Monday, 08 August 2016 05:43

የተስፋ እና የውጥረት ዓመት

Written by  አበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)
Rate this item
(7 votes)

*የኦሮሞ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች የተዋደቀበት ዓመት ነው!
*ህዝብን አልሰማህም ማለት ውጤቱ አደገኛ እንደሆነ የተማርንበት ዓመት!
*ፖለቲካዊ ስርዓቱ እንዴት ኋላ ቀር እንደሆነ የተገነዘብንበት ዓመት ነው!

   ከኋላቀርነት ወደ ስልጣኔ በሽግግር ላይ ባለ አገር፣ አለመረጋጋት በጊዜው የሚያጋጥም ክስተት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን አበክረው ይገልጻሉ፡፡ ያለ መረጋጋት በሚኖርበት ጊዜ የሰው ባህሪ ሆኖ፣ የመጨነቅና ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ተብሎ የተስፋ መቁረጥ አዝማሚያ ይከሰታል፡፡ ተገቢ ትኩረት (concern) ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ያለመረጋጋት ሁኔታ በደንብ ከተጠና እና አዎንታዊ ፍጻሜዎችን መገንዘብ ከተቻለ፣ አገሪቷና ህዝቦችዋ ወደ ቀጣይ ከፍተኛ አጠቃላይ የዕድገት ለውጥ ሊያሻግሩ (leap) የሚችሉ ክስተቶች ጎልተው ሊለዩና ሊወጡ ይችላሉ፡፡
 በ2008 ዓ.ም የታየው አለመረጋጋት፣ ተስፋም ጭምር የሰነቀ መሆኑን መገንዘብ ለቀጣይ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚሁም ሲባል ተስፋውን በማስቀደም፣ ያለመረጋጋቱ ያለበትን ደረጃና  ምክንያቱን በዝርዝር ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም በፃፍኳቸው መጣጥፎችና በሰጠኋቸው ቃለመጠይቆች፤ “ኢህአዴግ ቆሟል ወይም ወደ ኋላ እየነጎደ ነው” ማለቴን የሚጣረስ ሃሳብ ነው ብለው የተቹ አልጠፉም፡፡ በአንድ በኩል የሚያበረታታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እየተመዘገበ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህን ለውጥ ያመጣ ገዢ ፓርቲ ቆሟል ወይም ወደ ኋላ እየነጎደ ነው የሚለው ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ዕድገቱን ማመን ፖለቲካዊ ብልሹነት መኖሩን ለማሳየት እንደማያግድና የማይጣረስ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
በአሁን ጊዜ ኢህዴግን ከአራት ኪሎ ጠቅልሎ ለማስወጣት የሚፈልጉና የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ፡፡
ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው ነው፡፡ የተወሰኑት በሕገ-መንግስትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዓላማቸውን ለማስፈፀም እየታገሉ ነው። ከፊሎቹ የትጥቅ ትግልን እንደ ገንዘብ ማሰባሰብያ ሲያደርጉት፣ አንዳንዱ ደግሞ ሕገ-መንግስቱ ያለቀለት ነው በማለት ሌላ አማራጭ ሳያቀርቡና ሳይታገሉ በአቋራጭ ወደ ቤተ-መንግስት ሰተት ብለው ለመግባት ይፈልጋሉ:: ሕገ-መንግስቱ በኢህዴግ አቀንቃኝነት (መሪነት) የፀደቀ በመሆኑ፣ በኢህአዴግ በተለይ በህወሓት ላይ ባላቸው ጭፍን ጥላቻ ጭራሽ ስለ ሕገ-መንግስቱ እንዲነሳ የማይፈልጉ አሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ያለው የዴሞክራሲያዊ ምህዳር መጥበብና የሰብአዊ መብት መረጋገጥ፣ ከሕገ-መንግስት ግድፈት እንደሚመነጭ አድርገው በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም፣ ሕገ-መንግስቱን ውድቅ የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በኢህአዴግ መሪነት ይህን ሕገ-መንግስት በማጽደቃቸው ምስጋና የሚገባቸው ሲሆን