Monday, 05 March 2012 13:58

ጊዮርጊስ እና ቡና የማለፍ ዕድላቸውን ይወስናሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ብሄራዊ ቡድኑ ከጅምሩ አጣብቂኝ ገብቷል

በአፍሪካ ሁለት የክለብ  ውድድሮች ቅድመ ማጣርያ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የመልስ ጨዋታቸውን  ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባ ሊያደርጉ ነው፡፡ ከሜዳቸው ውጭ ከሳምንት በፊት የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የመልስ ጨዋታቸውን በደጋፊዎቻቸው  ፊት ሲያደርጉ ወደ ቀጣይ የማጣርያ ውድድር ለመግባት ሰፊ እድል ይኖራቸዋል፡፡ ዛሬ በኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆነው  ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 የረታውን የጋቦን ቡድን  ማንጋ ስፖርት ሲገጥም ነገ ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት የተሸነፈው ቡና የኮሞሮሱን ኮየን ኖርድ  ያስተናግዳል፡፡

በሌላ በኩል ለ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  28 ብሄራዊ ቡድኖች የተሳተፉበት ቅድመ ማጣርያ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሲጀመር በአዲስ አበባ ቤኒንን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 0ለ0 ተለያየ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በሜዳው የመጠቀም እድሉን አበላሽቷል፡፡ ከጨዋታው በፊት ብሄራዊ ቡድኑ በተጨዋቾች ስብስቡ ወሳኝ የተባሉ ልጆችን አላካተተም በሚል ውዝግብ ተጠምዶ የነበረ ሲሆን በቂ የዝግጅት ጊዜ አለማድረጉ ለውጤቱ መበላሸት ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፡፡  ዋልያዎቹ ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቤኒን ሲገጥሙ በኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ብልጫ አሳይተዋል፡፡ የአጥቂ መስመሩ በርካታ የግብ እድሎችን ሳይጠቀም መቅረቱ ግን በርካታ ስፖርት ቤተሰብን አበሳጭቷል፡፡ የመልሱ ጨዋታ ግንቦት ላይ  ሲደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለማለፍ ከማሸነፍ ሌላ ጎል  አግብቶ አቻ መውጣት ይኖርበታል፡፡ እዚያም 0ለ0 ከተለያየ ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ምእራፍ የሚሸጋገረውን ቡድን የሚለየው የመለያ ምት ነው፡፡ ይህም የብሄራዊ ቡድኑ ወደ ቀጣይ የማጣርያ ምእራፍ የመሸጋገር እድል አጥብቦታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከጨዋታው በኋላ በውጤቱ እድለቢስ ሆነናል ሲሉ ቢናገሩም ስፖርት አፍቃሪው የቡድኑ ችግርን ከአሰልጣኙ የተጨዋች አመራረጥ ጋር አያይዞታል፡፡ በተለይም የቡናዎቹን ምርጥ አማካዮች ዳዊት እስጢፋኖስና መሱድ መሃመድን ባለማካተታቸው እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱን አጥቂ አዳነ ግርማ በቤንች አስቀምጠው መቆየታቸው ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በአዲስ አበባ ስታድዮም ደጋፊ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲፈጥርባቸው አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በተደረጉ ሌሎች የቅድመ ማጣርያው  ጨዋታዎች 10 ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ምእራፍ የመሸጋገር ተስፋቸውን አለምልመዋል፡፡ ማዳጋስካር በሜዳዋ በኬፕቨርዲ 4ለ0 መሸነፏ ሩዋንዳ በሜዳዋ ከናይጄርያ ጋር 0ለ0 መለያየቷ  እንዲሁም ኬንያ ቶጎን ሜዳዋ ላይ 2ለ1 መርታቷ አስደናቂ ውጤቶች ተብለዋል፡፡ በሌሎች ጨዋታዎች ሲሸልስ በሜዳዋ በዲሪ ኮንጎ 4ለ0፤ ቻድ ማላዊን 3ለ2፤ ኮንጎ ብራዛቪል ኡጋንዳን 3ለ1፤ ላይቤርያ ናሚቢያን 1ለ0 ፤ ካሜሮን ከሜዳዋ ውጭ ጊኒ ቢሳዎን 1ለ0፤ ሳኦቶሜ ሴራሊዮንን 2ለ1፤ እንዲሁም አልጄርያ ከሜዳዋ ውጭ ጋምቢያን 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡

 

 

Read 1922 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:02