Monday, 08 August 2016 05:49

ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ላለፉት 9 ወራት በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ተቃውሞና ግጭት እንደ ሂዩማን ራይትስዎች ሪፖርት፤ ከ400 በላይ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጓል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ፤ የሟቾች ቁጥር 600
መድረሱን ይገልፃል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ሌሎች ብዙ ሺዎች ደግሞ ግጭቶቹን ተከትሎ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ አሁንም ውጥረቱና አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰሞኑን በአርሲና
ሀረርጌ አካባቢዎች ተቃውሞና ግጭቶች አገርሽተው የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞንም ቀደም ሲል ከቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ ከሰሞኑ ደግሞ በወልቃይት የማንነት
ጥያቄ ሳቢያ በተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶች የበርካቶች ህይወት አልፏል፡፡ ባለፈው እሁድ በብዙ ሺዎች የሚገመት ህዝብ በጎንደር የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄደ ሲሆን ተመሳሳይ ሰልፍ በኦሮሚያ ከተሞችና በባህር ዳር
ከተማ ዛሬና ነገ ለማካሄድ ጥሪ ተላልፏል፡፡ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የህዝብ ተቃውሞ መንስኤ ምንድነው? ችግሩን ለመፍታት መንግስት ምን ጥረት አደረገ? በምሁራን በኩል ለምን ዝምታ አረበበ? የፖለቲካ
ቀውሱ እንዴት ሊፈታ ይችላል? ያነጋገርናቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች፤ መንግስት በአፋጣኝ ወደ ውይይት ካልመጣ፣ አገሪቱ አስከፊ ሁኔታ ሊገጥማት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳንና አቶ ልደቱ አያሌውን እንዲሁም ዕውቅ የሃይማኖት ልሂቃንን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯል፡፡


“ሃገር እንዳትበታተን ሁሉም ለውይይት መቀመጥ አለበት”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
በ2007 ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል ተብሎ፣ ገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ የፓርላማ ወንበር በያዘ ማግስት፣ በኦሮሚያ እንዲህ ያለ የህዝብ ተቃውሞ መነሳቱ፤ በደቡብ ክልል ኮንሶ አካባቢ፣ በአማራ ሰሜን ጎንደር ደግሞ የቅማንትና የወልቃይት ጉዳይ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ህገወጥ በሚል የቤቶች መፈራረስ ያስከተለው ችግር ብዙ ጉዳዮችን አመላካች ነው፡፡
ህዝብ እንግዲህ በየቦታው እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ይዞ አደባባይ እየወጣ ነው፡፡ ባለፈው እሁድ በጎንደር እውቅና ሳይሰጥ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱ፣ ሌላው ህዝብ የመብት ጥያቄዎችን በዚህ መንገድ እንዲጠይቅ ማነቃቂያ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ካልሰጠ፣ ጉዳዩ ወደ መጥፎ ነገር ሊሄድ ወደ አሰቃቂ የእርስ በእርስ ጦርነትም ሊያመራ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የሚቀጥል ከሆነ ወደ ሀገር የመበታተን አደጋ አለው፡፡ ሀገር እንዳትበታተን ከተፈለገ እንግዲህ ሁሉም በሰከነ መልኩ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት አለበት፡፡ ኢህአዴግን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ምሁራን ተሰባስበው… ምን እናድርግ በሚለው ላይ መወያየትና የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ እዚህ ሀገር ቤት ያለነው ጉዳዩን ዝም ብለን የምንመለከት ከሆነ፣ የውጭ ኃይሎች ይሄን እድል ተጠቅመው ሀገሪቱን ሊያፈራርሷት ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፤ እነዚህን ችግሮች ብቻውን የሚፈታው አይመስለኝም፡፡ አሁን በየአካባቢው የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ወደ አልሆነ አቅጣጫ ቢሄዱ መመለሻ አይኖራቸውም፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተፈለገለት በጣም አስጊ ነው፡፡ መንግስት፤ የፀጥታ ሀይሉ የሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ጥብቅ ትዕዛዝ ማስተላለፍ አለበት፡፡ ተቃውሞና ግጭቱን ተከትሎ የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱበትን ሁኔታም መንግስት ማሰብ ይኖርበታል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣ ህዝብ ልክ እንደ ጎንደሩ፣ በፀጥታ ኃይሉ የደህንነት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ህዝቡም ልክ እንደ ጎንደሩ ሰልፍ፣ መሳሪያ፣ ዱላ የመሳሰሉትን ሳይዝ፣ ሰልፍ የማድረግ ልማድ ማዳበር አለበት፡፡
መንግስት የህዝብ ጥያቄዎችን በሙሉ የውጭ ተላላኪዎች ወይም የሽብርተኛ ድርጅቶች ነው በሚል ከመፈረጅ ይልቅ ራሱን መመርመር አለበት፡፡ ህዝቡ በአመራሩ ምን ያህል እርካታ አለው? የሚለውን በቅጡ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡

===============================

‹‹መንግስትና ህዝብ በችግሮቹ ላይ በጥሞና መነጋገር አለባቸው››

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን
(የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)
መንግስትና ህዝብ በሃገሪቱ በሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ላይ በጥሞና ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው፡፡
ህዝቡ ጥያቄውን በአግባቡ ለመንግስት ሲያቀርብ፣ መንግስት  ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት፤ ይሠጣል ብዬም እገምታለሁ፡፡ የሚነጋገሩበት አጀንዳ ግልፅ እስከሆነ ድረስ ከጥያቄና መልስ ውይይቶች መፍትሄ ሊገኝ ይችላል፡፡ በመንግስት በኩል ሊደረግ የሚገባው፣ ህብረተሰቡ የሚጠይቀውን ጥያቄ ማዳመጥ ነው፡፡ ማዳመጥ ብቻ አይደለም፤ የህዝቡን ጥያቄ ጠለቅ ብሎ አይቶ መንስኤው ምንድን ነው? መፍትሄውስ? የሚለውን በጥልቀት ማሠስ ይኖርበታል፡፡ ምላሽ በአንድ ጊዜ ላይገኝ ይችል ይሆናል፤ ግን መንግስት የሁሉንም ጥያቄ እየለየ በማጥናት በየተራ ምላሽ መስጠት ይችላል፡፡ በውሳኔ መልክ ሳይሆን በማማከር መልክ ነው ምላሽ መስጠት ያለበት፡፡ እንደ ገዥና ተገዥ ሣይሆን መንግስት እንደ አባት፣ ህዝብ እንደ ልጅ ሆነው መመካከር አላባቸው፡፡ ችግሮች ሁሉ በውይይት መፈታት ይችላሉ፡፡
የኛ ሃገር ብዙ አገሮች የሚቀኑባት ነች፡፡ በሌሎች አገራት እየታየ ያለው ችግር ወደ እኛ ሃገር እንዲመጣ አንፈልግም፡፡ ድንጋይ የሚያቀብሉ ሰዎችን ዞር በሉ ማለት አለብን፡፡ ያለችን ትንሽ ሠላም ከተናጋች ሁኔታዎች ፈር ይለቃሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ነገሮችን በአስተዋይነትና በጥንቃቄ መመልከት አለበት፡፡ መንገዳችን ላይ የሙዝ ልጣጭ ስላለ አወዳደቃችን ላያምር ይችላል፡፡
===========================

