Print this page
Monday, 08 August 2016 05:41

ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር (ንጉሱ-ደርግ-ኢህአዴግ)

Written by  አሰፋ ጫቦ
Rate this item
(5 votes)

ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ሳምንት አቶ አሰፋ ጫቦ በቃለ-መጠይቅ መልክ በኢሜይል ከላክንላቸው ጥያቄዎች ለአንዱ፡ - “ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ይገልጹዋቸዋል?” ለሚለው ሰፊና ዝርዝር ምላሽ ልከውልን ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ባለመቻላችንም ቀሪውን ክፍል አሳድረነው ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ አቅርበነዋል፡፡ አቶ አሰፋ ለሌሎች ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሾችም ወደፊት በተከታታይ የምናወጣው ይሆናል፡፡

--- ኃይለስላሴ ምክር የማይቀበሉ ነበሩ። ምክሩ ብዙ መልክ ይዞም መጥቶ ነበር። የእነ ቢትወደድ ነጋሽ፤የእነ ጄነራል መንግስቱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ፣ ምክር ብቻ ሳይሆን ግልጽ ማስጠንቀቂያም ነበር። መካሪዎችን ከመቅጣት በስተቀር “ወይ ፍንክች!” ከዚያም ከእነ መንግስቱ ንዋይ ሙከራ ማግስት፣ አቶ ሐዲስ አለማየሁ፤ ወዲያ ወዲህ በማይል፣ ቁልጭ ባለ ቋንቋ፣ ይህ የባሪያ አሳዳሪ ሥርዓት ሊዘልቅም ሊያዛልቅም አይችልም ብለው በደብዳቤ ጽፈው መክረው ነበረ። ግን ወይ ፍንክች! ለምን ነበር የማይሰሙት። ይህ ድብቅ ተፈጥሮ፤“ከእኔ ሌላ ለኔ የሚያስብልኝ የለም!” ከሚል የመጣ ይመስለኛል።
ወጣቱ ምንሊክ ወደሚለው ልመለስ። የምንሊክ መንግስት አስገባሪና የባሪያ አሳዳሪ መንግስት ነበር። የሚያስገብረው ይህን በጦር የተሸነፈውን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ነበር። ባሪያም የሚፈነገለው በአብዛኛው ከደቡብ ኢትዮጵያ ነበረ። በምንሊክና በኃይለሥላሴ የመጀመሪያ ዘመናት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ውስጥ 30% ባሪያ ነበር። ኃይለሥላሴ በዚሁ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ባሪያ ይገዙም ነበር። የተክለሐዋርያትን መጽሐፍ ማንበብ ነው። ባሪያ ነጻ ይውጣ የሚል የእንግሊዝ ድርጅት፤ አዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ስለዚህ ጉዳይ ቢጠይቃቸው፣ የኃይለሥላሴ መልስ፡-“ታዲያ ባሪያ አሳዳሪው እንዴት ሊኖር ነው!?” የሚል ነበር።
