Saturday, 30 July 2016 12:44

ከመሰለኝ ደግሞ ነው! ወይንስ አይደለም? (Reading: Bertrand Russell Philosopher and humanist)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

መጣጥፍ

  በርትራንድ ረስል ብዙ አይነት ፍልስፍናን እንዳራመደ ቢታወቅም ያራመደው አንድ ወጥ ፍልስፍና አቋም ግን አጠያያቂ ነው፤ ይላል ጆን ሉዊስ፡፡ ማጣፊያው ቢጨንቀው “Humanist” ብሎ ሰይሞት የመፅሐፉ ደራሲ ተገላገለ፡፡ ሰብዓዊነትን በዋናነት ያራመደ ፈላስፋ እንደማለት ነው፡፡ ሰብዓዊነት የ“ግብረገብ” ጥያቄ ነው፤ በፍልስፍና ዘርፍ፡፡ ግብረ ገብ “Morality” አስቸጋሪው ጥያቄ ነው፡፡
ጥያቄው በሰው ዘንድ ብቻ ያለና ሰው ደግሞ ምርጫ የሚያደርግ ፍጡር በመሆኑ የትኛው ነው “ጥሩ” ወይንም “መጥፎ” የሚለው አዝማሚያ እንደ መራጩ እምነት የሚዋዥቅ ነው፡፡ በአጭሩ ሳይንሳዊ የግብረ ገብ መለኪያ ሊኖር አይችልም። ምክኒያቱም፤ ሳይንስ ማቋረጫውን (means) እንጂ መነሻውን ወይንም መድረሻውን አይሰጥህም፡፡ …. ቆይ …ቆይ! እቺን ውስብስብ አረፍተ ነገር ግልፅ ላድርጋት፡፡
ለምሳሌ አንድ ወፍ ዛፍ ላይ አለች፡፡ አንተ ደግሞ ርቦሃል፡፡ ወፏን ገድለህ መመገብ ወይንም ሌላ አማራጭ መፈለግ አለብህ? ይህንን ምርጫ ለመወሰን ሳይንስ አያገለግልህም፡፡ ወፏን ለመብላት ከፈለክ ወንጭፍ ወይንም ባላ መስራት ግን ሳይንስ ወደ ፍላጎትህ ለመድረስ ጣልቃ ይገባል፡፡ … ወፏን ከዛፍ ላይ በወንጭፍ አማካይነት ከመታሃት በኋላ አሳዘነችህ እንበል፡፡ ልታድናት ፈለክ፡፡ ማዳን መወሰንህ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫህ የሚወሰነው እንደ እምነትህ ነው፡፡ እምነትህ ከሀይማኖት ጋር የተሳሰረም የተፋታም ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ መሰለህ የምትወስነው ነው፡፡ ወፏን ለማዳን ከፈለግህ የእንስሳት ሀኪም ዘንድ አቅፈህ ትወስዳታለህ፡፡ የእንስሳት ሃኪሙ ሳይንስን ነው በአንተ ውሳኔ ላይ ጣልቃ የሚያስገባው፡፡ ሳይንስ ለመግደል ስትወስን የጦር መሳሪያን በመስራት፣ ለማዳን ስትፈለግ ሀኪምን ተመስሎ ይመጣል፡፡ ወደ ምርጫህ ማቋረጫውን እንጂ የቅድመ ምርጫ ሚዛንህ አይሆንም፡፡ ሚዛንህ እምነትህ ነው፡፡ ስሜትህ ነው። ስሜትህ እንጂ ተጨባጩ እውነታ አይደለም ግብረ ገባዊ እሴትህን (moral value) የሚሰራልህ፡፡
ይህ ከላይ የፃፍኩትን ፅንሰ ሀሳብ የደመደመው ሰብዓዊ ተብሎ የተፈረጀው በርትራንድ ረስል ነው፡፡
“Science can only deal with means, not with ends; the ends must be supplied by feelings. For my part there are certain things that I value; I should mention especially intelligence, kindliness and self respect. Science can not prove that these things are good; it can only show how, assuming them to be good, they are to be obtained.”
