ ተማሪ ያለው፣ ‹‹መደርሳን›› ስለሚባለውና ለዘመናዊ ትምህርት ስላለው አስተዋፅኦ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ በኦርቶዶክስ በኩል መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ፣ እነ ዶ/ር መጋቢ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ፤ የእምነት አስተምህሮቶች ለንባብ ባህላችን ስለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ጥሩ ጥሩ ትንታኔዎችን አቅርበዋል፡፡
የአልታ የማማከር አገልግሎት ባለቤትና የስነ-ልቦና ባለሙያው ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነም ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበው ነበር። እንዴት እናንብብ፣ ምን እናንብብ በሚል ስለ ቅድመና ድህረ ንባብ፣ አንድን መፅሀፍ እንዴት መቼ ብናነበው ውጤታማ እንሆናለን በሚለው ላይ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌ በዶ/ር ወዳጄነህ ጥናት ላይ በቻይና አገር በዓመት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መፅሐፍት ታትሞ፣ ህይወት አጭር በመሆኑ ላለን ለምንቆይበት ህይወት ጠቃሚውና ቅድሚያ ተሰጥቶ ልናነብ የሚገባው የትኛው አይነት ነው የሚለው ላይ ጥልቅ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ይሄን ስትመለከቺ አውደ ርዕዩ መፅሐፍት የሚሸጥ የሚለወጥበት ብቻ ሳይሆን ብዙ እውቀትና ትምህርት፣ የልምድ ልውውጥ የሚገበይበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ተደክሞበታል፡፡
ንባብ ለህይወት ላይ የሚሳተፉ የመፅሐፍት አቅራቢዎች የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ የተባለው እውነት ነው?
እውነት ነው ይገደዳሉ ብቻ ሳይሆን ለመሳተፍም ዋነኛ መሰፈርት ነው፡፡ ታዲያ የዋጋ ቅናሹ በስም ብቻ በመናገር ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ቅናሽ  ነው። ምን ለማለት ነው----አንዳንዴ የበዓል ባዛር ላይ ህብረተሰቡ የዋጋ ቅናሽ አገኛለሁ ብሎ ሲሄድ እቃው ጭራሽ ገበያ ላይ ከሚሸጠው በጣም ተወድዶና ተጋንኖ ያገኘዋል፤ ግን የዋጋ ቅናሽ እንዳለ ይነገራል። በንባብ ለሕይወት ላይ እንዲህ አይነት ነገር የለም። በዚህ ዓመት ላመሰግን የምወደው ቡክ ላይት እና ቡክ ወርልድ ከ10 እስከ 80 በመቶ ቅናሽ በማድረግ፣ ለህብረተሰቡ ትርጉም ያለው ስራ ሰርተዋል፡፡
እስኪ መጻህፍት በሶፍት ኮፒ በነፃ ሲሰጡ ስለነበሩበት ሁኔታ አስረዱኝ? ምን ያህል መፅሐፍቶችን ለታዳሚ ሰጣችሁ?
የዘንድሮ የንባብ ለህይወት ትልቁ ውበትና መልካም ገፅታ ደግሞ የነዚህ ቀሊለ መፅሐፍት (ኢ-ቡክ) ጉዳይ ነው፡፡ ሰው የግድ በመፅሐፍ መልክ ተጠርዞ ማንበብ የለበትም፤ባገኘው አጋጣሚና በሚመቸው መንገድ እንዲያነብና እንዲበረታታ ማድረግ ተገቢ ነው ብለን አሰብን፡፡ የዛሬ ዓመት ከኢትዮጵያ እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር እንዲሁም ከቡክ ኤይድ ኢንተርናሽናል፣ ከቡክ ፎር አፍሪካ ጋር በመተባበር አንድ መቶ ሺህ ኢ-ቡኮችን በተለይም የትምህርት መፅሀፍቶች ላይ ትኩረት አድርገን በማቅረብ በነፃ ሰጥተን ነበር፡፡ በጣም የሚገርም ግብረ መልስ ነበር ከማህበረሰቡ ያገኘነው፡፡ ይህን መነሻ አድርገን ዘንድሮ ግማሽ ሚሊዮን ኢ-ቡኮችን  አመጣን፡፡ ወደ 40 የሚሆኑ ኮምፒዩተሮችን ደርድረን  ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የዳታ ቤዝ አደራደሩን እንዲያግዙን በማድረግና በየዘርፉ መፅሐፍቱን በመከፋፈል ጎብኚ በቀላሉ በፍላሽ፤ በሀርድ ዲስክ፣ በሲዲ ይዞ እንዲሄድ አደረግን፡፡ ይሄ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ እዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የምንሰራቸው መርሀ-ግብሮች አሉ፡፡
ምን አይነት መርሀ ግብሮች ናቸው?