ጣሊያን ገባና የዚህ የመሬት ይዞታውንም የባሪያ ሥርዓቱንም አፈራረሰው። ኃይለስላሴ ፈርጥጠው ከሔዱበት ሲመለሱ፣የመሬቱን ከምንሊክ ከወረሱት ዕጥፍ ድርብ አሳደጉት። አርበኛ ለተባለ መሬት ተሰጠ። ስደተኛ ለተባለ ጋሻ መሬት ተሰጠ። የውስጥ አርበኛ የሚባልም ነበርና ለዚያም ጋሻ መሬት ታደለ። መሬት የሚታደለው ያው ከደቡብ ኢትዮጵያ ነበር። ወለጋ ሲቀር። ወለጋም ጥንትም በስምምነት የገባ፣ በኋላም አምቻና ጋብቻ  በመሆኑ ነበር። ”የመሬት ለአራሹ!” ለመውደቂያቸው ዋናው ምክንያት የሆነው ሥረ-መሠረቱ ይኸው ነበር።
ኃይለስላሴ ራስ ወዳድ ነበሩ። አገር ምድሩ፤ ትምህርት ቤቱ፤ ከተማው ሳይቀር “የኃይለስላሴ” ነበር። አልጋ ወራሽም ሆነው ይኸው ነበር። ሐረርጌ “ተፈሪ በር” እንዴት ተፈሪ በር እንደተባለ የፊታውራሪ ተክለሐዋርያትን መጽሐፍ ማንበብ ነው። በአንጻሩ ለምንሊክ የነበረው፣ በምንሊክ ጊዜ የነበረው ብቻ ነበር። ለጣይቱ፤ ለቴዎድሮስ፤ ለራስ አበበ፤ ለገረሱ ዱኪና ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች የተሰየመ፣ የሚረባ የሚታይ ነገር አልነበረም። ደርግ ነው የቴዎድሮስ አደባባይ ያለው። ደርግ ነው የበላይ ዘለቀ መንገድ ያለው። ደርግ ነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያለው።
የኃይለሥላሴ ራስ ወዳድነት ቁንጮ፣በ1966 የሆነው ነበር። በኋላ ደርግ የሆነው የወታደሮች አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ እያንዳንዱን ሚኒስቴር አራተኛ ክፍለ ጦር ወስዶ ሲያጉር፣ ኃይለ ሥላሴን አስፈቅዶ፤ “ውሰዳቸው!” ተብሎ ተፈቅዶ ነበር። አድሮ ዉሎ ልጆቻቸውንም፣ የልጅ ልጆቻቸውንም አስፈቅደው ወህኒ አወረዷቸው። ይሄ የፈረንሳዩን ንጉስ ሊዊ 15ኛ ያስታውሰኛል። après moi le deluge ነበር ያለው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” እንዳለችው አህያ መሆኑ ነው። ወይም ሊዊ 14ኛ፤ እንደ ኃይለ ሥላሴ “ፀሐዩ ንጉስ!” ይባል የነበረው l’état, c’est moi አለ እንደሚባለው ነው፡፡ ”ኢትዮጵያ እኔ ነኝ፤ከኔ በኋላ……!”
ትልቁ ነገር እንግሊዝን እግዜር ይይላት! ፈርጥጠው የተገላገልነውን ለራስዋ የቅኝ ግዛት መስፋፋት መልሳ ባታመጣ ኖሮ፣ ጣሊያን በጠረገው መንገድ ኢትዮጵያ፤ በ1930ዎች ውስጥ ሬፑብሊክ ትሆን ነበር። አንድ የኃይለስላሴን ራስ ወዳድነት የሚገልጽ ዩኒቨርስቲ እያለሁ መጸዳጃ ቤት ያየሁት ነው። “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽንት ቤት!” ብሎ ተማሪ በጉልህና በማይለቅ ቀለም ጽፎ ነበር። ብለው! ብለው! በስንት ቀንና መከራ ሲያስለቅቁት እንደገና ይጻፋል። እኔ ታዲያ ወድጀው ነበር! ጥሩ ባህርይ ገላጭ ይመስለኝ ነበር!