--- እያለ ረስል ሀሳቡን ያብራራል፡፡ እንደ ረስል፡- አንድ ሳይንቲስት ስህተት ሰርቷል የሚባለው የተመረጠውን ምርጫ ስኬታማ ሆኖ ወደ ፍፃሜ የሚደርስበትን መንገድ ያለ ስህተት መገጣጠም ካልቻለ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሴትየዋ ከህመማቸው ለመዳን መርጠው ነው ሆስፒታል የመጡት። የሳይንቲስቱ (ሀኪሙ) ስራ የሴትየዋ ምርጫ እውን የሚሆንበትን መንገድ ያለ ምንም ስህተት ማከናወን የሚችልበትን ሳይንሳዊ ዘዴ መፈለግ ነው። መዳን መርጣ የመጣችውን ሴትዮ ከገደላት ሀኪም አይደለም፡፡ ወይንም ተግባሩን አልተወጣም፡፡
ይህ ምሳሌ በተቃራኒው ይሰራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ስርዓት ወንጀለኛ ወይንም ሽብርተኛ ነው ብሎ ያሰበውን ሰው እስር ቤት አስቀምጦ ማሰቃየት መረጠ እንበል፡፡ ሳይንቲስቱ ይኼንን ማሳኪያ ፈጠራ ፈልስፎ ሰውየውን አሳሩን እንዲበላ ማድረግ ተግባሩ ነው፡፡ “ሰውን ማሰቃየት ሰብአዊነት አይደለም” ካለ፤ ጥሩ ሳይንቲስት ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ለመሆን ዘርፉን ቢለውጥ ይሻለዋል፡፡
ይህ የበርትራንድ ረስል እይታ ነው፡፡ “በግል ምርጫ እንጂ በሳይንስ ግብረ ገብ ሊመረመር አይችልም” የሚል ነው እይታው ሲጨመቅ። ለምሳሌ የዓለም መንግስታት “አንድም እናት በወሊድ ምክኒያት መሞት የለባትም” ሲሉ የሰብዓዊነት ምርጫ እያደረጉ ነው፡፡ ምርጫው ትክክል ነው ወይንስ አይደለም? ለማለት ሳይንስ ጣልቃ አይገባም፡፡ ትክክል ነው፤ ከተባለ የእናት ሞትን ለመቀነስ ሳይንስ ተልዕኮውን ይወጣል፡፡ ተልዕኮ ምርጫን ከግብ ለማድረስ “እንደ መሳሪያ” ሆኖ ያስተሳስራል፡፡
ይህንን የረስል ፍልስፍና ለመሞገት ጆን ሉዊስ ይጥራል፡፡
መልካምና እኩይ ወይንም ባጠቃላይ እሴት በግለሰብ ስሜት ወይንም በመሰለኝ የሚመረጥ ከሆነማ ሂትለርም ትክክል ነበር ማለት ነው!? ሲል ይጠይቃል፡፡ … እንዲያውም ሂትለር የሚወደውንና ምርጥ ብሎ የወሰነውን የነጭ ዝርያ ከፍ ለማድረግ፤ እንዲሁም፤ ጠላቴ ያላቸውን (ዝርያዎች) ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሲወስን ሳይንስን መሳሪያ አደረገው፡፡ በእጁ ላይ በወቅቱ የነበረው የሳይንስ አቅም ከፍተኛ ስለነበር ግቡን ከበቂ በላይ ማሳካት ችሏል፤ ይለናል ሉዊስ፡፡
ስለዚህ የግብረገብ (Morality) ጉዳይ “ከመሰለኝ ደግሞ ነው!” ለሚል የግላዊ ምርጫ መተው የለበትም፡፡ ከተጨባጭ እውነታ (ሳይንስ) ጋር ካልተሳሰረ አደገኛ ነው ብሎ ረስልን ይሞግታል።
