Saturday, 30 July 2016 12:35

የሥነ - ግጥም ሕይወት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ከተካተቱት ዘውጎች፣እጅግ ጥንታዊ ነው የተባለለት ግጥም፤ የእስትንፋሱ ክር፤ የዘመኑ ጥግ፤ ዞሮ ዞሮ ከጥንታዊያኑ ሀገራት ጋር መዛመዱ ግድ ነው፡፡ ለምሳሌ በቻይና ታሪክ ውስጥ እጅግ ጥንታዊውና በእጅጉ የተለመደው ስነ ጽሑፋዊ ቅርፅ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ11ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 6ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያሉትን 305 ያህል ግጥሞች ያካተተው ‹‹The Book of ode›› ወይም የመውድሳዊ ግጥሞች መጽሐፍ የተባለው ጥራዝ በጥንታዊነቱ ይጠቀሳል። Guo Feng ወይም  Feng Falk songs, collected from chu-ci ሌላው የግጥም አይነት ነው፡፡ ይሄ የግጥም ዓይነት ደግሞ በቻይና እውነታዊነት /Realistic/ የተሠኘውን የግጥም- አይነት  ያስገኘ ነው፡፡ ፈቅ ሲል ደግሞ Li-Sao (ሊ-ሳኦ) ለቻይና ሮማንቲዝም- መንገድ ያበጀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በስነ ጽሁፋዊ ልዕቀቱ ዘውድ የደፋ ነው፡፡
ይሁንና የታንግ- ዘመን መንግሥት የቻይና ወርቃማ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ግጥም መፃፍና ግጥምን በቃል ማነብነብ፣ ከቤተ መንግስት እስከ ተራው ሰው ጎጆ፤ ከዚያም አልፎ እስከ መሸታ (ሴተኛ አዳሪ ቤት) ድረስ የተለመደ ሆኖ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በግጥም የተዋጣለት ሰው፣ በዘመኑ የነበረውን የንጉሳዊ ቤተ መንግስት ፈተና እንኳን ባያልፍ ለአስተዳደር የመመረጥ ዕድል ነበረው፡፡
ሌላኛው የገጣሚያንና የግጥም መፍለቂያ የዕብራዊያን ሕዝብ ነበር፡፡ ዕብራዊያን አኗኗራቸው በአንድ ሥፍራ ያልረጋና በዘላንነት የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡ የነርሱ ሥነ ጽሑፍ አፈጣጠሩ ከጨረቃ ፍቅርና ‹‹Sin›› ከተባለው የጨረቃ አምላክ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በዘመኑም በግመሎቻቸው አንገት የሚያንጠለጥሉት ‹‹ስሉሴ›› የሚባለው የጨረቃ ቅርፅ፣ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡
የብሉይ ኪዳን የቅርፅና ሥነጽሑፍ ሃያሲያን (ፕሮፌሰሮች) በፅሁፍ እንዳስቀመጡልን፤በሲና በረሀ በሚጓዙበት ወቅት ቀን ቀን ለመጓዝ በረሀው-- አስቸጋሪ ስለነበር፤ የምሽቱን ጉዞ የተቃና ለማድረግ፣ የጨረቃን መውጣት መጠበቅ ግድ ነበር፡፡ ታዲያ ጨለማውን መጥላትና ጨረቃን መናፈቅ፤ በድንገት ለምትገለጠው ጨረቃ፤ ከስሜት የፈነዱ - ስንኞችን፤ ከሙዚቃና ዳንስ ጋር አቆራኝቶ አምጥቶታል፤ በማለት የግጥምን በታሪክ ውስጥ መወለድ ከፌሽታ ጋር ያቆራኙታል፡፡ አፈጣጠሩም የቡድን ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የሥነ- ግጥም ምሁራን፤ ግጥም የመፃፍ የመጨረሻ ግቡ እርካታ ነው የሚሉንም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ግጥም እንደዚህ ተፈጠረ ካልን፣ ከነዚህ ከተፈጠረባቸው ሁለት ሀገራት- ያንዱ በቅዱስ መጽሐፍ ተጠርዞ እናገኛለን። በተለይ ጥንታዊው የዕብራይስጥ ግጥሞች በአምስት አይነት ይከፈላሉ፡፡