ኢህአዴግም የሚወቀሰው ሕገ-መንግስቱን በግልጽ በመጻረር አገሪቷን ለአደጋ እያጋለጣት በመሆኑ ነው፡፡ አሁንም ሕገ-መንግስቱ ይከበር እንላለን፡፡ የህዝቦችን መብቶች በተሟላ መንገድ በማረጋገጥ፣ኢህአዴግ ቢመረጥ እሰይ እንላለን፡፡ (ኢህአዴግ ስልጣን ላይ እያለ ይቻላል አይቻልም የሚለውን ለጊዜው ትተን) ኢህአዴግ ቢሸነፍ ደግሞ አመስግነን ለቀጣይ ተዘጋጅ እንለዋለን፡፡ ለሚያሸንፈው ፓርቲ/ፓርቲዎች ደግሞ እንኳን ደስ አለህ! ብለን ግን ወደ ስልጣን ያደረሰውን ሕገ-መንግስት እንዳይሸረሽረው እናስጠነቅቀዋለን፡፡ ለዚህ ሲባል የሁሉም ፖለቲካዊ ተቋሞች መመዘኛ ሕገ - መንግስቱ እንደሆነ ለማሳየት የሕገ መንግስቱን ይዘት በአጭሩ እንዳስሰዋለን፡፡
 ሕገመንግስታችን - የጋራ ዋስትናችን
ሕገ-መንግስታችን የአገሪቱ የበላይ ሕግ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ አሉ የሚባሉት መብቶችን በተሟላ መንገድ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው ማክበርና ማስከበር ያለብን፡፡ ሕገ-መንግስታችን ዋስትናችን፣ የሁሉም ችግሮቻችን መፍትሄዎች ማጠንጠኛና የጋራ እሴት መፍጠሪያ መሳሪያችን ነው ሲባልም ይህንን መጠነ ሰፊ የመብቶችና የእሳቤዎች አቃፊ ሰነድ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግስት አንዱን ህዝብ ወይም ባህል የበላይ፣ ሌላዉን የበታች ለማድረግ ያልተሰራና ሁሉንም በሕግ አግባብ እኩል ለማኖር፣ ዜጎች መብቶቻቸዉ እዉቅና አግኝተው፣ በሰላም ለጋራ አገር እሚሰሩበት፣አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ታልሞ የፀደቀ ሕገ መንግስት ነው።
 በተባበሩት መንግስታት ተቀባይነት ያገኙትን የሶስት ትውልድ ሰብአዊ መብቶች (Three Generation of human rights) ያቀፈ ነው፡፡ ሲቪል -ፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ፤የጋራ እና ልማት (Collective and Development Rights) ሰብአዊ መብቶችን ያረጋግጣል፡፡ ዓለም ዓቀፍ ሕጎች፤ህዝቦችና ሃገሮች በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው የመወሰን መብት ይሰጣሉ፤እስከ መገንጠል የሚለው መብት ሊጠቃለል ይችላል የሚለው ትርጉም አነጋጋሪ ቢሆንም::
 እነዛ መብቶች ከአንቀጽ 10- 44 ውስጥ የተካተቱ ሲሆኑ ከ45 – 84 እነዚህን መብቶች እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆነውን የመንግስት አወቃቀር ይዘረዝራል፡፡ ከአንቀጽ 85 – 93 እነዛ ሶስቱን የሰብአዊ መብቶች ትውልዶች ለማጠናከር የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎችን ይዘረዝራል፡፡ ከ94 -102 ፋይናንስና ታክስን የተመለከተ ሲሆን አንቀጽ 103 የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን፣ አንቀጽ 104 እና 105 የህገ-መንግስት ማሻሻያ አግባብን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ሕጋዊ እውቅና ስላለው ቅጅ ይመለከታል፡፡
ማንም ዜጋ ይህ መብት ያስፈልጋል አያስፈልግም ማለት መብቱ ሲሆን ፍጹም የሚባል ሕገ-መንግስት ባለመኖሩ ምክንያት የሚጨመሩና የሚቀነሱ አንቀጾች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ ግን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰላም፣ የዕድገትና የአንድነት ሕግ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሕገ-መንግስቱ አጨቃጫቂ የሆኑት ብሄርን ማእከል ያደረገ ፌደራላዊ ስርዓትና አንቀጽ 39/1፤ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ እና ህዝብ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መልክ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚለው ነው፡፡ ይህ አንቀጽ በሕገ-መንግስቱ ሲሰፍር፣ በኢትዮጵያ ልዩ (Unique) ቢያደርገውም በእኔ አመለካከት የዴሞክራሲ እሴት inherent Characteristic ነው። የትኛዉም ህዝብ በሆነ አገር ተገዶ መኖር የለበትም ከሚል የዴሞክራሲ መርህ የሚነሳ ነው።።