“ይሄ ሥርአት ሳይመሽበት የለውጥ እርምጃ መውሰድ አለበት››

አቶ ልደቱ አያሌው
በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካ ጤናማ እንዳልሆነ ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ ስንናገር ነበር፡፡ ሠሚ አልተገኘም፡፡ ሃገሪቱ በብዙሃን ፓርቲ ሳይሆን በአንድ ፓርቲ ብቸኛ አምባገነናዊ ስርአት ስር እየወደቀች ነው፤ ህብረተሰቡ በነፃነት ብሶቱን፣ ተቃውሞውን ሃሳቡን የሚገልፅበት መድረክ እያጣ ነው፤ መድረኩ እየጠበበ ነው፤ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ችግር ውስጥ እየወደቀ ነው፡፡ ሃገሪቱ የማትጋፈጠው አደጋ ሊመጣ ይችላል… እያልን ለረዥም ጊዜ ብንለፈልፍም ሰሚ አላገኘንም፡፡
አንድ መንግስት አምባገነን እየሆነ ከሄደና የህዝቡን ጥያቄዎች መመለስ ካልቻለ ወይም የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚችሉ የማሻሻያ እርምጃዎችን ማድረግ ካልቻለ፣ የመጨረሻ እጣ ፈንታው በትጥቅ ትግል ወይም በአመፅ ስልጣን ማጣት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በበርካታ ሃገሮችም በኛም ሃገር የተከሰተ ነው፡፡ ሆኖም ካለፈው መማር አልቻልንም፡፡ ትልቁ ችግር ይሄ አካሄድ መንግስትን በመለወጥ ብቻ መቆም አለመቻሉ ላይ ነው፡፡ ሃገራዊ ህልውናችንንም አደጋ ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ ላለፉት 25 አመታት ለህዝቡ ሲነገር የኖረው የጋራ ጉዳያችን ወይም አንድነታችን ሳይሆን ልዩነታችን ነው፡፡ ህብረተሰቡ በፖለቲካ አስተሣሠብ ሳይሆን በዘር፣ በቋንቋ የተደራጀበት፣ ለጋራ ጉዳይ ሳይሆን ለራሱ አካባቢ ብቻ የሚጨነቅ ማህበረሰብ ነው የተፈጠረው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ መንግስት በአመፅም ሆነ በተለየ ሁኔታ ሲቀየር፣ ውጤቱ መንግስት በመቀየር ብቻ የሚያበቃ አይሆንም፤ ሀገር አልባ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ይሄን ጉዳይ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ መንግስት የያዘው አቅጣጫ ትክክለኛ አለመሆኑን ተረድቶ፣ ተጨባጭ የሆነ የለውጥ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ይሄን ካልወሰደ ይህቺ ሀገር አመፅና የትጥቅ ትግልን ለማስተናገድ በደንብ እየተዘጋጀች እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይሄን መንግስት የምንቃወም የፖለቲካ ኃይሎች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ በአግባቡ መተንተንና ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ችግሩ ኢህአዴግን ከስልጣን በማውረድ ብቻ ላይቆም እንደሚችል ተገንዝበን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ የቱንም ያህል ይሄን መንግስት ጠልተን ለውጥ ብንፈልግም፣ ለውጥ የምናመጣበት መንገድ አመፅና የትጥቅ ትግል ከሆነ፣ ለውጡ ዋስትና እንደሌለው ማወቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ችግሩ መፈታት ያለበት ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው፡፡  ምናልባት በአመፅና በግርግር ይሄን መንግስት መለወጥ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን በሚገባ ካላሰብንበት ሀገር ማጣት ሊከተል ይችላል፡፡ ይህቺ ሀገር ከዚህ አንፃር አሁን በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ በአንድ በኩል፤ “ይህቺ ሀገር በኔ ብቻ ነው የምትለወጠው” የሚል መንግስት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “ይሄን መንግስት በማንኛውም መንገድ መጣል አለብኝ” ብሎ የሚንቀሳቀስ አለ፡፡ ይሄ ሁለት ፅንፍ፤ ይህቺን ሀገር እንዳያፈርሳት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት አለብን፡፡ ገዥው ፓርቲም እነዚህን ሁኔታዎች ተገንዝቦ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ “ይሄን ችግር የፈጠሩት ጥቂት ፀረ ልማትና ፀረ - ሰላም ኃይሎች ናቸው” እያለ የሚነዛውን ፕሮፓጋንዳ ማቆም አለበት፡፡ 25 ዓመት ሙሉ ይሄን አውርቶ ችግሩ አልተፈታም፡፡
መንግስት በህገ መንግስቱ የተቀመጡ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር አለበት፡፡ ህብረተሰቡ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆኑ መንገዶች እየታፈነ ነው ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ጉልበት የለሽ እንዲሆን ተደርጐ፣ ማንም ካድሬ በጉልበትና በተፅዕኖ የሚገዛው እየሆነ ነው ያለው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የተሰሩት ስራዎች በአጠቃላይ፣ ህብረተሰቡ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ያደረገ ነው፡፡ ወረቀት ላይ ካልሆነ በስተቀር በተግባር መብት የለውም፡፡ በሃገሪቱ የዲሞክራቲክ ተቋማት በወረቀት ላይ እንጂ በተግባር የሉም፡፡ ስርአቱ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ፓርቲ የሚዘወር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ዲሞክራሲ፤ የብዙሃን ፓርቲ አሰራር… አለ ማለት ፌዝ ነው፡፡ የፖለቲካ ስርአቱ እነዚህን ነገሮች በተግባር ለማዋል እንቅስቃሴዎችን መጀመር አለበት፡፡ ይሄ ስርአት እንዳለፉት ስርአቶች ሳይመሽበት የለውጥ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ መሰረታዊ ለውጥ ነው ማምጣት ያለበት እንጂ የይስሙላ መሆን የለበትም፡፡ ህብረተሰቡም ለውጦች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ሲመጡ ዋስትና ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅ አለበት፡፡ መንግስታት በአመፅና በትጥቅ እንዲወርዱ በተደረጉባቸው አገራት ሰላም ሲሰፍንና መረጋጋት ሲመጣ አላየንም …ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ የመን የመሳሰሉትን መመልከት እንችላለን፡፡ ህብረተሰቡ በሰከነ መንገድ ትግሉን ማካሄድ አለበት፡፡