ከዚህ ሌላ ኃይለሥላሴ የሐገር ሀብት ዘራፊ ነበሩ። ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ የአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያን፤ “የሕይወቴ ታሪክ”ን ማንበብ ነው። የአዶላ ወርቅ ገቢን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር አያውቀውም። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀሰ ነው። ደርግ ሲፈትሽ፤ የኃይለ ስላሴ ትራሳቸውና ፍራሻቸው ውስጥ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ተወሽቆ ተገኘ። የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን መጽሕፍ ማንበብ ነው።
የኃይለሥላሴ ነገር ብዙ ነውና ትንሽ መዝጊያ ጨምሬ ላብቃው። መላውን ዓለም ዞረዋል። በኢትዮጵያ ስም ነበር! ሳይጠሩ፤ አንዳንዴም “አይምጡ!” ሲባሉ ጭምር የግድ አስጨንቀው ይሔዱ ነበር። ለዚህ ምሳሌ 8 ጊዜ ወደ ዩጎዝላቪያ የተመላለሱትንና ማንን አስከትለው እንደሚሔዱ እንደገናም ከተክለ ጻድቅ መጽሐፍ ማንበብ ነው።
 አንዴ አሜሪካ አይምጡ ሲባሉ አስጨንቀው ሔዱ። በኒክሰን ዘመን መሆኑ ነው። በዚያ ላይ ለኒክሰን ያለ - የሌለ፤ አሁን የኢትዮጵያ ችግር ያልሆነ ይዘበዝባሉ። ሰውዬው ሰልችቶታል። አስተርጓሚ የሆኑት ዶክተር ምናሴ ኃይሌ፤ ንጉሱ ያልተናገሩትን ግን የኢትዮጵያ ችግር የሆነውን ለኒክሰን ያስተረጉማሉ። በኋላም ምናሴ ላይ ይጮሀሉ። ይህንን  ጆን ስፔንሰር (John Spencer) Ethiopia at Bay የሚለው መጽሐፍ ውስጥ ማንበብ ይቻላል።
ሌላው ከ1967 በፊት አዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያንን የምታውቁ የኃይለ ሥላሴ ፎቶግራፍ ከመላእከት፤ ጻድቃንና ቅዱሳን ምስል ጋር ተሰቅሎ አይታችኋል። ኦርቶዶክሱ ቤተክርስቲያን ሲገባም ሳይገባም ይሰግዳልና ለኃይለሥላሴም ሲሰግድ ኖሯል ማለት ነው። ይህ የ50 ዓመት የራዲዮ፤ የጋዜጣና የቤተ ክህነት፣ “ለንጉሱ ተገዙለት!” የኢትዮጵያን ህዝብ የተማረውን፤ ማወቅ የሚገባውን ጭምር የንጉሱ አምላኪ አደረገው። የአንጎል እጥበት Brain Washing የሚሉት ነው። ዛሬ የዚያ ሁሉ ውጤት ስለ ኃይለስላሴ ታሪካዊ እውነት ሲነገር፣ ማተብ እንደተበጠሰ አድርገው ያያሉ።
የመንግስቱ ኃ/ማርያም ዘመን
አሁን ደግሞ መንግስቱ ኃይለማርያምን ትንሽ እንየው። ስለ መንግስቱ ከማስታውሰው፤አንዴ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ (ያኔ ሻለቃ ነበር) የነገረኝ ነው። “ህዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም 60ዎቹ የኃይለሥላሴ ባለስልጣናት የተረሸኑ ለት ማታ ሸዋ ይነሳብናል!፤ ጦሩም ሊነሳብን ነው! በሚል ፍርሐት ብዙዎቻችን ያደርነው እዚያው ታላቁ ቤተ-መንግሥት ግቢ ነበር” አለ። “እንቅልፍ በዐይናችን ዞር አላለም! ጥዋት የምንጠብቀው መሪያችን፤ መንግስቱ ኃይለማርያም፣መጥቶ ማታ ከሰበሰበው መረጃ በመነሳት ያረጋጋናል የሚል ነበር” አለ። “በኋላም እንደተጠበቀው ጥዋት መንግስቱ መጣና ቦታውን ይዞ ተቀመጠ። ከዚያ ከቦርሳው የሆኑ ወረቀቶች አውጥቶ አደለን። ወረቀቶቹ የሚያሳዩት የወታደሩን አለባበስ (ዩኒፎርም) ንድፍ ነበር። ከዚያም ሲናገር፤ ያለፈው ሥርአት በመለዮና በልብስ ከፋፍሎን…!” ብሎ ቀጠለ፤” ትላንትና ማታ ስለሆነው አንዳችም ነገር አላነሳም! እንኳንስ ሊኖርበት የሰማዉም አይመስልም ነበር! የሚያውቀው ነገር ቢኖር ነው፤ እንዲህ ከመጤፍ ያልቆጠረው ብለን እኛም ተረጋጋን!” አለ።