 በሕገ-መንግስታቸው ባይሰፍርም ችግሩ ፈጥኖ ሲመጣ እንደ መብት የሚቀበሉና ተግባራዊ የሚያደርጉ ዴሞክራሲያዊ አገሮች አሉ፡፡ የተጻፈ ሕገ-መንግስት የሌላት ታላቋ ብሪታንያና ሰሜን አየርላንድ፤በስኮትላንድ ሕዝብ ጥያቄ መገንጠል ወይስ በህብረቱ መቆየት እንደ አማራጭ ተወስዶ ህዝብ ውሳኔ (Referendum) ተካሂዷል። በተመሳሳይ መንገድም በካናዳ የኩቤክ ግዛት ህዝበ ውሳኔ ተደርጓል፡፡ ቼኮዝሎቫኪያ ወደ ቼክ እና ስሎቫኪያ ለሁለት የተከፈሉበትና ቀደም ሲል ኖርዌይ ከስዊድን የተገነጠለችበት ሁኔታ ከዚሁ የዴሞክራሲ እሴት የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡
እንዲሁም ታላቋ ብሪታንያ፤ ብሄር ተኮር የሆነ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ባላቸው ክልሎች የተዋቀረች አገር ናት። እንግሊዝ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስና ሰሜን አየርላንድ ይባላሉ። ሌላው ቢቀር በአውሮፓ እግር ኳስ የራሳቸውን ቡድን ይዘው ነው የሚሳተፉት። በስፔንና በሌሎች አገሮች ተመሳሳይ የሆነ ብሄር ተኮር አስተዳደር መኖሩ ይታወቃል።  ብሄርን ማዕከል ያደረገውን የፌደራል ስርዓቱንና አንቀጽ 39/1 የሚደግፉም የሚቃወሙም መኖራቸው የታወቀ ሲሆን ሕገ-መንግስቱ ራሱን በራሱ የሚያሻሽልበት አንቀጾች ስላሉት ሶስት ትውልድ ሰብዓዊ መብቶች ከተተገበሩ፣ ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ የሚፈልጉትን ማስተካከል ይችላሉ፡፡ በሕገ-መንግስቱ ማሻሻያ አንቀጾች፣ ራሳቸው ለህዝብ ውሳኔ መቅረብ በሕገ-መንግስታዊ መርሆች የሚቻል በመሆኑ፣ ሕገ መንግስቱን እንደ አይረቤ ነገር አሽቀንጥሮ መጣል ለ ሕገ-መንግስት እንቅፋት መፍጠር ካልሆነ ሌላ የሚያዋጣ ሂደት በአሁኑ ሰዓት ሊፈጠር የሚችል አይመስለኝም። ለምናደርገው ሂደት አቃፊ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ሕገ መንግስታችን ነው። የአገራችንን ሰላም፣ ዕድገት፣ አንድነት የሚፈልግና ተጠቃሚ ለመሆን የሚሻ ሁሉ፣ ማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሰላምና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ ሊሆን ይገባዋል ብሎ መነሳት ያለበት ይመስለኛል። ፖለቲካዊ ድርጅቶች ተራማጅ ወይም ወደ ኋላ የሚነጉዱ መሆናቸውን መመዘኛው ያው ሕገ-መንግስታችን መሆን ይገባዋል፡፡ ሕገ-መንግስታችን ዋስትናችን፣ ጥላችን በመሆን ባልተሸራረፈ መልኩ ይከበር እንላለን፡፡
ሕገ መንግስቱን ማጣጣልና ሌላ አወቃቀር ለማምጣት መሞከር እነዚህ የሶስት ትውልድ መብቶች ለኢትዮጵያ ህዝቦች አያስፈልጋቸዉም እንደሚለው የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ነው። የኢህአዴግ ሕገ መንግስቱን መሸርሸር አዲስ “ደርግነት” እንዳይመጣ ስጋት ውስጥ እንደሚከተን ሁሉ፣ ሕገ መንግስቱን ለማስወገድ መሞከር አሮጌ “ደርግነት;ን ለማምጣት መከጀልን ያሳያል።
 2008 ዓ.ም፤የትግል አመት
 በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም የኢህአዴግ በሚባሉ ክልሎች (ኦሮሚያ፣አማራ፣ ትግራይና ደቡብ) በሕገ-መንግስታችን መሰረት፣ መብታችን ይከበር በሚል በተለያየ ደረጃ የሕዝቦች እንቅስቃሴ የታየበት፣በተወሰነ ደረጃም ድል የተገኘበትና ለቀጣይም ተሞክሮዎቻቸውን ቀምረው ከፍተኛ ትምህርት በመውሰድ፣ ትግላቸውን የሚያቀጣጥሉበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