 Lyric - ሙዚቃ-ንክር - አብዛኛው የዳዊት መዝሙር
Didactic - ከስሜት ይልቅ ዕውቀትና አእምሮ ላይ ያተኮረ
 Prophetic
Elegiac - የኤርምያስ ሰቆቃ - ሀዘንና ሙሾ
Dramatic - የኢዮብና የሰለሞን መዝሙር-በምልልስና በግለ መነባንብ (ሀሳቦችና እውነታዎች)
የመጽሐፈ ኢሳያስ ግጥሞች፤ በውበታቸው ከፍታ ከብሉይ መጻሕፍት የሚደርስባቸው የለም፤ በቃላት አጠቃቀምና በዘይቤዎች ሀብት የጠገበና ከፍ ያለ ነው፡፡
 ግጥም የስሜትና የሀሳብ ሃይል፣ በዜማ ተከሽኖ ወደ ሰዎች ጆሮና ልብ   የሚዘልቅ፤ የሚታይ ምናባዊ ሥዕል የሚሠራና ስልት ያለው የስነፅሑፍ ዝርያ ነው ማለት እንችላለን፡፡ የተመረጡ ሀሳቦች፣ በተመረጡ ቃላት ተገምደው በዜማ ጅረት ይፈስሳሉ፡፡ መነሻቸውም ስሜት ነው፡፡ ስሜት በራሱ ግጥም ነው ባንልም፣ ወደ ግጥም የሚነዳን ግን ስሜት ነው።
ታዲያ ግጥም በየዘመኑ የተለያዩ ክፍሎችና መደቦች  ይኖሩታል፡፡ አንዳንዶቹ በጀመሩበት ስያሜ ሲዘልቁ፣ ሌሎቹ በዘመንና በቦታ ለውጥ ስማቸውን በሌላ ስም ተክተዋል፡፡ ይሁንና ባለንበት ዘመን የግጥምን ዓይነቶች በሶስት እንከፍላቸዋለን፡፡
ተራኪ ግጥም፡- ቀላልና ወደ ተፈጥሮ የሚጠጉ፣ ገፀ ባህሪያትን ሊይዙ የሚችሉ
ሊሪክ ግጥም፡- ዜማዊ የሆኑና በስሜት የተሞሉ፣ መዝሙሮችና እንጉርጉሮዎች
ተውኔታዊ ግጥም፡-
በጥቅሉ ግጥም ሁለንተናዊ ቋንቋ፣ሰብዐዊ ስጦታና መግባቢያ ነው፡፡ ጥንታዊውም ሆነ ዘመናዊው ሰው፣ በየራሱ ዘመን ቅኝትና አውድ ይጠቀምበታል፡፡ በሁሉም ሀገር፣ በሁሉም ዘመን፣ ግጥም ይፃፋል ይደመጣል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ፣ በየትኛውም ደረጃ ያለ ሰው ለግጥም ጆሮው ክፍት ነው፡፡ በገጠር ከሚኖረው ፊደል ያልቆጠረ እረኛና ወፍጮ ላይ መጅ ጨብጣ ካጎነበሰችው ልጃገረድ አንስቶ፣ በከተማ ከጥበቃ ሰራተኛው እስከ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ድረስ ከግጥም ውበት አያመልጡም፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያገኙታል፡፡ በሰርግ ቤት ዘፈን፣ በለቅሶ ስፍራ ሙሾ፣ በቤተ ክርስቲያን መዝሙር፣በቤተ መስጊድ መንዙማ ሆኖ ብቅ ይላል፡፡
ግጥም አራስ ቤት ያለን ህፃን ልጅ የሚያወዛውዘው ለምን ይሆን? … ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡ የገጣሚና የደራሲው ኤድጋር አላንፖ ብያኔ፣ ለዚህ መልስ የሚሰጥ ይመስለኛል፡- “…ግጥም ማለት … ሙዚቃ እርካታ ከሚፈጥር ሀሳብ ጋር ሲቀየጥ ነው፡፡ ቃላዊ ሙዚቃ፣ ፍካሬ፣ ምሰላና ዘይቤያዊ ቋንቋን አጣጥሞ የሚሰራ ነው፡፡” ይለናል።
ህፃናቱን የሚያወዛውዘው፣ ዜማው ነው፣ ምቱ ነው፡፡
ወደ ግጥም ውስጥ ገብተን - ልናየው ካሻን ደግሞ የጆን ዶኔን ሀሳብ እንመልከት፡- “የግጥም ሀሳብ ነፍስ ነው ካልን፣ የስንኞቹ ቴክኒክ ደግሞ አካሉ ነው፡፡” ሁለቱ አይነጣጠሉም፣ ማለቱ ነው፡፡
ግጥም በመላው ዓለም ያለው የጋራ መልክ ይህ ከሆነ፣ የአማርኛ ግጥሞችስ ዕድሜና ዕድገት የት ድረስ ነው? በርካታ ሰነዶች እንደሚነግሩን፤ የአማርኛ ስነ ግጥም ወረቀት ላይ ያረፈው /በፅሁፍ የቀረበው/ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡
*           *       *