==================================

“የእምነት ተቋማት መስራት ያለባቸውን አልሰሩም”

መጋቢ ሀዲስ እሸቱ
እዚህ ሀገር ላይ ስኖር እንደ ሶስት ሰው ሆኜ ነው የምኖረው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አስባለሁ፡፡ እንደ ሰውነቴ አስባለሁ፡፡ እንደ እምነት ተቋም ሰውነቴም አስባለሁ፡፡ እንደ ሶስት ሰውነቴ ለማሰብ ግን ሀገርና ህዝብ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ሀገር መኖር አንችልም፡፡
 ተስፋ የቆረጡም ገደብ ያለፈ ተስፋ የሰነቁም ናቸው አለምን የሚያጠፏት፡፡ መንግስት ተቀያያሪ ነው፡፡
በሊቢያ የመጨረሻው ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ሆኑ፡፡ የኢራቁ ደግሞ ሳዳም ሁሴን፡፡ ሶርያ የምትባለው ሀገር ለመቀጠሏ ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ጎረቤቶቻችንም እየታመሱ ነው፡፡ እዚህ እየተፈጠረ ያለው ችግርም ከነዚህ ሀገራት ባልተናነሰ አስጊ ነው፡፡ ፖለቲካዊ አመለካከትን እንደ መለያያ ምክንያት ማቅረባችን ተገቢ አይደለም፡፡ የቋንቋ ልዩነታችንን፣ የሃይማኖት ልዩነታችንን በምክንያት ማቅረብ ለድክመቶቻችን ሽፋን እንደ ማበጀት ነው፡፡
ሁላችንም፡- መንግስትም ህዝቡም ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ውጭ ሃገር ያሉትም ከመቆስቆስ በፊት አርቀው ማሰብ አለባቸው፡፡ 4 ኪሎ ላይ ከሃጎስ ጋር የተጣላ ሰው፤ እስከ አድዋ፣ ሽሬ አክሱም ድረስ መሣደብ፤ ከሁሴን ጋር የተጣላ እስልምናን መስደብ ነውረኝነት ነው፡፡ በአንድ ቶሎሳ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ መስደብ፣ በአንድ ሃጎስ ምክንያት ሙሉ ትግሬን መስደብ፣ በአንድ የጎንደር ተወላጅ ምክንያት ሚሊዮን ጎንደሬን መስደብ ያልተገረዘ አንደበት ውጤት ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ የዚህ ሀገር ችግር ከፖለቲከኞቹ በላይ ሃይማኖቶቹ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የእምነት ተቋማት መስራት ያለባቸውን ስራ አልሠሩም፡፡ መንግስት ልማት ሲል እኛም ልማት እያልን ነው የምናስተጋባው፡፡ ሃይማኖቶች ለአገሪቱ የለማ ጭንቅላት ነው ማፍራት ያለባቸው እንጂ መንግስት ዶማ ሲያነሳ ዶማ እያነሱ፣ ህንጻ መገንባት አይደለም ድርሻቸው፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ድህነትን ከመቀነስ ይልቅ ሃጢአትን መቀነስ ላይ ቢተጉ መልካም ነው፡፡ እነሱ የሃይማኖት ስራቸውን አለመስራታቸው ነው ይህቺን ሃገር ለዚህ ችግር ያጋለጣት፡፡
ድሮ እርቅና ሠላም ለማምጣት ሃይማኖቶች ወሳኝ ነበሩ፡፡ “ፍቅር እስከ መቃብር“ ላይ እንኳን ሁለቱ ፊት አውራሪዎች ሲጣሉ ካህናት ናቸው ያስታረቁት፡፡ ይሄ የቀድሞ ጊዜ የገሃዱ አለም ነፀብራቅ ነው፡፡ ዛሬ የእምነት ተቋማት በዚህ መደብ ውስጥ የሉበትም፡፡ ራሳቸው የሠላምና የእርቅ ተቋም መሆን ስላልቻሉ ነው፤ አጥፊን መገሠፅና መቆጣት ያልቻሉት፡፡ የመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ሲከሽፍ፣ የፓትሪያርኩ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡ ወታደሩ መሳሪያውን የዘቀዘቀው በፓትሪያርኩ ተግሣፅ ነበር፡፡ አሁነ ግን ተቋማቱ በራሳቸው ቅቡልነት የሌላቸው ሆነዋል፡፡ የራሳቸውን ስራ ትተው የመንግስት ስራ እንስራ እያሉ ነው፡፡ ልማት ሲባሉ ሰው ማልማት ትተው፣ ሱቅና ህንፃ የመገንባት ፉክክር ውስጥ ነው የገቡት፡፡ እንደ እኔ የእምነት ተቋማት፤ ድንጋይ መቆለልና ሲሚንቶ ማቡካታቸውን አቁመው የሰው ጭንቅላት ያልሙ፡፡     