 የመጀመሪያ ተጠቃሽ የሚሆነው የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ ነው፡፡ ተቃውሞው በአዲስ አበባና አካባቢዋ ማስተር ፕላን ነው የተቀሰቀሰው ተብሎ ቢነገርለትም፣ ከዛ በላይ የቆየና የጠለቀ (deep) ችግሮች ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ሕገ-መንግስታችን ያረጋገጠልን፤ “ሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የጋራ መብቶችና የልማት መብቶች ይከበሩልን” ብለው ነው የጠየቁት። በአጭሩ ሶስቱ የሰብአዊ መብቶች ትውልዶች (Three generations of human rights) ይከበሩ ነው ያሉት፡፡ በአጠቃላይ 2008 ዓ.ም የኦሮሞ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች የተዋደቀበት ዓመት ነው፡፡ ራሳችንን የማስተዳደር ሙሉ መብታችንን ያረጋገጠልን በፌዴራል መንግስት ያለን ድርሻ ይስተካከልልን፣ የግለሰብ መብቶችም ይከበሩ የሚል ነበር እንቅስቃሴው። ተቃውሞው፤ 100% በምርጫ አሸንፌአለሁ እያለ ሲኮፈስ የነበረውን ኢህአዴግ በተለይም ኦህዴድን ያርበተበተ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ ቆሜያለሁ እያለ ሕገ-መንግስቱ በአንቀጽ 49/5 ያለውን ልዩ ጥቅም ሳይተገብር፣ ለ21 ዓመት ከአንቀላፋ በኋላ በህዝቡ ትግልና ቀስቃሽነት “እናጠናዋለን” ያለበትና የአዲስ አበባና አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች ማስተር ፕላን የህዝቡን ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው፣ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ የከሸፈበት እንቅስቃሴ ታይቷል፡፡
 በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኦሮሚያ መንግስት ላይ መነቃቃት ፈጥሮ፣ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ባይሆንም የተለያዩ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ የህዝብ ትግል ውጤት ነው፡፡ ለበለጠ ትግል የሚያደፋፍር፡፡
አክራሪዎች የህዝቡን አጀንዳ በመጠምዘዝ፣ በኦሮሞና በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች መካከል መሰረታዊ የጥቅም ግጭትና ጠላትነት እንዳለ በማስመሰል፣መተራረድን ሲሰብኩ ህዝቡ ግን ጨዋነትና ብልህነት በተሞላበት ሁኔታ ተከላክሎ፣ ትልቁ ብሄር የቻይነት ተምሳሌት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲ ከፍተኛ ዕድገት ምንጭ መሆኑን ባለማወላወል ያረጋገጠበት ዓመት ነበር፡፡
በቅርቡ በጎንደርና አካባቢዋ በተከሰተው ችግር፣ በተመሳሳይ መንገድ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የአክራሪዎች እንቅስቃሴ በህዝቡ ጨዋነትና ቻይነት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሊገታ ችሏል፡፡ ህዝቡ በጽንፈኞች ተገፋፍቶ በስህተትም ቢሆን ቢቀላቀል ኖሮ ሊደርስ የሚችለውን ጥፋት መገመት ይቻላል፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ብሄር ብሄረሰብን ለማጋጨት በጽንፈኞች የተደረገው ሙከራ የከሸፈበት ዓመት ነበር ማለትም ይቻላል። በግጭቱ የተጎዱትን ዜጎች ለማቋቋም በአንዳንድ አካባቢዎች እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅ ነው፡፡ በፌደራልና በአማራ ክልል የነበረው የጥምር እንቅስቃሴና ህጋዊነት፣ ለደረሰው ጥፋት ምን ዓይነት ሚና ነበረው የሚለው የሚያጠያይቅ ቢሆንም፡፡