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ በአብይ መሀመድ በመክፈቻው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሑፍ ውስጥ እነ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አንስተው፣ ንባብ ለህይወት የተባለው ፕሮጀክት በተለይ በኢ-ቡኮች ላይ አብሮን እንዲሰራ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ ሰው በአመት አንዴ በሚዘጋጅ አውደ ርዕይ ላይ ብቻ መፅሐፍ መውሰዱ ቀርቶ መፅሐፍቶች እንደ ልብ የሚያገኝባቸው ካፌዎች እንዲቋቋሙ የሚል ነው፡፡ እኛም በዚህ ላይ የያዝነው እቅድ ስለነበር በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
የንባብ አምባሳደሮችን መርጣችኋል አይደል?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የመፅሐፍ አውደ ርዕይ እከሌ ሀሳቡን አመጣው፣ እከሌ ጠነሰሰው የሚባል አይደለም፤ ሁሉም የራሱ መነሻ አለው። በጭውውታችን መነሻ ላይ የነገርኩሽ ግለሰቦችና ድርጅቶች መነሳሳትና እንቅስቃሴ በእኛ ላይ የፈጠረው በጎ ተፅዕኖ፣ ‹‹ንባብ ለህይወት››ን ይዘን እንድንመጣ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ አውደ ርዕዩን በዓመት አንዴም ሁለት ጊዜም ከዚያም በላይ ማካሄድ ይቻላል፤ነገር ግን ንባብ የዕለት ከዕለት የህይወት አካል እንዲሆን ካስፈለገ በተለይ በትምህርት ተቋማት ላይ መሰራት አለበት፡፡ ስለዚህ ይህን ስራ የሚያስቀጥሉ የንባብ አምባሳደሮች ከተለያየ የሙያ ዘርፍ መርጠናል። እነዚህ ሰዎች የበቁ አንብበው የጨረሱ፣ ከዚህ በኋላ ምሳሌ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን ለንባብ ፍቅር ያላቸው፣ በሙያቸው ቢናገሩ የሚደመጡ ናቸው ያልናቸውን መርጠናል፡፡ ለምሳሌ ከስነ-ፅሁፍ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ በእውቀቱ ስዩምና አለማየሁ ገላጋይን ይዘናል፡፡ በስነ- ጥበብ (ስዕሉ) አካባቢ ደግሞ ረዳት ፕ/ር በቀለ መኮንን መርጠናል። በትምህርት ዘርፉ ደግሞ የመጀመሪያዋ የባዮሎጂ ሴት ፕሮፌሰር በኢትዮጵያ የዓለምፀሀይን ስንመርጥ፣ የማነቃቃት ስራ ከሚሰሩ ደግሞ የትነበርሽ ንጉሴን ይዘናል፡፡ በስራ በአመራር በኩል የናሽናል ኦይል ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ታደሰ ጥላሁንን መርጠናል፡፡ አቶ ታደሰ ጥላሁን በተለይ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለንባብ በሚደርጓቸው ንግግሮች ነው የሚታወቁት። ከስፖርቱ ሰውነት ቢሻው፣ ከትወናው ግሩም ኤርሚያስ በአምባሳደርነት ተመርጠዋል። 97 ያህል ቤተ- መፅሐፍትን በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል በማቋቋም ከኦክስፋም ካናዳ ጋር ትልቅ ስራ የሰራችው ማህሌት ሐይለማሪያምም ተመርጣለች። እነዚህ ሰዎች ስራዎቻቸውን መስራት ይጀምራሉ፡፡
በዋናነት የአምባሳደሮቹ ስራ ምንድን ነው?