======================================
“ስሜታዊ ሆነን ይህቺን አገር አደጋ ላይ መጣል የለብንም”
ኡስታዝ ኑሩ ጀማል (የሃይማኖት መምህር)
በየሚዲያው በየማህበራዊ ገፆች የምንሰማቸውና የምናያቸው ነገሮች የህዝቦችን አንድነት ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ እያልን ኢትዮጵያ ተረስታ ጉዳዩ ወደ ብሄር ወርዷል፡፡ ይህቺ ሀገር የማን ናት? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ እንደኔ ከሆነ እቺ ሀገረ ማለት እኛው ነን፡፡ አማራው ኦሮሞው፣ ትግሬው ሌላውም ብሄር… ይህቺ ሀገር በእነዚህ ማህበረሰቦች የተገነባች ነች፡፡ ሀገሪቱ እንደ ሀገር ለመቀጠል የእነዚህ ማህበረሰቦች አንድነትና መተሳሰብ ወሳኝ ነው፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ መብትን መጠየቅ መልካም ነገር ነው፤ ግን በሰልፉ መሃል የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም፡፡ እንደኔ በሰልፍ ጊዜያችን ሲባክን የሀገሪቱ እድገት ወደ ኋላ እንዳይጎተት ስጋት አለኝ፡፡ ነገር ግን መንግስት ሁሉንም ሰው እኩል ማስደሰት ባይችልም ልዩነትን ማጥበብ ግን ይችላል፡፡ ካለፉት ስርአቶች አንፃር ስመዝነው በልማት አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በኢህአፓ ዘመን ለዚህች ሀገር ሊጠቅሙ የሚችለ በርካታ ምሁራን ተጠፋፍተዋል፡፡ ዛሬ እነሱ ቢኖሩ ኖሮ ሀገሪቱ የት በደረሰች ነበር፡፡ ዛሬም ብዙ የተማሩ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ወጣት ሆኖ የመጀመሪያ ዲግሪ የሌለው የለም፡፡ የመማር ፍላጎቱ እየጨመረ ነው፡፡ ይሄን የተማረና እየተማረ ያለ ኃይል ወደ ልማት ቀይሮ፣ ሀገሪቱ ወደተሻለ ደረጃ እንድትደርስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜያችንን በሁከትና በብጥብጥ የምናጠፋ ከሆነ ግን የዚህች ሀገር ህልውና አሳሳቢ ነው የሚሆነው፡፡ እነ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ የመንን… ካየን፣ በአንድ ወቅት በፍጥነት እያደጉ የነበሩ አገራት ናቸው፡፡ ዛሬ ዜጎቻቸው ከቤታቸው ወጥተው ዳቦ ለመግዛት እንኳ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ሰላም የለም፡፡ እኛ ጋ አሁን አንፃራዊ ሰላም አለ፡፡ ይሄን ሰላም መጠበቅ አለብን፡፡ ወጣቶች ስሜታዊ ከመሆን መቆጠብ አለባቸው፤ በኋላ ቁጭት ውስጥ እንዳንገባ፡፡ ከዚህች ሀገር ውጪ ሌላ ምንም የለንም፡፡ እያንዳንዳችን የዚህች ሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በዚህች ሀገር በፖለቲካ ችግር