እነዚህ የህዝቦች እሴቶች/ክብር (Values) አሁን የመጡ አይደሉም፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ ናቸው፡፡ በእኛ ትውልድ እንኳን በ1966 ዓ.ም አብዮት አካባቢ መንግስት ፈርሶ በሌላ በሚተካበት ሁኔታ፤ በ1983 ዓ.ም ደርግ ተደምስሶ ኢትዮጵያ መንግስት አልባ በሆነችበትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ወታደሮች (ከሞትና ከመማረክ የተረፉት) በተበታተኑበት ሁኔታ፣ ህዝቦች ባላቸው እሴት የከፋ ችግር ሳይታይ አልፏል፡፡ በግንቦት 1983 ዓ.ም በተለይ የአዲስ አበባን ሁኔታ ያየ፣ እሴቶቻችንን በሚገባ መገንዘብ ይችላል፡፡ የአገሪቱ ሃብት የተከማቸበት ከተማ ተብላ ስለምትታስብ፣ ብዙ ዝርፊያዎችና ግድያዎች ይፈጸሙ ይሆናል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም፣እዚህ እዚያም ካጋጠሙት ትናንሽ ችግሮች በስተቀር ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም  አዲስ አበባን ለመዞር ዕድል ያጋጠመው ሰው፤ በኩራት ስለ ህዝባችን ጠንካራ ትስስር ሊመሰክር ይችላል፡፡
በ1997 ዓ.ም  ምርጫ ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል፣ የዘረኝነት መርዝ ለማስፋፋት ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ (ትግሬ ወደ መቀሌ ዓይነት)፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት “ኢንተርሃምዌ” ቢሰራጭም፣ መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎችና መጣራት  ካለባቸው በቀር በህዝቦች መሃል ግጭት ሳይፈጠር አንድነቱን ጠብቆ አልፏል። እነዚህን እሴቶች እንወቃቸው፣ እንንከባከባቸው፤ ለምናደርገው ለውጥም እንጠቀምባቸው፡፡
 ለዓመታት ሲብላላ የቆየው የእምባስነይቲ “የወረዳ ይመለስልን” ጥያቄ፤በትግራይ ክልል በያዝነው ዓመት የተከሰተ መብት የማስከበር እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንደ ሌላው ሁሉ ብዙ መጽሐፍት ሊጻፍበት ይችላል፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤“ያ ህዝብ ፖለቲካዊ ብስለቱንና ሞራላዊ ብቃቱን ያስመሰከረበት እንቅስቃሴ ነው፡፡” የተለያዩ ሙከራዎች አድርጎ ሳይሳካ ሲቀር፣ ሕገ-መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ፣ ለክልልና  ለፌደራል ፓርላማ የመረጣቸውን ወኪሎች ለማንሳት (Recall) ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገ ሲሆን ሁከት እንዳይኖርም ጥንቃቄ የተመላበት አካሄድን ተከትሏል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትና በህዝቡ  በራሱ ተነሳሽነት ብቻ የተካሄደ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ሆኖም ተመዝግቦለታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በጎንደር በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፣ (ከመንግስት እውቅና ይኑረው አይኑረው እንተወውና) ህዝቡ ተቃውሞውን አሰምቶ ያለ ምንም ረብሻ በሰላም ወደ ቤቱ መግባቱ በእጅጉ ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡ የአንዳንድ አክራሪዎች ዘረኛ መፈክሮች ቢታይበትም ህዝቡ መብቱን ለማረጋገጥ የወጣበት ሰልፍ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