ይህም ለንጉስ አምደፅዮን የተፃፈው ታሪካዊና የውዳሴ ግጥም ነው፡፡ የንጉሱን ተጋድሎ፣ የግዛቱን መስፋፋትና ጀግንነቱን የሚመለከቱ ግጥሞች ናቸው፡፡ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ ለአፄ ዳዊት፣ ለአፄ ይስሀቅ፣ ለአፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ ለአፄ ገላውዴዎስ /አጥናፍ ሰገድ/ የተገጠሙ ናቸው፡፡
የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ግን የሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅጣጫ ከሰለጠነው ምዕራባዊ ዓለም ጋር ስለተጎዳኘ የአማርኛ ቋንቋም ከግዕዙ ይልቅ ስፍራ እያገኘ መጥቶ ነበር፡፡ በኋላም በቅድመ ፋሺስት ወረራ ጊዜ እነ ተስፋ ገብረሥላሴን የመሰሉ አገር ወዳዶች፣ የጣሊያንን ወረራ በመቃወምና ብሄራዊ ስሜትን ለመፍጠር ከፃፏቸው ጥቂት ግጥሞች በስተቀር ያን ያህል የተሻሻለ ግጥም አልነበረም፡፡ ነጋ ድራስ ተሰማ እሸቴ፣ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም፣ ቀኝጌታ ዮፍታሄ - ከሚጠቀሱት ውስጥ ነበሩ፡፡
ዘመናዊ የአማርኛ ስነ ግጥም ዕድገት አሳይቷል የሚባልበት መነሻ ድንበር በድህረ ፋሽስት ወረራ  ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን ተከትሎ በሀገር ውስጥ የትምህርት መስፋፋትና የውጭ ሀገር ትምህርት ዕድሎች መከፈት፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይህ የጥበብ ዘርፍ እንዲያድግ ዋነኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡
በዚህ ጊዜ የጀመረው የስነ ግጥም የተሻሻለ መልክ፣ እነ ከበደ ሚካኤልን የመሰሉ ገጣሚያንን ወልዶ ሀገሪቱን ከውጭው ዓለም ኪነ ጥበብና ሳይንስ ጋር ማገናኘት ችሎ ነበር፡፡ ከበደ ሚካኤል፤“የቅኔ ውበት”ን የመሳሰሉ ስራዎችን ይዘው ሲቀርቡ፣ መንግስቱ ለማም “የግጥም ጉባኤን” ይዘው ብቅ አሉ፡፡ በኋላ ደግሞ እነ ሰለሞን ዴሬሳ የዘመናዊውን ዓለም ሥነ ጽሑፍ ዝቀው በማምጣት፣ አዲስ አይነት ስልቶችን አስተዋወቁ፡፡ ይህንን ለውጥ አስመልክቶ መንግስቱ ለማ እንዲህ ብለው ነበር፡-
 “ባለንበት የስነ ጽሑፍ ዘመን ትልቅ ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ የጥንታዊውን ስነ ግጥም ባህል ከዘመናዊው አቀራረብና የገለጻ ነፃነት ጋር አቀናጅተን አዲስ አይነት ውጤት መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ እጅግም ደግሞ በአዳዲስ የፈጠራ ሙከራ ተጠምደን፣ በየጊዜው በሚመጣው የፈጠራ አቀራረብ ንፋስ ስራችንን ነቅለን መጣልን ማስወገድ አለብን፡፡”
በተለይ ሰለሞን ዴሬሳ ግጥሞች አስተማሪና ሰባኪ መሆን የለባቸውም፣ ሲል ያመጣው አዲስ ሀሳብ፣ የጥበቡን ዓለም - የማሸበር ያህል አናግቶት ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ግጥም ምስጢር መሆን የለበትም ማለቱ አቤ ጉበኛን የመሳሰሉትን ደራስያን አላስደሰተም ነበር፡፡
ከዚህ በመቀጠልም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንና ሰይፉ መታፈሪያን የመሳሰሉ ዘመናዊ ገጣሚያን መምጣት፣ በጥበቡ ዓለም ሌሎች ብርቅ ከዋክብትን የመጨመር ያህል ተቆጥሮ ነበር፡፡ በቋንቋ ልቀቱ ጣሪያ የነካው ፀጋዬና በቀላል ቋንቋ ሥዕል መሳል የሚችሉት ሰይፉ መታፈሪያ ጎን ለጎን ተቀመጡ፡፡

Read 3809 times