ተጨባጩ እውነታ ከተፈጥሮ የተቀዳ ነው፡፡ ተፈጥሮን አስተውሎ፣ ፅንሰ ሀሳብን (induct) አድርጎ ወደ ድምዳሜ (Deduction) ላይ እንድረስ ማለቱ ነው ሰውየው፤ ከበርትራንድ ረስል ጋር የገጠመው ሙግት ስሜት አደጋ አለው የሚል ነበር፡፡
የተፈጥሮ ህግ በዳርዊን አስተውሎት ብቻ የሚሰራ ከሆነ ምን ሊውጠን ነው፡፡ የዳርዊን “Survival of the fittest” ስለ እንስሳ አለም ብቻ ገልፆ እዛው የሚቆም አይደለም፡፡ ገለፃው ወደ ሰው ግዛትም ይሻገራል፡፡ ሲሻገርም ምን እንደሚመስል አቴናዊያኑ በግሪክ ሜሎስ ያሉትን ተፃራሪዎቻቸውን ካንበረከኩ በኋላ የተናገሩትን መፈክር መስሎ ሊቀርብ ይችላል፡፡
“In this world the strong do what they can, and the weak do what they must” ብለው ነበር አቴናዊያኑ፡፡ ከዚህ በከፋ ጥግ ሆኖ የአራዊትን ህግ በሰው ላይ ለመስበክ የሞከረው ኒቼ ደግሞ፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ ተገለጠልኝ” ይላል “ለህይወት የምንከፍለው ዋጋ የሚገለፀው በህይወት ለመቆየት በምናደርገው ምስኪን መፍጨርጨር አይደለም፡፡ ጉልበተኛና የሀይል ባለቤት ለመሆን በምናደርገው ጉዞ ነው የህያውነት ዋጋችን ትክክለኛ ስፍራውን የሚያገኘው፡፡ ራሳችንን ብርቱ ሌሎቹን ረግጠን ባሪያ በማድረግ ብቻ ነው የህያውነት ዋጋችን የሚለካው” ይላል ዱራንት በሚል “የፍልስፍና ታሪኩ” መፅሐፍ ላይ፡፡
የእንስሳት አለምን ከመረጥን ሰው መሆናችን ያከትማል፡፡ የሰው ልጅ ቁጥር ምድሪቱ ልትሸከመው በማትችል መልክ በዝቷል፤ እንበል። እንበል ሳይሆን የሚታይ ሁነት ነው፡፡ የበዛውን መቀነስ ነው የሚሻለው፡፡ ወይንስ ማንም ሳይጎድል የሚጨምረውንም አክሎ ማቻቻል?.... ሁለቱም ምርጫዎች ስሜታዊ ናቸው፡፡ ወሊድን መቆጣጠርም ሆነ አለመቆጣጠር ስሜታዊ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ሰው እንደ ተፈጥሮ ማሰብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ሀሳብም ሆነ ስሜት የላትም፡፡ ወፏን ብትገላትም ሆነ ብታድናት ጉዳዩዋ አይደለም፡፡ ሰው ግን ጉዳይ አለው፡፡ ጉዳይ ከራሱ ስሜትና ግላዊ ምርጫ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ግላዊነት የሰውን ልጅን በአጠቃላይ ከራሱ አንፃር መስሎ ልክ እንደ ራሱ አድርጎ ለመጠበቅ ከመፈለግ አንስቶ… የራሱን ዘር ከፍ ላለማድረግ ሲል አጠቃላዩን የሰው ዝርያ እስከ መፍጀት ሊያስመርጠው ይችላል። ሳይንስ እዚህ መሀል ሆኖ ምርጫው በቅልጥፍና ግብ የሚመታበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡
‹‹ማንም እናት በወሊድ መሞት የለባትም›› የሚለው ስሜታዊ (ሰብዓዊ) አቋም… የተወለደው ልጅ አድርጎ የሚበላው አጥቶ በስደት ባህር ላይ እንደ ጉደንዳን በአጥንቷ ጀልባ ላይ ተከምሮ ሲሰምጥ ስናይ….መጀመሪያውኑ ባልተወለደ ኖሮ ብለን…መሪር ሀዘን እናዝናለን፡፡
ኦምሌት በላተኞቹ ‹‹ጥቂት እንቁላሎች ተሰብረው በመጥበሻው ላይ መፍሰስ›› ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡ የምግብ ምርጫቸውን ከጫጩቶቹ የመፈልፈልና የመኖር ተፈጥሮአዊ ምርጫ ሲያስበልጡ፡፡ ይህ አግባብ አይደለም የሚሉም ሆኑ… ‹‹ታዲያ ምን ልመገብልህ?!›› የሚሉትም ለግል እሴታቸው (ምርጫቸው) ተገዢ ናቸው፡፡
መጀመሪያ ላይ ረሀቡን ለማስታገስ ወፏን በወንጭፍ ስለመታው ልጅ ምሳሌ ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን ምሳሌውን በራሴ ምርጫ ደግሜ ሳስተውለው ወፏን ከዛፉ ላይ በወንጭፍ መትቶ ከጣላት በኋላ…. እንደገና ያዘነላት ለምን እንደሆነ (በአዲስ አማራጭ) ትዝ አለኝ፡፡
ወፏን ወደ እንስሳ ሀኪም ወስዶ የተሰበረውን ክንፏን ለማስጠገን የመረጠው ወፋ አሳዝናው ሳይሆን የወፏን ላባ ነጭቶ መሸጥ እንደሚችል ድንገት ተገልጾለት ነው፡፡ ወፏ ሳትሞት ላባዋን እየነጨ መሸጥ ይችላል ለካ!.... በዛ ላይ ወፏን ቤት ሰርቆ በጎጆ ቢያስቀምጣትና ብትረባለት… የሚሸጠው ላባም ይጨምርለታል፡፡ የወፏ ዝርያ ፒኮክ ነው ብለን እናስብ (ምንም እንኳን ፒኮክ መሬት ላይ እንጂ ዛፍ ላይ ባይኖርም!)
ወፏን መግደል ወይንም ‹‹የእግዜር ፍጡር› ብሎ መተው ስሜታዊ ምርጫ ነው፡፡ ሰብዓዊነት ለሰው ማዘን ከሆነ፣ለወፍ ማዘን ደግሞ ‹‹ወፋዊነት›› ብሎ መሰየም ይቻላል፡፡ ‹‹ሰብዓዊም›› ሆነ ‹‹ወፏዊ››… ከተጨባጭ ምክኒያታዊነት ሳይሆን ከስሜት (እምነት) የመነጨ ግብረገብነት (Moral) በመመርኮዝ ነው መራጩ እሴቱን ከእምነቱ ጋር የሚያጣምረው፡፡
ጆን ሉዊስ፤በርትራንድ ረስል ተሳስቷል ብሎ ለመሞገት ቢሞክርም በስተመጨረሻ ግን የግብረገብን ጥያቄዎች ከጥያቄ ግዛት ወደ ሳይንስ ወይንም ጠቅላይ እውነት መሰብሰብ ሳይሰካላቸው ምዕራፍ አልቆ ሁለቱም ፈላስፎች ተለያይተዋል፡፡….. ግብረገብን በተመለከተ ‹‹ከመሰለኝ ደግሞ ነው!›› ብቻ እንደ አደገኛ ጦር በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ሾሎ በስተመጨረሻ መቅረቱ ብቻ እርግጠኛ ሆኖ ይጎላል።








Read 1429 times