 በእምባስነይቲ የግብር ጊዜ ሲደርስ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ግብር መክፈል አለብን ብሎ የተነሳበት ሁኔታም ታይቷል፡፡ የክልሉ መንግስት ይህን የህዝብ እንቅስቃሴ እንደ ትልቅ የማይገኝ ድል ቆጥሮ፣ችግሮችን ከህዝብ ጋር ተወያይቶ ከመፍታት ይልቅ እንደ ሽንፈት ቆጥሮ በማስፈራራት፣በመከፋፈልና ችግሩን ውጫዊ በማድረግ “ትምክህቶች በወልቃይት ጉዳይ እያስቸገሩን፣ እናንተ ደግሞ በስተጀርባችን ትወጉናላችሁ” በማለት ጉዳዩን ለማቀዛቀዝ ሞከረ። ትልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው የተባለውንና የታላቋ ብሪታንያ 52% ድጋፍ ያገኘውን ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ጥያቄ መቀበልና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሱን ከስልጣን ያገለለበት ሁኔታን፣ እስቲ ከ90% በላይ ድጋፍ ካለው የእምባስነይት “የወረዳ ይመለስልን” ጥያቄ እንቅስቃሴ ጋር አወዳድሩት፡፡
የቅማንት ህዝብም ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፍል ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በከፊልም ቢሆን ማረጋገጥ የቻለበት፤ ህዝብን አልሰማህም ማለት ውጤቱ አደገኛ እንደሆነ የተማርንበት ዓመትም ነበር። በአጠቃላይ ህዝቦች በተደራጀና ባልተደራጀ ሁኔታ ተጠናክረው መታገል የጀመሩበት ወቅት ሲሆን ፖለቲካዊ ስርዓቱ እንዴት ኋላ ቀር እንደሆነም የተገነዘብንበት ዓመት ነው፡፡ ከህዝቦች ጋር እንሰለፋለን የሚሉ ወገኖች÷የታየውን ድልና ኪሳራ በማስላት በሰላማዊ መንገድ ታግለው፣ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሕገ-መንግስቱን በመተግበር ፋና ወጊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ያጋጠመንን ከፍተኛ ድርቅ፤ በራሳችን አቅምና በለጋሶች እርዳታ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ መፍታት መቻላችን መጤን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አገራችን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በከፍተኛ ድምጽ መመረጥዋ፣ ከነችግርዋ ተቀባይነት እያገኘች መሆኗን ያረጋግጣል፡፡
ይህ ዓመት GTP 2 የታወጀበት፣ በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም ውይይት የተደረገበትና እንደ ህዳሴ ግድብ ወ.ዘ.ተ. ያሉት፣ በመጨረሻም “አዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ” ፍፃሜን  ያየንበት ወቅት ሆኖ ተመዝግቧል። የ2009 ዓ.ም በጀት መጨመሩም የሚሰመርበት ሁኔታ ነው። በተጨማሪም  ደምሒት ከኤርትራ መንግስት ስር ተጠግቶ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሃይል መሆን እንደማይችል ተገንዝቦ፣አባላቱ የመሰሪ ሃይሎች ተላላኪ ላለመሆን ወደ ሃገራቸው ገብተው፣ ምህረትና ተሃድሶ ተደርጎላቸው ሰላማዊ ህይወት የጀመሩበት ዓመት ነበር።
የፀጥታ አለመረጋጋት
በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ እንዲሁም በጎንደር አካባቢ ለታዩት አለመረጋጋቶች በአንድ በኩል የኤርትራ እጅ አለበት ሲባል፣ በቀጥታም በራሱ ኃይሎች የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ሲያተራምስ የታየበት ዓመት ነው፡፡
2008 ዓ.ም “ተመጣጣኝ” እርምጃ የሚለው “መፈክር; መነጋገሪያ የሆነበት ዓመት ነው፡፡ በጋምቤላ ክልል ዜጎች የተገደሉበትና የተዘረፉበት ዓመት ቢሆንም በንዝህላልነት ይሁን በሌላ እስከ አሁን ድረስ ተጠያቂነትና ግልጽነት ባለው መንገድ ለጥፋቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል አልተገኘም፡፡ በኦሮሚያ ለደረሰው ጉዳት በአንድ በኩል ይቅርታ የተጠየቀበት በሌላ በኩል ደግሞ “የተወሰደው እርምጃ” ተመጣጣኝ ነው” የተባለበት ዓመት ነው። የችግሩ ምንጭ መንግስት፣ወደ አላስፈላጊ ግጭት የመሩት ደግሞ አክራሪዎች በመሆናቸው ሁለቱም መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም በህዝቡ ላይ ለደረሰው ሞት፣ መቁሰል፣ መታሰር፣ ንብረት መውደም---- “የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ” ነው በሚል መታለፉ አሳዛኝ ነው።