ባለፈው ዓመት ከት/ቤቶች ጋር የተለያዩ ውጣ ውረዶች ስለገጠሙን በአምባሳደሮች በኩል ብዙ ስራ ሰርተናል ማለት አንችልም፡፡ ዘንድሮ ግን እሁድ ዕለት በተካሄደው የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ሁሉንም የትምህርት ቢሮዎችና የትምህርት ተቋማት አምባሳደሮቻችን፤በየት/ቤቱና በየተቋማቱ እየሄዱ ስለ ንባብ ያላቸውን ተሞክሮ እንዲያካፍሉ፣ ስለ ንባብ እንዲሰብኩ እንዲፈቀድላቸው ቃል አስገብተናል፡፡ ከመፍቀድም ባለፈ ተቋማቱ የመፅሐፍ አበርክቶት እንዲያደርጉም እንደሚነግሯቸው ሃላፊዎቹ ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ ቃል ሲገባልን አለማየሁ ገላጋይ፤ ‹‹እስካሁን የምንመክተው በዱላ ነበር፤ አሁን ጠብመንጃውን ሰጥታችሁናል›› ነው ያለው። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አምባሳደሮቹ በየቦታው እየሄዱ ያስተምራሉ፤ ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ዓመቱን ሙሉ ነው፡፡ ምን እንደሰሩ ሪፖርት ያደርጋሉ፤ ይገመገማሉ፡፡ ይህን እየጨመቅን ለሶሻል ለኤሌክትሮኒክስ፣ ለህትመት ሚዲያው እናሰራጫለን፡፡ በሚዲያ በኩል ድሬ ቲዮብ፣ የኛ ቲዩብ፣ አዲስ አድማስ፣ ቁምነገር መፅሄት፣ ኢቢኤስ፣ ሸገር ኤፍኤም፣ ናሁ ቴሌቪዥንና ሌሎችም አብረውን እየሰሩ ነው፡፡ እናመሰግናለን፡፡ ይሄ የሁሉም ትብብር ያለበት በመሆኑ ለውጥ ያመጣል የሚል ከፍተኛ እምነት አለን፡፡
በልጆች በኩል ትኩረት የምታደርጉበት ሌላ ፕሮግራም አለ?
አዎ ‹‹ንባብ ለህይወት ንባብ ለልጆች›› የተባለ ፕሮጀክት አለን፡፡ ይህ ፕሮጀክት ልጆችን እያዝናናን ንባብ እንዲያፈቅሩ የምናደርግበት ነው፡፡ ለዚህም ሙዚቃ የተደረሰላቸው ተረቶች ይኖራሉ፡፡ ይህንን በሁለተኛው ንባብ ለህይወት፣ በአራቱም ቀናት ሙያተኞች እየጋበዝን ሰርተንበታል፤በጣም ጥሩ ምላሽ አግኝተንበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር ተነጋግረን፣ ከመጪው አመት ጀምሮ ታች ድረስ በመውረድ፣ በልጆቹ ላይ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
በየኮንዶሚኒየምና በየሪል እስቴቶቹ የማንበቢያ ስፍራ ለመፍጠር ስለማቀዳችሁ ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ያብራሩልኝ ?
ንባብ ትልቁ ችግር ነው ብለን የምናስበው፣በአቅራቢያችን የንባብ ማዕከል አለመኖሩ ነው፡፡ በየኮንዶሚኒየም ቤቶች ቤተ-መፅሐፍት የሉም ግን እንዳለመታደል ሆኖ መጠጥና ጫት ቤቶች ይበዛሉ፡፡ ይህንን የምንቀይረው አማራጮች በማቅረብ ነው፡፡ በየክ/ከተማውና በየወረዳው አዲስ አበባ ውስጥ ከ80 በላይ ወጣት ማዕከላት አሉ፤ግን ምን ያህል በትጋት ይሰራሉ የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ወጣቱን ወደ ንባብ ለማምጣት እንደ እቅድ የያዝነውና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገርን አዎንታዊ ምላሽ ያገኘንበት ጉዳይ በየኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ግቢ አነስተኛና ተንቀሳቃሽ የሆኑ የመፅሐፍ ማንበቢያ ቦታዎችን መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም ፕሮጀክት ብሪቲሽ ካውንስል ከፍተኛ የመፅሐፍት ድጋፍ ሊያደርግልን ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ከአገር ውስጥ ደግሞ ሜጋ፣ ስፖትላይት፣ አስቴር ነጋ ኣታሚ፣ ቡክ ወርልድና ቡክ ኮርነር ያሉት ድርጅቶች እገዛ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ በቀጣይ ዓመት እነዚህን ድጋፎች በማሰባሰብ፣በሙከራ መልክ በተወሰኑ አካባቢዎች እንተገብራለን፡፡
በ2ኛው ንባብ ለህይወት ምን ያህል ተሳታፊዎች መፅሐፍት አቀረቡ? ከባለፈው አመትስ ጋር ሲነፃፀር በምን ያህል ጨመረ? የጎብኚውስ ሁኔታ እንዴት ነበር?
