Monday, 08 August 2016 05:30

አፕል ባለፉት 9 አመታት 1 ቢ. አይፎኖችን መሸጡን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአለማቀፍ የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚነትን ይዞ የዘለቀውና አይፎን ስልኮችን አምርቶ ለአለማቀፍ ገበያ ማቅረብ ከጀመረ ዘጠኝ ያህል አመታትን ያስቆጠረው ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤በእነዚህ አመታት 1 ቢሊዮን የአይፎን ስልክ ምርቶቹን ለደንበኞቹ መሸጡን ባለፈው ረቡዕ አስታወቀ፡፡
የአፕል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ኤንቢሲ ኒውስ እንደዘገበው፤የአይፎን ስልክ ምርቱን እ.ኤ.አ በ2007 በሰኔ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽያጭ ያቀረበው ኩባንያው፣ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ባሉት አመታት በድምሩ አንድ ቢሊዮን አይፎኖቹን ለደንበኞቹ ሽጧል፡፡
ኩባንያው የአይፎን ምርቶቹን ጥራትና የቴክኖሎጂ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻሻለ በአለም የስማርት ስልኮች ገበያ ውስጥ ቀዳሚ ሆኖ መዝለቁን ያስታወሰው ዘገባው፤በ2016 ሶስተኛ ሩብ አመት ብቻ 40.4 ሚሊዮን አይፎኖችን መሸጡን ገልጧል፡፡
አፕል ኩባንያ ባለፈው ረቡዕ 1 ቢሊዮንኛዋን አይፎን ስልክ መሸጡን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፤ስልኳ የተሸጠችበትን አገርና መደብር በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም ብሏል፡፡

Read 892 times