በቅማንት ህዝብ ላይ ለደረሰው ግፍ ተጠያቂው ቢለይም የተወሰደው እርምጃ ገና አልታወቀም። ከኦሮሞ ግጭት በምን እንደሚለይ ግን ለብዙዎች አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አስቦና አቅዶ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚወሰደው “ተመጣጣኝ” እርምጃ፣ ያው እንደ ሌላው ሁሉ የሚገርም ሆኗል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሻዕብያን የማተራመስ ዓቅም ከግምት ውስጥ ያስገቡ አንዳንድ ወዳጆቼ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት፤ለሻዕብያ የሚሰጠው የተመጣጠነ ምግብ ነው እንዴ?” ብለው እስከ መሳለቅ ደርሰዋል፡፡
  ፖለቲካዊ አለመረጋጋት
    የግንቦት 2007 ዓ.ም 100% የምርጫ ውጤት አስቂኝና አደገኛ ለመሆኑ አያነጋግርም፡፡  ከዚህም አንጻር የተከማቸውን የህዝቡ ብሶት በማቀጣጠል ረገድ ሚናው የጎላ ነበር፡፡
 በ2008 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ በተደረገው የኢህአዴግ ጉባዔ፣ በግንባሩ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውና የችግሮቹ ጥልቀትና ስፋት እንዲሁም ምንጭ በሚገባ ሳይታወቅ፣ በተዘበራረቀ ሁኔታ “የመልካም አስተዳደር ችግር” በሚል ተሸፋፍኖ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ህዝብ በነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳ  በህወሓት ጉባዔ ሁሉም “ጉዶች” ቢወጡም፣ቀስ በቀስ በመልካም አስተዳደር ሽፋን ሁኔታው እንዲቀዛቀዝ ተደርጓል፡፡  የኢህአዴግ ድርጅቶች በትምክህትና ጠባብነት መወነጃጀል የጀመሩበት፣ እንደ ወልቃይት ያሉ ጉዳዮችን ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ መፍታት አቅቷቸው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሲሆኑ ታዝበናል። በተጨማሪም እርስ በእርስ የመወነጃጀልና መጠነ ሰፊ ኔትዎርኪንግ የታየበት እንዲሁም በተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ መከፋፈልና መሰነጣጠቅ የበዛበት ዓመት ነው ሊባል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የመከላከያ አመራሮች ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ያሳዩበትና ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተመቻቸ ሁኔታ የተፈጠረበት ዓመት ነበር -2008።
  ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት
ታዳጊ ይሁን የበለፀገ ኢኮኖሚ ባላቸው አገራት፤ ከውጭ በሚመጣ ተፅእኖ ወይም ከውስጥ በሚከሰት ችግር መንገራገጮች ሊገጥሙ ይችላሉ። የፀጥታ ችግር፣ ድርቅ፣ እንደ ነዳጅ ያሉ ጥሬ ሃብቶች መዋዠቅ፣ የበለፀጉ አገሮች ኢኮኖሚ ወደ ውድቀት መግባት ወ.ዘ.ተ.  በሚፈጥረው ምስቅልቅል ሳቢያ በድሃ አገራት ኢኮኖሚ ላይ አለመረጋጋት ሊታይ ይችላል፡፡ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ለታየው ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት፡- ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ችግር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙም ቀጥሏል፡፡