እውነት ለመናገር ብዙ ተስፋ እያገኘንበት ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ ንባብ ለሕይወት። በጎብኚ ብዛት፣ በተሳታፊ ቁጥር፣ በጎብኚም አይነት እጅግ የተደሰትንበት ነው የዘንድሮው። አምና 117 ተሳታፊዎች ነበሩ፤ ዘንድሮ 132 ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው አመት 62 ሺህ ጎብኚዎች ነበሩ፤ ዘንድሮ ከ83 ሺህ ሰው በላይ ጎብኝቶናል፡፡ በአስተያየት መስጫ ደብተሮች ላይ እንዳየነው፣ከተለያዩ ሙያ ተቋማት የመጡ ብዙ አይነት ህዝቦች ጎብኝተዋል፡፡ ይሄን ያህል ባልልሽም እጅግ ብዙ መፅሐፍት ተሸጠዋል፡፡ የዋጋው ቅናሽ አቅም አጥቶ ከማንበብ የተገታውን ህዝብ መልሶ አምጥቶታል፡፡ ወደፊትም ወደ ንባብ ይመልሰዋል የሚል እምነት አለን፡፡
 ንባብ ለህይወት ከአዲስ አበባ የመውጣት ዕቅድ የለውም?
 ስንጀምር ከአዲስ አበባ ነው፤ ግን ተጓዥ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ኤግዚቢሽኑ እንደ ንግድ መታሰብ አለበት፡፡ ብዙ ወጪ አለው፤ የአዳራሽ ኪራይ የማስታወቂያና የሎጅስቲክ ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ ይህንን የሚሸፍኑ ያገባኛል የሚሉ ባለሀብቶች ያስፈልጉናል፡፡ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ በመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ፤‹‹የእግር ኳስ ፕሮግራሞችን በሬዲዮ ስፖንሰር ለማድረግ ብዙ ድርጅቶች ሲሻሙ እሰማለሁ፤ እግር ኳስን ስፖንሰር ማድረግ እግርን ሰፖንሰር እንደማድረግ ነው፤ባለሀብቶቻችን ጭንቅላትንም ስፖንሰር እናድርግ›› ሲሉ አሳስበዋል። አቅም ሲጎለብት፣ ስፖንሰር ስናገኝ በየክልሉ ንባብ ለህይወት ይንቀሳቀሳል፡፡
ፕሮግራሙ ምን ያህል ወጪ አስወጣችሁ?
ወረቀት ላይ የሰፈረውን መናገር ይቻላል፤ከ800 ሺህ ብር በላይ ወጥቶበታል፡፡ ግን ጥንታዊ ፅሁፍ ሳይከፈላቸው ያቀረቡ ምሁራን በጉልበትና በሙያ ያገዙንን እንዴት በገንዘብ እንተምነው? ምንስ ያህል ነው ዋጋው? ትልቅ አቅም የጠየቀ፣ ብዙ እውቀት የፈሰሰበት ነው፡፡
ዘንድሮ ማንን ነው የሸለማችሁት?
በመጨረሻው ቀን ኢ/ር ታደለ ብጡልንና ተስፋ ገ/ስላሴን ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሸልመናቸዋል፡፡
በእያንዳንዱ ቀን አዳዲስ መፅሐፍት በመመረቅ ነበር ፕሮግራም የምትከፍቱት ስንት መፅሐፍ ተመረቀ
በርካታ መፅሀፍት ተመርቀዋል ይሄ ባህል ይቀጥላል ብዙ መልካም ግብረ መልስም አግኝተንበታል፡፡



Read 2933 times