ከዚህ ሌላ በወቅቱ የነበርን በመንግሥቱ ላይ የመግደል ሙከራ በተደረገበት ማግስት በቴሌቪዥን ቀርቦ የተናገረውን የምናስታውስ ይመስለኛል። ”በዚች በኩል (እግሩን እያሳየ) አንዲት ጥይት አልፋለች!”  ብሎ እንደ ዋዛ አለፈው። የሆነው ነገር ደግሞ ሲታይ የነበረበት መኪና ብጥቅጥቁ ወጥቶ በተአምር ነበር የዳነው። ይህንን ሁለቱን ያነሳሁት እነዚህ ዋንኛ የዕቡይ ባሕርይ (Sociopath) መገለጫ ባህርይ መሆናቸውን ለማሳየት ነበር። ፍርሐት፤ ሐዘኔታ አልፈጠረባቸውም። ተፈጥሮ ያንን ነስቷቸው ከሆነ ደግሞ አስተዳደጋቸው ገድሎ ቀብሮታል ማለት ነው። ስለዚህ፤ በውሻ፤ ድመት፣ አይጥ፣የዱር አውሬና የሰው ልጅ ሞት መካከል ያለው ልዩነቱ አይታያቸውም! አይሰቀጥጣቸውም! የታወቀ የተረጋገጠ የሰው ልጅ የሐዘን ስሜት የምንለው የላቸውም። ስለዚህም ሁለንተናቸው ወደሚቀጥለው እቡይ ተግባር ይሸጋገራል።
እነዚህን የመንግስቱን ባህርያት እስቲ በድርጊት እንይ። ጥር 26 ቀን 1969 ጀኔራል ተፈሪ በንቲንና ሌሎች የደርግ ባለስልጣናት በረሸነ ማግስት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከአደረገው ንግግር እንጥቀስ፡- “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረኳቸው!” ነው ያለው። ልብ ማለት ነው! ምሳም ቁርስም ተፈጥሮ የሚያስገድደን፤ ለመኖር መሠረታዊና አስፈላጊዎች ናቸው። ምግብ ነው! መንግስቱ የሚለን እነዚህን ሰዎች  በላኋቸው ነው። ህመሙ ይህንን ይመስላል! ለማለት ነው።
 ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ለቁርስነት የሚያበቃ በአገሪቱ ላይ የፈጸሙት ነገር ነበር? መልሱን ፍቅረሥላሴ ወግደረስም ሆነ ፍስሀ ደስታ በየመጽሐፍቶቻቸው ላይ ገልጸዉታል። “የደርግ ጠቅላላ ጉባዔ ተሰብስቦ የመንግስቱን ኃይለማርያምን ሥልጣን ቀንሶ አዲስ አዋጅ ስለ አወጣ ይህንኑ አዋጅ በስራ ላይ አዋሉ!” ነው።  መንግስቱ ከደርግ ውስጥ መርጦ የገደላቸውን ሰዎች እንይ። ሻለቃ ሲሳይ ሐብቴ፤ ሻለቃ ኪሮስ አለማየሁ፤ ሻለቃ ሞገስ ወልደሚካኤል፤ የመቶ አለቃ አለማየሁ ኃይሌ የዩኒቨርስቲ ምርቁና ብቻ ሳይሆን አብዮቱን አብዮቱ ያሰኙትን ዋና ዋና ተግባርትን ያመነጩና በስራም ለመተርጎም የሚሯሯጡ የደርግ ሞተር የነበሩ ናቸው። እንደ መንግስቱ ደግሞ አዲስ አዋጅ ወጣ አልወጣ ይበልጡታልና ቁርስ ማድረግ ነበረበት።ሌላው ሽምቅ ተዋጊ መሆኑን ከሚያሳየው አንዳንድ ለመጥቀስ በኮሎኔል ሽታዬ፤ ኮሎኔል ወልዴ፤የፖለቲካ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪና ዲሬክተር በነበሩትና በሻለቃ ጌታቸው አግዴ ላይ የፈጸመው ነው። ጌታቸው ሊገደል ከመሔዱ ጥቂት ደቂቃ በፊት ከመንግስቱ ጋር በለሆሳስ ሚስጥር ይነጋገሩ ነበር። ሲገደሉ ደግሞ በጥይት አልተረሸኑም! መንግስቱ ቆሞ ሲመለከት ተቀጥቅጠው ነበር የተገደሉት! በመንፈንቅለ መንግስት ተካፍላችኋል የተባሉ ጄነራሎች የታሰሩበት ቦታ ሌሊት ሔዶ እያንዳንዱን በስም እየጠራ ያንቧርቅና ያዋርድ ነበር። ይህ እንግዲህ ጄኔራሎቹና ምስክርነት በተባሉ መጽሐፍት ላይ የተገለጸ ይመስለኛል። የዕቡይ ባሕርይ መገለጫ ነው!