  ዝምታ የሚያመረቅዝ መርዝ ሊሆን ይችላል
 በኦሮሚያ የደረሰውን ጉዳት ነፃ አጣሪ ቡድን አቋቋሞ፣ በሚገባ ከማጣራት ይልቅ “ተመጣጣኝ እርምጃ” ነው ብሎ አዳፍኖ ማለፍ፣ ነገ ከነገ ወዲያ የሚያመረቅዝ ቁስል ሆኖ እንዲያገረሽ ስለሚያደርገው ፍትሐዊ የሆነ መልስ ያስፈልገዋል፡፡ በጋምቤላ ለተከሰተው ችግር ተጠያቂው ማን ነው? ምን እርምጃ ተወሰደ? ሲባል አሁንም መልሱ ዝም ጭጭ ሆኗል። ይሄም የሚያመረቅዝ ቁስል ከመሆን አይተርፍም፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስኳር ኮርፖሬሽን በሜቴክ ላይ ያቀረበው ሪፖርት ተጣርቶ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ይባስ ብሎ የምክር ቤቱ አባላት አንዳንድ ፋብሪካዎችን በመጎብኘት አድናቆታቸውን ሲገልፁ ተመለከትን፡፡
“ሜቴክ ያሸማቅቀናል÷ ምንም ማድረግ እንደማንችል ታውቃላችሁ” እየተባለ አሁንም ዝምታ!! ከስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት በመነሳት ሌሎችም ትላልቅ የመንግስት ሃብት የሚያንቀሳቅሱ እንደ ቴሌ፣ ሲቪል አቪየሽን፣ ባቡር ኮርፖሬሽን ወ.ዘ.ተ ይፈተሹ እንደ ማለት አሁንም አገሪቱ ላይ ዝምታ! መከላከያና የተወሰኑ የፌዴራልና የክልል መንግስታዊ ተቋማት የአንድ ድርጅት ልሳን መደጎማቸው ፀረ - ሕገመንግስት ነው ሲባል ዝምታ!! ኤታማዦሩ ህ.ወ.ሐ.ት/ኢ.ህ.ዴ.ግ ከሌለ የትግራይ ህዝብ /ኢትዮጵያ የለም፡፡
ሁሉም ችግሮች በኢህዴግ ብቻ ነው የሚፈታው፤ ፖለቲካዊ አመራርን ማንኳሰስ በተለይም ፀረ-ሕገ-መንግስት አቋሞች ሲንፀባረቁ አሁንም ዝምታ ሆነ!! ሰራዊቱ ለኢህአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ነው የሚለው ከሰራዊት ግንባታ ይውጣ/ይታገድ ሲባል ዝምታ!! …. የሚያሰጋው ስርዓቱን መልሶ የሚያቃጥል ዝምታ እንዳይሆን ነው !
በአጠቃላይ ህዝቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች፡- በመንግስት መዋቅር የሚፈፀሙ ሕገ-መንግስቱን የሚጻረሩ ተግባሮች ወይም ባለመፈጸማቸው የሚከሰቱ ችግሮች እንደ አጣዳፊነታቸው መልስ የሚሰጥበት ሁኔታ የለም፡፡
 በዚህ የቆሰለው ህዝብ፤መንግስት የለም እንዴ? ብሎ ተስፋ ቆርጦ ሲነሳ ማጣፊያው ያጥረናል፡፡ ዝምታ የሚያመረቅዝ መርዝ ሆኖ ሁላችንም እንዳይበላን፣ የአገራችንን ሰላምና እድገትም እንዳይፈርስ ከወዲሁ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡  
 ለምን አለመረጋጋት?
 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሲኖር በህብረተሰቡ አዲስ ማህበራዊ መዋቅር፣ አዳዲስ ሃይሎች የነበሩት እየተቀየሩና እያደጉ ስለሚሄዱ፣ ህብረተሰቡ የተቋዳሽነት ደረጃው እየገመገመ የተለያዩ አዳዲስ ፍላጎቶች ማቅረቡ አይቀርም፡፡
ግሎባላይዜሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወ.ዘ.ተ. አጠቃላይ ፖለቲካዊ መብቶችና የኑሮ ሁኔታ ስታንዳርድ ማስቀመጣቸው ስለማይቀር ህብረተሰቡ ለበለጠ ዕድገት፣ ሰብአዊ መብቶቹም የበለጠ እንዲጠበቁለት ይጠይቃል፣ ይታገላልም፡፡ ተጨማሪና ፍትሐዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች በራስ ማስተዳደር (Self –rule)  እና በጋራ መስተዳደር (Shared rule) የበለጠ እንዲጠናከር ይፈልጋሉ፡፡ ግለሰቦችም በተለይ ወጣቶች ከስራ አጥነት ለመላቀቅ፣ ጥሩ መተዳደሪያ ለማግኘት ይሻሉ፡፡
በትምህርት ቤት፣ በመገናኛ ብዙኃን ወ.ዘ.ተ. የታወቁላቸውን መብቶች (Recognized Rights) ይበልጥ ለማረጋገጥ ይፈልጋሉ፣ ይታገላሉም። የወጣትነት እኩልነት ተጨምሮበት ሁሉም በአጭር ጊዜ እንዲፈጸሙላቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡  (ይቀጥላል)

Read 5652 times