ጥይት ጮሆ ይሆናል እንጂ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ጥይት ጮሆ አያውቅም፡፡ ሙስሊምና ክርስቲያኑ እርስ በእርሱ የተዋለደባትና የተዛመደባት ሀገር ነች፡፡ በብሄርም እርስ በእርስ ተዋልደናል፡፡ በህዝብና በመንግስት መካከል አለመግባባት ካለ፣ በሁለቱም በኩል በሰከነ ውይይት ልዩነቶችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ሲሆን ሀገሪቱን እንደ ሀገር ማስቀጠል እንችላለን፡፡ በቁጣ ብቻ የምንንቀሳቀስ ከሆነ ግን ብዙ ነገር እናበላሻለን፡፡  የኛ ሃገር ተቃውሞ የሠለጠነ አለመሆኑም ሌላው አሣሣቢ ጉዳይ ነው፡፡ ስንቃወም ለምን የህዝብ ንብረት እናቃጥላለን? ለምሳሌ ሠላም ባስ ተቃጥሏል፡፡ ይሄ መንግስት ሄዶ ሌላ መንግስት ቢመጣ፣ ንብረትነቱ የህዝብ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንደነዚህ አይነቱ ላይ ገና ግንዛቤ አልተያዘም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ችግሮችን በውይይት መፍታት መለመድ አለበት፡፡ የተማረው ህብረተሰብ ወደ ስራ ገብቶ የተሻለች ኢትዮጵያ መፍጠር አለበት፡፡በቁርአን፤ ‹‹እናንተ ሰዎች እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ በመካከላችሁ ብሄርና ጎሳን አደረግን፤ እንድትተዋወቁ፡፡” ነው የሚለው፡፡  በቃ አላህ በብሄርና በጎሳ የከፋፈለን እንድንተዋወቅ ነው፡፡ አገልግሎቱ ይሄ ብቻ ነው፡፡ በአላህ ዘንድ የብሄር የበላይነት አይኖርም የለምም፡፡ እንደ እስልምና አስተምህሮ በብሄርና በጎሳ የተከፋፈልነው እንድንተዋወቅ ነው እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳሳ ወይም እኔ የበላይ ነኝ ብሎ እንዲኮፈስ አይደለም፡፡የሃይማኖት አባቶች ሃገርን፣ ብሄርን የተመለከተ ትክክለኛውን ትምህርት ማስተማር አለባቸው፡፡ እስካሁን ብዙ የሃይማኖት አባቶች፣ ይሄን እየሠሩ ቢሆንም መቶ በመቶ ግን እየተሰራበት ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሃይማኖተኛ በመባል የኛ ሃገር የታወቀች ነች፡፡ ህዝቡ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ሰው መብቱን ሲጠይቅ እንኳ በዚሁ በሃይማኖተኛነቱ በአግባቡ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ የሃይማኖት አባቶችም በመብት ጥያቄው ላይ ከመንግስት ጋር እንዲነጋገሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስሜታዊ ሆነን ይህቺን ሃገር አደጋ ላይ መጣል የለብንም፡፡ የጤና ዋጋ የሚታወቀው ጤና ሲታጣ እንደመሆኑ፣ የሠላም ዋጋ የሚታወቀው ሠላም ሲታጣ ነው፡፡

Read 8486 times