ያለበለዚያ በሕይወቴ እንደ መንግስቱ አይነት አንድን ነገር የሚረዳ ፤ከተረዳም በኋላ የተውሶ ሳይሆን ገንዘቡ አድርጎ መልሶ የሚገልጽ፣ የሚያብራራ፤ስብሰባ መምራት ብቻ ሳይሆን የተንዛዛ የስብሰባ ውይይት ማጠቃለል የሚችል፤ሰውን ከፍቶ ማየት የሚችል ሰው አላጋጠመኝም።መንግስቱ ደግሞም እንደ ድመት ለስላሳ፤እንደ ለማዳ ውሻ ተለማማጭ፤ እንደ ነብር ቁጡም መሆን ይችልበታል! ያውቅበታል! ታዲያ ፈቶ አይቶና ገምቶ ነው! የባሕርዩ አካል ነው። መንግስቱን “ከኔ በላይ ማወቅ ላሳር!” የሚያሰኝ ያክል የማውቀው ይመስለኛል። የማውቀው ግን አይመስለውም ነበር። ይህ የመንግስቱ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ጭምር ይመስለኛል። የማውቃቸው የማይመስላቸው አሁንም ብዙ አሉ። ክፋት የለውም! ያለበለዚያ መንግስቱን ቤቱን፤ ባለቤቱን፣ ልጆቹን ጭምር አውቃለሁ። ልቆጥረው ከምችለው በላይ አብሬ በልቻለሁ፤ ጠጥቻለሁ። ሊያደርሰኝ የፈለገው የትና የት ቦታ ነበረው። እምቢ አልኩኝ። አሁን ሳስበው፣ “እንኳንም እምቢ አልኩኝ!” ከዚያስ የቁርጡ ማእከላዊ ይሻለኛል። በሕይወት ታሪኬ የምመለስበት ስለሆነ ልለፈው። የዚህ የህመሙ ምንጭ ምን እንደሆነም ሌላ ምክንያት ፈልጌ እመለስበታለሁ። ለአሁኑ የእያንዳንዱ ሰው ግምት ይበቃል ብዬ አስባለሁ።
የመለስ ዜናዊ ዘመን
በመጨረሻም መለስ ዜናዊን እንዴት ታየዋለህ? የሚለው ይመጣል። ለመንግስቱ ኃይለማርያም ያልኩት ለመለስ ዜናዊም እንዳለ እንኳን ባይሆን 75% የሚሰራ ይመስለኛል። አንድ ጉልህ ልዩነት ቢኖር መንግስቱ ሊቀ መንበር ሲሆን የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሻለቃ ነበር። ያም ማለት ቢያንስ የ20 ዓመት የመንግስት የስራ ልምድ ነበረው ማለት ነው። መለስ የአንድ ቀንም የስራ ልምድ አልነበረውም። ያ ብቻ ሳይሆን የስራ ልምድ አላቸው የሚለውንና የሚጠረጥራቸውን ሲቪሉንም ወታደሩንም “ዐይንህ ለአፈር!” አለ።ይህንን፤የእድሜም ልዩነት፤ የስራ ልምድ አለመኖርም ምክንያት አድርጌ መለስን በብርቱ መክሬው ነበር። ከልቤ የመከርኩት አንድ ሰው ቢኖር መለስ ዜናዊን ነበር። ይህም የሆነው በሐምሌ 1983 ነበር።
ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላ፤ ቀጠሮ ይዤ፤ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኜ፤ የመለስም ሰዎች በነበሩበት አጋጣሚ ነበር። ምናልባትም ከሁለት ሰአት በላይ የወሰደ ይመስለኛል። ያዳመጠኝም፤የገባውም፤የተረዳኝም ነበር የመሰለኝ። ቀጣይ ድርጊቱን ሳየው በተቃራኒው የተረዳኝ ነው የሚመስለኝ። ተረዳኝ ያልኩት መምስልና ማስመሰል መሆኑ ነው።መለስና ኢትዮጵያ እንዴት ይተያያሉ? የሚለውን አጥኝዎች ቢያዩት ጥሩ ይመስለኛል።ወያኔ የተነሳው ለትግራይ ሬፑብሊክ ነው። አድሮ ዉሎ አሜሪካኖችና ሌሎቹም ደጋፊዎቻቸው ”ኸረ ትልቁ ዳቦም ይቻላል!” ሲሏቸው፣ በተማረከ ወታደር ካምፕም ተሯሩጠው ኢሕአዴግ የሚል ፍጥረት ፈጠሩ። ያ ማለት እንግዲህ የመለስ ልቡ፤ቢያንስ ሙሉ ልቡ ኢትዮጵያ አልነበረችም ወደ ማለት ይወስዳል። መንግስታችንና ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሆነ በኋላ ብዙ ተናግሯል። ከተናገራቸው አንዳንዶቹ በኢትዮጵያዊነቱና አብረን የምንካፈለው ማዕድ ስለ መኖሩ ጥርጣሬ ላይ የሚከት ነው። ለምሳሌ ያክል “የአክሱም ሐውልት ለዎላይታ ምኑ ነው?” ያለውን እንውሰድ። ማለትም፣ አክሱም የትግሬ ስለሆነ ዎላይታን አያገባውም እንደ ማለት ነው። ዎላይታ ለምሳሌነት ተነሳ እንጅ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም በአክሱም ነገር የሚያገባው ነገር የለውም እንደ ማለት ነው። ይህም ድንገት “የኛው የኛ! የኛ ብቻ! የእናንተም የኛ!” ነው ወደሚለው የሚወስድ ይመስለኛል። በተግባር ላለፈው 25 ዓመት የታዩት ይህንኑ የሚደግፉ ይመስለኛል።ሌላው አንዴ መቀሌ ለምን ይሆን ሔዶ የተናገረው ነው። ቃል በቃል አላስታውሰውም። የትግራይን ሕዝብ፤ “እንኳን ከእናንተ ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርኩ!” አለ። ይህን ሲል ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር። የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ባያምንበት እንኳን እንዴት አንዱን ብሔረሰብ ወርቅ ሌላውን ጨርቅ ይለዋል። የአባትነት፣ የመሪነት፤ በሰፊ መነጽር የማየት ንግግር አይመስለኝም። ሌላው ስለ ሰንደቅ አላማው የሚናገረው ነው። ጨርቅ ይለዋል። ሰንደቅ አላማ’ኮ የትም አገር ከጨርቅ ነው የሚሰራው! አርማ ስለሆነ ክብር እንጎናጸፋለን! ሰንደቅ አላማ ሲወርድና ሲወጣ ትምህርት ቤት ጭምር መዝሙር ይዘመራል። መንገድ የሚሔደውም፣ ባርሜጣ ካለውም አውርዶ ይቆማል። እንዳልኩት ዓርማ ነው! አይዘረጠጥም! “ከሰው መርጦ ለሹመት! ከእንጨት መርጦ ለታቦት!” እንዲሉ። ይህና ከላይ ስለ ሕገ መንግስቱ የተናገርኩት ሲጨመር የመለስ ዜናዊን ለኢትዮጵያ ያለው ታማኝነት በራሱ አንደበት የተነገረው ሲታይ የሚያጠያይቅ ይመስለኛል። እኔም ይኸው ማጠያየቄ ነው።
ከኔ ጋር ከአፍሪቃ አዳራሽ “የሰላምና የዲሞክራሲ ስብስባ (ድንቄም!) ጀምሮ ብዙም አልተጣጣምንም። ወደ መጀመሪያው “አቶ አሰፋ ለመሆኑ ምንድነው የሚፈልጉት?” ይለኝ ነበር። ሹመት ሽልማት እፈልግ እንደሁ ለመሰለል ይመስለኛል። ባንድ ሁለት ወያኔ ወዳጆቼ በኩልም የጠየቀኝ ይመስለኛል። ያ ሳይሆን ሲቀር ወረደብኝ። “ነፍስ ገሏል!” ብሎ በሌለሁበት 16 አመት ፈረደብኝ። ነገሩ “ወደ ኢትዮጵያ ዝር እንዳትል!” የሚል መልእከት ነው። ይኸው ዝር አላልኩም! አንድ ቀን በጥር 1984 የወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ለአሰፋ ጫቦ ብቻ አደረገው። ተስፋዬ ገብረ አብ በመጽሐፉ እንደሚለው፤ ያንን መለሰ ዜናዊ ጽፎት በረከት ስሞዖን አምጥቶ፣ ሌላው ሁሉ ይቅር ብሎ ጋዜጣው ላይ አስወጥቶታል፡፡
ለማጠቃለል
“ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ትገልጻለህ?” ከባድ ጥያቄ ቢሆንም ሞክሪያለሁ። ዋናው ነገር ለኢትዮጵያ ለወደፊቱ የተሻለ መንግስት እንጅ ካለፈውም ካለውም ምኑንም ምኑንም አልፈልገውም። የግድ አማርጥ ከተባልኩ ደግሞ የንጉሱን አልፈልግም። አስገባሪ፤ ባሪያ አሳዳሪ ስለሆነ አልፈልገውም! ንጉስ በችሎታ ሳይሆን በዘር ማንዘር ተረታ-ተረት ስለሚመጣ እኔ የምመርጠው የዘር ሳይሆን የባለሙያተኞች መንግስት ነው፡፡ ደርግንም አልፈልገውም! በአንጻራዊ አመለካከት ከሶስቱ ምረጥ ብባል ደርግን እመርጣለሁ። ደርግ ንጉስ አስወግዷላ! ኢትዮጵያን ሬፑብሊክ አድርጓላ! የገጠር መሬት አዋጅ አውጇላ! ለምስኪኑ ቤት ሰጥቷላ! የብሔረሰቦችን ጥያቄ በጥናት ለመወሰን የጥናት ተቋም አቋቁሟላ! የደርግ ዋናው ችግሩ የወረሰው ነበር! አብዮቱ በአብዮትነቱ ያመጣው ነበር! እናውቃለን ባዮች ለስልጣን ሲባል የወታደሩን ቃታ የሳብንበት፣ የቀረነውንም በሌላው ተጽዕኖ ህዝብ የፈጀንበት፣ ያፋጀንበት ባይኖር ደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም ሊያገኘው የማይችለው አይነት መንግስት ነበር! “ከመሔድሽ ሌላ ምንሽንም ምንሽንም አልፈልግም!” የሚባል የረሳሁት አባባል አለ። በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት መልካም ምኞቴ ይኸው ብቻ ነው!

Read 4274 times